“የትግራይ ሕዝብ የሚፈልገው ሰላም እና ልማት ነው” – አቶ ጌታቸው ረዳ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ትናንት አዲስ አበባ ሸራተን አዲስ ሆቴል በክልሉ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ መግለጫ ሰጥተዋል። በወቅቱም ጋዜጠኞች የተለያዩ ጥያቄዎችን አቅርበዋል። ከእነዚህም ፡-የፌዴራል መንግሥት በክልሉ ጉዳይ ጣልቃ እንዲገባ ጊዜያዊ መንግሥቱ ጥሪ አቅርቧል ወይስ አላቀረበም ? የትግራይ ክልል ጉዳይ ሕዝቡን እያስጨነቀው ይገኛል፤ ክልሉ ወደየት እየሄደ ነው? የፕሪቶሪያው ስምምነት ዓላማው ምን ነበር? ወሰኑስ እስከምን ድረስ ነው? እንዴት እየተፈጸመ ነው? ምን ምን ተግዳሮቶች አጋጥመዋል? አሁን ያለው የትግራይ ወቅታዊ ሁኔታ ምን መልክ አለው? የሻዕቢያ መንግሥት ከሕወሓት ጥቂት ኃይሎች ጋር ግንኙነት እንዳለው ይሰማል፤ ይህ ምን ያህል እውነት ነው? በክልሉ የሻዕቢያ ሚና እና ተጽእኖ እንዴት ይገለጻል? ክልሉ የማዕድን ሀብቱን እንዴት እየተቆጣጠረ ነው? በማዕድን ንግድ ላይ ያለውን ሕገ-ወጥ ሥራ ለማስቆም ምን አድርጓል? በክልሉ የሚደረገው ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴ የመፈንቅለ መንግሥት መልክ ያለው ነው ይላሉ? የሚሉና ሌሎችም ጥያቄዎች ቀርበውላቸዋል። የፕሬዚዳንቱን ምላሽ ክፍል በሚከተለው መልኩ አቅርበነዋል።

አቶ ጌታቸው ረዳ ፦ መጀመሪያ የተነሳው ጥያቄ ከፌዴራል መንግሥት ጣልቃ ገብነት ጋር የተያያዘ ነው። የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ ያቀረብነው ፎርማል ጥያቄ የለም። በሁለት ምክንያቶች፤ ጊዜያዊ አስተዳደሩ በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት በሕወሓት እና በፌዴራል መንግሥቱ የተቋቋመ ነው። ስለዚህ የፌዴራል መንግሥቱ በራሱ ተሳትፎና በራሱ ፈቃድ የተቋቋመ መንግሥት አደጋ ላይ በሚወድቅበት ጊዜ አደጋውን የመቀልበስ ግዴታ ይኖርበታል።

ሌሎች ክልሎች የክልል አቅም የሚሉትን ሁሉንም ነገር ተጠቅመው አንድን ነገር መቆጣጠር አቅቶኛል በሚሉበት ሰዓት ምክር ቤት ጠርተው የፌዴራል መንግሥትን ጣልቃ እንዲገባ ይጠይቃሉ። አሁን ባለንበት የትግራይ ሁኔታ በእንደዚህ አይነት መልኩ ተሰብስቦ ጥያቄ ሊያቀርብ የሚችል ምክር ቤት የለም። ያ ማለት የፌዴራል መንግሥቱ ሊሠራቸው የሚገቡ ሥራዎችን በተመለከተ አስታዋሽ ያስፈልገዋል ማለት አይደለም።

በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በብዙ የትግራይ አካባቢዎች የፌዴራል ኃይል ነበር። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የለም። የጊዜያዊ አስተዳደሩ በሚያስተዳድራቸው አካባቢዎች ነበረ። ከእነዚህ አካባቢዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወጥቷል። በአሁኑ ሰዓት ትግራይ ውስጥ እየተፈጠረ ያለው ቀውስ አንድ የሕግ ተቀባይነት ያጣ የሕወሓት አንጃ ጉባዔ አድርጌያለሁ ስላለ ደጋፊዎቼ የሚላቸውን መኮንኖች በመያዝ እየሠራቸው ያሉ ሥራዎች ናቸው።

ይሄንን ሥርዓት ለማስያዝ በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ውስጡ ያለውን አቅም መጠቀም የሚያስችለው ዕድል ነው እየተነፈገ የመጣው በዚህ ሰዓት የፌዴራል መንግሥቱ ሁኔታውን ለማረም አግባብነት ያላቸውን ርምጃዎች መውሰድ አለበት ፤ይህን ስንል፣ ጦር አዝምቶ ጦርነት ይቀስቅስ እያልን አይደለም። በነገራችን ላይ አሁን እያደረግነው ያለው እንቅስቃሴ እያንዣበበ ያለውን ጦርነት ሊያስቀር የሚያስችል ሁሉንም አይነት ርምጃዎች ፌዴራል መንግሥቱ መውሰድ አለበት ብለን ስለምናምን ነው።

እኔ እንደ ጊዜያዊ አስተዳደር ዋናው ራስ ምታቴ በአንድም በሌላም መንገድ ትግራይ ውስጥ ሌላ ጦርነት ተከፍቶ ሕዝባችን መከራ ውስጥ የሚገባበትን ሁኔታ ማስቀረት እንጂ ኑ እንግጠም እያልኩ አይደለም። ኑ እንግጠም እያለ ያለ ኃይልን አደብ ለማስገዛት ፌዴራል መንግሥቱ መግለጫ መስጠትም ሆነ ሌሎች ከእዚያ በላይ መሄድ የሚገባው እንቅስቃሴ ካለ ሊያደርግ ይገባዋል፤ ለእዚህ የእኔ ግብዣ ያስፈልገዋል የሚል እምነት የለኝም።

ምክንያቱም ጊዜያዊ አስተዳደሩ የፌዴራል መንግሥቱ ውሳኔ አካል ነው። ስለዚህ ፌዴራል መንግሥቱ ከሌላ ፓርቲ ጋር ሆኖ ያቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር በሚፈርስበት ጊዜ የማስተካከል ግዴታ አለበት። ከእዚህ አንጻር መደበኛ ጥያቄ አላቀረብንም የምንልበት ምክንያት፤ እንደተለመደው አካሄድ ቢሆን ኖሮ ችግሩ ከፖሊስ አቅም ውጪ የማይሆን ነበር፤ አሁን ግን ከቁጥጥራችን ውጪ እየሆነ ነው።

ሥርዓት ባለው መልኩ በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት አንድ ሠራዊት ነው መኖር ያለበት። በስምምነቱ መሠረት የጀመርናቸው እንቅስቃሴዎች በአግባቡ ባለመሠራታቸው ምክንያት አሁንም በትግራይ ውስጥ ግዙፍ የሠራዊት አቅም አለ። ይሄ የሠራዊት አቅም በሙሉ አይደለም አሁን የጥፋት እንቅስቃሴ ውስጥ ገብቶ ያለው። በተወሰነ ደረጃ ጉባዔ አድርጌያለሁ ከሚለው ቡድን ጋር የአይዶሎጂ ሳይሆን የጥቅም ቁርኝት አለን የሚሉ ወገኖች ናቸው በረብሻው የሚሳተፉት።

እዚህ ውስጥ የእርስ በእርስ ግጭትን ማስቀረት ስላለብን፤ ሌሎች ጠላቶችም ገብተው ይሄን ዕድል እንዳይጠቀሙት መከልከል ስላለበት ፌዴራል መንግሥት ለእዚህ በቂ የሚባል ድጋፍ መስጠት አለበት የሚል እምነት አለን። የሻዕቢያን መንግሥት እና የሱዳንን ድንበር ለመጠበቅ ፌዴራል መንግሥት የእኔ ጥሪ አያስፈልገውም። የመከላከያ ካምፖች አሉት ትግራይ ውስጥ። እነዚህን የመከላከያ ካምፖች ለመረከብ የእኔ ጥሪ አያስፈልገውም። ስለዚህ አሁን እኛ ያቀረብነው መደበኛ ጥያቄ የለም የምንለው፤ እንደ ወጉ ቢሆን ኖሮ ጊዜያዊ አስተዳደሩን እየተገዳደሩ ያሉት ችግሮች ከፖሊስ አቅም በላይ የማይሆኑ በመሆናቸው ነው።

የፕሪቶሪያ ስምምነት በአግባቡ መፈጸም አለበት የሚለውን ጥያቄ እኛ ብቻ የምናቀርበው መሆን ያለበት፣ የፌዴራል መንግሥቱም ከዲዲአር እና ከመሳሰሉት ጋር የሚነሱ ጥያቄዎችን በአግባቡ ማስፈጸም ይገባዋል። በአሁኑ ሰዓት አጭሩ መልስ በምክር ቤት ወይም በካቢኔ ደረጃ ተሰብስበን ያቀረብነው ጥያቄ የለም። ጥያቄውም ያስፈልገዋል የሚል እምነት የለኝም። የፌዴራል መንግሥት ጦርነት ለማስቀረት ፣ ትግራይን ሌላ የጦርነት አዙሪት ውስጥ ላለማስገባት (ምክንያቱም ትግራይ ውስጥ የሚካሄድ ጦርነት ሌሎችንም ይጋብዛል ብቻ ሳይሆን ራሱን ችሎ ኢትዮጵያን ለማተራመስ በቂ አቅም አለው) መንግሥት በምንም መልኩ እንዲህ ያለ ቀውስ አሁን ባለበት ደረጃ እንዲቀጥል ወይም ከእዚህ በባሰ ደረጃ እንዲሄድ መፍቀድ ስለሌለበት ኃላፊነቱን መወጣት አለበት።

ሌላ ጦርነት ለመጀመር ሳይሆን ጦርነትን የሚያስወግዱ ሁሉም አይነት ርምጃዎች መወሰድ አለባቸው የሚል እምነት አለን። በእዚህ ጉዳይ ላይ ለመወያየትም ነው ወደ እዚህ የመጣሁት። ጊዜያዊ አስተዳደሩን በተመለከተ እንደተለመደው የክልሎች መንግሥት አድርገን ባንወስደው። ከውስጥ ገቢ የምናገኛቸው የተወሰኑ ነገሮች ቢኖሩም እስከ አሁን እየተጠቀምን ያለው ፌዴራል መንግሥቱ በሚመድበው በጀት ነው።

ለእዚህ ምክንያቱም ሁለት ዓመት አልፎን ሥርዓት ባለው መንገድ ገቢ መሰብሰብ እንዳንችልና ጊዜያዊ አስተዳደሩ እንደ መንግሥት ከላይ እስከ ታች እግሩን ለመትከል በፓርቲው ውስጥ የተፈጠረው መከፋፈልና ተከፋፍሎ ጉባዔ አደርጋለሁ የሚለው ፓርቲ ዕድሜ ልኩን የወታደርንም ሆነ የፖሊስን የሁሉንም አይነት ታጣቂ አቅም ተጠቅሞ ሥልጣን በሞኖፖል ይዞ የቀጠለ ስለሆነ እና ከዚህ ሊላቀቅ የሚችልበት ዕድል ስለሌለ አሁን በትግራይ ያለው መወናበድ የፕሪቶሪያ ስምምነትን በአግባቡ ካለመፈጸማችን ጋር ተያይዞ ያለ ነው።

ከእዚህ አንጻር እንደ መፍትሔ ፌዴራል መንግሥት መውሰድ ከሚገባቸው ርምጃዎች መካከል የፕሪቶሪያ ስምምነት ሳይውል ሳያድር በተሟላ መንገድ እንዲፈጸም የሚያስችል ሁኔታ እንዲፈጠር ከዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ጋር በመሆን እስከ አሁን ተንጠልጥለው የመጡ ለምሳሌ ከዲዲአር ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በአስቸኳይ እንዲፈጸሙ ማድረግ መቻል አለበት።

አሁን ባለንበት ሁኔታ ትግራይ ውስጥ እየተፈጠሩ ያሉት ማህተም መንጠቅና ቢሮዎችን ሰብሮ መግባት ሙሉ ለሙሉ ሕገ-ወጥ የሆኑ፣ ትግራይን ወደ ሌላ የከፋ ግጭት ውስጥ የሚከቱ መሆናቸው በተግባር እየታየ ነው። ትርፍ ያለው አይመስለኝም። ከምንም ነገር በላይ ጦርነቱ እንዳይፈጠር ወይም ጦርነቱ እንዲቀር የሚያደርግ በቂ ሥራ ያልሠራ አመራር ከጦርነቱ በኋላ ፕሪቶሪያ የፈጠረውን ዕድል ከመጠቀም ይልቅ ይህንን ዕድል ለትርምስ ተጠቅሞበት አሁን ያለበት ደረጃ ላይ ደርሰናል።

የትግራይ ሕዝብ ሰላም ይፈልጋል። የትግራይ ወጣት ሰላም ይፈልጋል። የትግራይ ሕዝብ መማር ይፈልጋል። የትግራይ ሕዝብ ሀብት ማካበት ይፈልጋል። ተገዶ የገባበትን ጦርነት መስዋዕትነት ከፍሎ እንደሚዋጋ ሁሉ፤ የተፈጠረን ሰላም ሁሉንም አቅሙን ተጠቅሞ ማቆየት እና መጠበቅ ይፈልጋል። በእንደ እዚህ ዓይነት ሁኔታ ከጦርነት ትርፍ እናገኛለን የሚል አባዜ የተጠናወተው ጥቂት በጥቅም የተሳሰረ ኃይል የትግራይን ሕዝብ ሰላም የሚነሳ እንቅስቃሴ ውስጥ እየገባ ነው።

ይህን እንቅስቃሴ ማስቆም በዋናነት የትግራይ ሕዝብ ሥራ ቢሆንም፤ አሁን ባለው ሁኔታ የፕሪቶሪያው ስምምነት ተስማሚ የሆነው የፌዴራል መንግሥትም ከእዚህ ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያላቸው የዓለም አቀፍ አካላትም በእዚህ ጉዳይ ላይ ማለት ያለባቸውን ማለት አለባቸው። የፌዴራል ጣልቃ ገብነት ብዙ ጊዜ ሠራዊት ከማዝመት ጋር ብቻ የሚያያዝ ሆኖ እንጂ፤ እዚህ ግርግር ውስጥ ከፍተኛ እጅ ያላቸው ምርጫ ቦርድ አላውቅህም፤ ያደረግከውን ጉባኤ አልቀበልህም ብሎት ነገር ግን ምርጫ ቦርድ ያልከኝን አልቀበልም ስለዚህ ጉባኤ አድርጌያለሁ እኔ ነኝ መንግሥት መሆን ያለብኝ ብሎ የወረዳ እና የቀበሌ ማህተም፤ አሁን ደግሞ የከተሞች ከንቲባዎችን ማህተብ እየለቀመ የሚውስድ ኃይል ኮስተር ብሎ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ልደራደር ነው ብሎ እየመጣ ነው።

አንዳንዴ ለራሴም ግራ ይገባኛል። ትንሽ ማፈር የሚቻልበት ሁኔታ ቢኖር ይህንን የማፈር ግዴታ ባያስተናግዱ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ይህንን በደንብ ፈር ቢያስይዙት ጥሩ ነው የሚል እምነት አለኝ። ስለዚህ ችግር የፈጠረ ሰው ሁሉ ከረቫት አስሮ እደራደራለሁ የሚልበት ሁኔታ መፍጠር መቻል፤ እኔ ይህንን አጋጣሚ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለመገሰፅ ልጠቀምበት እፈልጋለሁ።

አዎ! ሰላም ለመፍጠር ሲባል ከሁሉም ጋር መደራደር እንዳለባቸው ይሰማኛል። ነገር ግን ጊዜያዊ አስተዳደሩን በአደባባይ አላውቅም ብሎ፤ በሥርዓት የተሾመን ፕሬዚዳንት የቀድሞ ፕሬዚዳንት እያለ ከተማ ውስጥ የመንግሥትን በጀት እየተጠቀመ የሚያምሰን ኃይል በምን ዓይነት መልኩ ተቀብሎ መደራደር ይቻላል?

እኔ ማንም ሰው ፕሬዚዳንት፣ ማንም ሰው ጊዜያዊ አስተዳደር ሆኖ ሊያገለግል ይችላል። ለራሱ የግል ጥቅም፣ ለራሱ የቡድን ጥቅም ሲባል፣ የሕዝብን ሰላም የፕሪቶሪያን ስምምነት፣ የሕዝቡን መረጋጋት እንደ መያዣ ይዞ ከረቫት አስሮ የሚመጣ መስተናገድ የለበትም። ምናልባት እንዳትገረሙ ግርግር ውስጥ ተሳትፎ ያደረጉ ሰዎች፤ ዛሬ ከሰዓት መጥተው ይኸው ማህተም ስለነጠቅን መንግሥት እንድንሆን ፍቀዱልን እንደሚሉ ፍፁም እንዳትጠራጠሩ፤

እንደ እዚህ ዓይነት ነውራም ተግባር አለማስተናገድን መጀመር የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ ገብነትን ማረጋገጫ አንዱ መንገድ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ።

የትግራይ ሕዝብ ወደየት እየሔደ ነው? ለሚለው የትግራይ ሕዝብ የሚፈልገው ወደ ሰላም መሄድ ነው። የፖለቲካ ኃይል የፈጠረው ብልሽት እና አሁን ተፈጥሮ ያለው ግርግር ግን የትግራይ ሕዝብ ነገን በተስፋ ሳይሆን በስጋት በሰቀቀን እንዲያይ ያደረገበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ማንም በኢትዮጵያ መንግሥትም ላይ ይሁን በትግራይ ሕዝብ ላይ የቆየ ቂም ያለው ይህን አጋጣሚ ተጠቅሞ የትግራይን ሕዝብ ወደ ባሰ መከራ ለማስገባት ርብርብ እያደረገ ይገኛል።

እንደ እኔ እምነት እና ፍላጎት ትግራይ ውስጥ የእርስ በእርስም ሆነ ከሌላ አቅጣጫ የመጣ ግጭት እንዲፈጠር ፍፁም ፍላጎት የለኝም። ፍፁም ፍላጎት ስለሌለኝ ብቻ የማስቀረው ስላልሆነ፤ ማድረግ የሚችል ሁሉ አቅሙ የፈቀደውን ማድረግ መቻል አለበት የሚል ተደጋጋሚ ጥሪን አቀርባለሁ።

እንደ እዚህ ዓይነት የሽፍታ እንቅስቃሴዎችን ለመጋፈጥ ሕዝባችን እንቅስቃሴ ያደርጋል፤ የትግራይ ክልል 75 በመቶ ወጣት ያለበት ነው። ወጣቱ ጠመንጃ አንስቶ ከታንክ ጋር ሲጋጭ ምንም ዓይነት ስጋት የሌለበት ነው። አሁን በሆነ አጋጣሚ የሆኑ ሰዎች ማህተም ይገባናል ስላሉ እነርሱን ፈርቶ ወደ ጦርነት የሚገባበት ሁኔታ የለም። ነገር ግን ወደ ሌላ ግጭት ከመግባታችን በፊት፤ ሌሎች ጠላቶችም ይህንን አጋጣሚ ተጠቅመው እዚህ ውስጥ ለመግባት የሚሞክሩት ለትግራይ ሕዝብ አስበው አለመሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል።

ፕሪቶሪያ ያጨናገፈባቸውን የትግራይ ሕዝብን የመጨፍጨፍ፣ ትግራይን የማዳከም እና ሙሉ ለሙሉ የማጥፋት ዕቅድ ለመፈፀም ዕድሉን አግኝተናል የሚሉት ሳይቀሩ ይህን አጋጣሚ እየተጠቀሙበት ነው። ከእዚህ አንጻር የትግራይ ሕዝብ መስቀለኛ መንገድ ላይ የሚቆምበት አጋጣሚ ተፈጥሯል። የትግራይ ሕዝብ ሰላም፣ መረጋጋት፣ መልማት እና መክበር እየፈለገ ነው። ግን ደግሞ ከእዚህ አጀንዳ እንዳይወጣ የቡድናዊ ጥቅምን የግል የሥልጣን ፍላጎትን ለማረጋገጥ ሲባል ሁሉም አይነት የወንጀል እንቅስቃሴ ውስጥ የገቡ ኃይሎች አደጋ ላይ እየከተቱት ይገኛሉ። ይሔ ግምት ውስጥ መግባት አለበት። ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ የእዚህ አጋዥ መሆን አለበት።

አሁንም ከተመፅዋችነት ያልወጣ አካባቢ አለ። በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ድንኳን ውስጥ መኖራቸው ብቻ ሳይሆን፤ ድንኳን ውስጥ ኖረውም ጭምር የተፈጥሮ ጣጣ እንዳይበቃቸው ሕክምና እና ርዳታ የማያገኙበት ሁኔታ ውስጥ እየገቡ ነው። ስለዚህ ስለተፈናቃዮች ጉዳይ ስናወራ፤ የፌዴራል መንግሥቱ ግዴታ አለ። እንደጊዜያዊ አስተዳደርም እዚህ ውስጥ የተሳተፉ ሌሎች ኃይሎችም እያደናቀፍን ያመጣነው ጉዳይ አለ።

የፌዴራል መንግሥት የሄደበት ርቀት አለ። እውነት ለመናገር የፌዴራል መንግሥትን በበቂ መልኩ ስለወቀስን እና በበቂ መጠን ስላማረርን በእኔ እምነት በአሁኑ ሰዓት እንደ እዚህ ዓይነት ችግሮች እንዳይፈቱ ከማድረግ አንጻር ትልቁ አደናቃፊ ሆኖ ያለው ጊዜያዊ አስተዳደሩ ውስጥ ያለው ትርምስ እና አሁን ጉባኤ አድርጌያለሁ እያለ ትግራይን ወደ ሌላ ትርምስ ለማስገባት እየሞከረ ያለ ኃይል መሆኑ መታወቅ መቻል አለበት። የትግራይ ሕዝብ ወደ የት እየሄደ ነው? ለሚለው ጥያቄ መሄድ የሚፈልገው መረጋጋት እና ልማት እንዲሁም ወደ ሰፈሩ መመለስ፤ ከመፈናቀል ነፃ ወጥቶ ጥሎት ወደ መጣበት ቀዬ መመለስ ብቻ ነው። ነገር ግን ተጨማሪ ተፈናቃዮችን ማስተናገድ የጀመርንበት ሁኔታ አለ።

አሁን ይሄ ማህተም በመንጠቅ ላይ ያለ ቡድን በባህሪውም ምንም ዓይነት የሃሳብ ልዩነት የሚፈቅድ፤ የሃሳብ ልዩነት ብቻ ሳይሆን ሃሳብ በሌለውም ሰዓት ከሃሳብ ልዩነት በትንሽ ሴንቲ ሜትር ርቀት ድንገት ለየት ብሎ ፈጥኖ የሚንቀሳቀስን የሚቆጥረው እንደ ጠላት ነው። ሁላችንም ተመሳሳይ አመራር ውስጥ ጦርነት ውስጥ ገብተን የምንሰቃየውን ያህል ተሰቃይተን እና የምንከፍለውን ከፍለን፤ ከሥልጣን ጋር በተያያዘ ግጭት ተፈጥሯል። ወይም የሚገባኝን አጥቻለሁ በሚልበት ሰዓት ሁሉንም በጠላትነት ይፈርጃል። ይህ እኛንም አሳቆናል።

እኔ እንደ መንግሥት ኃላፊ ፌዴራል መንግሥት የሠራቸውን በጎ ነገሮች መጥቀስ በዚህ ቡድን ውስጥ ተቀባይነትን የሚያሳጣኝ ስለሆነ ብዙ ጊዜ የፌዴራል መንግሥትን መውቀስ ላይ ትኩረት እናደርጋለን። በረሃ እያለን የተጠቀምናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩንም ሆነ ማንንም በተመለከተ በስሜት የተናገርናቸውን ቃላት ካልደገምክ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አድረኻል ብሎ መደምደም ላይ የሚደርስ ግን ደግሞ በየዕለቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር እየደወለ ስልጣን የሚገባው ለእኔ ነው እያለ የሚለምን ኃይል ነው። ሃፍረትም ሆነ ምንም የሌለው ነው።

ይሄ ኃይል የትግራይን ሕዝብ የመልማት ፣ የሰላም እና የመረጋጋት አጀንዳን ነጥቆ የትርምስ እና የግርግር እያደረገ ነው። ይሄ የትግራይ ሕዝብ ወዴት እየሔደ ነው ለሚለው መሔድ ወደ ሚፈልገው ሳይሆን በእንደ እዚህ ዓይነቱ ትርምስ ምክንያት በእኛም ስንፍና እና ኃላፊነት የጎደለው አንድነታችንን ለማስጠበቅ በሚል በምንፈጥረው ትርምስ ምክንያት የትግራይ ሕዝብ መስቀለኛ መንገድ ላይ ነው። ስለዚህ ሁሉም ትግራዋይ ብቻ ሳይሆን የትግራዋይ ሕልውና ያስፈልጋል። ለኢትዮጵያም ይጠቅማል ብሎ የሚያምን ሁሉ ከእዚህ ቀውስ እና አደጋ እንዲወጣ በሚያደርግ መልኩ የሚቻለውን ሁሉ ማድረግ አለበት የሚል መልዕክት ማስተላለፍ እፈልጋለሁ።

የፕሪቶሪያ ስምምነት ዓላማ ምንድን ነው? ለሚለው ጥያቄ መልሱ ተኩስ ማቆም ነው። ከእዛም ከተኩስ ማቆም ጋር የሚያያዙ ነገሮችን የያዘ ነው። ትግራይ የሚያስፈልጋትን የፀጥታ ኃይል ትይዛለች። የተስማማነው ስምምነት አንድ የመከላከያ ኃይል ይኖራል የሚል ነው። የዲዲአር ፕሮሰስ ብቻ አይደለም። ብዙ ሰው የሚያተኩረው ጠመንጃ ማስረከብ ላይ ብቻ ነው። እርሱ የራሱ ጉዳይ ይኖረዋል። ወደ እርሱ እመለሳለሁ። ትግራይ በአሁኑ ሰዓት በጊዜያዊ አስተዳደሩ አማካኝነት ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር ያላት ግንኙነት እንዳለ ሆኖ፤ ከፌዴራል ሥርዓቱ ጋር የምትወከልበት ምንም ዓይነት ግንኙነት የላትም።

የትግራይ በጀት በሚፀድቅበት ሰዓት ይሄ ይጎድለናል ብለው የሚሟገቱበት ሁኔታ የለም። በአጋጣሚ ባለፈው ቋሚ ኮሚቴው የተወሰነ ሙከራ እንዳደረገ አውቃለሁ። ከእዚህ ውጪ የተመደበልህን ትቀበላለህ ትግራይ የፌዴሬሽኑ አካል መሆን የሚያስችላት የፖለቲካ ንግግር በሥርዓት መካሄድ ነበረበት፤ ያን በማድረግ ረገድ በእዚህ ዙሪያ ያልተሠሩ ሥራዎች አሉ። ጊዜያዊ አስተዳደሩ ይሠራቸዋል ብለን ያስቀመጥናቸው ነገሮች ነበሩ። መጀመሪያ ተፈናቃዮች መመለስ ፣ ተቋርጠው የነበሩ ማህበራዊ አገልግሎቶች እንዲጀምሩ ማድረግ፣ ትምህርት፣ ጤና እና ሌሎችንም ማስጀመር ነበር።

ከኢኮኖሚ ድቀት አንጻር ጠቅላላ የትግራይ መሠረተ ልማት በአጋጣሚ በተፈጠረ መንገድ ብቻ ሳይሆን ሙሉ ለሙሉ የጠፋበት ሁኔታ ነው ያለው። ብዙ ፋብሪካዎች ወይ ሙሉ ለሙሉ ወድመው ወይ በከፊል ወድመዋል። ወይ ደግሞ የተወሰነ ጥገና ተደርጎላቸው ሊድኑ የሚችሉበት ሁኔታ ቢኖርም ባለው በርካታ ችግር ምክንያት ወደ ሥራ የማይገቡበት ሁኔታም አለ።

ስለዚህ የኢኮኖሚ መልሶ ግንባታ ማድረግ የሚያስችሉ መሠረቶችን መጣል ያስፈልጋል። የሰላምና ጸጥታ ሁኔታዎችን ማረጋገጥ። ቀጣይ ምርጫ እስኪደረግ ድረስ የተሻለ ኢንቫይሮመንት ለመፍጠር የሚያስችሉ ትንንሽ የሪፎርም ሥራዎችን ማካሄድ ያስፈልጋል። እነዚህ ናቸው የጊዜያዊ አስተዳደሩ ዓላማዎች።

ስለዚህ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ከዓላማው ውጪ የተንቀሳቀሰባቸው ጊዜዎች አሉ ብዬ አላምንም። ግን ለምሳሌ የዲዲአር ፕሮስስ አንዱ አካል ነው። የዲዲአር ፕሮሰስ ለማስፈጸም የሄድንበት ርቀት በቂ አይደለም። እዚህ ላይ በእዚህ አጋጣሚ በዛሬው ዕለት ተቋርጦ የነበረውን ዲዲአር ለማስቀጠል የፌዴራል መንግሥት ኃላፊዎች እንደሚሄዱ ነበር የማውቀው። አሁን የሰማሁት አሁን ባለው ያልተረጋጋ ሁኔታ ምክንያት የዲዲአር ሂደቱን ለማስቀጠል ቡድኑ እንደማይሄድ ነው የማውቀው። ይሄን አሁን የፌዴራል መንግሥቱ ጥፋት ነው ብዬ ላስቀምጥ አልችልም።

ትግራይ የመረጋጋት አጀንዳ ሊሆን ሲገባው ትኩረታችን ከምዕራብ ትግራይ ተፈናቀለ ከየትም ቦታ የተፈናቀለ ሰው ወይ ማስመለስ መሆን ሲገባ የተረጋጋ አንጻራዊ ሰላም የነበረበትን መቀሌን ሳይቀር የትርምስ ማዕከል ያደረገ አጀንዳ አደገኛ አስተሳሰብ አደገኛ እንቅስቃሴ ማቆጥቆጥ ብቻ ሳይሆን አሁን ባለንበት ደረጃ ሙሉ ሕዝቡን ወደ ትርምስ እንዲገባ የሚያደርግ ሁኔታ ተፈጥሯል።

ይሄንን ትርምስ የፈጠረ ኃይል ግን ደግሞ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ታጣቂዎች ዓላማቸው እስከተፈጸመ ድረስ በዲዲአር ተካትተን ወደ ሰላማዊ ኑሮ እንመለሳለን ብለው በጉጉት በሚጠብቁበት ሁኔታ ባለፈው የተቋረጠው የራሳችን የአመራር አካሄድ የፈጠረው ችግር ነው። እኔ ግጥም አድርጌ ደብዳቤ የጻፍኩት ፌዴራል መንግሥቱ ለምን ያቋርጣል ብዬ ነው። ውስጤ ያውቀዋል የፌዴራል ኃላፊዎቼም ቢያንስ አንተ እንኳ እንዴት እውነት አታወራም ይሉኛል።

እውነቱ እኛው ራሳችን በፈጠርነው ትርምስ ምክንያት ነበር የተቋረጠው። ስለዚህ ከ75ሺህ በላይ የእዚህ ተጠቃሚ እሆናለሁ ብሎ ይጠብቅ የነበረው ታጋይ ማነው ያስቆመው ንገሩን ብሎ አንገታችንን ነው ጠፍንጎ የያዘን። አሁንም በ10ሺህዎች የሚቆጠር ታጋይ አለ። ግን ይሄንን ዲዲአር ርምጃ የሚጠብቅ ፣ ግን ይሄን ከመፈጸም ይልቅ የቀበሌ ማህተም ወደ መንጠቅ የምንገባበት አካሄድ ስለተፈጠረ ይሄንን ማስፈጸም አልተቻለም።

ፕሪቶሪያ ብዙ ነገሮች አሉት። ፕሪቶሪያ በተሟላ መልኩ ከተፈጸመ ጊዜያዊ አስተዳደሩ አያስፈልግም። በምርጫ የተመረጠ መንግሥት ነው ትግራይ ሊኖራት የሚገባው። በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት ከሆነ ሁሉንም ኃላፊነቶች በተሟላ መልኩ ይሰጣል።

ስለዚህ የዲዲአር እንቅስቃሴ በተሟላ መልኩ መፈጸም መቻል አለብን። ተፈናቃዮች በትክክል መመለስ መቻል አለባቸው። ከእዚህ አንጻር ያልተሠሩ በርካታ ሥራዎች አሉ። እነዚህን ሥራዎች ፌዴራል መንግሥቱ የሚወስደውን የድርሻውን ይውሰድ፤ መቀሌ ተቀምጬ ሚዲያ በመጣ ቁጥር አምባሳደር በመጣ ቁጥር ፌዴራል መንግሥቱን በስፋት የወቀስኩበት ጊዜ በቂ ስለሆነ አንዳንዴ ትንሽ ፈሪሃ እግዚአብሔርም ያስፈልጋል። በራሳችን ጥፋት የተፈጸሙ ነገሮችንም ጭምር ለፌዴራል መንግሥቱ እየሰጠሁ መቀጠል አልችልም።

 

የተፈናቃይ ጉዳዮችን መመለስ። ፌዴራል ጋ የማልግባባቸው በርካታ ነጥቦች ቢኖሩም፤ ፕላን አውጥተን ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንግባ ካልን ከተስማማን በኋላ ያስቆመው የፌዴራል መንግሥቱ አይደለም። ራሳችን ነን ያስቆምነው።

ፖለቲካ ጥቅም ይገኝበታል። ማን አጀንዳ ይሆናል? ተፈናቃዮች ከተመለሱ ለተፈናቃዮች እኔ ነኝ ጥብቅና የምቆመው፤ እገሌማ አሳልፎ ሰጥቷችኋል፤ መሬት ወስዶባቹኋል እያለ ወሬ ሲፈበርክ የሚውለው ኃይል አጀንዳ ያጣል።

አጀንዳ እንዳያጣ ተፈናቃዮቻችን ድንኳን ውስጥ ይሰቃያሉ። ድንኳኑ ቢሆን ፀሐይና ቁር የሚከላከልም ድንኳን አይደለም። ለአራት ዓመት ድንኳን ውስጥ የተቀመጠ ሕዝብ ሕክምና የማያገኝ፣ ምንም ዓይነት የምግብ ርዳታ የማይደርሰው በእንደ እዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ፖለቲካ ፖለቲካ እየተጫወተ ነው። አንድም ቀን ለምንድነው ፌዴራል መንግሥቱን ብዙ ጊዜ የምንወቅሰው ቢባል ፌዴራል መንግሥት ባጠፋው ደረጃ መውቀስ ነውር አለው ቢባል ነውር አለው ብዬ አላስብም።

እኔ ሥራዬ ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር በየጊዜው እየተገናኘሁ እነዚህ ችግሮች እንዲፈቱ ማድረግ ነው። እንደ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት በዚህ እኔ መሪ በሆንኩበት ፓርቲ ውስጥ ያለው የተምታታ አስተሳሰብ ግን ፈለግነውም አልፈለግነውም አጋርህ ከሆነው የፌዴራል መንግሥት ጋር ተቀራርበህ መሥራት በባንዳነት ነው የሚያስጠረጥው ብቻ ሳይሆን የሚያስፈርጀው።

አሁን ሹኩቻው ጊዜያዊ አስተዳደሩን ለመምራት ነው። አሁን ላይ እኔ ልሁን የሚል ሦስት አራት ሰው አለ። አሁን እዚህ ይመጡ ይሆናል።

እኔ ተፈጥራ የነበረችው ሰላም መረበሽ ስለጀመረች እንድትጠበቅና ወደሌላ ጦርነት እንዳንገባ እንረባረብ፣ የፌዴራል መንግሥትም ያግዘን እያልኩ ያለሁት። ሥልጣኔን አቆይልኝ፤ አስጠብቅልኝ የሚል አጀንዳ ውስጥ አይደለሁም።

እዚህ ጉዳይ ውስጥ የሚገባ ኃይል ፕሪቶሪያ አልተፈጸመም ይላል። ስለዚህ ፌዴራል መንግሥት ጋር ግንኙነት ማድረግ ሳይሆን ራሱም ግንኙነት እያደረገም ጭምር ይቃወማል። እኔ አንዳንዴ እሳቀቃለሁ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዘንድ ሄጄ የነጋዴ እና የገበሬ ጉዳይ ይዤ መሞገት በሚገባኝ ሰዓት አሁን የትግራይ ጥቅም አሳልፎ ሰጠ እንዳልባል እንደዚህ አይነቱ አምታችነት እኔም ጭምር የገባሁበት አምታችነት ነው የትግራይን ሕዝብ ለአደጋ እየዳረገ ያለው።

ይህንን ክስ የሚያቀርቡ ሰዎች እኔ ከማደርገው ግንኙነት የበለጠ ግንኙነት አላቸው። እነዚህም እየመጡ እኛ እኮ እንሻል ነበር ብለው ደጅ ሲጠኑ የሚውሉት ናቸው። ሥልጣንን ብቻ ማዕከል ያደረገ ትንሽ አባላት ስላሉት ቡድን ነው እያወራን ያለነው።

ትግራይ ውስጥ ያለው የጸጥታ ኃይል እዚህ ትርምስ ውስጥ መግባት አይፈልግም፤ ትግራይ ውስጥ ያለው የጸጥታ ኃይል በዲዲአር ማካተት የሚፈልገው በዲዲአር ይካተታል፤ የቆምኩላቸው ዓላማዎች ይሳካሉ፤ ተፈናቃዮች ይመለሳሉ፤ ትግራይ ወደ ልማት ተመልሳ ትገባለች የሚል ተስፋና እሳቤ ውስጥ ካልሆነ በስተቀር አሁን በምታዩት የማህተም መንጠቅ ትርምስ ውስጥ ድርሻም የለውም።

እውነት እንነጋገር ከተባለ ሰላም ከእዚህ ታጣቂ በላይ የሚፈልገው የለም፤ ግን ሰላም ከተፈጠረ ድንገት የፌዴራል መንግሥት ይይዘናል የሚሉ ጥቂት ሰዎች አሉ። የፌዴራል መንግሥት ምህረት አድርጌአለሁ፤ እገሌ እገሌ የምትባሉ ሰዎች ግቡ፤ ምህረት ብቻ ሳይሆን እገሌ የምትባል ሰው እባክህን ወደ ፈለግከው ቦታ መሄድ ትችላለህ ብለህ ንገርልኝ እየተባለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እየነገሩኝ እኔም እየሄድኩ ኧረ እንደ እዚህ እየተባላችሁ ነው እያልኩ ነግሬአለሁ። እነርሱ ሰላም ተፈጥሮ ልንያዝ የምንችልበት እድል አለ ብለው ከሚሰጉ ይልቅ ሕዝቡ ወደ ሙሉ ትርምስና ስጋት ገብቶ እነርሱም የሚያዙበት እድል እንዳይኖር ማድረግ ይመርጣሉ።

በምን ልታስረዳቸው ትችላለህ? በምን ልታሳምናቸው ትችላለህ? ይሄ ስለሁሉም የጦር አዛዥ አይደለም እያወራሁ ያለሁት፤ ስለሁሉም የፖለቲካ መሪ አይደለም እያወራሁ ያለሁት። ጥቂት ሰዎች ናቸው፤ ግን ደግሞ የፈጠርነው የፖለቲካ ባህል እንዳልኩት ነው።

በሥርዓት በይፋ የተቋቋመ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ደብዳቤ የተሾመ ፕሬዚዳንት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያገኛቸው መድረኮች ላይ በየጊዜው መገኘት አለበት። የትግራይን አጀንዳ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀጠሮ ጋር በማያያዝ ብቻ ሳይሆን ባገኘኸው አጋጣሚ መጠየቅ፣ መፈጸም አለብህ ብለህ መጠየቅ የምትችልበትን ለመጠቀም እዚያ ከታየህ ጥቅም አሳልፎ ሰጥቷል ትባላለህ፤ መባል የለበትም።

ካሜራ በማይኖርበት ቦታ ግን የትግራይ ተፈናቃይ ይመለስ የሚል አይደለም የሚጠይቀው። ወደ ወንበሬ መልሰኝ እያለ እየሞገተ ነው። ይህንን አይነት ብልሽት ፕሪቶሪያን በተሟላ መልኩ በማረጋገጥ ብቻ ልንፈታ ይገባ ነበር። እዚህ ላይ የቀሩ ነገሮች አሉ። ቢያንስ ቢያንስ አንዳንዴ እንመን ብዬ ስላሰብኩ ነው። የፌዴራል መንግሥቱን መውቀስ ባለብኝ በሚገባ ወቅሻለሁ፤ የሚገባው ርቀት ሄጃለሁ፤ ምናልባት ከሚገባ በላይ ርቀት የሄድንባቸው አጋጣሚዎች አሉ።

እውነት ለመናገር ተፈናቃዮችን ከመመለስና ዲዲአር ተግባራዊ ከማድረግ አንጻር የመጨረሻው ጥሪ በቅርብ የተደረገው ከሁለት ሦስት ሳምንት በፊት ፌዴራል መንግሥቱ ምንድነው እያደረጋችሁ ያላችሁት ይህንን ነገር ቶሎ እንፍታው ቶሎ እንዝጋው —።

ሪፈረንደም የሚባል ነገርን እኔ አልስማማም ብያለሁ። እርግጥ ነው ጊዜያዊ አስተዳደር ሪፈረንደም ምንም ማድረግ አይችልም። ግን ደግሞ መመለሳቸው በሚመለከት የተስማማንባቸውን ሂደቶች ሳይቀር ያቆምነው እኛ ነን፤ ስለዚህ እየተጠራና እየተቀሰቀሰ ነው።

ለወራት በሌላ ጉዳይ ትርምስ ውስጥ ስንገባ ሕዝቡን ችግር ውስጥ ስንከት ተጨማሪ ተፈናቃዮች እየፈጥርን ነው። ከመቀሌ በአውሮፕላን ፣ በእግርና በአውቶቡስ ባገኘው አጋጣሚ ተጠቅሞ የሚወጣው ብዙ ነው። ምክንያቱም የጦርነት ድባብ በሚታይበት ሁኔታ ውስጥ ሕዝብ ተረጋግቶ መቆየት አይችልም።፡

ይህንን ሁኔታ ለማስቆም እንደተባለውም ፕሪቶሪያን በተሟላ መልኩ ማሟላት አለብን። ፕሪቶሪያ ግን ተኩስ አቁመና ብቻ ሳይሆን ዲዲአር (በዲሞባላይዜሽ )የጀመርናቸው ሥራዎች አሉ። ትጥቅ አስረክበናል፤ አንዳንድ ሰው ሰባራ ነው ይላል። ያልነበሩን ጠመንጃዎች ናቸው በጦርነቱ ጊዜ የያዝናቸው። ስለዚህ ትግራይ የሚያስፈልጋት የጸጥታ ኃይልና የሚያስፈልገው ጠመንጃ ይዞ የማይቀጥልበት ምክንያት አይኖርም፤ እንደሌላው ክልል። ይሄንን ከማድረግ አንጻር የዘገዩ ነገር አሉ፤

አሁን የዲዲአር ሂደቱን በማስቆም ረገድ ከፌዴራል መንግሥት በላይ ተጠያቂዎቹ እኛ ነን። ይህንን ነው እያልኩ ያለሁት። ምክንያቱም 75 ሺ ብቻ አይደለም በሁለት ዙር 175 ሺ ትጥቅ እናስፈታለን፤ ወደ ሰላማዊ ኑሮ እንዲመለስ እናደርጋለን። በሚል የያዝናቸውን ዕቅዶች ያስቆመው ፌዴራል መንግሥት አይደለም።

ይህንን እያምታታሁ መቀጠል አልችልም። ነገር ግን ደብዳቤ ጽፌያለሁ። ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ፌዴራል መንግሥት አስቆመ የሚል ደብዳቤ ነው የጻፍነው።

አሁን ይሄ መቆም መቻል አለበት፤ ምክንያቱም ወጣቱ ይፈልገዋል። ወደ ሰላማዊ ኑሮው መመለስ ይፈልጋል። ገንዘቡ ይህን ያህል አይደለም። አካሉን ያጣ የትግራይ ታጋይ 90 እና መቶ ሺ ብትሰጠው በምንም መልኩ ልትክሰው አትችልም። ነገር ግን ካምፖች ውስጥ ተቀምጦ የሚኖርበት ሁኔታ ያክትም፤ መንግሥትም የድርሻውን ይወጣ።

ፌዴራል መንግሥቱና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ብቻ ሳይሆን ጊዜያዊ አስተዳደሩም ኋላ የሚቋቋመው በሕግና በምርጫ የሚቋቋም መንግሥት ካለ ድርሻቸውን የሚወጡበት ሁኔታ መፈጠር መቻል አለበት። ይህን ከማድረግ አንጻር አሁን ኃላፊነቱን ለፌዴራል መንግሥት ልወረውር አልችልም።

ተፈናቃዮችን ከመመለስ አንጻር አሁን ኃላፊነቱ የፌዴራል መንግሥት ጥፋት ብቻ ነው ብዬ መቀመጥ አልችልም። የፌዴራል መንግሥትን የወቀስኩት ይበቃኛል። አሁን ራሳችንን ማየት መቻል አለብን። ስለዚህ ተፈናቃዮቻችን ወደ ቀያቸው እንዳይመለሱ ከማንም በላይ በማደናቀፍ በታታሪነት እየሠራ ያለው የትግራይ የፖለቲካ ኃይል ነው። በተለይ ሥልጣን ለእኔ እና ለእኔ ብቻ ነው የሚገባው የሚል ጥቂት አባላት ያሉት የግርግርና የትርምስ ቡድን ማለት ነው።

በትግራይ ውስጥ የፖለቲካ ትኩሳት የሻዕቢያ ሚና የሚባለው ትግራይ ውስጥ በሚፈጠር ትርምስ እናተርፋለን የሚሉ ብዙ ወገኖች አሉ። የኤርትራ መንግሥት አንዱ እንደሆነ አውቃለሁ። ማለትም የኤርትራ መንግሥት ከፌዴራል መንግሥት ጋር የመጀመሪያ ግጭት የገባው ፕሪቶሪያ ከተስማማን በኋላ ነው።

ፕሪቶሪያ ከተስማማን ለምንድነው ግጭት ውስጥ የሚገባው፤ ምክንያቱም ትግራይን ሙሉ ለሙሉ ከካርታ ለማውጣት የነበረ እንቅስቃሴ ያስቆመ ስምምነት ስለሆነ ነው። ከኤርትራ መንግሥት ጋር ሰላም መፍጠር አለብን የሚል እምነት ነበረኝ፤ የተወሰነ እንቅስቃሴም ነበረኝ።

የኤርትራ መንግሥት ሰዎች ፍላጎት የኢትዮጵያ መንግሥት ኤርትራን ይወራል ብለው በሚሰጉበት ሰዓት ትግራይን ማቀዝቀዣ ማድረግ ነው። ወይ ደግሞ ጠንከር ያለ አጋጣሚ ተፈጥሯል ብለው ካመኑ ደግሞ ከእኛ ሰዎች ጋር ሆነው ምናልባት ወደ አዲስ አበባ ጉዞ ማድረግ የሚቻልበት ዕድል ካለ ማማተርም ሊሆን ይችላል። ሁሉንም ዕድሎች ክፍት አድርጎ የማሰብ እንቅስቃሴ አለ።

በዚህ ጉዳይ ውስጥ የሆነ ጤነኛ አዕምሮ ያለው የትግራይ የፖለቲካ ኃይል ወይም ደግሞ የጸጥታ ኃላፊ ወይም ደግሞ ለትግራይ ደማቸውን ያፈሰሱ ጀነራሎች ከነብዙ የፖለቲካ ችግሩ የትግራይን ህልውና አረጋግጣለሁ ብሎ የቆመ የፖለቲካ አመራር በእዚህ ሰዓት ምንም የተለወጠ ነገር ሳይኖር ከእነዚህ ሰዎች ጋር ሆኜ የሆነ ነገር አደርጋለሁ ብሎ ይህንን ኢንተርቴይን ሲያደርግ በጣም ያስደነግጣል።

ይሄ ችግር የሁሉም ሰው ችግር አይደለም። ሁሉም ጀነራል ከኤርትራ ጋር ተግባብቼ የሆነ ነገር አደርጋለሁ ብሎ የሚል አድርገን አንውሰደው። ሁሉም ፖለቲከኛ ከኤርትራ ጋር ተግባብቼ የሆነ ነገር አደርጋለሁ አይልም።

ነገር ግን ጭር ካለ አደጋ ላይ እንወድቃለን የሚሉ ወገኖች ግን ራሳቸውን ከፍ ያለ ዋጋ ላቀረቡ ብቻ ሳይሆን ትርጉም የሌለው ዋጋ ላቀረበውም ጭምር አገልጋይ ለመሆን ዝግጁ ሲሆኑ ይታያል። በተወሰነ ደረጃ እዚህ ትርምስ ውስጥ እንድንገባ ከማድረግ አንጻር ይህን ኃይል ለመጠቀም እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ቡድኖች እንዳሉ አውቃለሁ።

እነዚህ ቡድኖች ስለ ትግራይ ሕዝብ ምንም ደንታ የላቸውም። የወርቅ ንግድ ወደ አዲስ አበባ የሚያዋጣ ከሆነ ያደርጋሉ፤ የወርቅ ንግዱ ወደ አዲስ አበባ የማያዋጣ ከሆነ ወደ አስመራ ያደርጋሉ።

ይህ ከትግራይ ሕዝብ ተጠቃሚነትና ከትግራይ ሕዝብ ህልውና ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም። የተጠያቂነት ጉዳይ አለ፤ እኔ ከኤርትራ መንግሥት ጋር ሰላም እናምጣ ማለት የኤርትራ መንግሥት በተግባር ኢትዮጵያ የትግራይ ሕዝብ ላይ የፈጸመውን ጭፍጨፋ በመካድ ሊሆን አይችልም። ሁሉም የፌዴራል ኃይሎች ለፈጸሙት ጥፋት ተጠያቂ መሆን አለባቸው። የትግራይ ኃይሎችም የፈጸሙት ጥፋት ካለ ተጠያቂ መሆን መቻል አለባቸው።

በጋዜጣው ሪፖርተሮች

አዲስ ዘመን መጋቢት 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You