
በአፅዋማት የደም እጥረት እንዳይፈጠር የሃይማኖት አባቶች የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ
አዳማ፦ የአፅዋማት መግባትን ተከትሎ የደም አቅርቦት እጥረት እንዳይፈጠር የሃይማኖት አባቶች ምዕመናን ደም በስፋት እንዲለግሱ በማስተማርና በመቀስቀስ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ የኢትዮጵያ ደምና ኅብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ጥሪ አቀረበ።
የኢትዮጵያ ደምና ኅብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት የአፅዋማት መግባትን ተከትሎ የደምና የደም ተዋፅዖ አቅርቦት እንዳይከሰት ከእምነት አባቶች፣ ከአባገዳዎችና አደ-ሲንቄዎች ጋር የጋራ የምክክር መድረክ ትናንት በአዳማ ከተማ አካሂዷል።
የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አሸናፊ ታዘበው በመድረኩ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉም በሚባል ደረጃ በሃይማኖት የሚያምንና ለእምነቱም ቀናዒ ነው። የሃይማኖት አባቶቹም የሚሉትን ልብ ብሎ የሚያደምጥና የሚባለውን ለመተግበር ወደኋላ የማይል የአባቶቹን ቃል የማያጥፍ ሕዝብ ነው።
በመሆኑም የአፅዋማት መግባትን ተከትሎ የደምና የደም ተዋፅዖ አቅርቦት እጥረት ተከሰቶ የአንድም ዜጋ ሕይወት እንዳይታጣ የሃይማኖት አባቶች ምዕመናን ደም በስፋት እንዲለግሱ በማስተማርና በመቀስቀስ ባላቸው ተደማጭነትና ተቀባይነት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
የአደባባይ በዓላት በሚበራከቱበት፣ ትምህርት በሚዘጋበትና በክረምት እንዲሁም በአፅዋማት ወራቶች የደም እጥረት እንደሚከሰት ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመው፤ አሁን ላይ የክርስትናና የእስልምና ትላልቆቹ አፅዋማቶች መግባቱን ተከትሎ፤ የእምነቱ ተከታዮች ከምግብና ውሃ ለረጅም ሰዓት ተከልክለው ይውላሉ። በዚህም ሰዎች ወይም ምዕመናን በፈለጉት ሰዓት ደም መለገስ ስለማይችሉ፤ በአፅዋማት ወራት የደም እጥረት እንደሚከሰት ተናግረዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ ዶክተር አሸናፊ፤ በአፅዋማት ወቅት የደም እጥረት እንዳይከሰት በየዓመቱ መጋቢት ወርን “የደም ልገሳ ንቅናቄ ወር” በሚል ሰፊ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ አመልክተው፤ በደም ልገሳ ንቅናቄ ወሩ የሃይማኖት አባቶች ስለ ደምና ዓይን ብሌን ልገሳ ዙሪያ በምዕመናኑ ዘንድ ያለውን የተሳሳተ አመለካከት በማረም፣ ምዕመናን በቋሚነት ደም እንዲለግሱ በማስተማርና በመቀስቀስ የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
በ2017 በጀት ዓመት ግማሽ ሚሊዮን ዩኒት ደም ለመሰብሰብ ታቅዶ በሰባት ወራት ውስጥ ከ243 ሺህ በላይ ዩኒት ደም መሰብሰቡን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸው፤ በሰባት ወር ከተሰበሰበው አኳያ እንደ ሀገር በቀን አንድ ሺህ 100 ዩኒት ደም አካባቢ እንደተሰበሰበ ተናግረዋል።
ሆኖም የደም ሕክምና ከሚያስፈልጋቸው ዜጎች አኳያ እንደ ሀገር በቀን ከ2 ሺህ 800 እስከ 3 ሺህ 500 ዩኒት ደም እንደሚያስፈልግ አመላክተው፤ እንደ ሀገር በቀን ከሚያስፈልገው ደም አኳያ አሁን ላይ እየተሰበሰበ ያለው ከግማሽ በታች ነው። ዜጎች በስፋትና በቋሚነት ደም እንዲለግሱ የሃይማኖት አባቶች በሃይማኖት ተቋማት ጭምር ምቹ የደም ልገሳ ቦታ በማመቻቸትና በማስተማር አይተኬ ሚናቸውን እንዲወጡ አስገንዝበዋል።
የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ታዬ በበኩላቸው፤ ደም የሰውን ልጅ ሁሉ አንድ ከሚያደርጉ ነገሮች ዋነኛው እንደሆነ ገልፀው፤ ደም ልገሳ ቀለም፤ ፆታ፣ ዘርና ሃይማኖት ሳይለይ ለሚያስፈልገው ሁሉ የሚሰጥ ሕይወት አድን ሕክምና እንደሆነ ገልጸዋል።
በርካታ የደም ሕክምና የሚያስፈልጋቸው ዜጎች በየሕክምና ተቋማት የወገናቸውን ክንድ አንጋጠው እየተጠባበቁ እንደሚገኙ ጠቁመው፤ ሁሌም ደም ያስፈልጋል። ስለዚህ ወራትና ወቅት ሳይለይ ሁሌም ማኅበረሰቡ ደም እንዲለግስ በዚህ አጋጣሚ ጥሪ አስተላልፈዋል።
ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ እንደ ሀገር ከሚለገሰው ደም ውስጥ 70 በመቶ ሴቶች እንደሚጠቀሙ ጠቁመው፤ ይሁን እንጂ 35 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች ብቻ ደም እንደሚለግሱ ገልጸዋል።
ነገር ግን በአደጉ ሀገራት ሴቶችና ወንዶች እኩል 50 በመቶ፤ 50 በመቶ እንደሚለግሱ አመልክተው፤ ሴቶች በወሊድና መሰል ምክንያቶች በስፋት ደም ስለሚያስፈልጋቸው እንደሀገር የሴቶችን ደም የመለገስ ባሕል ለማጎልበት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሠራ ተናግረዋል።
በመድረኩ የደምና የዓይን ብሌን ልገሳን አስመልክቶ የሁሉም ሃይማኖት አባቶች ባለአምስት ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥተዋል። በመግለጫቸውም ሕይወት ማዳንን ሁሉም ሃይማኖት ተቋማት መርሕ አድርገው እንደሚደግፉት ገልጸው፤ ምዕመናን የደም ሕክምና ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ክንዳቸውን ዘርግተው የወገናቸውን ሕይወት እንዲታደጉ በመግለጫቸው አሳስበዋል።
የእምነት አስተምሕሮ ልዩነት ያለ ቢሆንም ሁሉም ተቋማት ያለ ልዩነት የደምና የዓይን ብሌን ልገሳን እንደሚደግፉ የሃይማኖት አባቶች በመግለጫቸው አስታውቀዋል።
በተለይ በዚህ በአፅዋማት ወቅት የደም ልገሳ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የእምነት ተቋማት በቁርጠኝነት እንደሚሠሩ ቃል እንገባለን ያሉት የሃይማኖት አባቶች በመግለጫቸው፤ በአፅዋማቱ የደም እጥረት እንዳይከሰት የጤንነት ሁኔታ የሚፈቅድላቸው ዜጎች ደም በመለገስ ሕይወት እንዲታደጉ የሃይማኖት አባቶች ጥሪ አቅርበዋል።
በመድረኩ ከ40 በላይ ሰዎች ከኅልፈት በኋላ የዓይን ብሌናቸውን ለመለገስ ቃል በመግባት የክብር ፊርማቸውን በቃል ኪዳን ሰነዱ ላይ አስፍረዋል።
ሶሎሞን በየነ
አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 5 ቀን 2017 ዓ.ም