
አዲስ አበባ፡– ሴቶች በሁሉም ዘርፍ አመርቂ ውጤት እንዲያስመዘግቡ የመገናኛ ብዙኃን የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሴቶች ሕጻናት እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ገለጸ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሴቶች ሕጻናት እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ዳይሬክተር ወይዘሮ ስፍራሽ አልማው ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ሴቶች የቁጥራቸውን ያህል በኢኮኖሚ ተጠቃሚ አልሆኑም፤ ለዚህም አንዱ ምክንያት አብዛኛውን ጊዜ የቤት ውስጥ ኃላፊነትን ለመወጣት ቅድሚያ ስለሚሰጡ ነው። ሙሉ ጊዜያቸውን ቤት ውስጥ ስለሚሰማሩ፤ ገቢ የሚያስገኝ ሥራ ላይ የመሠማራት እድላቸው ውስን ነው ብለዋል።
ከቤት ወጥተው ኢኮኖሚ ወደ ሚያመነጩ ሥራዎች እንዲሠማሩ፤ መገናኛ ብዙኃን እና ማህበራዊ ሚዲያዎች ማበረታታት ይኖርባቸዋል ያሉት ዳይሬክተሯ፤ በሴቶች እና በማህበረሰቡ ላይ መልካም ተፅእኖ የሚፈጥሩ የሚዲያ ዝግጅቶችን መሥራት ለሚፈልጉ፤ የሴቶችን ጥንካሬ እና ኃላፊነትን የመወጣት ሚና የሚያመላክቱ ፊልሞችንና ዜናዎችን ለሚሠሩ ቢሮው ትልቅ ግብዓት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች ሰላምና ጸጥታ ላይ ከፍተኛ ሚና እየተወጡ መሆኑን የጠቀሱት ኃላፊዋ፤ የተለያዩ ሃይማኖታዊ በዓላት ሲከበሩ የሰላም ሠራዊት ሆነው በመሳተፍ፣ በምሽት አካባቢ ጥበቃ ላይ በመሠማራት እና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ዕርቅ እና መግባባት ለመፍጠር በሰላም ዙሪያ የሚሠሩ በርካታ ሴቶች ስለመኖራቸውም ጠቅሰዋል።እነዚህም ሥራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ቢሮው ከሚሰጣቸው ዕውቅና በተጨማሪ ሚዲያውም ሊያበረታታቸው ይገባል ነው ያሉት።
ሴቶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከተለያዩ ባንኮች ጋር እየተሠራ ነው ያሉት ኃላፊዋ፤ ከእዚህ አንጻር ተሳትፏቸው በቁጥር ሲታይ ግን አነስተኛ ነው ብለዋል፤ ስለሆነም ይህም ሴቶች የመቻል ስሜት በውስጣቸው እንዲሰርፅ በመገናኛ ብዙኃን ቀጣይነት ያለው ሥራ መሥራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
በተለይ በገጠር ያሉ ሴቶች ለዘመናት ስር ሰዶ በቆየው ልማዳዊ አስተሳሰብ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ተጠቃሚ እንዳልሆኑ እና ያለ ዕድሜ ጋብቻ እና የጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ተጠቂ እንደሆኑ ገልጸው፤ ይህን ለማስቀረትም ሚዲያው ወሳኝ ሚና እንዳለው መረዳት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በማህበረሰቡ ዘንድ ያለው የግንዛቤ እጥረት ለመቅረፍም ቢሮው የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን እና እውነተኛ ለውጦች እንደታዩ፤ እንዲሁም በፖለቲካ እና በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ እኩል ተሳታፊ እንዲሆኑ እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል።
የማህበራዊ ችግር ተጎጂ የሆኑ ሴቶችን ለመደገፍ እና ራስን ለማስቻል በተለይ በከተማ ደረጃ እየተሠሩ ካሉት ፕሮጀክቶች መካከል ‹‹የነገዋ ተሐድሶ ማእከል›› ተጠቃሽ ነው ያሉ ሲሆን፤ የለሚ ኩራ እንጀራ ማዕከል፣ የጉለሌ ማዕከል በምሳሌነት የሚጠቀሱ መሆናቸውን አንስተዋል።
በሀገር ደረጃ ፕሮጀክቶች ሲቀረፁ ሴቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታስቦ እየተሠራ መሆኑን በመግለጽ፤ ሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ ለማሳደግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መሥራት ይጠበቅባቸዋል ሲሉ አሳስበዋል።
ሔርሞን ፍቃዱ
አዲስ ዘመን መጋቢት 6 ቀን 2017 ዓ.ም