
አዲስ አበባ፡-ሀገር አቀፋዊ የቁርኣን ውድድሩ ለሀገር ሰላም፤ እድገት፤ ሥልጣኔ እና የማኅበረሰብ ከፍታን ለማረጋገጥ እራሱን የቻለ ሚና እንዳለው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አስታወቀ።
‹‹ቁርኣን የእውቀትና የሰላም ምንጭ›› በሚል ሀሳብ ሀገር አቀፍ የቁርኣን ሂፍዝ የክልሎች የማጣሪያ ውድድር የመክፈቻ ፕሮግራም በአዲስ አበባ በትናንትናው ዕለት ተካሂዷል።
የውድድሩ የመክፈቻ ፕሮግራምን አስመልክተው ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ እና የውድድሩ አስተባባሪ ኡስታዝ አቡበከር አሕመድ፤ ቁርኣን ለሀገር ሰላም እና እድገት እንዲሁም ለማኅበረሰብ የሥልጣኔ ከፍታን ለማረጋገጥ እራሱን የቻለ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
ቁርኣን የሰው ልጆችን በሥነምግባር የሚገራ ለማኅበረሰብ እውቅና በመስጠት መተባበርንና መደጋገፍን የሚያጎለብት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ቁርኣን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለተከሰቱ ታሪካዊ ክስተቶች እና ችግሮች መፍትሔ በመስጠት ሚና እንዳለው የሚገልጹት ኡስታዝ አቡበከር፤ አሁንም በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ጉዳዮች፣ ለሰላም፣ ለእውቀት፣ ለአብሮነት እና ለመከባበር የራሱ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል፡፡
ኡስታዙ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ግለሰቦች እና ድርጅቶች አዘጋጅነት የቁርኣን ሂፍዝ ውድድር መደረጉን ገልጸው፤ የዘንድሮው ውድድር ግን ቁርኣን በሚገባው ክብር እና ቦታ እየተደረገ እንደሚገኝም አብራርተዋል፡፡
ሀገር አቀፋዊ የቁርኣን ውድድሩ ለሀገር ሰላም፤ እድገት፣ ለማኅበረሰብ እውቅና ለመስጠትና ቁርኣንን የተሸከሙ ወጣቶችን ወደ ፊት ለማምጣት የሚጠቅም መሆኑን የሚገልጹት ኡስታዝ አቡበከር፤ መድረኩም በዚህ ቅርጽ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡
ለተወዳዳሪዎቹም ውድድር ስለሆነ ብቻ ደረጃ የሚሰጥ እንጂ ሁሉም በያዙት ቁርኣን አሸናፊዎች መሆናቸውም ገልጸዋል፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ እየተካሄደ ያለውን የቁርኣን ውድድር አስመልክተው ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሸይክ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ በበኩላቸው፤ የረመዳንን ፆም ለማደናቀፍ የሚሰነዘሩ ትንኮሳዎችን ባለማባባስ፣ ባለማባዛት በትዕግስት ማሳለፍ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ቁርኣን ሰላምና አብሮነትን የሚያስተምር በመሆኑም ልናከብረው እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
የረመዳን ወርም የሰላም ወር መሆኑን ገልጸው፤ ሰላም ከሌለ ምንም ነገር የለም፡፡ ለሰላም ሁላችንም ዘብ ልንቆም ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
ውድድሩ በሀገር አቀፍ ደረጃ የመጀመሪያው መሆኑን እና ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል፡፡
የቁርኣን ውድድሩም መጋቢት 7 በመስቀል አደባባይ የማጠናቀቂያ መርሐ ግብር የሚኖር ይሆናል፡፡
መክሊት ወንድወሰን
አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 5 ቀን 2017 ዓ.ም