
አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነችውና ትኩረቷን በሕጻናት ላይ ያደረገች በአፋን ኦሮሞ በየወሩ የምትታተም ‹‹ናኦታ ›› የተሰኘች የሕጻናት መጽሔት ለንባብ አበቃ፡፡
በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የናኦታ የሕጻናት መጽሔት እና የበሪሳ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ቸርነት ሁንዴሳ እንደተናገረው፤ መጽሔቷ በአፋን ኦሮሞ ተዘጋጅታ በየወሩ የምትታተም ናት፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ታትማ በየካቲት ወር መጨረሻ በገበያ ላይ ውላለች ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የሕጻናት መጽሔት በተለያዩ ቋንቋዎች በማሳተም ቀዳሚ መሆኑን የገለጸው ጋዜጠኛ ቸርነት፤ ናኦታ መጽሔት በተለይ እንደ አፋን ኦሮሞ ፈር ቀዳጅ መሆኗን ጠቁሟል፡፡
እንደ ዋና አዘጋጁ ገለጻ፤ መጽሔቷ 40 ገጾች እና የናኦታ መልዕክትን (ርዕሰ አንቀጽን) ጨምሮ 20 ዋና ዋና ርዕሶችን አካታ የያዘች ናት፡፡ መጽሔቷ ሕጻናትን ማዕከል አድርጋ የምትዘጋጅ ናት፡፡ ከይዘት አንጻር በርካታ የሕጻናት ጉዳዮች የሚዳሰሱባት በመሆኗ ሕጻናትን እያዝናናች ትልቅ ቁም ነገር የምታስጨብጥ እንዲሁም በመልካም ሥነ ምግባርና አስተዳደግን በማስተማርና በማሳወቅ ለነገ ሀገር ተረካቢ ዜጋ ለማፍራት ያላት ሚና ከፍተኛ ነው፡፡
ናኦታ መጽሔት ሕጻናት በአዕምሮ ብስለት እንዲጎለብቱ ከማገዝ ጎን ለጎን ሕጻናቱ ቋንቋቸውንና ባሕሎቻቸውን አውቀው እንዲያድጉ ትልቅ መሠረት የምትጥል መሆኗን ጋዜጠኛ ቸርነት አመልክቶ፤ በተጨማሪም አካባቢያቸውንና ሀገራቸውን የሚያው ቁበት ዕድል የምትፈጥር መሆኑን ገልጿል፡፡
መጽሔቷ ከያዘቻቸው ርዕሶች አኳያ ስለሀገራቸው ከማወቅ በተጨማሪ ሕጻናት የቴክኖሎጂ ዝንባሌ እንዲኖራቸው እንዲሁም የፈጠራ ባለቤት እንዲሆኑ ዕድል የሚያመቻች መሆኑን ጋዜጠኛ ቸርነት አስረድቷል።
እንደ ዋና አዘጋጁ፤ መጽሔቷ በልዩ ፈጠራና ጥንቃቄ የምትዘጋጅ ወርሐዊ መጽሔት መሆኗን ጠቅሶ፤ ሕጻናት አዳዲስ ነገር የሚቀስሙባት፣ የኑሮ ዘይቤ ከታላላቆቻቸው የሚወስዱባትና ለነገ ሕይወታቸው አብነት የሚሆኗቸው በየዘርፉ ታላላቅ ታሪኮችን ሠርተው ያለፉ ሰዎች የሚያስተምሩበትና ልምዳቸውን የሚያካፍሉበት መድረክም ናት፡፡
አባ መላ፣ ኩንስ ቢየ ኮት፣ ዋልትነ፣ አፎለ፣ ካሜቱማ፣ ፋነ ጎቶታ መጽሔቷ ከያዘቻቸው ዋና ዋና ርዕሶች መካከል እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል፡፡
መጽሔቷ በአጠቃላይ ሕጻናት የሚማሩበት፣ ልምድ፣ የሚቀስሙበትና ስለሀገራቸው የሚያውቁበት ዓምዶችን (ርዕሶችን) በይዘት ማካተቱንም አመልክቷል፡፡
መጽሔቷ በትምህርት ቤቶች፣ በሕጻናት ማሳደጊዎች እና ሕጻናት ላይ የሚሠሩ ድርጅቶች፣ ጨምሮ በድርጅቱ የመሸጫ ሱቆች ላይ ማዕከል ተደርጎ እየተሰራጨች እንደምትገኝ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ከጥቂት ወራት በፊት ‹‹ብላቴናት›› የተሰኘች በአማርኛ ቋንቋ የምትታተም የሕጻናት መጽሔት ለንባብ ማብቃቱ የሚታወስ ነው፡፡
ልጅዓለም ፍቅሬ
አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 5 ቀን 2017 ዓ.ም