
የትግራይ ሕዝብ ትናንትም ሆነ ዛሬ በቀጣይም ቢሆን የሚፈልገው ሰላም እና ልማት ነው። ለዚህ ደግሞ በተለያዩ ወቅቶች የገባባቸው ጦርነቶች፣ ጦርነቶቹ ያስከፈሉት ዋጋ በብዙ አስተምረውታል። አሁን ካለበት ድህነት እና ኋላ ቀርነት ለዘለቄታው ወጥቶ የተሻለ ሕይወት ለመኖር ያለውን መሻት እውን ለማድረግም ከሰላም እና ልማት ውጪ ተስፋ የሚሆነው ነገር አይኖርም።
ይህን ተጨባጭ እውነታ በአግባቡ ለመረዳት የተለየ የፖለቲካ እሳቤም ሆነ ምልከታ አይፈልግም። ያለፉትን ስድስት አስርተ ዓመታት የትግራይ ሕዝብ የሄደባቸውን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ መንገዶች፣ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ በአንድም ይሁን በሌላ ሕዝቡ የከፈለውን እና ዛሬም እየከፈለ ያለውን ዋጋ መመልከት በራሱ በቂ ነው።
የትግራይ ሕዝብ በነዚህ ዓመታት የተለያዩ ምክንያቶች እና ስሞች በተሰጧቸው ጦርነቶች ተስፋዎቹን አጥቷል፣ ከፍ ያለ ቁሳዊ እና ሰብዓዊ ውድመት ደርሶበታል፣ አንዱ ጦርነት ከፈጠረው ጠባሳ ሳያገግም በሌላ አውዳሚ ጦርነት ብዙ ዋጋ ለመክፈል ተገድዷል። በብዙ ስለ ሰላም እና ልማት በፈለገ ቁጥር የጦርነት ፈተናዎች ጥላ ሆነውበታል።
በየትኛውም የዓለም ክፍል እንዳለ ማኅበረሰብ የትግራይ ሕዝብ ከጦርነት አተርፋለሁ ብሎ የሚያስብ እና ለዚህ ስንኩል አስተሳሰብ ጠብመንጃ አንግቦ ቃታ ለመሳብ የሚሽቀዳደም ሕዝብ አይደለም። ሃይማኖታዊ ሆነ ማኅበረሰባዊ እሴቶቹ፤ ከዚህ የሚመነጨው ማንነቱ ይህንን እንዲያደርግ አይፈቅዱለትም።
ከዚህ ይልቅ የሰላም እጦት ካስከፈለው ዋጋ አኳያ ስለሰላም አብዝቶ የሚዘምር፣ ሰላም የቱን ያህል ለዕለት ተዕለት ሕይወቱ፣ ከዚያም አልፎ ተስፋ ለሚያደርጋቸው ከአብራኩ ለወጡ ልጆቹ ነገ፤ የተስፋ ስሌት ትልቁ አቅም እንደሆነ በአግባቡ የተረዳ፤ በዚህ መረዳት ውስጥ ነገዎቹን ተስፋ የሚያደርግ ሕዝብ ነው።
ይህንን ተጨባጭ እውነታ እንኳን ከሕዝቡ አብራክ ለወጣ ቀርቶ ትግራይ ውስጥ በእንግድነት ገብቶ ለወጣ ሰው የተሰወረ አይደለም። ጤነኛ አዕምሮ ያለው ሰውም ቢሆን ሕዝቡ ከመጣባቸው የሕይወት ውጣ ውረዶች ተነስቶ ይህንን የሕዝቡን የሰላም እና የልማት መሻት ለመረዳት ብዙም የሚከብደው አይደለም፤ እውነታውን ለመረዳትም የተለየ ሙያ እና እውቀት የሚጠይቅ አይደለም።
አብዛኛው የክልሉ ሕዝብ በወጣትነት የእድሜ ክልል የሚኖር ከመሆኑ አኳያ፣ ይህ የማኅበረሰብ ክፍል ከሁሉም በላይ እንደ አንድ ጤናማ ትውልድ ሠርቶ ማግኘትን፣ ባለው አቅም ሕልሙን መሆንን፣ ከራሱ አልፎ ለሌሎች መትረፍን፣ ለሀገር እና ለሕዝብ ተስፋ መሆንን የሚመኝ ነው።
ተምሮ ከፍ ያለ ደረጃ መድረስን፣ አግብቶ እና ወልዶ ለወግ ማዕረግ መብቃት የሚፈልግ፤ ከቀደሙት ትውልዶች ተምሮ የራሱን ታሪክ የመሥራት እና ከራሱ አልፎ ለመጪው ትውልድ የተሻለ ሀገር ፈጥሮ የማለፍ ተፈጥሯዊ መነቃቃት፤ ራሱን የመሆን ፍጥረታዊ ነፃነትም ያለው ነው።
ከሁሉም በላይ ያለበት ዘመን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ አስተሳሰብ በየትኛውም መንገድ ከጦርነት አትራፊ እንደማይሆን በቂ ግንዛቤ ያስጨበጠው፣ ከቀደሙ የታሪክ ትርክቶች በብዙ መማር በሚያስችሉ መልካም አጋጣሚዎች መሐል ያለ እና የሚኖር የማኅበረሰብ ክፍል ነው፡፡
ይህን የማኅበረሰብ ክፍል ባልተገቡ ትርክቶች ለግል እና ለቡድን ፍላጎቶች ማሳኪያ መሣሪያ አድርጎ የመጠቀም መሻት በየትኛውም መልኩ ተቀባይነት ሊኖረው የሚገባ አይሆንም። ከዚህ ይልቅ የዚህም የማኅበረሰብ ክፍል ሆነ የመላውን የትግራይ ሕዝብ የሰላም እና የልማት ጥያቄ ተቀብሎ ለዚህ የሚሆን የፖለቲካ ቁርጠኝነት መፍጠር ከሁሉም የሚጠበቅ ነው።
በተለይም አሁን ላይ ለትግራይ፣ ሕዝብ ከዚያም አልፎ ለሀገር ሠላም እና መረጋጋት ስጋት በሆነ መንገድ ላይ ያሉ ኃይሎች ለሕዝብ ጥያቄ ያላቸውን ቀናዒነት በተጨባጭ ማሳየት የሚችሉት የሕዝቡን የሰላም እና የልማት ጥያቄ ተቀብሎ ማስተናገድ የሚያስችል ማንነት መገንባት፤ የትግራይ ሕዝብ ወደሚፈልገው የሰላም እና ልማት መንገድ እንዲሄድ ዕድል ሲሰጡት ብቻ ነው!
አዲስ ዘመን መጋቢት 5 ቀን 2017 ዓ.ም