
ዜና ሀተታ
ጥበባትና ባህሎች የደመቁበት ትዕይንት ነው፡፡ የምሥራቅ አፍሪካ ሕዝቦች ጥበባትና ባህሎች ጎልተው የታዩበት ፌስቲቫል የብዙዎችን ቀልብ ስቦ ሰንብቷል፡፡ ላለፉት ተከታታይ ቀናት በአዲስ አበባ ሲካሄድ የሰነበተው ሁለተኛው የምሥራቅ አፍሪካ የጥበባትና ባህል ፌስቲቫል ትናንት የማጠቃለያ ፕሮግራም ተካሂዷል።
ፌስቲቫሉ”ጥበብና ባህል ለቀጣናዊ ትብብር” በሚል መሪ ሃሳብ ከመጋቢት 11 ቀን 2017 ዓ .ም ጀምሮ በመዲናችን በአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል ተካሂዷል ። ከኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሩዋንዳ፣ ዩጋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ከቡሩንዲ የተውጣጡ 140 የኪነ-ጥበባት እና ባህል ልዑካን ቡድን በፌስቲቫሉ መሳተፋቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ፌስቲቫሉ በሀገራቱ መካከል ሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን ለማጠናክር፣ የባህል ዲፕሎማሲና ቀጣናዊ ትስስር እንዲጎለብት ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር መሆኑ ተገልጿል። ሀገራቱ ባህሎቻቸውን እንዲያስተዋውቁና በሀገራት መካከል ሙያዊ የልምድ ልውውጥ እንዲኖር የሚያስችል መሆኑም ነው የተገለጸው።
የሀገራት ልዑካን ቡድን መካከል ከኡጋንዳ ኦቶ ሉሲ፣ ይህ የኪነ ጥበብ እና ባህል ፌስቲቫል እንደ ምሥራቅ አፍሪካ ለእርስ በእርስ ትውውቅ በጣም አስፈላጊ ነው ይላሉ። ኪነ-ጥበባት እና ባህል የሰላም፣ የልማት፣ የእድገት እና የለውጥ መሣሪያ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በሀገራቸው ከ65 በላይ ብዝሃ-ማንነቶች ያሉ መሆናቸውን የጠቀሱት ኦቶ ሉሲ፣ እነዚህ ብዝሃ-ማንነቶች ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጠቀሜታ እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡ ኢትዮጵያ ያዘጋጀችው ሁለተኛው የምስራቅ አፍሪካ ፌስቲቫል ብዝሃ-ማንነታችንን ለማስተዋወቅ ትልቅ እድል የፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተለይ መድረኩ ያሉንን ቅርሶች፣ ቋንቋዎች፣ ሙዚቃዎች፣ ውዝዋዜዎችና ሌሎች መሰል ብዝሃ ማንነቶችን ከምስራቅ አፍሪካ ባሻገር ለተቀረው ዓለም እንድናሳይ አድርጎናል ነው ያሉት።
ከኢትዮጵያ ሲዳማ ክልል ዳዊት ፈይሳ በበኩሉ፣ ፌስቲቫሉ ባህላችንን ለማስተዋወቅ እና ከቀጣናው ሀገራት ጋር የገበያ ትስስር ለመፍጠር ይረዳናል ብሏል።
መጀመሪያ ፌስቲቫሉ ባህላችንን እንድናስተዋውቅ እድል ፈጥሮልናል፣ ቀጥሎም ስላሉን ባህላዊ ምርቶች ግንዛቤ በመፍጠር ቀጣይነት ያለው የገበያ ትስስር እንድንፈጥር የሚያደርግ መሆኑን ነው የተናገረው።
በፌስቲቫሉ ምሥራቅ አፍሪካ ምን ያክል የኪነ ጥበባት እና የባህል ባለጸጋ መሆኑን መገንዘብ ችያለሁ ያለችው ደግሞ ከቡሩንዲ ኤሚ ቢታሎ ናት። ፌስቲቫሉ አንዳችን የሌላኛችንን ማንነት እንድናውቅ እድል ከመፍጠሩ ባሻገር የቀጣናውን ሀገራት በሰላምና በልማት ለማስተሳሰር ትልቅ እድል እንዳለው ገልጻለች።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ፌስቲቫሉ ጠንካራ የባህል ዲፕሎማሲን ለመገንባት በየሀገራቱ ያለውን እምቅ የባህል፣ ኪነ ጥበብና ፈጠራ ኢንዱስትሪን በሚገባ ለመጠቀም ዕድል አንደሚፈጥር አስገንዝበዋል። ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትን በባህልና በኪነ ጥበብ በማስተሳሰር የጋራ የማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየሠራች ትገኛለችም ብለዋል።
ለዚህም ሁለተኛው የምሥራቅ አፍሪካ ጥበባትና ባህል ፌስቲቫልም አንዱ ማሳያ ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ ተሳታፊ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትንም ድንበር የሌለውን ባህልና ኪነ ጥበብን በጋራ ለማሳደግና ለማልማት ላሳዩት ቁርጠኝነትና ለወሰዱት ተነሳሽነት ምስጋና አቅርበዋል።
የሚኒስትሮች የጋራ ምክክር መድረክ ላይ የተሳተፉት ከ8 አፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ሚኒስትሮች ኢትዮጵያ የቀጣናውን ሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት እና ትስስር የሚያጠናክር መርሃ ግብር ማዘጋጀቷ አብሮ የማደግና በትብብር ለመሥራት ያላትን ቁርጠኝነት ማሳያ መሆኑን በማንሳት በዝግጅቱ ደስተኛ መሆናቸውንም ማንሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ኢትዮጵያ አፍሪካ ሀገራት ሊኖራቸው የሚገባ ኮንቬንሽን ማዕከል እንዳላት፣ አዲስ አበባ ከተማም ሁለንተናዊ የለውጥ ጎዳና ላይ እንደምትገኝ ያስታወሱት ሚኒስትሮቹ ፤ ይሄ ለውጥ ለኪነ ጥበብና ባህል የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ተሰፋ ሰጪ መሆኑን ገልፀዋል።
በሀገር በቀል እሴቶች ያሸበረቀው 2ኛው የምስራቅ አፍሪካ ጥበባትና ባህል ፌስቲቫል የዕደ ጥበብ ውጤቶች፣ ባህላዊ አልባሳትና ጌጣጌጦች፣ ባህላዊ ምግቦች፣ የስዕል አውደ ርዕይ ጨምሮ ልዩ ልዩ የሙዚቃ መሣሪያዎች ለዕይታ ክፍት ሆነው የትውውቅና የግብይት ሂደት ተከናውኖበታል።
በሲምፖዚየሙ የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ተሳታፊዎች፣ የመዲናዋ ነዋሪዎች፣ የክልልና ከተማ አስተዳደር ተሳታፊዎች እንዲሁም በመዲናዋ የሚገኙ የተለያዩ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ታድመውበታል።
ቀጣናዊ ብሎም የርስበርስ የማህበረሰብ ትውውቅና አንድነት እየተጠናከረበት የጥበባትና ባህል ፌስቲቫል የዲፕሎማሲ እና የገበያ ትስስር የተፈጠረበትም መሆኑንም ታውቋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 15 ቀን 2017 ዓ.ም