“የሆኑ ሰዎች እንዲህ ስላደረግን እንዲህ ይደረግልን ስላሉ በምን መልኩ መንግሥት ይሆናሉ ” – አቶ ጌታቸው ረዳ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት

ክፍል ሁለትና የመጨረሻው

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ከትናንት በስቲያ በአዲስ አበባ ሸራተን አዲስ ሆቴል በክልሉ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ መግለጫ ሰጥተዋል ። በወቅቱም ጋዘጠኞች የተለያዩ ጥያቄዎችን አቅርበዋል።

በወቅቱም የፌዴራል መንግሥት በክልሉ ጉዳይ ጣልቃ እንዲገባ ጊዜያዊ መንግሥቱ ጥሪ አቅርቧል ወይስ አላቀረበም ? የትግራይ ክልል ጉዳይ ሕዝቡን እያስጨነቀው ይገኛል ፤ ክልሉ ወደየት እየሄደ ነው? የፕሪቶሪያው ስምምነት ዓላማው ምን ነበር? ወሰኑስ እስከምን ድረስ ነው? እንዴት እየተፈጸመ ነው? ምን ምን ተግዳሮቶች አጋጥመዋል? አሁን ያለው የትግራይ ወቅታዊ ሁኔታ ምን መልክ አለው? የሻቢያ መንግሥት ከህወሃት ጥቂት ሃይሎች ጋር ግንኙነት እንዳለው ይሰማል ፤ ይህ ምን ያህል እውነት ነው ? በክልሉ የሻቢያ ሚና እና ተጽእኖ እንዴት ይገለጻል? ክልሉ የማዕድን ሀብቱን እንዴት እየተቆጣጠረ ነው? በማዕድን ንግድ ላይ ያለውን ሕገ-ወጥ ሥራ ለማስቆም ምን አድርጓል? በክልሉ የሚደረገው ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴ የመፈንቅለ መንግሥት መልክ ያለው ነው ይላሉ ? የሚሉና ልሎችም ጥያቄዎች ቀርበውላቸዋል ።

በትናንትናው እትማችን በክልሉ ስላለው ተጨባጭ ሁኔታ ፤ስለ ችግሩ እና የችግሩ ምንጭ ስላሏቸው ነገሮች ፤ ችግሩን ለመፍታት ሊደረጉ ይገባል ያሏቸውን የመፍትሄ ሃሳቦ አቅርበዋል ፤ በዛሬው እትማችን የሻቢያ መንግሥት በችግሩ ውስጥ ስላለው ሚና እና በሌሎች ጉዳዮች የሰጡትን ምላሽ የመጨረሻ ክፍል በሚከተለው መልኩ አቅርበነዋል ።

ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ፦ እነዚህ ቡድኖች/ከሳቸው በተጻራሪ የቆሙ/ ስለ ትግራይ ሕዝብ ምንም ደንታ የላቸውም። የወርቅ ንግድ ወደ አዲስ አበባ የሚያዋጣ ከሆነ ያደርጋሉ፤ የወርቅ ንግዱን ወደ አዲስ አበባ የማያዋጣ ከሆነ ወደ አስመራ ያደርጋሉ።

ይህ ከትግራይ ሕዝብ ተጠቃሚነትና ከትግራይ ሕዝብ ህልውና ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም። የተጠያቂነት ጉዳይ አለ፤ ከኤርትራ መንግሥት ጋር ሰላም እናምጣ ማለት የኤርትራ መንግሥት በተግባር በኢትዮጵያ ፤ በትግራይ ሕዝብ ላይ የፈጸመውን ጭፍጨፋ በመካድ ሊሆን አይችልም። ሁሉም፤ የፌዴራል ኃይሎች ለፈጸሙት ጥፋት ተጠያቂ መሆን አለባቸው። የትግራይ ኃይሎችም ለፈጸሙት ጥፋት ካለ ተጠያቂ መሆን መቻል አለብን።

በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ቢያንስ ከፌዴራል መንግሥት ጋር የሚታወቅ ስምምነት አለ። የሚታወቅና እዚህ ግባ የሚባል ስምምነት ሳይኖው ፕሪቶሪያ በመፈረሙ ምክንያት አኩርፎ ከኢትጵያ መንግሥት ጋር የተጣላ ኃይል ጋር ተሰልፈህ የኢትጵያ መንግሥትን ምናልባት ማስወገድ የሚቻልበት ዕድል ካለ ብለህ መንቀዥቀዥ በጣም አደገኛ ነው። እኔ የማውቃቸው የትግራይ ከፍተኛ ወታደራዊ ኃላፊዎች እንደዚህ አይነቱን እብደት እንደማይቀበሉት አውቃለሁ።

የተወሰነ ከዚህ ግርግር ጋር በተያያዘ ፤ ግርግር የተጣባውና ፍጹም ጤናማ ሁኔታ ከተፈጠረ አደጋ ላይ እወድቃለሁ ብሎ የሚስብ ጥቂት ግን ደግሞ ብዙ ሰው የማወናበድ አቅም ያለው ቡድን እንደዚህ አይነት እንቅስቃሴ ውስጥ እንደገባ አውቃለሁ።

ይህ ሁኔታ ፖለቲካችንን ከማመስ አንጸር አስተዋጽኦ የለውም አይባልም፤ አስተዋጽኦ የለውም አይባልም ብቻ ሳይሆን በተግባር ክልላችንን የጦርነት ቀጣና ለማድረግ ያለው እድል በየቀኑ እየሰፋ እየሰፋ የመጣበት ሁኔታ አለ።

እዚህ ውስጥ የታጠቁ ሃይላት የሚባለው አሁን ታጣቂ አለ ብለን እየገለጽን ያለነው ”ዲዲአር” የሚጠብቀን ነው። እንደማንኛውም ክልል የፖሊስ ሃይል ይኖረናል፤ ሚሊሺያም ይኖረናል፤ የመከላከያ ሠራዊት ግን ሊኖረን አይችልም። ትግራይ ሀገር ናት ብሎ ማሰብ የሚፈልግ ብዙ ሰው እንዳለ አስባለሁ፤ እኔም ስሜት ውስጥ ስገባ እንደዛ አስባለሁ። መመኘት ችግር የለውም። መሆን ካለበት ትግራይ ሀገር እንድትሆን እታገላለሁ፤ ችግር የለውም፤፤

አሁን ያለውን እውነታ መቀበል ጨዋነት ነው፤ ትግራይ የኢትዮጵያ አካል ነች፤ በጀት አለ፤ ፓስፖርቴ የኢትዮጵያ ፓስፖርት ነው የሚለው፤፤ ድንገት ሀገር መሆን ስለተመኘህ ብቻ ሀገር የሆንክ መስሎህ ሠራዊት እስከ መጨረሻው አስቀጥላለሁ ልትል አትችልም።

የፕሪቶሪያው ስምምነት እሱንም አይፈቅድም። የፕሪቶሪያውን ስምምነት እናሳካው ማለት ፍላጎትን መተው ማት አይደለም። ከምንም ነገር በላይ አሁን ያለውን እውነታ ተቀብለህ ግን ደግሞ የትግራይ ህልውናና ሉዓላዊነት፤ ሕገመንግሥቱ ለትግራይ ያስቀመጣቸው ሁሉንም ነገሮች እንዲሟሉ መጣር ማለት ነው። ይህን ለማድረግ የግድ ነፍጥ ማንሳት፣ ታንክ ማንጋጋት አያስፈልግም።

በእዚህ ጉዳይ ላይ ታጣቂዎች ፖለቲካውን አመሱት የሚለው ትንሽ ማስተካከያ የሚፈልግ ነው። አብዛኛው ታጣቂ ወጣት ለውጥ የሚፈልግ ነው። እዚህ ውስጥ ካሉት አመራሮች ጥቂት የሚሆኑት ከራሳቸው ጥግ ጋር ተያይዘው ጉባዔ ያደረገው ነው ትክክለኛ ድርጅት ይላሉ፤ ጉባዔ ያደረገ ነው የሚባለው የፌዴራል ተቋማትን ለምሳሌ የምርጫ ቦርድን ውሳኔ አልቀበልም ብሏል፤ ግን ደግሞ ምንም ችግር የለበትም በአውሮፕላን ተሳፍሮ እዚህ መጥቶ ሥልጣን ይገባኛል ሲል ምንም ሀፍረት አልተሰማውም።

ይህንን የሚል ሃይል እኔ ነኝ የምደግፈው ስትል የፌዴራል ተቋማትን ያልተቀበሉትን ጉባዔ እቀበላለሁ ማለት ግጭትን መጋበዝ ነው። የፌዴራል መንግሥቱ በምን ዓይን ያየዋል ፤ እርግጠኛ አይደለሁም። እንዳ ልኳችሁ እየተሳቀቅን ብዙ ጊዜ ከፌዴራል መንግሥቱ ሃላፊዎች ጋር እንገናኛለን።

ይሄ ነገር ማብቃት አለበት። አሁን ያለው ጉዳይ እገሌ የሚባለው ሰው ኃላፊ መሆን አለመሆኑ አይደለም። አሁን ያለው ትርምስ ተፈጥሮ ትግራይ ውስጥ የሚፈጠረውን ግጭት እንተወውና ሌሎችንም ጭምር ጋብዞ ሌላ የትርምስ ምእራፍ የሚፈጥር ከምንም ነገር በላይ የትግራይ ሕዝብ የሚገባውን ሰላም የሚያሳጣ ፣ እንደገና ሌላ ጥፋት የሚጋብዝ እንቅስቃሴ ነው።

ይሄ ሁሉም ታጣቂ የገባበት እንቅስቃሴ አይደለም፤ ታጣቂው ሰላም ይፈልጋል፤ አለ የሚባለው ሠራዊት ሰላም፣ መቋቋም የሚፈልግ ወደቤቱ መመለስ የሚፈልግ ነው። አንዳንድ የሚያሳዝኑ አጋጣሚዎችም አሉ፤ ከሁ መራ መጥቶ የታገለን በዲዲአር አካተን 94 ሺህ ብር ተሰጥቶት ወደድንኳን ነው የሚመለሰው፤፤ እንደዚህ አይነት ሁኔታ እንዲያቆም ነው መሥራት ያለብን።

እንዳልኩት ፌዴራል መንግሥትን በበቂ መልኩ ወቅሰናል። አሁን እዚህ ላይ ትኩረት ከማድረግ ይልቅ ምን ላይ ነው የምንውለው የሚለው በደንብ መታየት አለበት። እዚህ ጉዳይ ውስጥ የሚገቡ ጥቂት ሰዎችን በሚመለከት የምናነሳቸው ነገሮች ሰላም የሚፈልገውን አብዛኛውን ታጣቂ ወይም አመራር የሚመለከት እንዳልሆነ ለመግለጽ እፈልጋለሁ።

የፌዴራል መንግሥት ዝምታ ህወሃትና የጊዜያዊ አስተዳደሩ የጥቅም ግጭት የሚለው ምን የጥቅም ጉዳይ የሥልጣን ጉዳይ ነው፤ የህወሃትን ጉባዔ አደረኩ የሚለው ወገን ቀላል ጥያቄ ነው ያነሳው። ፕሬዚዳንቱን አውርጃለሁ ይላል፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሬዚዳንቱን የማውረድ ሥልጣን የእናንተ አይደለም አሏቸው፤ እገሌን አድርግልን አሉ፤ አይመለከታችሁም ተባሉ ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለመለመን ሲሆን ያከብሯቸዋል። ይህን ካሉ በኋላ ግን እኛ አንቀበልም ከንቲባ የምንሾመው እኛ ነን፤ ፕሬዚዳንቱንም አንቀበልም ይላሉ፤ እንደዚህ አይነት ለያዥ ለገራዥ የሚያስቸግሩ ሁኔታዎች ገጥመውናል።

የጥቅም ግጭት የሚባለው ይህ ሃይል የመንግሥትን በጀት ይጠቀማል፤ ወረዳ አስተዳደር ተቆጣጥሮ ማህተም ነጥቆ በጀት ለእኔ ነው የሚገባው ይላል፤ ስብሰባቸው ስም የሚያጠፉባቸው መድረኮች በሙሉ በመንግሥት በጀት ነው የሚካሄዱት።

ይህን ከማስቆም አንጻር መሥራት የሚገባንን መሥራት አልቻልንም። ይሄ አኔ እንደ አንድ ትልቅ የሥራ ሃላፊ የምወቀስበት ነው። ከምንም ነገር በላይ ግን ምን አልባት ነገ ከነገ ወዲያ እናስተካክለዋለን በሚል የዋህነት ልቅ የሄደ ነገር አለ። የፌዴራል መንግሥት እኔን ይወቅሰኛል። ማድረግ ያለብህን ባለማድረግህ የተፈጠረ ችግር ነው እባላለሁ፤ እቀበላለሁ፤

የጥቅም ግጭት ነው ስለሚለው እኔም እስማማለሁ። የፌዴራል መንግሥት ለምንድነው ዝም ያለው ይሉኛል። አላውቅም፤ ይዋጣላቸው ብሎ ይሆናል እላለሁ። የፌዴራል መንግሥት ሁሉም ያየው ቦታ ሁሉ እየገባ ጦርነት የመክፈት አባዜ ሊኖረው አይችልም። በቻይና ወታደራዊ ስትራቴጂ ጥሩ የሚሆነው ሳትዋጋ የምታገኘው ድል ነው ይባላል። ለእዚህ ብሎ ሊሆን ይችላል እላቸዋለሁ።

ግን ቢያንስ አሁን ከጠቅላይ ሚኒስትሩም ጋር ከሌሎች የሥራ ኃላፊዎች ጋር ስነጋገር ኖ ልምድ ያለው ድርጅት ነው፤ ልምድ ያላችሁ ሰዎች ናችሁ ተመልሳችሁ ወደ ጦርነት ትገባላችሁ የሚል እምነት የለንም። ስለዚህም በውስጣችሁ ያለውን ችግር ፍቱ። ትግራይ ላይ አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነት ማድረግ ስለማንፈልግ ነው ይሉናል። እርሱንም እቀበላለሁ። የፌዴራል መንግሥት ዝም ማለት የለበትም ።

እኔ እዚህ ጋር ጦር ያዝመት እያልኩ አይደለም። ቃል አያስፈልገውም በሥርዓት ኃላፊነቱን መወጣት አለበት። ትግራይ ውስጥ ራሱ ፌዴራል መንግሥቱ ተቋማት አሉት። እንዲሠሩ ማድረግ አለበት። የትግራይን ድንበር መጠበቅ መቻል አለበት።

የትግራይን ድንበር የሚያስጠብቅ አቅም ፤ አውት ሶርስ ይደረግ ከተባለ ቁርጣችንን አውቀን እናድርገው። ሶ እንደዚህ አይነት ነገሮች መደረግ አለባቸው። አሁን በተፈጠረው ክራይስስ ግን ዝም ማለት የለበትም። ዝም ማለት ብቻ ሳይሆን አሁን የዚህ ትርምስ አካል የሆኑ ሰዎች እኛ እንሻላለን ለማለት እየመጡ ነው እርግጠኛ ነኝ። ብዙ ነው እንደዚያ የሚያደርገው። እናም እንደዚህ አይነቱን ነውር ተግባርም ይቅርባችሁ ማለት አለበት ፌዴራል መንግሥቱ የሚል እምነት አለኝ።

ክልሉ ጦርነት ያስተናግዳል በፍጹም ማስተናገድ አይችልም። አንድም የትግራይ ወጣት ለእንደዚህ አይነት ርካሽ ተግባር መሥዋዕት ለመሆን ዝግጁ አይደለም። አንድ ነገር በእርግጠኝነት የምናገረው ትግራይ ላይ ጦርነት በሌላ አካል ከታወጀ ብቻ ነው የትግራይ ወጣት ሊዋጋ የሚችለው። ከዚህ ውጪ የእገሌን ወንበር ለማዳን ብሎ መሥዋዕት የሚሆን ወጣት የለም። በምንም መልኩ። ሰው የሰረቀውን ገንዘብ ለማቆየት ብሎ ወዲያ ወዲህ የሚንከላወስ የሆነ ሰው አይጠፋም። እርሱ ብቻውን ነው። አላፊ አግዳሚውን በክርኑም በምኑም ሊያስቆመው የሚችለው።

ትርምሱን የሕዝቡ ትርምስ ለማስመሰል፤ የግል አጀንዳቸውን የሕዝብ አጀንዳ ለማስመሰል የሚያደርጉት ጥረት ምን ያስመስለዋል ትግራይ ሌላ ዙር ጦርነት የናፈቀው በሚያስመስል ደረጃ ነው ሲገልጹት የሚታየው። ሁኔታው እንደዚያም ነው። አይደለም። የትግራይ ሕዝብ  በፍጹም ሌላ ጦርነት ማስተናገድ አይፈልግም። በቂ ሞተናል፤ በቂ ረግፈናል። በቂ መሠረተ ልማት ወድሟል። ቢያንስ እኔ የሚያሳስበኝን ሁሌ እናገራለሁ።

መፎከር በእኔ ነበር የሚያምረው። በበቂ ብለናል። ያኔ የምንለውን ብለናል። አሁን ሌላ የሰላም ምዕራፍ ሲፈጠር ሁሉንም አጋጣሚ ተጠቅመህ… በጀት ጉዳይ ካለ፤ የትግራይ ተጠቃሚነት ጉዳይ ካለ ፤ በተሟላ መልኩ መንግሥት መሥርተን ፓርላማ ገብተን የምንሟገትበት ሁኔታ በሌለበት ሁኔታ ከፌዴራል መንግሥት ጋር በቅርበት ከመሥራት ውጪ አማራጭ የለም።

ስብሰባዎቻችን በጣም የሚያስገርሙ ናቸው። ታማኝነታችን ለሆነ “ኮዝ ”ትክክለኛ ታጋይ ነን ብለን ለማስረዳት በምናደርጋቸው ውይይቶች ማን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ርቋል የሚለውን ለማስተላለፍ ነው የምንሯሯጠው። ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ተቀራርቦ መሥራት ነው ለትግራይ የሚጠቅመው። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ያስባሉ ብሎ ለመረዳት የሚያስችል ቅርበት መፍጠር ነው ለትግራይ ሕዝብ የሚጠቅመው።

ሶ ሁሏም ተደብቃም የምታገኘውም ሆነ የማታገኘው ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር ግንኙነት የለኝም እያለ በሚያወጣው ድምጽ ፤ በሚያወጣው ጩኸት ነው ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ የሚሞክረው። ይህ ደግሞ አደገኛ አካሂድ ነው የተፈጠረው። ግን እንደዚያም ሆኖ የተፈጠረው የዚህ የፖለቲካል ግሩፕ የምንለው ጠባብ ጥቅሙን ብቻ የሚያይ ቡድን አባዜ ከመሆን አልፎ የትግራይ ሕዝብ የፌዴራል መንግሥት ጋር ፣ የነጋዴዎችም ጉዳይ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ቀጠሮ ያዝልን›› ነው የምጨቀጨቀው። አዲስ አበባ ሄደህ በማድረግህ ክብራችንን አስነካህ የሚል ሕዝብ የለም።

ይህ ሕዝብ ሰላሙን ይፈልጋል። ፌዴራል መንግሥቱ የሰላም አካል እንደሆነው አሁንም አስከመጨረሻው የሰላም አካል ሆኖ እንድናውቀው በምናደርገው ጥረት ውስጥ ሁሉንም ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል ብሎ የሚያምን ነው። ወጣቱ በዛ ልክ ነው የሚያምነው።

ግጭት ለማስቀረት ግጭት የሚቀሰቅሱ ወገኖች ግጭት ሊያመጣ የሚችለው ጣጣ አለው ብለው እንዲያስቡ በማሳመን ነው በመጀመሪያ ደረጃ ። ግርግር ፈጥረው ተመልሰው እንደ ትልልቅ እንግዶች የሚጠሩበትን መድረክ ከፈጠርክ ይለምዱታል። የሰፈር ‹‹ጉልቤ›› የሆነ ነገር ይበጠብጥና ተመልሶ የሚሸመገል ከሆነ ይቀጥልበታል።

እኔ ትግራይ ጦርነት ያስተናግዳል ፣ አያስተናግድም የሚለውን አያስተናግድም በሚል ብንዘጋው ሕዝቡም ፍላጎት የለውም፣ ታጣቂው ፍላጎት የለውም በዚህ ደረጃ ብናየው። እሱ ላይ አለአግባብ ኢ ፍትሃዊ በሆነ መንገድ የሚጫን ጦርነት ካለ ብቻ ነው ራሱን ለመከላከል የሚተጋው። አሁን ባለው ሁኔታ መፈንቅለ መንግሥት እየተፈጸመ ነው ወይ ? በትክክል ድርጊቱ እየተፈጸመ ነው። ማህተሙ ምን እንደሚሠራ አላውቅም። በትክክል ሥልጣኑ ያለውን መንግሥት አውርደህ ማህተም ስለያዝክ በተለየ መልኩ የምትፈታው ችግር የለም።

መሬት የማደል አባዜ አለ። አመራሩ መሬት በመሸንሸን ላይ አባዜ አለው። ኦሮሚያም ብትመድበው ፣ አማራም፣ አፋርም ብትመድበው የመጀመሪያ የሚታየው መሬት መሸንሸን ስለሆነ አሁን ትግራይ የተመደበውም ሃይል አለሁ የሚለውም የፖለቲካ ሃይል መጀመሪያ የሚታየው መሬት መሸንሸን ነው። አሁን ሸንሽኖ ጨርሶታል ሥልጣን ሳይኖረው ድጋፍ መሰብሰቢያ መንገዱ አሁን መሬት መሸንሸን ነው።

ምንአልባት ማህተም የሚነጥቁበት ምክንያት መሬት ለመሸንሸን ካልሆነ በስተቀር እንዳልኩት ፌዴራል መንግሥቱ በዓመት የሚመድበው ፌዴራል ድጋፍ ላይ የማዘው እኔ ነኝ፤ ስለዚህ እኔ ካስቆምኩት በምን መሠረት ነው ሊሠራ የሚችለው። ሌሎች ብዙ ማህበራዊ አገልግሎቶችን ማስቆም ይቻላል ይሄ ነውርም ስለሆነ ነው። ሕዝቡ ተጠቃሚ መሆን ያለባቸውን ነገሮች በእንደዚህ ያለ ፖለቲካዊ ትርምስ ምክንያት ሕዝቡ አደጋ ላይ መውደቅ የለበትም። ግን በተግባር የመፈንቅለ መንግሥት ሥራ እየተሠራ ነው። መፈንቅለ መንግሥት ነው እየተደረገ ያለው።

እንደተባለው ታጣቂዎች ትጥቅ አለመፍታት የፈጠረው ነው። ትጥቅ መፍታት አለበት። ትጥቅ ፈትቶም ጭምር ግን 40 ሺህ 50ሺህ ፖሊስ ሊኖረን ይችላል። 40 ሺህ ፣ 50ሺህ ፖሊስ ሥርዓት ማስከበር ሲገባው ማህተም ወደ መንጠቅ ካስገባነው ያኔም ቢሆን አደጋ ነው የሚሆነው። እስካሁን ትጥቅ አለማስፈታታችን የፈጠረው ጉዳይ ብቻ አይደለም። ትጥቅ በማስፈታቱ ሂደት እኛ የምንወስደውን ኃላፊነት በግልጽ አስቀምጫለሁ። እንዳልኩት ከማደናቀፍ አንፃር ፌዴራል መንግሥቱ ሀብት /ሪሶርስ እስካፈላልግ ብሎ ረጅም ጊዜ ወስዷል። ሪሶርስ ከተገኘ በኋላ ውሱንም ቢሆን ወደ ተግባር ከመግባት አንጻር ግን ተለቅ ያለው ዳተኝነት የራሳችን ነው ብዬ ቅድም ስላስቀመጥኩት።

የወርቅ ንግድ ሕገወጥ እንቅስቃሴ ፤ የሰዎች ዝውውር በጣም አደገኛ በሆነ ደረጃ ነው ያለው። ”ኢን ፋክት” እዚህ ትርምስ ውስጥ እንድንገባ አስተዋጽኦ ከሚያደርጉት ችግሮች አንዱ ፤ የዚህ ቡድን ደጋፊዎች ነን፤ ወይ በአንድ በሌላ መልኩ ከኤርትራ ጋር ልንሠራ ነው ምናምን የሚሉት ወገኖች የምራቸውን ከኤርትራ ጋር የመሥራት፤ የምራቸውን የፌዴራል መንግሥት የመጣል ፍላጎት ስላላቸው ብቻ አይመስለኝም።

ትንሽ መስከን ካለ ለፍርድ የሚቀርቡበት ሁኔታ ይፈጠራል። ስለዚህ የሰዎች ሕገወጥ ዝውውር በስፋት ነው ያለው። እዚህ ላይ የተሳተፉ ሰዎች መረጋጋትን ቢጠብቁ በጣም ነው የሚገርመኝ። ወርቅ ንግድ ውስጥ የሚሳተፉ ሰዎች መረጋጋት ቢመርጡ በጣም ነው የሚገርመኝ። ወርቅ ማዕድን ቁፋሮን እናስቁም ብለን ታስክ ፎርስ አቋቁመን እዛ ያሉ ሰዎች እንዴት እኛ ሳንታመን ቀርተን ነው ወይ ከሌላ ቦታ ኮሚቴ የምታቋቁሙት ብለው ተጨባጭ /ፕራክቲካል ሥራ እንዳይሠራ አደረጉ። ጥፋት የሌለበት ሰው እኛ እንዴት አንታመንም ብሎ ይጀምራል እንዴ ? እንዲጀመር አይፈልጉም። ይህም አሁን ለሚደረገው ፤ እየተፈጠረ ላለው ትርምስ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው።

የትግራይ ኢኮኖሚ ማገገም አልቻለም። የተነሳው ጥያቄ በጣም አስፈላጊ ነው። ትግራይ ኢኮኖሚ የሚያገግምበት ‹‹ሮድ ማፕ›› ከፍተኛ የትግራይ ምሁራን በጣም ብዙ ሥራ የሠሩበት ዶክመንት በካቢኔ ደረጃ ገና በተወሰነ ወረዳ ክላስተር የሚባል አለ። ይሄ ለሥልጣን ለወንበር የሚደረገው ግርግር፤ እሱን እንኳን (‹‹ሮድ ማፕ››)አልተወያየንበትም ። ሁለት አመት ሊያልፈን ነው። የትግራይ ማገገም ሥርዓት ባለው መልኩ በተደራጀ መልኩ ሁሉን አቅም ተጠቅሞ የሚሠራ ሥራ ነው እንጂ፤ የንግድ ማህበረሰቡ የደረሰበት ጥፋት ሳይበቃ የደረሰበት ውድመት ሳይበቃ ጉዳይህን እራስህ ጨርስ የምትይው አይደለም።

ስለዚህ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደርም ቢሆን እዚህ ላይ ‹‹በሲሪየስ›› አልሠራም። ምክንያት ግን ነበረው። ግን የጀመርናቸው ሙከራዎች ነበሩ። እኔ አሁን የትግራይ የንግዱ ማህበረሰብ ‹‹ዲፖዚት›› በጣም ብዙ ነው። የሚያገኘው ብድር እጅግ አነስተኛ ነው። አንዳንድ ባንኮች በርካታ ዲፖዚት ከትግራይ እየወሰዱ ሌላ ቦታ ነው የሚያበድሩት። የሚያሳዝነው ሁለት አመት እና ሶስት ጦርነት ውስጥ በነበረ ሰአት ወለዱ ተከምሮ የዲፖዚቱን የሚያህል ወለድ እየደረሰበት ነው።

ይሄንን እንዴት ነው የምናደርገው? ከብሄራዊ ባንክ ጋር በመነጋገር አንድ አመት እንዲራዘም ተደርጓል። ይህንም ማድረግ ግን ወለዱ ለአንድ አመት እንዲቀጥል ማድረግ ነው። ‹‹ነን ፕርፎርሚንግ ሎን›› የሚባሉትን አንድ አመት ማራዘም ነው። ከዛ በዘለለ ሌላው የፖሊሲ ርምጃ ይጠይቃል ተብሎ ለብሄራዊ ባንክ እና ለሌሎችም ደብዳቤ አስገብተናል። የንግድ ማህበረሰቡ የሚፈልገው ተቅላይ ሚኒስትሩ ሠራዊት ልከው እገሌን ይያዙልኝ አይደለም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፖሊሲ ውሳኔን ይወስንልኝ የሚል ነው። ሰላሙን ነው የሚፈልገው። ይሄንን ከማድረግ አንጻር እዚህ ግባ የሚባል ነገር ለነጋዴው አልሠራንም።

ትግራይ የታታሪ ሕዝብ ሀገር ነው። በትንሽ ነገር ብዙ መሥራት የሚችል ሕዝብ ያለበት አካባቢ ነው። ግን ይሄንን ከማድረግ አንጻር የፖለቲካ ትርምሱ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል። አሁንም ግን እንደተባለው በፖሊሲ ጣልቃ ገብነት ያስፈልገዋል። ዝም ተብሎ በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎች ማለት ብቻ አይበቃም። ትግራይ ላይ የተፈጠረው ‹‹ኤክሴብሽል›› ነው።

ሌሎች በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎች የሉም ማለቴ ግን አይደለም። ቢያንስ ግን ‹‹የስቴት ስትራክቸሩ›› ቦታው ላይ ሆኖ ነው። አማራ የተወሰኑ ዞኖች ላይ የነበረ ጥፋት ሊኖር ይችላል ነገር ግን መንግሥቱ ከባህርዳር ላይ አልተፈናቀለም። የትግራይ ሁሉም ተቋማት እንደነበሩ ሆነዋል። ግን እንአዲስ ለማገገም ነው ጥረት እየተደረገ ያለው። ይሄ የማገገም ሂደት ፖለቲካል ጉዳይ ያበላሸው ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ በፌዴራል መንግሥት ደረጃ የሚገባውን ያክል እኛም ‹‹ፑሽ›› በማድረግ ሂደት ላይ ክፍተት ነበረብን።

ያ ማለት ግን በፌዴራል መንግሥቱ በርካታ ድጋፎች የተደረጉባቸው ጉዳዮች አሉ። እንደየሁኔታቸው ቢለያይም ሁሉም የሚኒስቴር መሥሪያቤቶች የትግራይ ቢሮዎችን ለመደገፍ ይሯሯጣሉ። በትግራይ ውስጥ ሊሠሩ የሚገቡ ‹‹የሪሃቢቴሽን›› ሥራዎችን ለመሥራት የሚቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ። የሚቻላቸውንም የማያደርጉም አሉ። ግን ይሄንንም በተደራጀ ሁኔታ ከመጠቀም አንጻር በርካታ ችግሮች አሉ። በተለይ የንግዱ ማህበረሰብ እንዲወያይባቸው ጥያቄ አቅርበናል።

የታሪክ ምጣኔ የተባለው ከድሬዳዋ ከሻሸመኔ ልምድ እንውሰድ ተብሎ ትግራይ ለማገገም በምታደርገው እንቅስቃሴ ውስጥ አንድ ሰው ብድር መበደር ከፈለገ የሆነ ንብረት ማሲያዝ ካለበት የሚያሲዘው ንብረት 100 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ከሆነ ምንም ሥራ ሳይጀምር 7 ሚሊዮን አወጣ የሚል ደንብ አወጣን። መጥቶ ሲከሰኝ እኔን ሊሆን አይችልም አልኩኝ። በርግጥ እኔም ብኖር አሳልፈው ነበር። ግን እኔ አልነበርኩም። ይሄንን አስቁመናል። ሰው ያለችውን ንብረት አሲዞ ለመበደር በሚያደርገው ጥረት ብር እቀበላለሁ ይላል። እሱን አሁን አስቁመነዋል። ግን አሁንም ሌላ ተጨማሪ ድጋፍ ያስፈልጋል።

ከጸጥታ አካላት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጥያቄዎች ለራሴም የሚገርሙኝ አሉ። የኔ ምክትል ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ ነው። አንዳንዴ የመንግሥት አካል መሆናቸውን ይረሱታል። የኔ ምክትል መንግሥት እንደዚህ አይነት ነገር መሥራት አለበት ብሎ ሲያማርር እሰማለሁ። የትግራይን ጸጥታ እና ሰላም የማስከበር ሥራ ጌታቸው በብዕር ወይም በመግለጫ ሊያረጋግጠው አይችልም። ምን ያክል ‹‹ዲታችድ›› እንደሆነ ነው የሚያሳየው።

የጸጥታ ሃይሉ የመንግሥት አካል መሆኑ አይደለም ችግር የሆነው። የጸጥታ ሃይሉን ወክለው የገቡ ሰዎች ራሳቸውን የመንግሥት አካል አድርገው አለመቁጠራቸው ነው ችግሩ። ራሳቸውን‹‹ ኢንዲፔንደንት›› አድርገው የሚያምኑ፤ የጊዜያዊ አስተዳደር መቋቋሚያ ደንቡ የሾመው ፕሬዚዳንት ነው። ፕሬዚዳንቱ ካቢኔውን ያደራጃል። ከስሩ ሁሉንም አይነት ተቋሞች ይመራል ይላል።

ሠራዊቱ በተሟላ መልኩ እስኪከናወን ድረስ የትግራይ ሠራዊት ነው፤ ‹‹ዲዲአር›› መሟላት መቻል አለበት። በተሟላ መልኩ መሳካት መቻል አለበት። እሱ ቅድም ያነሳሁት ጉድለቶች ስላሉበት ያን አለማድረጋችን እንደ ችግር ሊሆን ይችላል። ከዚህ ውጪ ግን የጸጥታ ኃይሉ ወኪሎች የሚባሉት ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ማካተት መቻል አለበት።

አካታች እንዲሆን ስለተደረገ፤ በእርግጥ በቂ አካታችነት አለው ብዬ አላምንም ምክንያቱም አሁን በርከት ያለ ተሳትፎ ማድረግ የሚገባው ኃይልም ጭምር ያልገባበት ሁኔታ ነበረ፣ ግን ደግሞ ሌሎች መግባታቸውም ጭምር የሚያስመርረው እኔና እኔ ብቻ ካልያዝኩ የሚል አደገኛ አባዜ ያለው ቡድንም ስላለ ይህንንም ውስብስብ ከማድረግ አንጻር ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል።

እገሌ ከሻቢያ ጋር ግንኙነት የለኝም ይላል፤ ግንኙነት አለኝ የሚል ሰው አለ ብዬ አላስብም። እንዳልኩት እኔ በማውቀው ደረጃ እንደ መንግሥት ሃላፊ የተወሰኑ ወታደራዊ አመራሮች ግን አደጋ መፍጠር የሚችሉ። የተወሰኑ ፖለቲካዊ አመራሮች ግን አደጋ መፍጠር የሚችሉ ግንኙነት አላቸው። የለኝም የሚል ሰው ያስተባብል አላቸው የሚል ሰው ደግሞ ማስረጃ ያቅርብ።

ጥያቄው ይሄ አይጠቅመንም የትግራይ እንም ሆነ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትን ፣ አደጋ ላይ ይጥላል ፣ የትግራይ እና የኢትዮጵያንም ህልውና አደጋ ላይ ይጥላል። ምክንያቱም እነዚህ ግንኙነቶች ለትግራይ ሕዝብ ማር በማዝነብ ከሚታወቁ ሰዎች ጋር የተደረጉ ግንኙነቶች ስላልሆኑ። ስለዚህም እገሌ ግንኙነት የለኝም ካለ እግዜር ይርዳው፤ አላቸውም የሚላቸው አሉ እነዚህ ሰዎች ጥቂትም ቢሆኑ አደጋ የመፍጠር አቅማቸው ከፍተኛ ስለሆነ ከዚህ አንጻር ነው መታየት ያለበት።

ከተሞቹን ተቆጣጥሬያለሁ የሚለው ሃይል /ደጋገምኩት መሰለኝ/ ብዙ ወጣት ብዙ ታጣቂም ጭምር የሚደነግጠው አዲግራትን ተቆጣጠርኩ ይላል፤ ጉባዔ አድርጌያለሁ የሚለው አንጃ። ሁመራን የተቆጣጠረ ያስመስለዋል ይላሉ ። የሆነ ተዓምር…. ማህተም ነው የነጠቁት። ተሰባስበህ ከበህ ማህተም ትነጥቃለህ ። ሥራቸውን እንዳይሠሩ በጀት ይቋረጣል ወይ ለሚለው ፌዴራል እኮ ማቋረጥ አይጠበቅበትም።

እንዳይንቀሳቀስ ማድረግ ነው፤ ከዚያ በኋላ ሽፍቶች ናቸው፤ ዘራፊዎች ናቸው። ግን አደጋው የሕዝብ አገልግሎትን ጭምር ለማስቆም ለምን እንገደዳለን ነው። የፌዴራሉ መንግሥት መውሰድ ያለበትን ራሱ ነው የሚወስነው፣ የፌዴራሉ መንግሥት መውሰድ አለበት የምላቸውን ሀ፣ለ ፣ ሐ ብዬ ብዬ ማቅረቤ አይቀርም።

ፌዴራል መንግሥቱ ደግሞ ያለውን አቅምና ሪሶርስ ግምት ውስጥ አስገብቶ ይሄን ይሄን ብሠራ ነው የተሻለ የሚያዋጣኝ ሊል ይችላል። ከዚህ አንጻር እንደተባለው ነው፤ እኛ ነን ሕጋዊ። የፌዴራል መንግሥቱም የሚያውቀው እኛን ነው። በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት የተቋቋመ አስተዳደር ነው።

የሆኑ ሰዎች አድርገናል እና በሆነ ዳስ እቁብ ጥለናል እና በዚህ መልኩ እንዲህ ይደረግልን ስላሉ በምን መልኩ መንግሥት ይሆናሉ። ፍላጎቱ አለ ሃሳቡ ምንድነው ይህን ካደረግን መሬቱን ረመጥ ካደረግነው ተመልሰን መጥተን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከእኛ ጋር ከመደራደር ውጪ ምንም አማራጭ የላቸውም …፤ ይሠራል ወይ የምናየው ይሆናል።

እንግዲህ እኛም መሀል ሀገር ደርሰን በነበርንበት ሰአት እጅ ስጡ እንል ነበር ፣ አሁን ይሠራል ወይ ምናልባት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰከን ስላሉ ባለፉት ሁለት ዓመታት ሊሰሟቸው ከቻሉ እሰማለሁ ።

መንግሥትነት ማህተም በመንጠቅ አይመጣም፤ የሕዝብን ልብ በማሸነፍ ሕዝቡ ምንድነው የሚፈልገው የሚለውን በመመለስ ነው፡፡ ማህተም የያዘ ነው የሚመራኝ የሚል ሕዝብ የለም። የደጋፊዎችን ቁጥር ማወቅ ካስፈለገ 90 ከመቶው ጌታቸውን ሳይሆን ሰላምን፣ ልማትን፣ መረጋጋትን የተፈናቃይ መመለስን ስለሚፈልግ የዘጠና ከመቶ ሕዝብ ድጋፍ አለኝ ብዬ አምናለሁ።

ይሄ ዝም ብሎ የፈጠርኩት ተረት አይደለም ሁሉም ቦታ ያለ እውነት ነው። ሰባ ከመቶ ወጣት ነው ስል ሽማግሌ ይቃወመኛል ማለት አይደለም። ወጣቱ ለውጥ ይፈልጋል። የትግራይ ሕዝብ ለውጥ፣ መረጋጋት ሰላም ይፈልጋል። የጥይት ድምጽ መስማት አይፈልግም። መዋጋት ካለበት ለህልውናው ሲል ነው እንጂ ማህተም ለመንጠቅ አይደለም።

እኔን ጨምሮ ደፍሮ ወንበር ላይ ሊያስቀምጥ የሚያስችል ሥራ የሠራ የለም። ደፍሮ ለእኔ ነው የሚገባው ብሎ ለመሟገት ቀርቶ ያለችውን አጋጣሚ እንኳን ቶሎ የሚጨርሰውን ጨርሰን የሚከናወነውን አከናውነህ ለመውጣት ነው መሯሯጥ ያለብህ። ግን እስከ መጨረሻው ሥልጣን ብቻ ነው መቋደሻዬ ብሎ የሚያምን ማህተም ሲነጥቅ የሚውል አለ።

ሕጋዊነትን ሊያገኝም አይችልም በዚህ መንገድ ፤ እንደተባለው ተሳክቶለት ተደራድሮ ትሻሉናላችሁ ከተባለ እናያለን። ለወንበር የሚሟሟት የለም ፤ ጦርነት ይዘው የሚመጡበት ዕድል ስላለ ነው አሁን እየተጨናነቅን ያለነው ፤የፌዴራል መንግሥቱን በዚህ ደረጃ ሊያየው ይገባል የምንለው።

እኔ ለሕዝባችን የማስተላልፈው መልዕክት ቀላል ነው እነዚህ የጦርነት እና ግጭት አባዜ ያለባቸውን ሰዎች አደብ ማስገዛት መቻል አለበት። ሠራዊቱም የዚህ አጀንዳ አካል አይሆንም፣ በተወሰነ ደረጃ በዚህ ውስጥ እየተሳተፉ ያሉ የበላይ የሠራዊቱ ኃላፊዎቹም ቢሆኑ እንደማያዋጣቸው አውቀው ሥርዓት ወዳለው መንገድ መሄድ መቻል አለባቸው።

በትግራይ ሥራ የለም የሚባለው እውነት ነው ፤ ይገባል ከሰዓት በኋላ ይወጣል። ይሄ የምላችሁ ቡድን የቆየ ልምድ ስለሆነ ሃምሳ አመት የቆየ ስለሆነ የመንግሥት ሠራተኞችን የሆነ ቀን እሮብ ቀን ስብሰባ ይጠራል። ከዚያ የሚሆነው ስለማይታወቅ ማሰር ምናምን የሚባል አባዜ የለብኝም፣ በነገራችን ላይ ቢያንስ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ያስተዋወቃቸው ብዙ ነገሮች አሉ፣ በርካታ ሥራዎች ሠርተናል፣ ገበሬውን፤ ባለሀብቱን ማዕከል ያደረጉ ሥራዎችን ሠርተናል የሚገባውን ውጤት አያግኙ እንጂ፣ ወደ ልማት ወደ ኢንቨስትመንት ሊያስገባ የሚችል በርካታ ሥራዎች አሉ። ከፌዴራል መንግሥትም ጋር በመተባበር ሠርተናል። ትምህርት፣ ማህበራዊ ግልጋሎት፣ ተቋርጠው የነበሩ ነገሮች ወደቦታቸው እንዲመለሱ ለማድረግ የተሠሩ በርካታ ሥራዎች አሉ።

አለመታደል ሆኖም ስለነዚህ ሥራዎች እንድናወራ ብቻ ሳይሆን በእነዚህ ሥራዎች ላይ መጠመድ ሲገባን ወደማይሆኑ ጉዳዮች እንድንገባ ስለተገደድን ነው እንጂ በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል። ግን ጌታቸውን ወይም ሌላ የጊዜያዊ መንግሥት ኃላፊ ሲዘነጥል መገደል አለበት እያለ ሲያስፈራራ የሚውልን የሚያስተባብል ሰው የለም። እነዚህ ሰዎች ተሰብስበው እነዚህ ባንዳዎች መገደል አለባቸው ይላሉ። የእኔ ምክትል ባለበት ጄኔራል ጻድቃን ለምን አልገደልክም ፤መገደል እንዴት አቃተህ አንተን የመሰለ ጀግና ተብሎ፤ ማስተባበያ የሰጠ የለም።

ይሄ ቡድን የወንጀል ተቋም ነው ፤ የሚፈጥሯቸው መድረኮች ፤ የወንጀል መድረኮች ናቸው ፤ እነ እገሌ ለምን አልተገደሉም ይላል። አጠገቤ ቢደርሱ እፈጃቸው ነበር ይላል ፤ነገር ግን አንድም ርምጃ ወስደን አናውቅም። አሁን ያለው መንፈስ ሰውን እያሳደዱ በማሰር የመናገር ነጻነትን በማፈን የሚፈታ ችግር አለ ብለን አናምንም። ግን ይሄ ቡድን የመንግሥት ንብረት ይዘርፋል፤ የመንግሥት ሀብት ያባክናል ብቻ ሳይሆን የመንግሥት ሠራተኞችን ለአንድ ሳምንት ስብሰባ ጠርቻለሁ ይላል። በዛ ላይ ደግሞ ነገ ወደ ስልጣን እንመለሳለን ከወር በኋላ ወደ ሥልጣን እንመለሳለን ከዐቢይ ጋር ተነጋግረናል ይላል። ስምንት ወር ሞላው ።

እነ ጌታቸው አይቀጡም እነዚህ ግን ወደ ሥልጣን ከተመለሱ በደንብ ስለሚገርፉን ብሎ ይሰጋል፣ ይህንን የፍርሃት ቆፈን የመስበር ሥራ በአብዛኛው ተሠርቷል ። ግን የመንግሥት ሥራ አንዳንዱ ለ17 ወራት ደመወዝ ስላልተከፈለን ይላል፣ እውነት ነው አስራ ምናምን ወር ደሞዝ አልተከፈለንም፣ ያለውን ገንዘብ ማቆየት ስላለብኝ የመንግሥት ሠራተኛው ደመወዝ ተከልክሏል፤ ቢያንስ ግን የ5 ወሩን መክፈል ይገባል። የ12 ወር የሚባለው የ2014 ዓ.ም መንግሥት የማዳበሪያ ዕዳችሁን ከፍዬበታለሁ ተመልሳችሁ የባከነ ነገር መጠየቅ አትችሉም ይላል ሌላም ሌላም። ይሄ ሁሉም ምክንያቶች የቀረቡት የሥራ መንፈሱን የተዳከመ ነው የሚለው ትክክል ነው።

አዲጎፎም አዲግራት …. ምክር ቤቶች —በነገራችን ላይ 2012 ምርጫ በክልል ደረጃ ነው ያደረግነው ተውት፣ ሕገ ወጥ ነው ብለን ፕሪቶሪያ ላይ ተስማምተን ወጥተናል፣ ከዚያ በፊት 12 ዓመት ያደረጉ ምክር ቤቶች ናቸው፣ እንደምታውቁት ፌዴራል መንግሥቱ ምርጫ ሲያራዝም ውሳኔውን አንቀበልም ብለን ነው፣ ታስታውሳላችሁ ከመስከረም 25 በኋላ ፌዴራል መንግሥት የሚወስነውን አንቀበልም በሚል ያኔ አምነንበት፣ አቋም ወስደን ነበር። አሁን ድንገት ይሄን አቋም የወሰዱ ሰዎች ሳይቀር አይ ፌዴራል መንግሥቱ ምርጫ ስላላደረገ እነዚህም አይፈርሱም ብሎ ይሞግታል።

“አት ሊስት” ፌዴራል መንግሥቱ የወረዳ ምክር ቤቶች እድሜያቸውን የሚያራዝም ደንብ አውጥቶ ሊሆን ይችላል አላውቅም፣ አብዛኞቹ ምክር ቤቶች ከነበራቸው 150 ሰው ሃያ ሰው ነው ያላቸው። አንዳንድ ቦታዎች ላይ የሚያስገርመው ታህታይ ማጨው ይባላል ሰው አጥተው አፈ ጉባዔው ስለጠፋ ከቀበሌ አንድ አፈጉባዔ ተጠርቶ የምክር ቤቶች ስብሰባ ተብሎ ወረዳ አስተዳዳሪ አንስተናል ሾመናል አሉ። እንደዚህ አይነት ድራማ እድሜ ልክ ሲሠራበት የነበረ፣ የዚህ ጥፋት አካል ሆነን ቆይተናል።

በዚህ ደረጃ ወጥቶ ስታየው በጣም አስደንጋጭ ነው፣ ምንድነው ያደረግነው የሕዝብ ውክልና እንዲኖር ምክር ቤቶቹ አይፍረሱ ግን የተጓደለውን አሟልተን ደንብ አወጣን፣ በዚያ ደንብ መሠረት መመሪያ አውጥተን አላግባብ ወደ ሥልጣን የሚመጣም የሚወርድም እንዳይኖር፣ ግን ደግሞ የመጥረግ አባዜ የእኔ ተቃዋሚዎች የእኔ ደጋፊዎች የሚል ነገር እንዳይኖር ብለን ልናስተካክለው ሞከርን፣ ኖ አሁን ጠመንጃ የያዙ ሰዎችን የሚያዙ የተወሰኑ ሰዎች ሕገ መንግሥት መተንተን ጀምረዋል፣ ሕገ መንግሥቱ የትግራይ ሕገመንግሥት ምን ቀበሌ በሕገ ፣መንግሥቱ መሠረት ወረዳ በሕገ መንግሥቱ መሠረት እንዳልኳችሁ ነው 20 ሰው አባል ያለው ምክር ቤት ምክር ቤት አይደለም፣ 12 ዓመት አልፎታል እድሜውን ምናምን እሱንም ትተን በዚህ መልኩ እናስተካክለው አልን፣ ካቢኔው የወሰነውም ይሄንን ነው።

የሠራዊቱ አመራሮች ይሄን ይሄን እናደርጋለን ካላችሁ ቢያንስ በሕግና በደንብ እናድርገው እንጂ ዝም ብሎ አርጩሜ ይዞ ሄዶ አንተ በሕገ መንግሥት የተመረጥክ ነህ አይደለህም ለማለት ማነው መብት የሰጠው፣ አሁን የምናየው ሁኔታ ይሄን ትርምስ ነው፣ የሚያሳዝነው ጥይት እየተተኮሰ ሰዎች እየቆሰሉ ትናንት የተደገለም ሰው አለ።

ወደዚህ አይነት የሚያመራ ሕገ ወጥነት ጋጠወጥነት ጭምር ነው እየተስፋፋ ያለው ፤ ይህ የተወሰኑ የሠራዊት አመራሮች በአብዛኛው ግን ይህን አድርጌያለሁ እያለ የሚያምታታ ከፍተኛ የሥልጣን አባዜ ያለው ጦርነትን ጨምሮ ሁሉንም የግርግር መንገዶች ተጠቅሞ ወደ ቦታው መመለስ የሚፈልግ አሁን እንደዚህ ካላደረጋችሁልኝ የሆነ ነገር አደርጋለሁ ብሎ ደግሞ አስፈራርቶ ድንገት ከፌዴራል መንግሥት ጋር ተደራድሬ እመለሳለሁ የሚል ቡድን እየፈጠረው ያለው ነው። ሕዝቡን እያስፈራሩት /ቴረራይዝድ/ እያደረጉት ነው። በሁሉም ቦታዎች ሕዝብ ተቃውሞ አለው።

ጊዜያዊው ምክር ቤት ሕጋዊ ነው ለሚለው አማካሪ ምክር ቤት ነው፤ ደንብ አውጥተን ያቋቋምነው ፤ መንግሥት ሥራውን ለመሥራት የሚያስችለውን ሁሉንም ተቋማት ያደራጃል ይላል ፤ ይህ እራሱ ደንቡ የሚለው ነው።

በጀት እራሴ ከማጸድቅ፣ ክፍት ሆኖ ይሻላል በሚል የምታደርገው ነው። አሁን የአማካሪው ምክር ቤት ሕጋዊ አይደለም የሚለው ሳይሆን በአሁኑ ሰዓት እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ጊዜያዊ አስተዳደሩ እንደጊዜያዊ አስተዳደር የፌዴራል ተለጣፊ /አፐንዴክስ/ ነው ትልና ልታፈርሰው ትሞክርና ግን ደግሞ ይሁንታና ፈቃደኝነት ከፌዴራል መንግሥት ትጠይቃለህ ፤ ሁለቱንም በአንዴ ጊዜ ልታደርግ አትችልም።

አሁን ባለው ሁኔታ ጊዜያዊ አስተዳደሩን ለማፍረስ እየተደረገ ያለው ጥረት ጊዜያዊ አስተዳደሩን ከማፍረስ በላይ ሀገሪቱን አደጋ ላይ ከመጣል በላይ ፕሪቶሪያ ስምምነትን ከማፍረስ በላይ በዓይናችን የሚታይ ያፈጠጠ የጦርነት እድል የሚፈጠርበት ሁኔታ ስላለ በፍጥነት መገታት አለበት የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ ነው።

/ይህ ቃለ መጠይቅ ፕሬዚዳንት ጌታቸው በትግርኛ ተጠይቀው በትግርኛ የመለሱትን አያካትትም/

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 6 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You