የቅናት ዛር

ቅናት በሕይወት ውስጥ መርዛማ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው። የጓደኝነትን ክር የሚበጥስ ከሰው ጋር ያለ ግንኙነትን የሚያጠለሽ ነው ቅናት። የራስ ያሉትን የሚየሳጣ የሌላውንም ሕይወት የሚረብሽ እስከ ነፍስ ጥፋት የሚያደርስ ነው ቅናት። ቅናት ውስጥን አብግኖ የሚገድል ከባድ ስሜት ነው።

ቅናት የሰዎችን ውስጥ የሚበላ በጣም ደስ የማይል አሰቃቂ ስሜት ነው። ይህ አሰቃቂ ሰሜትም የሰዎች ንፁህ ሕልሞች ይመርዛል። በዚህም ምክንያት ቅናት ሰዎችን ቅር የሚያሰኝና መራር ሕመም ትቶ የሚያለፍ ጉዳይ ነው።

ቅናት ለአንዳንዶች በተለይ ወጣት ወንዶች እና ሴቶች መካከል ለፍቅር ወሳኝ እይታ ነው ብለው ያምናሉ። ቅናት የፍቅር ማጣፈጫ እንደሆነ የሚያምኑ ቢኖሩም በቅናት የተነሳ ቤት ንብረታቸውን ያጡ፤ ከንብረትም በላይ የቤተሰብ ፍቅር የተነጠቁትን ቤት ይቁጠራቸው።

የቅናት ስሜት ሚስት ወይም ባል ላይ እኩል ጥቃት የሚያደርስ ጉዳይ ነው። በቤተሰብ ሕይወት ውስጥ ችግሮች ብዙ ይፈጥራል። ብዙውን ጊዜ እንዲህ ያለ ነገር ፍቺን፤ አካላዊ ጥቃትን፤ የመንፈስ ጭንቀት የመሳሰሉ ሁኔታዎችን የሚያመጣ ነው።

ከላይ ያነሳነው የቅናት ጉዳይ ሳይሸነቁጠው ያለፈ ሰው ይኖራል ተብሎ ባይገመትም ለዛሬ የተዘጋው ዶሴ አምድ ይዘንላችሁ የመጣነው ጉዳይ እንዲህም ያለ ቅናት አለ እንዴ የሚያሰኝ ነው። ይህን መረጃ በዚህ መልኩ ለአንባቢ እንዲደርስ ለፈቀዱልን የአዲስ አበባ ፖሊስ መዝገብ ቤት ባልደረቦች አመስግነን ፅሁፉን እንድታነቡት ጋብዘናል።

ሮባ አበበ የተባለ ግለሰብ ሚስቱን ከምንምና ከማንም በላይ አብልጦ ይወዳት ነበር። መውደድ በዝቶብት አቅሉን አስቶታል ቢባልም ሀሰት ነው የሚል ሰው አይገኝም ነበር። ሚስቱን ከመውደዱ የተነሳ ፍቅሩ ወደ እብደት ተቀይሮበታል። በዚህም የተነሳ ያየ ያነጋራትን ሰው በሙሉ ባገኘው ነገር መምታት፤ ሄዶ መደባደብ ዋናው ሥራው ሆነ።

ከሥራ በሰበብ በአስባቡ እየቀረ ሚስቱን መከታተል፤ መግቢያ መውጫ ማሳጣት ቋሚ ተግባሩ አደረገው። ድንገት መንገድ ላይ ሰው አግኝታ ከቆመች ሴቶቹን ለሌላ ወንድ ሊያቃጥሯት ነው በማለት አስበርግጎ ያባርራቸዋል። ወንዶቹን ሲፈልግ በስድብ ባስ ሲል ደግሞ በዱላ አንክቶ አንክቶ መልቀቅ ልዩ ምልክቱ ሆነ። አብዛኛው የሰፈራቸው ሰው ሚስቱን ማናገር አይደለም ስለሚስቱ ማሰብ በጭራሽ አይፈልጉም ነበር። ማኅበራዊ ሕይወት የሚባለውን ነገር ከቤታቸው አውጥቶ ከጣለ በኋላ በሀዘንም ሆነ በደስታ እሱም ሆነ ሚስቱም ከሰው መቀላቀል አቆሙ።

የግድ መሄድ ያለባት ለቅሶ እንኳን ቢኖር እሱ መርጦ አልብሶ አጅቦ አድርሶ ይዟት ይመለስ ነበር። ከቤት ውጭ ወላጆቿ ጋር እንኳን ቢሆን ማደር አይፈቅድላትም ነበር።

ሚስቲትም ከወዳጅ ጎረቤት ተቆራርጣ አንድ መተንፈሻዋ የሆነውን ሥራዋን እንዳታጣ ተግታ ትሰራ ጀመር። አርፋጅ ላለመሆንም ማልዳ ከቤታ ወጥታ አመሻሽ ላይ ወደ ቤቷ ትመለስ ጀመር። ሥራዋ ባለቤቷ ከሚያደርስባት ተፅእኖ መደበቂያም ስለሆናት ቢያማት እንኳን መቅረት አትፈልግም ነበር

ከእለታት በአንዱ ቀን

ሮባ ሚስቱ በጠዋት ተነስታ ሥራ መሄዷና ከሰው ሁሉ ኋላ መምጣቷ እጅግ በጣም እየከነከነው መምጣት ጀመረ። በየመንገዱ ከሰው እየተጣላ ያስቸገራትን ባል ሽሽት በሻርፕ ተሸፋፍና ስለምትወጣ ከመንገድ ላይ ፀብ ተገላግላለች። እሱም ቢከተል ቢከታተል እንከን የሚባል ነገር ስላጣባት አይኑን ወደ ምትሰራበት ትምህርት ቤት አዙሯዋል።

በንግግሯ መካከል እንኳን ተሳስታ የወንድ ስም ከጠራች ተከታትሎ የሚያጠቃው ባል አሁን ሚስቱን እያሽኮረመመ ይሆናል ብሎ ያሰበውን ሰው ለማግኘት መረቡን ጎፋ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ላይ ጥሏል። ሥራውን በሰበብ አስባቡ እያስተጓጎለ ሚስቱን የሚከታተለው ባል ሚስቱ አንድ ወንድ ጓደኛ እንዳላት ይመለከታል።

ነገሩን ለማረጋገጥ የንዴቱ መጠን ባይፈቅድለትም ያን ቀን ግን ምንም ሳይናገር ወደ ቤቱ ይሄዳል። ማታም ሚስቱን ምንም ሳይል አድሮ በቀጣዩ ቀንም ምቹ ቦታ ፈልጎ ትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ ገብቶ ይደበቃል። ማንም ሳያየው ከተማሪዎች ጋር ተቀላቀሎ በመግባት ያደፈጠው ሮባ ዳግም ባለቤቱ ከጓደኛዋ ጋር ወጣ ገባ ስትል ያመለክታል።

በአንድም በሌላም ምክንያት ፈገግታ ያቆመችው ሚስቱ የሚወድላተን ውብ ጥርሷን ለእሱ ነፍጋ ለወንድ ጓደኛዋ ማሳየቷ እርር ድብን አድርጎ ቆሽቱን አሳረረው። ምንም አሮ ቢደብንም እንኳን የሆዱን በሆዱ ይዞ ባላጋራውን እስከ ወዲያኛው ለማጥፋት ያቅድ ጀመር።

ባላጋራዬ ነው ብሎ ያሰበውን የናኒሳን ትንፋሽ እስከ ወዲያኛው ለማቋረጥ ምቹ ጊዜና ሁኔታ መጠበቅ ጀመረ። ወጥቶ እስኪገባ ድረስ የማይለየውን የተሳለ ቢላ ተጠቅሞ የሚስቴ ውሽማ ነው ያለውን ሰው ነፍስ ለማጥፋት ያደባ ጀመር።

ክፉዋ ቀን

ናኒሳ ተጫዋች ተግባቢ ወጣት መምህር ነው። ቋንቋው ያማረለት በትምህርት ቤቱ ከሚደነቁ መምህራን መካከል አንዱ ነው። በግቢው ማኅበረሰብ በሙሉ ጥሩ ተቀባይነት ያለው ይህ ወጣት በተይም ከሮባ ባለቤት ጋር የልብ ጓደኝነት መስርተዋል።

ያጋጠማቸውን ክፉም ይሁን ደግ ነገር የሚካፈሉት እነዚህ ጓደኛሞች አንዳቸው የአንዳቸውን ጭንቀት በማቅለል ረገድ ወደር አይገኝላቸውም ነበር። የሮባ ባለቤትም የቤቷን መከፋት በሙሉ የሚጋራት እንደ ወንድም የሚሳሳላትና የሚረዳት ጓደኛ ማግኘቷ ብዙ ሸክምን አቅልሎላታል።

ምንም እንኳን ጓደኝነታቸው ከወንድማዊና ከእህታዊነት ባያልፍም ባል ሌላ ግንኙነት ያላቸው ስለመሰለው ሊያጠፋው ያደባ ጀመር።

ናኔሳ ከሚስቴ ጋር የፍቅር ገንኙነት አለህ በማለት ቂም ይዞ የቆየው ሮባ እጀታው የእንጨት የሆነ ቢላ ለዚሁ የወንጀል ድርጊት እንዲሆነው በማሰብ ቀደም ብሎ ገዝቶ ካስቀመጠበት ቁም ሳጥን ውስጥ በማውጣት በሆዱ ሽጦ ወደ ሟች ተጠጋ።

ሟችም የጓደኛው ባለቤት መምጣቱን ሲመለከት በፍቅርና በአክብሮት ሊቀበለው ብድግ ባለበት ነበር በስለት በመውጋት ጉዳት ያደረሰበት።

ወንጀሉ በትምህርት ቤት ግቢ ወስጥ በመፈፀሙ መምህራንና ተማሪዎች ላይ ድንጋጤም ፈጥሮ ነበር። በእለቱ ድርጊቱ እንደተፈፀመ በአቅራቢያው የነበሩ ፖሊሶች በመድረስ ወንጀል አድራጊውን በቁጥጥር ስር አውለው የሟችን አስክሬን ወደ ሆስፒታል ላኩ።

የፖሊስ ምርመራ

ፖሊሶች በአካባቢው እንደደረሱ የሟች አስክሬን መሬት ላይ ወድቆ የተመለከቱ ሲሆን ሌሎች ሁለት ግለሰቦችም ላይ በስለት ጉዳት እንደደረሰባቸው ማየት ቻለ። ፖሊስ አንቡላንስ በማስመጣት ጉዳት የደረሰባቸውን ሕክምና እንዲያገኙ ልኮ ያረፈውን ሰው አስክሬን ወደ ፎረንሲክ ምርመራ ክፍል እንዲገባ ያደርገዋል።

ወንጀለኛው አስቦና አልሞ ሰው ለመግደል ባዘጋጀወ ስለት የሰው ነፍስ ማጥፋቱን በ አይን ምስከሮችና በእምነት ክህደት ቃሉ የተረዳው ፖሊስ ወንጀለኛው በፈፀመው ከባድ የሰው ግድያ ወንጀል፤ እና በተመሳሳይ በ2ኛ እና በ3ኛ ክሱ ላይም ተከሳሽ በያዘው ስለት በመውጋት በሁለት ግለሰቦች ላይ ጉዳት ያደረሰባቸው በመሆኑ በፈፀመው ተራ የሆነ የሰው ግድያ ሙከራ ወንጀል ክስ ተመሰረተበት።

ምርመራው እንደተጠናቀቀ በፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በመላክ ክስ እንዲመሰረትበት አድርጓል።

የአቃቤ ሕግ ክስ ዝርዝር

በፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ የክስ ዝርዝር እንደሚያመለክተው ሮባ አበበ የተባለው ተከሳሽ በተለያየ 3 ክሶች የተከሰሰ ሲሆን በአንደኛ ክሱ ላይ ተከሳሽ ሰውን ለመግደል አስቦ መጋቢት 27 ቀን 2015 ዓ.ም ከቀኑ 5፡25 ሰዓት ሲሆን በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 05 ጎፋ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የመምህራን ማረፊያ ክፍል ውስጥ ሟች ናኔሳ በሻዳ የተባለውን ግለሰብ ከሚስቴ ጋር ግንኙነት አለህ በማለት ቂም በመያዝ እጀታው የእንጨት የሆነ ቢላ ለዚሁ የወንጀል ድርጊት ቀደም ብሎ ገዝቶ ካስቀመጠበት ቁም ሳጥን ውስጥ በማውጣት ሟችን በስለት በመውጋት ጉዳት በማድረሱ ምክንያት ሕይወቱ ያለፈ በመሆኑ በፈፀመው ከባድ የሰው ግድያ ወንጀል፤ እና በተመሳሳይ በ2ኛ እና በ3ኛ ክሱ ላይም ተከሳሽ በያዘው ስለት በመውጋት በሁለት ግለሰቦች ላይ ጉዳት ያደረሰባቸው በመሆኑ በፈፀመው ተራ የሆነ የሰው ግድያ ሙከራ ወንጀል በፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ሰው ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት በፈፀመው ወንጀል ክስ አቅርቦበት ክርክር ሲደረግ ቆይቷል፡፡

                                                            ውሳኔ

በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ሰው ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት በፈፀመው ወንጀል ክስ አቅርቦበት ክርክር ሲደረግ ከቆየ እና ተከሳሽ በክርክሩ ሂደትም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ከተሰማ በኋላ ተከሳሽ እንዲከላከል ብይን ተሰጥቶ ተከሳሽ የመከላከያ ምስክር አቅርቦ ያሰማ ቢሆንም በዐቃቤ ሕግ የቀረበበትን ክስ መከላከል አልቻለም።

ተከሳሽም ክሱን ማስተባበል ባለመቻሉ ምክንያት በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ሰው ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት ባስቻለው ችሎት በተከሳሽ ላይ የጥፋተኛነት ፍርድ በመስጠት የቅጣት ውሳኔ በማሳረፍ በ14 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ሲል ወስኗል፡፡

አስመረት ብስራት

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 6 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You