
-ከ8 ሺህ በላይ የሰደድ እሳት መከላከያ መሣሪያዎች ለክልሎች ተሠራጨ
አዲስ አበባ፦ በደን ሀብት ላይ ጥፋት የሚያደርሱ ግለሰቦች በደን ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 1065/2018 እና በአዋጁ ማስፈጸሚያ ደንብ ቁጥር 544/2024 መሠረት ሕግ ፊት ቀርበው ተጠያቂ እየሆኑ አይደለም ሲል የኢትዮጵያ ደን ልማት አስታወቀ። ተቋሙ በተያዘው በጀት ዓመት ከ8 ሺህ በላይ የሰደድ እሳት መከላከያ መሣሪያዎችን ለክልሎች ማሠራጨቱም ተጠቁሟል።
በኢትዮጵያ ደን ልማት የደን አደጋ መከላከል ዴስክ ኃላፊ አቶ አዱኛ አበበ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ ደን ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 1065/2018 እና በአዋጁ ማስፈጸሚያ ደንብ ቁጥር 544/2024 ላይ ለደን ሀብቱ መደረግ ያለበት ጥበቃና እንክብካቤ በግልጽ ተቀምጧል። እንዲሁም አንድ ግለሰብ በደን ሀብቱ ላይ ጥፋት ቢያደርስ በሕግ ፊት ቀርቦ ምን ምን ዓይነት ተጠያቂነት እንደሚከተለው በአዋጁና ደንቡ ላይ ተዘርዝሯል።
በአዋጁና ደንቡ መሠረት በደን ሀብቱ ላይ ጥፋት የሚያደርሱ ግለሰቦች ሕግ ፊት ቀርበው ተጠያቂ ሆነው አስተማሪ ርምጃ ሊወሰድባቸው እንደሚገባ አመልክተው፤ በሽምግልናና በእርቅ ይለቀቃሉ ብለዋል።
ቀደም ሲል የደን ጥበቃ አዋጁ እ.ኤ.አ በ2018 ወጥቶ እስከ 2023 ድረስ ማስፈጸሚያ ደንብ ስላልወጣለት “ጥፋተኛ ይዘን በምን አግባብ እንቅጣ፤ አዋጁን ተፈጻሚ ለማድረግ ተቸገርን” የሚል ቅሬታ ክልሎችና ባለድርሻ አካላት በስፋት ያነሱ እንደነበር አቶ አዱኛ አውስተው፤ በቀረበው ቅሬታ መሠረት የአዋጁ ማስፈጸሚያ ደንብ ቁጥር 544/2024 ተረቆ ወደ ሥራ ከገባ አምስት ዓመት ገደማ ሆኖታል። ነገር ግን በደን ሀብት ላይ ጥፋት የሚያስከትሉ ግለሰቦች ዛሬም በአዋጁና ደንቡ መሠረት ሕግ ፊት ቀርበው ተጠያቂ እየሆኑ አይደለም ብለዋል ዴስክ ኃላፊው አቶ አዱኛ።
ዴስክ ኃላፊው፤ በአዋጁና ደንቡ መሠረት ጥፋተኞች ሕግ ፊት ቀርበው አስተማሪ ርምጃ ስለማይወሰድባቸው እና ማኅበረሰቡም ጥፋተኞችን ለሕግ አሳልፎ ከመስጠት አኳያ ያለው ተሳትፎ አናሳ በመሆኑም በደን ሀብቱ ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች መበራከታቸውን ያስረዳሉ።
በደን ሀብቱ ላይ ጥፋት የሚያደርሱ ግለሰቦች በአዋጁና በደንቡ መሠረት ሕግ ፊት ቀርበው ተጠያቂ እንዲሆኑ ክልሎችና ዘርፍ መሥሪያ ቤቶች በቁርጠኝነት ሊሠሩ እንደሚገባ ዴስክ ኃላፊው አሳስበው፤ ደን የብዝኃ ሕይወት ዋስትናና የዓለም ሳምባ መሆኑን ገልጸዋል።
አንድን አካባቢ ብቻ ሳይሆን ሀገርን ብሎም ዓለምን የሚጎዳ ወንጀል እየተፈጸመ በሽምግልናና እርቅ የሚታለፍበት አግባብ ሊኖር እንደማይገባ በአፅንዖት ተናግረዋል።
ማኅበረሰቡ የደን ሀብቱን እንደ ዓይኑ ብሌን ከመጠበቅ ባለፈ ጥፋተኞችን ሕግ ፊት በማቅረብ ተፈጥሮ ሀብቱን ከጉዳት ለመጠበቅ በሚደረገው ርብርብ የበኩሉን ሚና ሊወጣ ይገባል ያሉት አቶ ዴስክ ኃላፊው፤ ማኅበረሰቡ በደን ሀብት ላይ ጥፋት በሚያደርስ ግለሰብ ላይ ማኅበራዊ ርምጃ መውሰድና ከማኅበራዊ ተሳትፎ (ከእድር፣ እቁብ ወዘተ) የማግለል ርምጃ ሊወስድ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በእኛ ሀገር ነባራዊ ሁኔታ ከ90 በመቶ በላይ የደን እሳት ቃጠሎ መንስኤው ሰው ሠራሽ ነው የሚሉት አቶ አዱኛ፤ በተለይ የደን እሳት ቃጠሎ በቶሎ በቁጥጥር ሥር ካልዋለ በአጭር ጊዜ ውስጥ መጠነ ሰፊ የደን ሀብት ውድመት ያስከትላል። በተለያዩ ጊዜያቶች በተቀሰቀሰ ሰው ሠራሽ የሰደድ እሳትም ሀገር ከፍተኛ የደን ሀብት ማጣቷን አመልክተዋል።
በደን ሀብቱ ላይ የሚከሰት የእሳት ቃጠሎን ቀድሞ ለመከላከል ተቋሙ በየወቅቱ ለክልል የዘርፉ አካላት የሥልጠና፣ የቴክኒክና የቁሳቁስ ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቁመው፤ በተያዘው በጀት ዓመት ዘመኑን የዋጀና ወቅቱን የጠበቀ ሥልጠና ከመስጠት ባለፈ ድንገት እሳት ቢቀሰቀስ በቁጥጥር ሥር ለማዋልና ለመከላከል የሚያገለግሉ 8 ሺህ 30 የእሳት መከላከያ የእጅ መሣሪያዎች (አካፋ፣ ዶማ፣ የአደጋ መከላከያ ኮፍያ/ሄልሜት፣ የእሳት ማጥፊያ ዛቢያ፣ ጓንት፣… ወዘተ) ለሁሉም ክልሎች በፍትሐዊነት ማሰራጨቱን ተናግረዋል።
በተጨማሪም አንድ ሺህ 900 የእሳት አደጋ ሲከሰት የመጀመሪያ ሕክምና ርዳታ መስጫ ኪት ለሁሉም ክልሎች መከፋፈሉን ገልጸው፤ የተደረገው ድጋፍ ድንገተኛ እሳት ሲከሰት ተቀናጅቶ ቶሎ ምላሽ ለመስጠትና ለመከላከል ያስችላል ብለዋል።
ሶሎሞን በየነ
አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 5 ቀን 2017 ዓ.ም