
ኢትዮጵያ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ያሉባት ሀገር ናት፡፡ የባህላዊ አልባሳት፣ አሠራር እና የአለባበስ ሥርዓቷ እንዲሁ በየአካባቢው የተለያየ መልክ አለው፡፡ አልባሳቱ የማንነታችን መገለጫ ነው። ልዩ ድምቀታችንና መታወቂያ በመሆን ያገለግላል። አሁን አሁን ደግሞ ጥበቡ ዲዛይኑ ስፌቱ ሁሉ ዘመኑን የዋጀና ከዘመኑ ጋር አብሮ በመዘመን የሚሄድ እየሆነም መጥቷል፡፡ ይሄ አሠራራቸውም በበዓላት ቀን የሚለበሱ በርካታ የክት ባህላዊ ልብሶች ሰርክ የሚለበሱበትን ዕድል እየፈጠረ ይገኛል፡፡ ምቹና ቅልል ብለው የሚቀርቡ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። ሆኖም ዋጋቸው የሚቀመስ አይደለም፡፡ በመሆኑም በአዘቦት ቀናት የሚለበስ መሆን አልቻለም፡፡
ለመሆኑ የባህላዊ አልባሳት አሠራርና የይዘት ትርጉም ምን ያህሎቻችን በጥልቀት እናውቃለን? በዚህ ጉዳይ ላይ የዝግጅት ክፍላችን መልስ የሚሰጥ አንድ ዳሰሳ እንደሚከተለው ለመሥራት ወድዷል። እንደሚታወቀው የሁሉንም አካባቢ አልባሳት ዓይነት፣ ይዘትና መገለጫ እዚህ ዘርዝሮ ማቅረብ አይቻልም፡፡ በመሆኑም ለዛሬ በሽመና ጥበቡ የተንቆጠቆጡ አልባሳት በማምረት የሚታወቀውን የወላይታ ዞን የባህላዊ አልባሳት አሠራር እና የአለባበስ ሥርዓት እናስቃኛችኋለን፡፡
ዳሰሳውን ያሰናዳነው ባህላዊ አልባሳቱ በብዛት የሚሠሩበትና ሽያጭ የሚከናወንበት ሽሮ ሜዳ ብቅ ብለን ነው። በአንዳንድ የልብስ መደብር እንደቃኘነው የአልባሳቱ ዓይነት ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ የአለባበስ ሥርዓቱም ቢሆን ለየቅል መሆኑን አስተውለናል፡፡ ዕድሜንና ጾታን ማዕከል አድርገው በመዘጋጀታቸው ይለያሉ፡፡ ማህበራዊ ደረጃን አስመልክቶም የሚዘጋጁ ብዙ ናቸው፡፡ የንግስ በዓላትን ጨምሮ ጀግንነትን ለማንፀባረቅ፣ ለአደን፣ ለሀዘን፣ ለደስታና ለአምልኮት በተለያዩ አውዶች ለመልበስ የተሠሩም ይገኙበታል፡፡
ሁሉም በዘመናዊ ፋሽን እንዲሁም በባህላዊ አልባሳት ስፌት ባለሙያዎች ስለመዘጋጀታቸውም ተረድተናል። ይሄን ሁሉ ስንቃኝ ማብራሪያቸው ያልተለየን በሽሮ ሜዳ የባህላዊ አልባሳት መደብር ባለቤት ወይዘሮ ፀሐይ ማዳ ናቸው። እሳቸው በተለይ የወላይታ ሕዝብን ማንነትንና ባህል አጉልተው የሚያንፀባርቁ አልባሳት በአብዛኛው በትዕዛዝ ያዘጋጃሉ፡፡ የተዘጋጁ ልብሶችንም ያቀርባሉ፡፡
ከወላይታ ቀደምት ሥልጣኔዎች መካከል የሽመና ጥበብ አንዱ እንደሆነ ደጋግመው በኩራት የሚገልጹት ወይዘሮዋ፤ ፈላጊያቸው ብዙ እንደሆነም ያነሳሉ። የአሠራር ዲዛይናቸውና ውበታቸው ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ቱሪስቶችን ዓይን የሚስብ ስለመሆኑ ያስረዳሉ፡፡ በተለይ ‹‹ሀዴ›› የተሰኘውና ከወላይታ ብሔር አልባሳት አንዱ የሆነው ልብስ ለዓይን ማራኪና ሳቢ ስለመሆኑ ይናገራሉ፡፡ በተለያየ ቀለም ባላቸው ጥለቶች የተዥጎረጎረው ይሄው አልባሳት የቱሪስትን ቀልብ ከሚስቡት የወላይታ አልባሳት በዋነኝነት የሚጠቀስ ስለመሆኑም ያብራራሉ፡፡ እርሳቸው እንደገለጹልን፤ አብዛኛው በወላይታ ብሔረሰብ ተወላጆች የሚለበሰውና የሚወደደው ይህ ልብስ በሸማኔ ነው የሚሠራው። አሠራሩ በጥለት ተዥጎርጉሮ ፣ ከወገብና ከዳሌ ሰፋ ብሎ ከባትና ከጉልበት መካከል የሚውል የወንዶች ሱሪ ነው፡፡ ልብሱ በተለያዩ አውዶች የሚለበስና የራሱ የሆነ የአለባበስ ሥርዓትም አለው፤ ዓይነቱም የተለያየ ነው፡፡
ሽሮ ሜዳ የገበያ ቦታ በመሆኑና ዝርዝሮቹን ለእኛ መናገር ጊዜያቸውን የሚሻማ በመሆኑ የባህላዊ አልባሳት ባለቤቷ ወይዘሮ ከዚህ በላይ ሊያብራሩልን አልቻሉም፡፡ ፊታቸውና ቀልባቸው ወደ ገበያቸው ሲዞሩ ከመደብራቸው ወጣ ብለን ሌሎች መደብሮችን መቃኘቱን ተያያዝነው፡፡
ወቅቱ የጾም በመሆኑ የአልባሳት መደብሮቹ እንደቀድሞው ሞቅ ደመቅ አላሉም፡፡ የአብዛኞቹ ገበያ ተቀዛቅዟል፡፡ ሆኖም እኛ የሄድንበት ቀን ዕለተ ቅዳሜ ከሰዓት በመሆኑ እንቅስቃሴው ይሄን ያህል የተቀዛቀዘ ነው ተብሎ የሚታማ አይደለም፡፡ የተጨናነቀ ባይሆንም አልባሳቱን ለፎቶ ፕሮግራም፣ ለማህበር እንዲሁም በማህበረሰቡ መካከል ያለውን አንድነትንና ፍቅር አጉልቶ ለማሳያ በርካታ በግሩፕ የሚለበሱ ባህላዊና ዘመናዊ አልባሳትን የሚጎበኙና የሚሸምቱ ነበሩ፡፡ የወላይታውን አልባሳት ቃኝተን ለማስቃኘት እንደመነሳታችን አሁንም በየአልባሳት መደብሩ አፈላልገን አልባሳቱን አገኘን፡፡
እንዳጋጣሚ ሻጭውም ሸማቾቹም የወላይታ ብሔረሰብ ተወላጆች ናቸው፡፡ ልብሶቹን እያስወረዱ ይመለከታሉ፤ ይነጋገሩ የነበረው የጋራ ባደረጋቸው በሚያግባባቸው በወላይትኛ ቋንቋ በመሆኑ ብዙ ልንረዳቸው አልቻልንም፡፡ ለእኛም ማብራሪያ የሚሰጡበት ጊዜ አልነበራቸውም፡፡ ሆኖም እዚህ የተዘጋጁ ባህላዊ አልባሳትም ይሸጣሉ፡፡ ደግሞም በትእዛዝ የተሠሩ አሉ፡፡ በርከት ብለው በትዕዛዝ የተሠሩትን ባህላዊ አልባሳት በጥድፊያ ሲረከቡ ከነበሩት መካከል አንዱን ጎምቱ አዛውንት በእጃቸው ስለያዙት አንድ ልብስ ምንነትና አሠራር ጠየቅናቸው፡፡ ከጥድፊያቸው አንጻር መልስ ላይሰጡን ይችላሉ በሚል ጥያቄያችንን ፈራ ተባ እያልን ነው ያቀረብንላቸው፡፡
ቢሆንም መልስ አልነፈጉንም፤ ከየት እንደመጣንና ለምን ማወቅ እንደፈለግን ጥያቄ መጠየቅ ውስጥ አልገቡም፡፡ በቅንነት ልብሱ ‹‹ዱንጉዛ ሀዲያ›› እንደሚሰኝ ነገሩን፡፡ በአብዛኛው እዛው ወላይታ ሶዶ ዞን ውስጥ ገጠር አካባቢ በእጅ ተሠርቶ ከተዘጋጀ በኋላ ጨርቁ ለአለባበስ በሚመች ሁኔታ በእጅ ተሠፍቶ በሸማኔዎች የሚዘጋጅ ልብስ ስለመሆኑም አልሸሸጉንም፡፡ ልብሱ ከሀዴ ዓይነት ልብሶች የሚፈረጅ ነው፡፡ አዘገጃጀቱ ታጥፎ ሊታጠቅ በሚያስችል ሁኔታ በወገብ አካባቢ ሰፋ ተደርጎ ስለመሠራቱ፤ በተለይ ድሮ ቢሆን ሽሮ ሜዳ ገበያ ውስጥ ልብሱ እንደማይገኝም አከሉልን፡፡ ‹‹ሻማጭያ›› የተባለውና የያዙት አላባሹ እንደሆነም ነገሩን፡፡ ‹‹ዱንጉዛ ሀዲያ›› የተሰኘውን ልብስ የሚለብሱት እንደ እሳቸው ያሉ በዕድሜ የገፉ አዛውንቶች፤ በተለይም በማህበረሰቡ ዘንድ ከበሬታና ዝናን ለማሳየት በበዓላት፣ በሸንጎና በተለያዩ ስፍራዎች የሚለበስ ስለመሆኑ አብራሩልን፡፡
እኛም በእሳቸው ላይ ለሙከራ ተለብሶ እንዳየነው የተለየ ግርማ ሞገስን ያጎናጽፋል፡፡ በልዩ ዲዛይን የተመልካቹን ዓይን በሚስብ መልኩ በተለያዩ ህብረ ቀለማት አሸብርቋል፡፡ ጥቁር፣ ቢጫና ቀይ ቀለማት ልብሱን እንዲዋብ ካደረጉት ቀለማት ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡
ዱንጉዛ ሀዲያ ከሚሰኘው ከዚሁ ከወላይታ ብሔረሰብ ዞን አልባሳት ስር ሌሎችም ባህላዊ ልብሶች አሉ፡፡ ሰሬ ሀዲያ እና ጉቱማ ሀዲያ የተሰኙት የልብስ ዓይነቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እሳቸው እንዳሉን በወላይታ ብሔር ዘንድ ልዩ ስፍራ የሚሰጣቸው የማህበረሰቡ አካላት ከሚለብሷቸው የሀዴ ዓይነት አልባሳት መካከል ሰሬ ሀዲያ አንዱ ነው፡፡ እንደ ድንጉዛ ሀዴ ሁሉ ሴሬ ሀዴም በአብዛኛው እንደሚታወቀው ሥራው ተሠርቶ ከተጠናቀቀ በኋላ ቅርጹና ይዘቱ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ በእጅ ከታች ወደ ባት አካባቢ ሰፋ ተደርጎ ለአለባበስ በሚመች ሁኔታ ይሠራል፡፡ ወገቡ ላይ ደግሞ ሙሉ ወደ ላይ ከለበሱ በኋላ በአካባቢው አባባል ‹‹ጊቷ ጊስኳ›› ለሚባለው አለባበስ በሚመች ሁኔታ ወደ ታች በማጠፍ አመቻችተው ይሰፉታል፡፡ ይህን ልብስ የሚለብሱት የጦር ጀግኖች፣ የአደን መሪዎች፣ እንዲሁም ባለሀብቶች ናቸው፡፡ በሚያምር መልኩ የሚሠራው ይሄው አልባሳት በወላይታ ብሔር ዘንድ ልዩ ስፍራ የሚሰጣቸው የማህበረሰቡ አካላት ከሚለብሷቸው የሀዴ ዓይነት ሁለተኛው ነው፡፡
እኛም እንዳስተዋልነው ሰሬ ሀዲያ የተሰኘው ይሄው ከዱንጉዛ ሀዲያ ልብስ ዓይነት የሚፈረጀው እንደ ዱንጉዛ ሀዲያ ሁሉ በደማቅ ጥቁር፣ ብጫና ቀይ ሦስት ቀለማት በዝግዛግ አሸብርቋል፡፡ የብሔረሰቡ ተወላጅ አዛውንት እንዳብራሩል፤ ሌላኛውና ሦስተኛው ዱንጉዛ ሀዲያ አልባሳት ዘር እንዲህ ዓይነት ቀለማት ባላቸው ደማቅ ክር የሚሠራው ጉቱማ ሀዲያ በእጅ የሚዘጋጅ ነው። ልብሱን ለየት የሚያደርገው ማንኛውም ሰው ለሥራ ሲሄድ የሚለብሰው መሆኑ ነው፡፡ አሠራሩ እንደሌሎቹ ቢሆንም ለማንኛውም ሥራ በሚመች ሁኔታ ከሌሎቹ የሀዲያ ዓይነቶች በትንሹ ተለይቶና ወገብ ላይ ልክ እንደ ዘመናዊ ሱሪ ሆኖ ይዘጋጃል፡፡
በታዋቂው የባህል አልባሳት የገበያ ቦታ ሽሮሜዳ ከዚህ በላይ በመቆየት የወላይታ የባህላዊ አልባሳት አሠራር እና የአለባበስ ሥርዓት መቃኘት አልፈለግንም። ‹‹ነገርን ከስሩ ውሃን ከጥሩ›› እንዲሉ ተረት በሽመና ጥበብ ስልጣኔ ቀደሞ ስሙ ከሚጠቀሰው ዋናው ምንጭ ከወላይታ መቃኘቱ የተሻለ መሆኑን በመገንዘብ ወደ ወላይታ ዞን ስልክ ደወልን፡፡
ለጠየቅናቸው ምላሽ የሰጡን በወላይታ ዞን የመንግሥት ኮሚኒኬሽን መምሪያ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን አቅም ግንባታ ባለሙያ አቶ ደስታ ወጋሶ ናቸው፡፡ አቶ ደስታ በተለይ ከፈትል የሚዘጋጁ የሸማ ባህላዊ አልባሳት አሠራር እና የአለባበስ ሥርዓትን ከአባትና እናቶቻቸው፣ ከአያትና ቅድመ አያቶቻቸው ከስር መሠረቱ አሳምረው ሲገነዘቡ ያደጉ ናቸው፡፡ ከዚህ ቀደምም በወላይታ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ በቋንቋ ልማትና ከባህልና ባህል አልባሳት ጋር በተያያዘ በመሥራት የማይናቅ ልምድ ሲያካብቱ የቆዩ ናቸው፡፡ ታድያ የባህላዊ አልባሳት እና የአለባበስ ሥርዓትን አስመልክተው እንደነገሩን ቡሉኮ አንዱ ነው፡፡ ቡሉኮ በወላይታ ብሔር ዘንድ ከጥንት ጀምሮ እንደ ዘመኑ እየተሻሻለ የመጣ አሠራር የሚከተልና በተለያዩ አውዶች ከሚለበሱ አልባሳት መካከልም ይጠቀሳል፡፡
በክብደትና በአሠራር ጥበብ የቡሉኮ ዓይነቶች የተለያዩ ናቸው፡፡ ዓይነታቸው ስድስት ሲሆን፤ ቀዳሚው ፓታላ ቡሉኮ፣ ቀጣዩ ቆጦጦ ቡሉኮ፣ ሰላሹ ጫጫፎ ቡሉኮ ይሰኛሉ፡፡ ቀሪዎቹ ሦስቱ ደግሞ ሻሎ ቡሉኮ፣ ጊጤቷ ቡሉኮ ጥብቋ በመሰኘት ይጠራሉ፡፡ እሳቸው እንዳብራሩልን ፓታላ ቡሉኮን የሚለብሱት ነገሥታት፣ የጦር መሪዎችና ጀግኖች ሲሆኑ፤ የሚለብሱትም መንግሥት ሲፈቅድ እና ግዳይ ሲጥሉ ነው፡፡ የሚሠራው ከድርና ከማግ ነው፡፡ አሠራሩ ድርብ ሲሆን፤ በአካባቢው አጠራር አራት እጥፍ በመሰኘትም ይታወቃል፡፡ 16 ክንድ የሚደርስ ርዝመት አለው፡፡
ሁለተኛውና ቆጦጦ ቡሉኮ የተሰኘው የሚሠራው ከቀይ እና ጥቁር ጥለት (ቀለም) ፈትል ሲሆን፤ የሚለብሱት ጾታ ሳይለይ የጦር መሪዎች፣ የአደን መሪ እና በብሔሩ ባህል ብዙ ሀብት ያከማቹ ናቸው፡፡ በተለይ ከብት በማርባት የታወቀች እና ከመቶ በላይ ከብት አርብታ ያስቆጠረችና ሴት ግሟ የተሰኘውን የሀብት ማብሰሪያ ሥነሥርዓት የፈፀመች ሴት እንደ እዚህች ሴት ሁሉም ተመሳሳይ ሥርዓት የፈፀሙ ባልቴቶች ይለብሱታል፡፡ ከቅቤና ከቀይ አፈር ተለውሶ የሚሠራው ጫጫፎ ቡሉኮ አዘገጃጀቱ እጅግ ውብ ነው፡፡ ግዳይ የጣሉ የጦር ጀግኖች እና የአደን መሪዎች ይለብሱታል፡፡
እንዲሁም ሻሎ ቡሉኮ የተሰኘውን ሌላኛው ዓይነት እንደ ጫጫፎ ከቀይ አፈር በመጠኑ በተለወሰው ማግ ይሠራል፡፡ የሚሠራው በሸማኔዎች ሲሆን፤ ከሌሎቹ ቡሉኮ ዓይነቶች በመጠን ያንሳል፡፡ ይሄን ዓይነቱን ቡሉኮ ማንኛውም ባለሀብት እና ጀግኖች ይለብሱታል፡፡ ጊጤቷ የተሰኘው ቡሉኮ እንደ ሌሎች የቡሉኮ ዓይነቶች በባህላዊ የሽመና መሳሪያ የሚሠራ ነው፡፡ ነጭ ጥጥ ተፈትሎ ከተገመደ በኋላ ተለቅሞ በሥርዓት ተደውሮ ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ይህንን ልብስ ሴቶች ከወገባቸው ዙሪያ ካገለደሙ በኋላ በመቀነት አስረው ወደ ላይ በኩል የሚቀረውን አጥፈው ወደታች ይለቁና ከላይ ጥብቆ በመደረብ ይለብሱታል፡፡ የመጨረሻውና ጥብቆ የተሰኘው የቡሉኮ ዓይነት አዘገጃጀቱ ጥበብ የተሞላበት ነው፡፡ ልብሱ ሴቶች በቡሉኮ ላይ የሚደርቡት አላባሽ ሲሆን፤ ጥብቆ በአንድ ፈርጅ በነጠላም ሆነ በድርብ ተሠፍቶ ይለበሳል፡፡ ጥብቆ እንደ ሌሎች የቡሉኮ ዓይነቶች ወጥ በሆነ መንገድ ተሠርቶ በእጅ የሚሰፋ ስለመሆኑ አጫውተውናል፡፡
አቶ ደስታ ወጋሶ እንደነገሩን፤ በወላይታ ባህል ልዩ እና ተመልካችን የሚያስደምሙ የሠርግ ወቅት የአለባበስና የአጊያጊያጥ ሥርዓት አለ፡፡ ሙሽራው ሙሽሪትን ከቤተሰቦቿ ዘንድ ለማምጣት ሲሄድ የሚለብሰው ሀዲያ የተባለው ባህላዊ ልብስ አንዱ ተጠቃሽ ነው፡፡ ይሄን ባህላዊ ሱሪ በመታጠቅ ከላይ አሳራ የተባለውን መለስተኛ ጋቢ በመደረብ ጦር ይይዛል፡፡ ሚዜዎቹም ከጎኑ በመሆን ሴሬ ሀዲያ በመልበስ በላያቸው ላይ አሳራን በመደረብ በፈረስ ላይ ተቀምጠው ወደ ሙሽሪት ቤት ያመራሉ፡፡ ሙሽሪት ቡሉኮ አገልድማ ሻማጭያ የተሰኘውን ጥብቆ ደርባ ፊቷ እንዳይታይ በነጠላ ተሸፍና ትቆየዋለች፡፡ የሙሽሪት(ጓደኞች) ሚዜዎቿ በፊናቸው ቡሉኮ አገልድመው ጥብቆ በመደረብ ሙሽሪትን አጅበው ‹‹ለባኦ አዛይ›› ለተባለው ሚዜ ያስረክቧታል፡፡ ሙሽሪት በዚህ የአለባበስ ሥርዓትም የጫጉላ ጊዜዋን ጨርሳ ከመውጣቷ በፊት በባህሉ መሠረት የሚከናወነውን የሶፌ ሥርዓት ትፈጽማለች፡፡ በዚህ ወቅት ከምትለብሳቸውና ከምትዋብባቸው አልባሳትና ጌጣጌጦች መካከል ቡሉኮ ጋቢ፣ ወይንም ነጠላ፣ ሻማጪያ የአንገት መስቀል፣ የጣት ቀለበት የሚጠቀሱ ስለመሆናቸውም ይናገራሉ፡፡ በእነዚህ አልባሳት ከተንቆጠቆጠች በኋላም የሶፌ ሥርዓት የምትፈጽመው ከዘንባባ እና ከቀርከሃ የሚሠራውን ዲባቢያ የተሰኘው ባህላዊ ጃንጥላ በመያዝ ነው፡፡
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን መጋቢት 5 ቀን 2017 ዓ.ም