የዩኒቨርሲቲው የማዕድናት ጥናትና ምርምር ሥራዎች

ኢትዮጵያ በበርካታ የማዕድን ሀብቶች ብትታደልም፣ እነዚህን ሀብቶቿን በሚገባ ለይቶ ለማወቅ የተደረጉ ጥናትና ምርምሮች እምብዛም እንደሌሉ ይገለጻል፡፡ ይህም እነዚህን የማዕድን ሀብቶች አውቆና ለይቶ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ለማድረግ ከዩኒቨርሲቲዎችና ከምርምር ተቋማት ብዙ የሚጠበቁ ሥራዎች እንዳሉ ያስገነዝባል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች በዘርፉ የተማረ የሰው ኃይል በማፍራትና ሥልጠና በመስጠት የሚያደርጉት ድጋፍ አንድ ነገር ሆኖ በተለይ በማዕድን ዘርፉ ጥናትና ምርምር ብዙ ርቀት መጓዝ እንዳለባቸው ይታመናል፡፡

አብዛኞቹ ዩኒቨርሲቲዎችም በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚገኙባቸውን ክልሎች የማዕድን ሀብቶች ለማወቅና ለመለየት የሚያስችሉ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን እያካሄዱ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዱ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲው በአማራ ክልል ያሉ ማዕድናትን በማጥናት የመለየትና የማሳወቅ አበረታች ሥራዎች እየሠራ መሆኑን ከዩኒቨርሲቲው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የወሎ ዩኒቨርሲቲ በማዕድን ዙሪያ በራሱም ሆነ ከአጋር አካላት ጋር በመሆን በማዕድን ዘርፉ ላይ እንደሚሠራም የዩኒቨርሲቲው የምርምር ኅትመት ሥነ ምግባርና ስርጸት ዳይሬክተር ሰይድ ሙሄ ዳውድ (ዶ/ር) ይናገራሉ፡፡

እሳቸው እንደሚሉት፤ ዩኒቨርሲቲው ሦስት ተልዕኮዎች ተሰጥተውታል፡፡ አንደኛው መማር ማስተማር፣ ሁለተኛው ምርምር ሲሆን፤ ሦስተኛው ደግሞ የማኅበረሰብ አገልግሎት ነው፡፡ በመማር ማስተማሩ በኩል የጂኦሎጂና የቴክኖሎጂ ትምህርት ክፍል አለው። በዚህም ከማዕድን አጠቃቀምና ሥርዓት ጋር የተያያዙ ሥልጠናዎችን ይሰጣል፡፡

ከማዕድን ጋር የተያያዙ ብዙ የምርምር ሥራዎችን በራሱና ከአጋር አካላት ጋር በመሆን ይሠራል፡፡ በማኅበረሰብ አገልግሎቱም በማዕድን ልማት ለሚሳተፉ አካላት ሥልጠና የመስጠትና ግንዛቤ የማስጨበጥ እንዲሁም የቴክኖሎጂ ሽግግር ሥራዎችንም ይሠራል፡፡

በተለይ ዩኒቨርሲቲው በሚገኝበት አማራ ክልል ወሎ አካባቢ ሰፊ የማዕድን ሀብት እንዳለ ጠቅሰው፣ በዚህ ላይ ጥናትና ምርምር እያካሄደ መሆኑን ዳይሬክተሩ ያመላክታሉ፡፡ እንደ ደላንታ ኦፓል ያሉት ደግሞ በመልማት ላይ እንደሚገኙ ተናግረው፣ ከእነዚህ ጋር ተያይዞ የማኅበረሰብ አገልግሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ሥራዎች እንደሚሠሩም ጠቁመዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በሚሠራባቸው አካባቢዎች እንደ ድንጋይ ከሰል፣ የኖራ ድንጋይ፣ ለጌጣጌጥ የሚሆኑ የከበሩ ማዕድናት እና ሌሎችም ማዕድናት እንዳሉ አመልክተዋል፡፡ የዓባይ ገባር በሆኑት ወንዞች ላይም እንዲሁ ማዕድናትን የማወቅና የመለየት ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸው አንስተዋል፡፡

እሳቸው እንዳብራሩት፤ በየትኛው አካባቢ ምን አይነት ማዕድን ይገኛል? የሚለውን ለማወቅ የልየታ ሥራ የተሠራበት ሁኔታም አለ፡፡ በቀጣይም ማዕድናቱ ሊገኙባቸው በሚችሉባቸው ሁኔታ ላይ ጥልቅ ጥናቶች ይደረጋሉ፡፡ ለአብነትም በአምባሰል የድንጋይ ከሰል የሚገኝበትን ቦታ ለማመላከት የሚያስችል የአለኝታ ቦታ ልየታ ሥራ ተሠርቷል፡፡ ይህንን ተንተርሶ በቦታው ላይ ምን ያህል መጠን ያለው የድንጋይ ከሰል ክምችት እንዳለ ለማወቅ የሚያስችል ጥናት ከአማራ ክልል ማዕድን ቢሮ ጋር እየተካሄደ ነው፡፡

ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ወቅት አዳዲስ አራት የሚሆኑ ፕሮጀክቶች የአለኝታ ቦታ ልየታ ጥናቶችን አካሂዶ ለክልሉ ማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ አስረክቧል የሚሉት ሰይድ (ዶ/ር)፤ ክልሉ ተጨማሪ ጥናት ይደረግባቸው ባላቸው ማዕድናት ላይ ደግሞ ጥናት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ አምባሰል ያለው የድንጋይ ከሰል ምን ያህል ለኢንቨስትመንት ብቁ ሊሆን ይችላል የሚለውን ለማወቅ በተያዘው ዓመት የጥናት ሥራ መጀመሩን ይገልጻሉ፡፡ በኦሮሞ ብሔር ብሔረሰብ ዞንም እንዲሁ የጂኦሎጂካል ካርታ በመሥራት ያለውን የሀብት መጠን እና የማዕድናቱን ዓይነት ለመለየት በጣም በጥልቀት እየተሠራ ያለ ፕሮጀክት እንዳለም ይጠቁማሉ፡፡

በተጨማሪም የዓባይ ገባር ወንዞች ላይ ምን ያህል መጠን ያለው ለኮንስትራክሽን ግብዓቶች ሊውል የሚችል የኖራ ድንጋይ ክምችት እንዳለ ለማወቅ ከከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስትቲዩት ጋር ጥናት እየተካሄደ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

እሳቸው እንደሚሉት፤ ዘንድሮ በአዲስ መልኩ ከኢንዱስትሪ ማዕድን ልማት ኢንስትቲዩት በተገኘው የገንዘብ ድጋፍ የወሎ፣ መቀሌና ቡሌሆራ ዩኒቨርሲቲዎች በጥምረት በጌጣጌጥና የከበሩ ማዕድናት ማምረት ሥራ ላይ የተሳተፉ ሰዎችን አቅም ለማጎልበት የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው፡፡ ፈጠራ በታከለበት መንገድ በቴክኖሎጂ በማምረት ከገበያ ጋር የሚያገናኙበት ዌብ ሳይት በመፍጠር ጭምር እየተሠራ ይገኛል፡፡ በዚህም ማዕድናቱን ማምረት፣ በአምራችና ሻጭ መካከል የገበያ ትስስር እንዲፈጠር ማድረግንና ምርት ማስተዋወቅን ያካተተ ሥራ ይሠራል፡፡

በማዕድን ልማት ወቅት ሊገጥሙ የሚችሉ አደጋዎችን በመቀነስ ላይም እንደሚሠራ ጠቁመዋል። ደላንታ አካባቢ በባሕላዊ መንገድ የኦፓል ልማት እንደሚካሄድ ጠቅሰው፣ በዚህም ብዙ ጊዜ ሰዎች ለተለያዩ ጉዳቶችና አደጋዎች ሲጋለጡ ይስተዋላል ይላሉ፡፡ ይህንን አደጋ ለመቀነስ የግንዛቤ ማስጨበጫ እንዲሁም ቴክኖሎጂ የሚያስፈልገው ቦታ ላይ ደግሞ ቴክኖሎጂ እንዲጠቀሙ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

ዳይሬክተሩ እንዳስታወቁት፤ የኦፓል አውጪዎች ወደ ቆፋሮ ሲገቡ በሚጨልመበት ጊዜ ሶላር እንዲጠቀሙ በማድረግ የሚደርስባቸውን ጉዳትና ችግር ለመቀነስ እየተሠራ ነው፤ በተለይ ብርሃን ማግኘት የሚችሉባቸውን መሣሪያዎች በማቅረብ በኩል እገዛ እየተደረገላቸው ይገኛል፡፡ በተጨማሪም የአደጋውን መጠንና ሁኔታ በመረዳት ራሳቸውን ለጉዳት ሳያጋልጡ እንዴት መከላከል እንዳለባቸው ግንዛቤ የማስጨበጫ ሥራዎች ተሠርተዋል። በኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስትቲዩት በኩል ሥራቸውን በቀላሉ ለመሥራት እንዲችሉ የሚረዱ ቴክኖሎጂዎችንና ሌሎች ድጋፎችን ያደርጋል፡፡

‹‹የኦፓል ማልማት ሥራ ከመጀመሪያ አንስቶ እስከ መጨረሻው ባለው ሂደት ብዙ ሰዎች የሚሳተፉበትና ብዙ ሀብት የሚወጣበትም እንደመሆኑ በዚህ ላይ በየጊዜው ብዙ ጥናቶች ይካሄዳሉ›› የሚሉት ሰይድ (ዶ/ር)፤ በእዚህም በኩል ዩኒቨርሲቲው ከሌሎች አጋር አካላት ጋር የሚያደርጋቸው ጥናቶችና በግለሰቦች በኩል የሚደረጉ ጥናቶች እንዳሉ ይጠቁማሉ፡፡ በግለሰብ ደረጃ የሚካሄዱ ጥናቶች ከጥናት አልፈው በፕሮቶታይፕ ደረጃ የደረሱ ሊኖሩ እንደሚችሉም ይጠቁማሉ፡፡

እሳቸው እንደሚሉት፤ ዩኒቨርሲቲው ከማዕድን ጋር ተይይዞ ከሚሠራቸው ፕሮጀክቶች መካከል ግማሹ ዘንድሮ የተጀመሩ ናቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል አንዱ የጌጣጌጥ ማዕድናት አልሚዎችን፣ ሻጭና ገዥን በማካተት ሥራው ዲጂታላይዝድ እንዲሆን ለማድረግ የሚካሄደው የአልሚዎችን አቅም ለማጎልበት የሚሠራ ፕሮጀክት ነው። ይህ ፕሮጀክት በጥሩ ሁኔታ እየተሠራበት ነው፡፡

በዚህም ላይ የቴክኖሎጂ፣ የጂኦሎጂና የኬሚስትሪ ባለሙያዎችና ብዙ ዩኒቨርሲቲዎችም ተሳትፈውበታል። የአማራ ብረታ ብረት ኢንስትቲዩት /ኢንተርፕራይዝ/፣ የሙያና የትግበራ ኮሌጆችም እየተሳተፉበት በቅንጅት እየተሠራ ያለ ፕሮጀክት ነው፡፡ ይህን ሥራ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለማስፋት በማሰብ መቀሌና ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሳተፉበት ተደርጓል፡፡

በዓባይ ወንዝ የኖራ ድንጋይ ላይም ጥናት እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ሌሎቹም ከክልሉ ማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ ጋር የሚሠሩ ሦስት ፕሮጀክቶች እንዳሉ ጠቅሰው፣ በዩኒቨርሲቲው ብቻ አምባሰል ላይ ያለው የድንጋይ ከሰል ሀብት ክምችት ምን ያህል ነው የሚለው እየተጠና እንደሚገኝ አመላክተዋል፡፡

የመጀመሪያው ሥራ የትኛው አካባቢ ላይ ምን ዓይነት ማዕድን አለ የሚለውን በጥልቀት አጥንቶ ካርታ መሥራት እንደሆነም ዳይሬክተሩ ይገልጻሉ፡፡ የድንጋይ ከሰል ጥናቱ የመጀመሪያ ሥራ አልቆ ለክልሉ ማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ መተላለፉን ጠቁመው፣ የድንጋይ ከሰሉ ያለበት ቦታ ከተለየ ቀሪው ሥራ የሚሆነው ለአልሚ ኢንቨስተሮች ለመስጠት ምን ያህል አቅም አለ የሚለው ጥናት እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ በመሆኑም በቀጣይ የክምችቱን መጠን ለማወቅ ጥናት እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡

በከበሩ ማዕድናት ላይ የሚካሄደው ጥናት የሀገሪቱን ዩኒቨርሲቲዎች በሚያሳትፍ፤ አልሚዎች፣ ሻጮችንና ገዥዎችን በማስተሳሰርና ፈጠራ የታከለባቸው መፍትሔዎችን ለማቅረብ በሚያስችል መልኩ እየተሠራ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

ዳይሬክተሩ እንዳብራሩት፤ ዩኒቨርሲቲው ሥልጠ ናዎችንም ይሰጣል፤ ይህም በሁለት መልኩ ይካሄዳል፡፡ በግል የሚሠሩ ተመራማሪዎችን ሥራዎች ወደ ምርምር ኅትመት የማይቀየሩ ከሆኑና ለማኅበረሰቡ አገልግሎት ላይ እንዲውል ከተፈለገ እስከ 40 የሚሆኑ ሰዎች የሚሳተፉበት የአንድ ጊዜ ሥልጠና ይሰጣል፡፡ ይህንን ዓይነት ሥልጠና በተደጋጋሚ ጊዜ ተሰጥቷል፡፡

ሌላው የሥልጠና ዓይነት ደግሞ ፍላጎት መር የሆነው ሲሆን፣ ሥልጠና ለአልሚዎች አልያም ለቢሮ ባለሙያዎች አልያም ለወረዳ ባለሙያዎች የሚሰጥ ይሆናል፡፡ ይህም በእነርሱ ፍላጎት ላይ መሠረት ተደርጎ የሚሰጥ ነው፡፡ ይህ ሥልጠናም ለብዙ ጊዜ በብዙ ቦታዎች ላይ ተሰጥቷል፡፡

በተለይ የኦፓል አልሚዎች ሆኑ ሌሎች ቴክኖሎጂ ከመጠቀም አኳያ ሶላር ኃይል ያላቸው መሣሪያዎችን እንዲጠቀሙ እየተደረገ እንደሚገኝ የሚገልጹት ዳይሬክተሩ፤ ስጋትን በቀነሰ ሁኔታ ሀብትን ማውጣት እና ማኅበራት እንዲጠናክሩ የሚያስችሉ ሌሎች መሰል ሥልጠናዎች እየተሰጡ መሆናቸውንም አመላክተዋል። ሕጋዊ በሆነ መንገድ ምርታቸውንና ራሳቸውን የሚያስተዋወቁበት መንገድ መፍጠርን ያለሙ ሥልጠናዎች እየተሰጡ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

የክልሉን የማዕድን ሀብት ለማጥናት አንዳንድ ጊዜ የአቅም ማነስ እንደሚጋጥምም ሰይድ (ዶ/ር) ያመለክታሉ፡፡ ሥልጠናውን ለሁሉም ለማዳረስ የአቅም ውስንነት ያጋጥማል ሲሉ ጠቅሰው፣ ለአብነት ለአሠልጣኞች የተሰጠውን ሥልጠና ለሁሉም ለማዳረስ ወረዳዎችና ማኅበራት አቅም ሊያንሳቸው እንደሚችል አመልክተዋል፤ ይህ ችግር ሥልጠናዎችን በሚፈለገው ልክ ለብዙዎች ተደራሽ ለማድረግ የታሰበውን አሠራር ለመዘርጋት ተግዳሮት እንደሚሆን ይጠቁማሉ፡፡

በተጨማሪም አሁን በአንዳንድ አካባቢዎች ያለው የፀጥታ ችግር ሁሉም ቦታዎች ላይ ተደራሽ ለመሆንና አስፈላጊው ድጋፍ ለማድረግ ተግዳሮት እየሆነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

ዳይሬክተሩ ክልሉ እምቅ የማዕድን ሀብት ያለው እንደመሆኑ ዩኒቨርሲቲው አሁን ያሉትን የማዕድን ሀብቶች የማወቅ፣ የመለየትና ለማልማት የሚያስችሉ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ባሻገርም ተዛማጅ የሆኑ እንደገና ቢፈለጉ አቅም ያላቸው ሌሎች ማዕድናት የሚገኙበትን ሁኔታ እንዳለም አመልክተው፣ ይህንን በስፋት ተደራሽ ለማድረግ ግን ዩኒቨርሲቲው የበጀትና የቴክኖሎጂ እጥረት እንዳለበት ይገልጻሉ፡፡ በተለይ በነዚህ ሁለት ዓመታት ያለው የፀጥታ ችግር ሥራዎችን በሚገባ ተከታትሎ ለመሥራት አስቸጋሪ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የክልሉ የማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ በማዕድን ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ ባደረጋቸው እንቅስቃሴዎች አበረታች ለውጦች እያመጡ ናቸው ይላሉ፡፡ ምርምር ቢደረግባቸው ተብለው የተለዩትን የማዕድን ሀብቶች ዩኒቨርሲቲዎቹ በምርምር እንዲያግዙት እያደረገ መሆኑን ተናግረው፣ የተገኘውን ውጤትም አልሚዎች ገብተው እንዲሠሩበት ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

እሳቸው እንዳስታወቁት፤ ክልሉ ዩኒቨርሲቲዎችን ባሳተፈ መልኩ እየሠራ እንደመሆኑ ወሎ ዩኒቨርሲቲም ከቢሮ ጋር በተቀናጀ መልኩ እየሠራ ይገኛል፡፡ ዩኒቨርሲቲው የማዕድናት ጥናት ኃላፊነቱን በጥራት እየተወጣ ይገኛል፡፡ በዘርፉ መሠማራት ለሚፈልጉ አልሚዎች ያለውን የማዕድን መጠንና ክምችት የተመለከተ መረጃም ለሚመለከተው ክፍል እያቀረበ ነው፡፡ እነዚህ ጥናቶች ከስር ከስር ለልማት እየዋሉና አቅም እየተፈጠረ ሲመጣ ብዙ የማዕድን ሀብቶችን የማወቅና የማልማት ዕድሉ እየሰፋ ይመጣል፡፡

ዳይሬክተሩ እንዳብራሩት፤ ዩኒቨርሲቲው አሁን ባለው አቅም ደረጃ ማዕድናት የሚመረምርበትና የሚለይበት ቤተሙከራ አለው፡፡ ቤተሙከራው ያለው አቅም አሁን ያሉትን ሥራዎች መሥራት ያስችሉታል፤ ከአቅሙ በላይ የሆኑ ሥራዎች ሲያጋጥሙት ደግሞ ከአጋር አካላት ጋር በፈጠረው ቅንጅት በእነርሱ ቤተ ሙከራዎች ይጠቀማል። በተጨማሪም የአንዳንድ ማእድናት ናሙዎች ወደ ውጭ የሚላኩባቸው ሁኔታዎችም አሉ፡፡ ለአብነት የከበሩ ማዕድናትን ለማወቅና ለመለየት በራሱም በአዲስ አበባ ካሉ አጋር አካላት ጋር የሚሠራቸው ሥራዎች ይኖራሉ፤ ናሙናዎችን ወደ ውጭ ሀገሮች የሚልክባቸው ጊዜያትም ሊኖሩ ይችላሉ፡፡

‹‹የክልሉ ማዕድን ሀብት ይቅርና ደቡብ ወሎ የሚገኘው የማዕድን ሀብት በውል ተለይቶ መጠኑ ታውቆ የትኛው መልማት ይቻላል፣ የትኛው ደግሞ መልማት አይችልም የሚለው ተለይቶ አይታወቅም›› ሲሉ ዳይሬክተሩ ገልጸው፣ ይህም ዩኒቨርሲቲው ገና ብዙ መሥራት እንዳለበት እንደሚያመለክት አመልክተዋል፡፡

በቀጣይ ዩኒቨርሲቲው አሁን የጀመራቸውንና በሂደት ላይ ያሉ ፕሮጀክቶችን በማጠናቅቅ ለሚመለከተው አካል እንደሚያሳወቅ ያመላክታሉ፡፡ በተለይ የክልሉ ማዕድን ልማት ቢሮ፣ ከከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴርና ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስትቲዩት ጋር በሚፈለገው ልክና መጠን ለማቅረብ ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

ወደፊትም ይህንን መሠረት አድርጎ የሚሠራቸው ሥራዎች እንዳሉ አስታውቀዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው የተግባር /አፕላይድ/ ዩኒቨርሲቲ መሆኑን ጠቅሰው፣ በቴክኖሎጂ የትምህርት ክፍሉ በኩል ከአጋር አካላት ጋር ልማቱ ላይም ሊሠራ የሚችላቸው ሁኔታዎች እንዳሉም አመላክተዋል። በተለይ እነዚህ የምርምር ሥራዎች ውጤታማ እየሆኑ ሲሄዱ የማዕድን ልማቱን በማስፋት ሌሎች የምርምር ሥራዎች የሚሠራበት ሰፊ ዕድል እንደሚፈጠር ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን መጋቢት 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You