የደኅንነት ጥበቃን በቴክኖሎጂ የመደገፍ ጉዞ

አዲስ አበባ፡– ጊዜው የቴክኖሎጂ እንደመሆኑ፤ ከግለሰብ ቤት እስከ ሀገር የሰዎችን ሥራ በማቃለል ረገድ ቴክኖሎጂ እየተወጣ ያለው ሥራ ከፍተኛ ነው። በአሁኑ ዘመን በቤት ውስጥ፣ በተቋማት እና በከተማ የሚስተዋሉ እንቅስቃሴዎችን በመከታተል፤ ለደኅንነት አስጊ የሆኑ ጉዳዮችን ለመቆጣጠር እና ችግሮች ሲፈጠሩ መንስኤያቸውን ለመረዳት የቴክኖሎጂ ፍሬ የሆነው የደኅንነት ካሜራ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ማኅበረሰቡ በአካባቢው የሚፈጠሩ የደኅንነት እና የፀጥታ ችግሮች ለሚመለከተው አካል ባለበት ሆኖ ጥቆማ እንዲያደርስ ቴክኖሎጂ ሥራዎችን አቃሏል፡፡ እነዚህን ቴክኖሎጂዎች ተጠቅሞ ሕዝብ ማገልገል ደግሞ ከዘመኑ ጋር መጓዝ ነው፡፡

የመዲናዋ ነዋሪ በአካባቢው የሚስተዋሉ የፀጥታ ችግሮች ማኅበረሰቡ ባለበት ሆኖ እንዲጠቁም የሚያስችል ነፃ የስልክ መስመር 8882፤ የኅብረተሰብ ተሳትፎ መተግበሪያ እና ሌሎች የቴክኖሎጂ ውጤቶች በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ትናንት ይፋ ተደርጓል፡፡

በወቅቱ የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ ሊዲያ ግርማ እንደተናገሩት፤ አዲስ አበባ ከተማ ስማርት ሲቲ እንደመሆኗ መጠን የሰላምና የደኅንነት አጠባበቅ ሂደት የከተማዋን ሁሉን አቀፍ አካሄድ የሚመጥንና በዚሁ ልክ ጠንካራ እንዲሆን ከምንግዜውም በላይ መሥራት ያስፈልጋል፡፡

የሰላምና ፀጥታ ቢሮው በአዋጅ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት እስከ ወረዳ ባለው መዋቅር ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡ ከዚህ ወስጥ አንዱ የከተማውን የፀጥታ ሥራዎችን በቴክኖሎጂ አማካኝነት መስጠት እና የከተማው ነዋሪ ባለበት ሆኖ፤ የሚስተዋሉ የፀጥታ ችግሮች መጠቆም የሚያስችል የቴክኖሎጂ ሥርዓት ተዘርግቷል ሲሉም ያስረዳሉ፡፡

ከዚህ አንጻር በቢሮው በበጀት ዓመቱ 10 የሚሆኑ ቴክኖሎጂዎች ለማልማት ተችሏል፡፡ ከአራቱ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ውጭ የቢሮውን ሥራ ከወረቀት የፀዳ እንዲሆን የሚያስችሉ ሲሆን፤ አራቱም ለከተማው ነዋሪ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ተደራሽ እና ቀልጣፍ ማድረግ የሚያስችሉ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡

የመጀመሪያው በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊሲ የለማው የኅብረተሰብ ተሳትፎ መተግበሪያ ሲሆን፣ ነዋሪው በአካባቢው የሚስተዋሉ የፀጥታ ችግሮች በመተግበሪያው አማካኝነት ለቢሮው ጥቆማ እንዲያቀርብ የሚያስችል ነው። ይህም መተግበሪያ ማኅበረሰቡን በማሳተፍ በከተማው አስቀድሞ የፀረ-ሰላም ኃይሎችን እንቅስቃሴ ለመከላከል ያስችላል ሲሉ ይናገራሉ፡፡

ሁለተኛው 8882 ነፃ የስልክ መስመር ነው፡፡ ይህም የጥሪ መስመር ነዋሪዎች አጠቃላይ የፀጥታ ችግሮች ለቢሮው እንዲያሳውቁ የሚረዳ ነው፡፡ ሦስተኛው ቢሮው አጠቃላይ የሚሠራቸውን ሥራዎች ለነዋሪዎች የሚያሳውቅበት እና በስልክ መስመሩ መጠቀም ያልፈለገ ጥቆማዎችን የሚያቀርብበት ድረ ገጽ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የአዲስ አበባ ፀጥታ ቢሮ ጉባኤዎች እና የተለያዩ ሁነቶች ሲዘጋጁ ዝግጅቱ በሰላም እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ሥራ ስለሚሠራ፤ የሁነት ፍቃድ የሚሰጠው ቢሮው መሆኑን የሚያነሱት ኃላፊዋ፤ ለዚህም የሁነት አዘጋጁ በአካል የሚመጣ ሲሆን፤ አሁን በኦንላይን እንዲያገኝ የሚያስችል አሠራር መዘርጋቱን ይገልጻሉ፡፡

ስለ መተግበሪያው ማብራሪያ የሰጡት ኢንስፔክተር ዓለሙ ተሰማ በበኩላቸው፤ መተግበሪያው የለማው በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ሲሆን፤ ዜጎች ባሉበት ሆነው የሚያጋጥሟቸውን ነገሮች ለፀጥታ አካላት ሪፖርት እንዲያደርጉ የሚያስችል ነው ይላሉ፡፡

ኢንፔክተሩ እንደሚሉት፤ መተግበሪያው እንዲለማ የተፈለገበት ዋና ዓላማ ዜጎችን ያሳተፈ የወንጀል መከላከል ሥራ ለመሥራት፣ በመረጃ የተመራ የፀጥታ አገልግሎት ለመስጠት እና ቴክኖሎጂን መጠቀም የሚችሉ የፖሊስ አካል ለመፍጠር ነው፡፡

አሁን ላይ መተግበሪያው ተደራሽ የሆነው በአዲስ አበባ እና በድሬዳዋ ከተማ ሲሆን፤ በቀጣይ በመላ ሀገሪቱ ተደራሽ እንዲሆን ይደረጋል፡፡ ዜጎች በተለያዩ አማራጮች በቪዲዮ፣ በፎቶ፣ በመልዕክት እና በሰነድ መልክ አድርገው መረጃዎችን መላክ እንደሚችሉም ያስረዳሉ፡፡

መተግበሪያው ከ991 ጋር የተያያዘ ሲሆን፤ በአንዳንድ ሁነቶች ምክንያት የሚዘጉ መንገዶች ሲኖሩ በመተግበሪያው አማካኝነት ማወቅ ይቻላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በሕግ የሚፈለጉ ወንጀለኞች፤ የጠፋ ሰው ወይም ንብረት በመተግበሪያው አማካኝነት ስለሚለቀቅ ለመፈለግ ያስችላል ይላሉ፡፡

በተጨማሪም በመተግበሪያው ላይ መረጃዎች ሲላኩ ማን በምን ሰዓት እንደላከ እና ሌሎች መረጃዎች ስለሚመዘገብ የተደራጀ የወንጀል ክትትል ለማድረግ ያስችላል፡፡ ፈጣን ምላሽ በመስጠት ዜጎች በፀጥታ አካላት ላይ እምነት እንዲኖራቸው ያደርጋል፡፡ ምንአልባትም ዜጎች ለሚያቀርቡት ጥያቄ ተገቢው ምላሽ ካልተሰጠም ቅሬታ ለመስጠት ያስችላል ይላሉ፡፡

ኢንስፔክር ዓለሙ እንደሚሉት፤ መተግበሪያው የፀጥታ አካላት የወንጀል መረጃዎችን በመተንተን ውሳኔዎችን እንዲያስተላልፉ የሚረዳ ሲሆን፤ እስካሁን ድረስ 55 ሺህ ሰው መተግበሪያውን አውርዶ እየተጠቀመ ነው፡፡

በሰላምና ፀጥታ ቢሮ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቡድን መሪ እና የፀጥታ መረጃ ክፍል አስተባባሪ አቶ አበበ ተካ፤ እንደሚሉት፤ ማኅበረሰቡ ሰላምና ፀጥታን የተመለከተ ማንኛውንም ጉዳይ፤ ዘረፋ ሊሆን ይችላል ወይም የሚያጋጥሙ የደኅንነት ስጋቶች ሲኖሩ፤ በተወሰነ መልኩ በነፃ የስልክ መስመር 8882 በመደወል እየጠቆመ ይገኛል።

ምላሽ ከመስጠት አኳያ መረጃው ከደረሰ በኋላ፤ ችግሩ አለ ወደ ተባለበት ክፍለ ከተማ፤ በእዚህ አካባቢ ላይ እንደዚህ አይነት ችግር ተፈጥሯል እየተባለ ነው ምላሽ ስጡ የሚል መልዕክት ይላካል፡፡ ምንአልባት ምላሽ ካልተሰጠ በዚሁ መስመር በመደወል ቅሬታ ማቅረብ እንደሚቻል ያስረዳሉ፡፡

የሰላምና ፀጥታ ጉዳይ ቅንጅት የሚፈልግ እንደመሆኑ፤ ከደንብ ማስከበር፣ ከፖሊስ አካላት እና ከአደጋ ስጋት ኮሚሽን ጋር በቅንጅት ይሠራል። በዚህም መረጃዎች ሲኖሩ ከእነዚህ አካላት ጋር በመነጋገር አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ ይደረጋል ይላሉ፡፡

አሁን ላይ በቀን በአማካኝ እስከ 20 መረጃ ወደ ተቋሙ እንደሚመጣ ገልጸው፤ ነፃ የስልክ መስመሩ በስፋት እየታወቀ ሲመጣ እያደገ ይሄዳል ተብሎ ይጠበቃል ሲሉ ይናገራሉ፡፡

ዓመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You