
‹‹ጥይት›› ሲባል ወደ አዕምሯችን የሚመጣው ገዳይነቱ ነው፡፡ አዎ! ገዳይ ነው! ዳሩ ግን ይህን ተዓምራዊ ኬሚካል ማምረት ደግሞ ሌላ አስገራሚ ጥበብ ነው፡፡ ችግሩ ግን የሠለጠኑት ሀገራት ሲያደርጉት የዕድገትና የሥልጣኔ መገለጫ፤ ታዳጊ ሀገራት ሲያደርጉት ደግሞ የኋላቀርነት መገለጫ አድርጎ የማየት የአመለካከት መዛባት አለ፡፡
የሀማስ ታጣቂ ኃይል ከእስራኤል የሚተኮስበትን ተተኳሽ እየለቀመ በድጋሚ አገልግሎት ላይ ያውለው ነበር፡፡ ይህ ድርጊቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ይደነቅለት ነበር። ዒላማቸውን የሳቱ ተተኳሾችን፣ የተጣሉ መሣሪያዎችን በድጋሚ አገልግሎት ላይ ማዋል ሳይንሳዊ ጥበብ ነው፡፡ እዚህ ላይ የሀገራችን ገበሬዎችን ጥበብ ማስታወስ የግድ ይላል፡፡
በተለምዶ ‹‹ቆመህ ጠብቀኝ›› የሚባሉ የድሮ የጦር መሣሪያዎች አሉ፡፡ ከእነዚህ መሣሪያዎች አንዳንዶቹ ተተኳሾቻቸውን ለማግኘት የሚያስቸግሩ ናቸው፡፡ ዳሩ ግን የሀገራችን ገበሬ ጥበበኛ ነውና ዘዴ አላጣም፡፡ የአንዱን መሣሪያ ቀለሐ ለሌላ መሣሪያ ማዋል ጀመረ። ይህም በባሕላዊ መንገድ የሚሠራ ሲሆን ‹‹ክልስ›› ይሉታል፤ እንደገና የተከለሰ ማለት ነው፡፡ አሠራሩ እንዲህ ነው፡፡
ጥይቱ የተተኮሰለት ባዶ ቀለሐ ይዘጋጃል፡፡ የተዘጋጀው ቀለሐ ለክልስ ይሆናል አይሆንም የሚለው ይታያል፤ ቀለሐው ሁሉ አይሆንም፡፡ የሚሆነው ቀለሐ ተመርጦ በውስጡ አመድ ይደረግበታል፡፡ አመድ ሲባል የየትኛውም እንጨት አመድ አይደለም፡፡ ለዚህ አገልግሎት የሚውል የተመረጠ ተክል አለ፤ ይህ ተክል በገደል አፋፍ ላይ የሚበቅል ሲሆን እንጨቱን አንድደው አመዱን ይጠቀሙታል፡፡ የዚህ እንጨት አመድ ‹‹ድኝ›› ይባላል፡፡
የተዘጋጀው አመድ(ባሩድ) በቀለሐው ውስጥ ይደረጋል፡፡ ከዚያም ከብረት ዘንግ (ፌሮ) የተቆረጠ የጥይት ቅርጽ ያለው ጫፍ ይደረግበታል፡፡ ከፌሮ መሳይ ብረት ላይ የሚቆረጠው በቀለሐው አፍ እስከሚገባ ድረስ ይሞረዳል፡፡ ከጫፉ በኩልም በጥይት ቅርጽ ይሞረዳል፡፡ ይህ ጥይት ክልስ ይባላል፡፡ ተተኳሽ ሆኖ ይተኮሳል ማለት ነው፡፡
ይህ ሁሉ የሚሆነው እንግዲህ በልማዳዊ መንገድ ብቻ ነው፤ አስገራሚው ነገር ለባሩድ የሚሆነውን ተክል መለየታቸው ነው፡፡ እንዲህ አይነት የጥበበኛ ሀገር የሆነችው ኢትዮጵያ ሰሞኑን ዘመናዊ የጥይት ፋብሪካ ገንብታ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት ተመርቋል፡፡ ለመሆኑ ይህ የጥይት ፋብሪካ መመረቅ ምን ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ጥቅም አለው?
አንዳንዶቹ ‹‹ጥይት›› የሚለውን ቃል በመውሰድ ‹‹እንዴት እንደ ትልቅ ነገር ይታያል?›› ሊሉ ይችላሉ። በዚህ የጥይት ፋብሪካ መገንባት ውስጥ ግን ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ጥበብ አለ፡፡ ዲፕሎማሲ ማለት የግድ አንደበተ ርቱዕ የሆነ ንግግር ማለት ብቻ አይደለም፤ ስምን እና ገጽታን መገንባት ነው፡፡ ኃያላን ሀገራትን የምናከብራቸው ስማቸውን እና ገጽታቸውን ስለገነቡ ነው፡፡
ስም እና ገጽታ ከሚገነባባቸው ነገሮች አንዱ የጦር መሣሪያ አቅም ነው፡፡ ያስከብራል፤ ተፈሪ ያደርጋል፡፡ የመከላከያን ኃይል እናውቃለን፤ ታዲያ ይህ የመከላከያ አቅም ከምን የመጣ ነው? አስተዳደራዊ ጥበብ እንዳለ ሆኖ፤ አንዱ ኃይል ግን የትጥቅ አቅም ነው፡፡
ኢትዮጵያ የጥይት ፋብሪካ ማቋቋሟና ማምረት መጀመሯ ምን ዲፕሎማሲያዊ ፋይዳ አለው?
ቀደም ሲል እንዳልነው ዲፕሎማሲ ማለት ምርጥ ቃላትን በአፍ መናገር ብቻ አይደለም፡፡ ራስን የሚያስከብር ኃይል መገንባት ነው፤ ያኔ ሁሉም አክባሪ ይሆናል፡፡ እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ የቀጣናው ተፅዕኖ ፈጣሪ ናት፡፡ የአፍሪካ ሀገራት እንደ እናት የሚያዩዋት ሀገር ናት። በዚያው ልክ ደግሞ ተቀናቃኝ የሚበዛባት ናት፡፡
በቀይ ባሕርና አካባቢው፣ በምሥራቅ አፍሪካና አካባቢው…. ብዙ ጥቅም ያላቸው ሀገራት አሉ፡፡ እነዚህ ሀገራት ጥቅማቸውን ለማስከበር ሴራቸውን የሚጎነጉኑት በጎረቤት ሀገራት በኩል ነው፡፡ የጦር ሰፈር ከመገንባት ጀምሮ ብዙ አይነት አካሄዶችን ይጠቀማሉ፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ይከታተላሉ ማለት ነው፡፡
እንደሚታወቀው ላለፉት ዘመናት ኢትዮጵያ የጦር መሣሪያና ተተኳሽ ከውጭ ስትገዛ የቆየች ናት፤ ይህ ብዙ ሀገራት የሚያደርጉት ስለሆነ ችግር የለውም፡፡ ተተኳሽ ማምረት መጀመር ግን ትልቅ ስኬት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ተተኳሽ ማምረት ጀመረች ማለት በቀጣናው አካባቢ ፍላጎት ላላቸው ኃይሎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አንቂ ይሆናቸዋል ማለት ነው፡፡ እስከዛሬ ድረስ ታፍሮ እና ተከብሮ የኖረው የኢትዮጵያ ገጽታ አሁን ደግሞ የበለጠ የሚፈራና የሚከበር ይሆናል ማለት ነው፡፡ በአካባቢው ምንም ነገር ለማድረግ የሚያስብ አይኖርም ማለት ነው፡፡
በሌላ በኩል ሀገራዊ ምሥጢርና ደኅንነትን ከመጠበቅ አኳያም ትልቅ ሚና አለው፡፡ እንደሚታወቀው የጦር መሣሪያ ግዥ ከፍተኛ የደኅንነት ጥንቃቄ የሚጠይቅ ነው፡፡ እንደማንኛውም ሸቀጥ በማንኛውም መንገድ የሚገዛ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ተተኳሽ በማምረት ይህን ምሥጢር መጠበቅ ችላለች ማለት ነው፡፡ በገንዘብ በኩል ካየነውም ብዙ ወጪ ማዳን ችላለች ማለት ነው፤ ከምንም በላይ ግን ሀገራዊ ደኅንነትን ለመጠበቅ ያስችላል፡፡
ኢትዮጵያ ባለፉት ዘመናት ተተኳሽ ከውጭ በመግዛት ሀገራዊ ክብሯንና ደኅንነቷን ካስጠበቀች፤ ራሷ ማምረት ስትጀምር ምን ይሆናል? የሚለውን ነው ማሰብ! ይሄን ነገር ተቀናቃኝ ሀገራት ያስቡታል፡፡ ከውጭ እየገዛች የቀጣናው አውራ የነበረች ሀገር፤ ራሷ ስታመርት ደግሞ ምን ሊሆን ይችላል? የሚለው በዲፕሎማሲው ዘንድ ልብ የሚባል ነው፡፡
አንዳንድ የዋህ ወገኖች የጥይት ፋብሪካ ምን ይጠቅመናል? ሊሉ ይችላሉ፤ ጥይት ገዳይ መሆኑን በማሰብ ብቻ ማለት ነው፡፡ ዳሩ ግን ዓለም እየተሽከረከረች ያለችው በጦር አቅም ነው፡፡ የትኛውም ዓለም ‹‹በዚህ ዘመን የጦር መሣሪያ ምን ያደርግልኛል?›› ብሎ ባዶውን የተቀመጠ የለም፡፡ ዓለም የአሸናፊዎች ናት፡፡ ቀደም ሲል እንዳልነው የጥይት ፋብሪካው አንዱ ጥቅም ክብርን ለማስጠበቅ አቅም ያለ መሆኑን ማሳየት ነው፡፡
በሌላ በኩል አንድ የቴክኖሎጂ ውጤት ነው። ከክላሽ እስከ ሌሎች ከባድና ዘመናዊ መሣሪያዎች የሚሆን ተተኳሽ ማምረት ብዙ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ደረጃዎችን የሚያልፍ ነው፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዕድገትንም ያሳያል፡፡ ጥይት ሲባል ከቴክኖሎጂነቱ ይልቅ ጦርነቱ ትዝ ስለሚለን እንጂ የማምረት ሂደቱ የረቀቀ የሳይንስ ውጤት ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ፋብሪካውን በጎበኙበት ወቅት እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ስትራቴጂክ አቅሟን ካልገነባች በሆነ ጊዜ ማንም መጥቶ በቀላሉ ጥቃት ሊፈጽምባት ይችላል የሚል ግምገማ እንደነበረም ጠቅሰዋል፡፡ በ2014 ዓ.ም ጥይት ትገዛ የነበረችው ኢትዮጵያ በ2015 ዓ.ም መትከል በተጀመረው ፋብሪካ ዛሬ ላይ ለራሷ ብቻ ሳይሆን ለገበያም ማቅረብ የምትችል ሆናለች፡፡
በጣም አጭር በሚባል ጊዜ ውስጥ የተገነባው የጥይት ፋብሪካ በቴክኖሎጂ ተደራጅቶ በጥራት እና በብዛት ማምረት የሚችል እንደሆነ፣ ኢትዮጵያ ፋብሪካ ጀምራ መጨረስ እንደምትችል ማሳያ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡ ፋብሪካው ዘመናዊ እና በሰዓት ከፍተኛ የማምረት አቅም ያለው ነው ተብሏል፡፡
ስለዚህ ይህ ፋብሪካ የሀገሪቱን የቴክኖሎጂ ዕድገትም የሚያሳይ ነው ማለት ነው፡፡ በዋናነት ግን ኢትዮጵያ በየትኛውም በኩል ሊታሰብባት የሚችለውን ጥቃት ማክሸፍ የሚችል አቅም ያላት መሆኑን ማሳያ ይሆናል ማለት ነውን፡፡ በዘመናዊው ዓለም ውጊያ ጀምሮ ከማሸነፍ ይልቅ ውጊያ እንዳይጀመር አቅምን ማሳየት የበለጠ አሸናፊነት ነው፡፡
ይህ የጥይት ፋብሪካ በመደበኛዎቹ መገናኛ ብዙኃን ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ሚዲያዎችም እንዲሠራ ሊደረግ ይገባል፤ ምክንያቱም የዲፕሎማሲ ኃይልም ይኖረዋልና!
ሚሊዮን ሺበሺ
አዲስ ዘመን መጋቢት 5 ቀን 2017 ዓ.ም