የንግድና ኢንቨስትመንት እድሎችን ለማስፋት ያለመው የንግድ ትርዒት

የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ለሀገራት ኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ ግብዓት ነው፡፡ የንግድና ኢንቨስትመንት እድሎችን ማስፋት የግሉ ዘርፍ ተሳታፊነትን ለማሳደግና ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት ጉልህ ሚና ይኖረዋል፡፡ የግሉ ዘርፍ የንግድ ማህበረሰብ ድምጽ የሆነው የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት በአዋጅ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ላይ የሚገኙ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ኢንተርፕራይዞች ራሳቸውን የሚያስተዋውቁበት፣ የሚገበያዩበት ብሎም ከሌሎች አቻ የንግድ ተቋማት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር የልምድ ልውውጥ የሚያደርጉበትን መድረክ ይፈጥራል፡፡

ዘንድሮም ‹‹የኢትዮጵያን ይግዙ›› በሚል መሪ ቃል 14ኛው ኢትዮ-ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት መጋቢት አራት ቀን 2017 ዓ.ም በይፋ ተከፍቷል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትና የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከተባባሪ አካላት ጋር ያዘጋጁትና ለአምስት ቀናት የሚካሄደው ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት የሀገር ውስጥ፣ የአፍሪካ ሀገራትና የዓለም አቀፍ አምራች ኩባንያዎች ምርትና አገልግሎታቸውን ይዘው የቀረቡበት ነው፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ዓለም አቀፍ ትርዒቱ የንግዱን ማህበረሰብና ሸማቹን በማገናኘት ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡ እንደሚኒስትሩ ገለጻ፤ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያን የአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ ያለመ የረጅም ጊዜ ስትራቴጂና ፖሊሲ በመዘርጋት ቀጣይነት ያለውን እድገት በማረጋገጥ፣ ምርታማነትንና ተወዳዳሪነትን በማሻሻልና ተቋማዊ ለውጥ በማድረግ የግሉ ዘርፍ ኢኮኖሚ እንዲጠናከር የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡

በአጭርና በረጅም ጊዜ በሚጠበቁ የማክሮ ኢኮኖሚ ውጤቶች ረገድ በመንግሥት የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች በፍጥነትና በጥራት እንዲጠናቀቁ እየተሠራ ይገኛል፡፡ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት የግሉን ዘርፍ የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ለማጎልበት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በእዚህም ለንግድ ሥራ ምቹ ከባቢ ለመፍጠር የንግድ ፈቃድ አገልግሎቶች በኦንላይን እየተሰጡ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

ሚኒስትሩ አክለውም፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ ለሀገር ውስጥ ንግድ ብቻ ታጥሮ የነበረውን የአስመጪና ላኪ ንግድ ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት መደረጉን ጠቁመው፤ ለንግዱ ማህበረሰብ ከፍተኛ ተግዳሮት የነበረው የውጭ ምንዛሪ በገበያ እንዲመራ በመደረጉ በመስኩ የተሻለ የአስተዳደር ሁኔታ መታየቱን ተናግረዋል፡፡

ለአፍሪካ አህጉራዊ የነፃ ንግድ ቀጣና ትግበራ እንዲሁም ለዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት ሰፋፊ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያ አምራቾች የንግድና ኢንቨስትመንት ተወዳዳሪነታቸውን ማሳደግ እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን ጥራት ለማሳደግና ተወዳዳሪ ለማድረግ የጥራት መንደር ተገንብቶ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ በበጀት ዓመቱ ባለፉት ሰባት ወራት ከወጪ ንግድ ከሦስት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ዶላር በላይ የአሜሪካ ዶላር ገቢ ተገኝቷል፡፡

ውጤቱ ከእዚህ ቀደም በዓመት ይገኝ የነበረውን በግማሽ ዓመት ውስጥ ማሳካት መቻሉን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ ወርቅና ቡናን ጨምሮ የግብርና፣ የማዕድንና የኢንዱስትሪ ምርትና አገልግሎቶች ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዙ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ሰብስብ አባፊራ፤ ምቹ የንግድና ኢንቨስትመንት ከባቢ ለአንድ ሀገር ዕድገት መሠረት መሆኑን ገልጸው፤ የግሉ ዘርፍ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የመሪነት ሚና እንዲኖረው እየተሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቱ የኢትዮጵያን የንግድና ኢንቨስትመንት ዕድሎችን በማስፋት የገበያ ትስስርን ለመፍጠር ያለመ ነው ብለዋል።

የንግድ ትርዒቱ የኢትዮጵያን ምርትና አገልግሎቶች በማስተዋወቅ የሀገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎችን የገበያ ትስስር፣ የዕውቀትና የልምድ ልውውጥ ያሳድጋል ተብሎ ይጠበቃል። በእዚህም በሀገር ውስጥ ኢንተርፕራይዞችና በዓለም አቀፍ የንግድ ተቋማት ምርትና አገልግሎቶች ቀርበው የአቻ ለአቻ የንግድ የምክክር መድረክ ይካሄዳል።

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን መጋቢት 6 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You