ከአጼ ኃይለስላሴ የንግስና ዘመን ጀምሮ ያሉ መንግስታትን የማየት እድል አግኝተዋል። ከሸቀጣሸቀጥ ንግድ ባለቤትነት እስከ አነስተኛ የጨርቃጨርቅ ንግድ ላይ ተሰማርተው ኑሮን ሲገፉ ቆይተዋል። የህይወትን ውጣ ውረድ ቢረዱም መንገድ ዳር ቁጭ ብሎ ከመለመን ይልቅ ጥረህ ግረህ ብላ የሚለውን የአምላክ ቃል በመተግበር ቤተሰባቸውን ያስተዳድራሉ። አብዛኛውን ጊዜ ቆመው ነው በስራ ቦታቸው ላይ የሚያሳልፉት ስራቸው እንደእርሳቸው አጠራር «አሮጌ ልባሽ ጨርቆችን መሞሸር» ይባላል። መሞሸር የሚሉት ደግሞ ልብሶችን በሙቀት ተኩሶ ማሰማመሩን ለመግለጽ ነው።
ግርግር እና ሁካታ ከበዛበት ከአዲስ አበባው ቀራንዮ አካባቢ መንዲዳ የአሮጌ ልብሶች መሸጫ መንደር በጠዋት ይገኛሉ። ከቤት ሲወጡ የያዟትን ከሰል አያይዘው በቀጥታ ወደ ስራቸው ይሰማራሉ። አንድ ጥግ ላይ በላስቲክና በአሮጌ ቆርቆሮ በተበጀችው አነስተኛ ቦታቸው ቆመው ደንበኞቻቸውን ይጠባበቃሉ። ከሰሉ ተያይዞ ካውያ ውስጥ መጨመራቸውን ያዩ አሮጌ ልብስ ሻጮችም ሱሪም ይሁን ሸሚዝ ሰጥተዋቸው ወደ ስራቸው ይመለሳሉ። እርሳቸው ደግሞ ልብሱን ተኩሰው በወግ በወጉ ደርድረው ይጠብቋቸዋል።
ደንበኞቻቸው ሲመለሱ ለገበያ የሚያቀርቡትን የተተኮሰውን ልብሳቸውን ወስደው በምትኩ ሶስትም አራትም ብር ይከፍሏቸዋል። በእንዲህ አይነት የስራ ዑደት ከሰኞ እስከ ቅዳሜ የተለያዩ ልብሶችን ሲያስቡ እና ሲሞሽሩ የሚውሉት ክንደ ብርቱው የቤተሰብ አስተዳዳሪ እሁድን ደግሞ ወደ ቤተክርስቲያን በመሄድና ከቤተሰባቸው ጋር በመጫወት ያሳልፋሉ። የዛሬ እንግዳችን አቶ መውለድደግ ባሜ ይባላሉ። ጠቆር ያለ መልካቸውና ፈገግታቸው ልዩ መለያቸው ነው።
ትውልድ እና ዕድገት
አቶ መውለድደግ ትውልዳቸው በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል ጉራጌ ዞን ነው። ከጉራጌ አካባቢ ደግሞ ከጓደኞቻቸው ጋር ከብት ጠብቀው ከወንዝ ውሃ ጠጥተው እና ተራጭተው ያደጉበት አካባቢ ቋንጤ ምዳቻረ የተባለ ቦታ ላይ ነው። በ1960 ዓ.ም የተወለዱት እንግዳችን በመንደራቸው ትምህርት ቤት ከቶውንም ባለመኖሩ የአንድ ሰዓት ተኩል መንገድ በእግራቸው ተጉዘው እንደተማሩ ያስታውሳሉ። ከትምህርት ቤት መልስ ደግሞ የከብት እገዳው ስራ አይቀርም። እናም እስከ ስድስተኛ ክፍል ቤተሰብ እያገዙ ጎን ለጎን ተምረው በዚያን ጊዜው የመጀመሪያ ደረጃ ማጠናቀቂያ ፈተናቸውን ስድስተኛ ክፍል ላይ ይወስዳሉ።
ወቅቱ አዲስ የፖለቲካ እሳት የጀመረበት፤ ትንሽ ትምህርት የቀመሰው ደግሞ የአጼውን መንግስት በመቃመም አዲስ መሪ እንዲመጣ የተነሳበት ነበር። እናም የአጼ ኃይለስላሴ ዘመን ያበቃበት ክስተት በመፈጠሩ ደርግ ወደስልጣን የመምጣቱ ዜና በመላ ሀገሪቷ ተሰማ። አቶ መውለድደግ በአፍላ የወጣትነት እድሜያቸው ከማያውቋቸው ፖለቲከኞች ጎን ጎን ቆመው መሬት ላራሹ ይሰጠው እያሉ መንደር ለመንደር እየዞሩ መፈክር ማሰማታቸውን ተያያዙት።
አንድ እግራቸው ወደ ፖለቲካው ሊያዘነብል ያለው እንግዳችን ግን ህይወት መስመሯን ቀይራ ወደሌላ ከተማ ልትወስዳቸው አቅዳለችና ምክንያቷን ፈጠረች። የቤተሰብ እርሻቸው ላይ ዘርተው ያፈሩትን ሰብል የጎረቤት ከብቶች ገብተው ሜዳ ሲያረጉት ይመለከታሉ። እናም ከከብቶቹ ባለቤት ጋር ፀብ ገጥመው በመደብደባቸው ችግር ተፈጠረ። በመሆኑም ጉዳዩ እስኪበርድ ድረስ ሁሉንም ነገር ጣጥለው ወደአዲስ አበባ ጉዞቸውን አደረጉ።
ህይወት በሸገር
እናም በ20ዎቹ አጋማሽ እድሜ ላይ እያሉ 255 ኪሎ ሜትሮችን በ10 ብር ትራንስፖርት አቆራርጠው አዲስ አበባ ደረሱ። በመዲናዋ ከደረሱ በኋላ የአጎታቸው ልጅ ጋር ያርፋሉ። ወዲያውም የዘመዳቸው ሸቀጣሸቀጥ ሱቅ ነበርና እዚያው ተቀጥረው መስራት ጀመሩ። በሱቅ ስራው ግን ከዘመዳቸው ጋር መስማማት ባለመቻላቸው ከስድስ ወራት በኋላ የሊስትሮ ዕቃ ተገዝቶላቸው እየተዘዋወሩ እንዲሰሩ ትዕዛዝ ተሰጣቸቸው።
«በየመንደሩ እየተዘዋወርኩ የብዙዎችን ጫማ በመጥረግ መጠነኛ ገንዘብ አግኝቼ ነበር» የሚሉት እኚሁ ግለሰብ በቆጠቡትም ገንዘብ ሱቅ ለመክፈት ያቅዳሉ። አቅደው ብቻም አልቀሩም ከአንድ ሌላ ሰው ጋር በመሆን አማኑኤል አካባቢ የመንግስት ቤት ውስጥ የሚገኝ የሸቀጣሸቀጥ ሱቅ በሽርክና ከፍተው የእራሳቸው ንብረት ባለቤት መሆን ቻሉ። ከአጋራቸው ጋር በፈረቃ እየሰሩ እንደነበር ያጫወቱን አቶ መውለድደግ፤ ይሁንና የአጋራቸው የአዕምሮ ጤና በተለያዩ ምክንያቶች ይታወክና ከአጋራቸው ቤተሰቦች «ሱቁን ጠቅልለው ቢዘጉት የተሻለ ነው» የሚል ሃሳብ ያቀርቡላቸዋል። በሃሳቡ ተስማምተው የሸቀጣሸቀጥ ንግዱን ሙሉ ለሙሉ ጠቅልለው ገዙ።
የሱቅ ባለቤትነቱንም ወደራሳቸው አስተላልፈው ለመንግስት ኪራይ ለመንግስት መክፈሉን ቀጠሉ። ከተወሰኑ ዓመታት የሸቀጣሸቀጥ ንግድ ስራው በኋላ ባከራየው እጠቀማለሁ በሚል እሳቤ ሱቁን ለሌላ ሰው ያከራዩታል። በዚህ ወቅት ነበር ታዲያ ገቢያቸውን የሚያሳጣ ክስተት የተፈጠረው። የተከራይ አከራይ መሆን አይቻልም በመባሉ ሱቃቸው ተወርሶ ባዶ እጃቸውን ቀሩ። በዚህ ወቅት ገቢ በመራቁ የሚላስ የሚቀመስ መጥፋት ጀመረ። ለቤት ኪራይም የሚሆን ገንዘብ ጠፋ።
እጅ አልሰጥም በሚል መንፈስ የተነሱት አቶ መውለድደግ የውስጥ ሱሪ እና የተለያዩ ልብሶችን በአነስተኛ ዋጋ በመግዛት በእጃቸው አንግተው ማዞር ጀመሩ። በመርካቶ አካባቢዎች በመዟዟር «ምርጥ አልባሳት በቅናሽ ቀርቦልዎታል» እያሉ የቀን ጉርሳቸውን ለመሸፈን ይሯሯጡ ጀመር። የህፃናት፣ የአዋቂዎች እና የሌሎችንም ልብሶች በእጅ እና ትከሻቸው ላይ አድርገው በሌሊት ከወጡ የተወሰነውን ሸጠው ማታ ወደቤታቸው ይመለሳሉ። በሱቅ በደረቴ ንግዱ በሚያገኟት አነስተኛ ገቢ ደግሞ የቤት ኪራይ ክፍያቸውን መሸፈን ቻሉ። የቤት ኪራዩ አንዳንድ ጊዜ ሲያጥራቸው ልብሶቹን በአነስተኛ ዋጋ ሽጠውም ቢሆን ማደሪያቸውን ያስቀድሙ ነበር። በእንዲህ አይነት ስራ የዕለት ጉርሳቸውን በመሸፈን ህይወታቸውን ለመታደግ ጥረት ያደርጉ ነበር፡፡
በስራው ላይ እያሉ ግን ቀበሌ በመመላለስ «የንግድ ቤቴ ተወርሶብኛልና የመኖሪያ ቤትም ስለሌለኝ ቢያንስ ጎኔን የማሳርፍበት ቤት ይሰጠኝ» እያሉ መወትወታቸውን አላቋረጡም። ቀበሌውም የቤት ችግረኛ ናቸው በሚል ከብዙ ክርክር በኋላ አንድ አነስተኛ የመንግስት ቤት ሰጣቸው። ማረፊያቸውን ያገኙት ነጋዴ ታዲያ ትዳር መስርተው አንድ ልጅ ወለዱ። የልብስ ንግዱንም ቀስበቀስ ሊያሳድጉ ቢሞክሩም የቤተሰብ ቀለብ፣ የትምህርት ወጪ እና ሌሎችም ቀዳዳዎችን ለመሸፈን በሚያወጡት ወጪ ሱቅ ከፍተው መስራት አልቻሉም ነበር። እናም ወደተክለሐይማኖት አካባቢ ሔደው ልብስ በመተኮስ ተጨማሪ ገቢ መሰብሰብ ጀመሩ።
ልብስ መሞሸር
አሁን ቤተሰባቸውም እየሰፋ በየዓመረቱ ቁጥሩ እይጨመረ በመሆኑ ገቢያቸውንም ማሳደግ እንዳለባቸው ወስነዋል። በመጨረሻ ደግሞ አሮጌ አልባሳት በብዛት ለገበያ በሚቀርቡበት ወደ ቀራንዮው መንዲዳ ገበያ አመሩ። ቦታው በላስቲክ እና ሸራ የተሸፈኑ በርካታ ጊዜያዊ ሱቆች ይበዙበታል። በቦንዳ የታሰሩ ልብሶች ሲፈቱ ያም ያም እጁን እየሰነዘረ «ልግዛው ልግዛው ስንት ነው?፤ ይሄን ያህል» እየተባባለ ድምጹን ከፍ አድርጎ የሚያወራበት ቦታ በመሆኑ ሁካታ እና ግርግር ይበዛበታል።
በገበያ ስፍራው ደግሞ ከአሮጌ ልብስ ሽያጩ በተጓዳኝ አስፈላጊ የሆነውን የልብስ ተኩስ ስራ የሚያከናውኑ ጠቆር ያሉ ሰው በስተግራ በኩል በተንጠለጠሉ ሱሪ እና ጃኬቶች ተከበው ይታያሉ። የህይወትን ውጣ ውረድ ለማሸነፍ በከሰል የጋለ የልብስ መተኮሻ ይዘው በየቀኑ የተጨማደዱ እና ታጥበው ያልደረቁ አሮጌ ልብሶችን የሚሞሽሩትና ባለብረት ያረጀች የከሰል ካውያ ባለቤት አዛውንቱ አቶ መውለድደግ ናቸው።
«በየቀኑ የ20 ብር ከሰል እገዛለው፤ ከሰሉን ካያያዝኩ እና ባለብረት ካውያዋን አፍ ከፍቼ ፍሙን ከስገባሁ በኋላ ቢያንስ እስከ 11 ሰዓት ድረስ 100 የተለያዩ አልባሳትን እተኩሳለሁ» በማለት ይናገራሉ፡፡ ለአንድ የተጨማደደ ሱሪ ሶስት ብር የሚከፍሉ ቢኖሩም ለሸሚዝ ደግሞ አምስት ብርም የሚከፍሉ አሉ። በመሆኑም የአዛውንቱ የቀን ገቢ ቢያንስ ከሶስት መቶ ብር በላይ መገመት አያዳግትም። ይሁንና አንዳንድ ጊዜ ኪሳራ ሊያጋጥም እንደሚችል አጫውተውኛል።
ድንገት ጨዋታ ይዘው እንዲተኩሱ የተሰጣቸውን ልብስ በካውያ ቢቃጠል ከደንበኞቻቸው ጋር ጭቅጭቅ ውስጥ ከመግባታቸው ባለፈ ኪሳራውን መጋራት እንደሚጠበቅባቸው ይገልፃሉ። «እንዲተኮስለት ልብሱን የሰጠ ነጋዴ ተመልሶ ሲመጣ ልብሱ በካውያ ከተቃጠለ በድርድር ኪሳራውን በጋራ ለማድረግ ስምምነት ለማድረግ ጥረት አደርጋለሁ። አለፍ ካለም የተናደደ ሰው ሙሉውን ሊያስከፍለኝ ይችላል። ይሁንና ሁል ጊዜም የማያጋጥም በመሆኑ ገቢ መገኘቱ አይቀርም» ይላሉ።
እናም በየቀኑ ከተኮሷቸው ልብሶች የሚያገኙትን ገንዘብ ይዘው ስምንት ቤተሰብ ያስተዳድራሉ። በዚሁ ስራ ልጆችን አስተምረው ለወግ ለማዕረግ ማድረስ እንደቻሉ ይናገራሉ። በእያንዳንዷ ቀን የምትገኝ አንድ ብር ለእርሳቸው ዋጋ አላት፤ ምክንያቱም ቤታቸው ውስጥ የሚጠብቋቸው ልጆቻቸውን የሚያለብሱት፣ የሚያጎርሱት አለፍ ብሎም ህይወታቸውን የሚያቆዩት በዚህችው በየቀኑ በምትጠራቀም ገንዘብ አማካኝነት በመሆኑ ነው፡፡
አዛውንቱ ልብስ ተኳሽ የመጀመሪያ ልጃቸውን በነርሲንግ ሙያ አስመርቀው ስራ አስይዘዋል። ሁሉንም ልጆቻቸውን በዚሁ ሙያ እያስተማሩ ያኖሩት እኚሁ ሰው የመጨረሻ ልጃቸው ሰባት ዓመቱ ነው። ባለቤታቸው ደግሞ የቤት እመቤት በመሆናቸው ገቢ የማምጣቱ ሙሉ ኃላፊነት በእርሳቸው ላይ መውደቁን ጠንቅቀው ያውቃሉና በየእለቱ ሳይዘናጉ በጠዋት እንደሚነሱ ነው የሚናገሩት።
ቀጣይ ጉዞ
«አንድም ቀን ጎዳና ላይ ወጥቼ የሰው እጅ ለማየት አልፈልግም» የሚሉት አቶ መውለድደግ፤ በልብስ መሞሸር ስራቸው ብቻ ኑሮን መግፋቱ እየከበዳቸው እንደመጣ የሚሸሽጉት ሃቅ ግን አልሆነላቸውም። ከዕጅ ወደአፍ የሆነ ኑሯቸውን ለመግፋት እና ቤተሰባቸውን ለማስተዳደር ቢጠቅማቸውም የተሻለ ለማድረግ ግን ሁልጊዜም ሃሳባቸው ነው። እጃቸው አጥሮ ጠርቀም ያለ ገንዘብ ባለማግኘታቸው ወደቡቲክ ንግድ መሸጋገር እንዳልቻሉ አጫውተውኛል።
በተለይ ደግሞ በገንዘብ የሚረዳቸው ሰው ባለመኖሩ ንግዳቸውን ማሳደግ ብሎም ሕይወታቸውን የተሻለ ማድረግ አልቻሉም። ይሁንና መስከረም ሲጠባ ከአሮጌ ልብሱ ተኩስ ስራ ጎን ለጎን ልብሶቹንም በቦንዳ እያሸጉ ወደተለያዩ ክፍላተ ሀገራት ለመላክ አቅደዋል። ለዚያም ደፋ ቀና እያሉ እየሰሩ ይገኛል። በዚህ ጥረታቸው ላይ ግን የከተማ አስተዳደሩም ሆነ ግለሶቦች ድጋፍ ቢያደርጉላቸው የተሻለ ሕይወትን መምራት እንደሚችሉ በመግለጽ ጥሪ ያቀርባሉ።
ለብዙዎች ተምሳሌት የሚሆኑት አዛውንት የነገው ትውልድ አካል የሆኑ ልጆቻቸውን ጥረው ግረው ለመልካም ነገር ለማብቃት እየታተሩ ይገኛል። ይህ ይበርቱ የሚያሰኝ ተግባራቸው ታዲያ ጉልበት እና ዕውቀት ይዘው በተለያዩ አልባሌ ቦታዎች ለሚገኙ ወጣቶችም ተምሳሌት የሚሆን ስራ ነውና ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ባዮች ነን፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሀምሌ 20/2011
ጌትነት ተስፋማርያም