ታራሚዎች በሥነ ምግባር የታነጹ እንዲሆኑ ማረሚያ ቤቶች በትብብር መሥራት ይኖርባቸዋል

ቢሾፍቱ፦ ታራሚዎች ወደ ማህበረሰቡ ሲቀላቀሉ በሥነ ምግባር የታነጹና የተሻለ አምራች ዜጋ እንዲሆኑ ማረሚያ ቤቶች በትብብር መሥራት አለባቸው ሲሉ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ ምህረት ገለጹ።

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ ምህረት 19ኛው የፌዴራል እና የክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽነሮች የጋራ ጉባኤ “ማረሚያ ቤቶችን በአዲስ አስተሳሰብ ወደ አዲስ ምዕራፍ” በሚል መሪ መልዕክት ትናንት በቢሾፍቱ ከተማ መካሄድ ሲጀምር እንደተናገሩት፤የፍትሕ ሥርዓቱ ያሉበትን ችግሮች ለመፍታት የዘርፉ ተቋማት ቅንጅታቸውን በማጠናከር ተግባሮቻቸውን መከወን አለባቸው። ታራሚዎች ወደ ማህበረሰቡ ሲቀላቀሉ በሥነ ምግባር የታነጹና የተሻለ አምራች ዜጋ እንዲሆኑ ማረሚያ ቤቶች በትብብር መሥራት ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡

የማረሚያ ቤቶች ኮሚሽነሮች ጉባኤም የፍትሕ ሥርዓቱን በማሻሻል የሕግ የበላይነትን ለማስጠበቅ የጋራ አረዳድና ግንዛቤ መፍጠር እንደሚያስችል የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፤ በአዋጁ 1231/2013 መሠረት ተቋማት በተናጠል ከሚሠሩት ባሻገር ቅንጅታዊ ግንኙነት እንዲኖራቸው ያስፈልጋል። ሀገራዊ ግብን፣ የጋራ ራዕይንና የወል መዳረሻን እውን ለማድረግ በቅንጅታዊ አሠራር የጋራ ሀገራዊ እይታ መፍጠር ወሳኝ ነው ብለዋል።

ከምንከተለው የአስተዳደር ሥርዓት አንፃር ለተቋማትና ለክልሎች የተሰጡ የተናጠል ሠልጣኞች እንደተጠበቁ ሆኑ በቅንጅት መሥራት በሚገባቸው ሥራዎች ላይ ትኩረት በማድረግ የሕግ ታራሚዎች የተሻለ ዜጎች ሆነው ከኅብረተሰቡ ጋር በቀላሉ መቀላቀል እንዲችሉ መሥራት ያስፈልጋል ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ታራሚዎች ወደ ማህበረሰቡ ሲቀላቀሉ በሥነ ምግባር የታነጹና የተሻለ አምራች ዜጋ እንዲሆኑ ማረሚያ ቤቶች በትብብር መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የፍትሕ ሥርዓቱን ለማሻሻል የዘርፉን ተቋማት ቅንጅታዊ አሠራር ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ኮሚሽነር ከጄነራል የኑስ ሙሉ በበኩላቸው፤ የሕግ ታራሚዎች በሥነ ምግባር የታነጹ፣ አምራችና ሕግ አክባሪ ዜጎች እንዲሆኑ ተቋማዊ ሪፎርም መደረጉን የገለጹት ኮሚሽነሩ፤ በሪፎርሙም ታራሚዎች ዘመናዊ ትምህርትና ሥልጠና ወስደው ሕግ አክባሪ እንዲሆኑ የሚያስችል አሠራር መዘርጋቱንም ገልጸዋል።

ማረሚያ ቤቶች የሕግ ታራሚዎች ታርመው ሕግ አክባሪ ሆነው የሚወጡበት ሥፍራ እንዲሆኑ የሪፎርም ሥራዎቹን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ የሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።

ለሦስት ቀናት በሚዘልቀው ጉባኤ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትንት፣ የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር እና የፌዴራልና የክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽነሮች እየተሳተፉ እንደሚገኙ ታውቋል።

ተስፋ ፈሩ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ግንቦት 21 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You