በዛሬው «መጋቢ አዕምሮ» ዓምድ ላይ በአንድ ወቅታዊ ጉዳይ ጥቂት ማለት ፈለግኩ። ከዚህ ቀደም በነበሩት ጽሑፎቼ ላይ ኢትዮጵያውያን በተለይ ወጣቶች አስተሳሰባቸውን፣ አመለካከታቸውን፣ በጎ እይታን እና ራስን ከፍርሃት አሸንፎ ለስኬት መብቃት ጋር በተያያዙ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ መጣጥፎችን አድርሼ ነበር። ዛሬ ደግሞ ከሃሳብ ፈቀቅ ያሉና ተጨባጭ በሆኑ ወቅታዊ ጉዳይ ጋር የተያያዙ ቁልፍ ነጥቦችን አነሳለሁ። ነገረ ጉዳዬ የወጣቶችን ምልከታ በመቀየር ወደ ስኬት ይመራል ብዬ አምናለሁ፤ በዚህ ምክንያት እንደሚከተለው አንዳንድ ሀሳቦችን ለማለት ወደድኩ። የዛሬው ጽሑፌ ፍሬ ነገር ከዓለም አቀፉ የዲጂታል አብዮት እና የኢትዮጵያውያን ወጣቶች ብሩህ ተስፋ ጋር በቀጥታ ይገናኛል።
የዲጂታል አብዮት ዓለምን በአዲስ መልክ እየቀረጸ ነው። የኢትዮጵያ ወጣቶችም በዚህ የለውጥ ዘመን ግንባር ቀደም ተጠቃሚ ከሚሆኑት መካከል ናቸው። በምድራችን ላይ የቴክኖሎጂ ተደራሽነት እየጨመረ በመምጣቱ ወጣቶች የወደፊት ስኬታቸውንና ሕይወታቸው የመወሰን፣ በሀገራቸው ኢኮኖሚ ላይ የበኩላቸውን አስተዋፅዖ ለማድረግ፣ የኅብረተሰቡን ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ዕድል ከፊት ለፊታቸው ተደቅኗል።
በርካታ ወጣቶች በዩኒቨርሲቲና በቴክኒክና ሙያ የትምህርት መስክ ተምረው ያለ ሥራ ተቀምጠው ሲያማርሩ እንመለከታለን። ከሥራ ፈጣሪነት ወደ ጠባቂነት የሚያዘነብል አስተሳሰብ እና አሉታዊ ምልከታም በስፋት ይታያል። ይህ አሁን ካለንበት የዲጂታል ዘመን አንፃር ስንመለከተው ፍፁም የተሳሳተ ሆኖ እናገኘዋለን። ለዚህም ነው በዛሬው ርዕሰ ጉዳይ ላይ የዲጂታል አብዮት አንዱ ክንፍ የሆነው የኦንላይን ትምህርትና ሥራ ለኢትዮጵያውያን ወጣቶች ይዞ የመጣውን ዕድል በዝርዝር እንደሚከተለው ለማንሳት የፈለኩት።
የኦንላይን ትምህርት፣ በበይነ መረብ የሚከናወን የርቀት ሥራ (ፍሪላንሲንግ) ለወጣቶች የማይታመን የስኬት መንገዶችን ይዞ መጥቷል። ሥራ ፈጣሪ ለሆኑ፣ ለአዳዲስ ሃሳቦች በጎ ምልከታ ላላቸው፣ ደፋርና በራስ መተማመን ለገነቡ ወጣቶች ቴክኖሎጂን እንደ ዕድል እንጂ እንደ እርግማን ለማይቆጥሩ ወጣቶች ዲጂታል አብዮት የስኬት መንገድን ይዞ ብቅ ብሏል። ለዚህ ነው በዚህ መጣጥፌ ላይ የኢትዮጵያ ወጣቶች ቴክኖሎጂን መጠቀም የሚችሉባቸውን ዘርፈ ብዙ መንገዶች፣ አነቃቂና እውነተኛ የሕይወት ታሪኮችን እንዲሁም ወደፊት ሊያጋጥሟቸው ስለሚችሉ ተግዳሮቶችና ዕድሎች በስፋት ቅኝት ላደርግ የሻትኩት። ለመሆኑ አንተ ‹‹የዲጂታል አብዮት ምን ዕድሎችን ይዞልኝ መጥቷል›› ብለህ ታስባለህ፤ የሚከተለው ሃሳብ ጥሩ ምላሽ እንደሚሰጥ እተማመናለሁ።
ክህሎትን የሚያዳብሩ የኦንላይን ትምህርቶች
እንደሚታወቀው ትምህርት የግል ሙያዊ እድገት የምታረጋግጥበት መሠረት ነው። የዘመኑ ዲጂታል አብዮት፤ ቴክኖሎጂ ደግሞ የእውቀት ተደራሽነትን ዲሞክራሲያዊ አድርጓል። አጫጭር የክህሎት ትምህርቶችን የት ላገኝ እችላለሁ ብለህ ተጨንቀህ ይሆን፤ ዲጂታሉ ዓለም ለዚህ ቁልፍ መፍትሔና ምላሽ አለው። ለኢትዮጵያውያን ወጣቶች እንደ (Coursera፣ edX፣ Khan Academy፣ YouTube) ያሉ የኦንላይን የክህሎት መገንቢያዎች ርቀትን ትርጉም አልባ አድርገው ዓለም ላይ ያሉ እውቀቶችን ደጃፍህ ድረስ ይዘውልህ መጥተዋል። በእነዚህ መድረኮች ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት በነፃ ወይም እጅግ አነስተኛ በሆነ ክፍያ የማግኘት ዕድል ታገኛለህ።
ፕላትፎርሞቹ ወጣቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ተፈላጊነት ያላቸውን ችሎታዎች እንዲያገኙ የሚያስችላቸው እንደ ፕሮግራሚንግ፣ ዲጂታል ግብይት፣ ዳታ ሳይንስ እና የንግድ ሥራ አስተዳደር ባሉ ዘርፎች እውቀትን ያጋራሉ። ታዲያ አንተ ምን እየጠበክ ነው? ለመሆኑ ራስህን ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር ምን ያህል አዛምደሃል?
ደጋግሜ እንደነገርኩህ የኦንላይን ትምህርቶች ለኢትዮጵያውያን ወጣቶች ብዙ ዕድሎችን የሚሰጡ ናቸው። ልብ በል! ለዘመናዊው ዓለምና ወቅቱ ለሚሻው የሥራ ገበያ ውድድር አስፈላጊ የሆኑትን እንደ ኮዲንግ፣ ግራፊክስ ዲዛይን እና ቪዲዮ ኤዲቲንግ ያሉ ቴክኒካል ክህሎቶችን አቀላጥፈህ ለማወቅ ከፈለግህ አላግባብ ጊዜህን ከሚገድሉ የአሉባልታ ማኅበራዊ ድረገፅ እንቶ ፈንቶዎች ወጥተህ እነዚህን ፕላትፎርሞች ተቀላቀል።
አብዛኛውን ጊዜ እነዚህ ፕላትፎርሞች ማንኛውም ሰው ሥልጠናውን ካጠናቀቁ ሰርተፍኬቶችን ይሰጣሉ፤ ይህ ደግሞ የሥራ ልምድህን ከፍ ያደርግልሃል፤ የሥራ ዕድልንም በእርግጠኝነት ይጨምርልሃል። በተጨማሪም የኦንላይን ትምህርት ጊዜና ርቀት ስለማይገድበው አንተም ሆንክ ሌሎች ተማሪዎች በምትፈልጉት ፍጥነት እውቀትን ማግኘት እንድትችሉ ያግዛችኋል። ለዚህ ነው የዲጂታሉ አብዮት ይዞት ለመጣው ስር ነቀል ለውጥ ምን ግንዛቤ አለህ የምልህ። ፈጠን ብለህ ራስህን ከዘመኑ ጋር አዛምድ። ፍጠን!!
እዚህ ጋር አንድ ምሳሌ ልሰጥህ እወዳለሁ። ገና በታዳጊነቷ በቴክኖሎጂ አጠቃቀምና በሙያ ጉዞዋ የምናደንቃት የቴክኖሎጂ ባለሙያ ወጣት ቤተልሔም ደሴን የሕይወት ልምድ መውሰድ ትችላለህ፤ ይህቺ እንስት አንዷ ከእንቅልፍህ ልታባንንህ የምትችል አበረታች ምሳሌ ነች። ቤተልሔም እራሷን በኮዲንግ እና በሶፍትዌር ልማት በኦንላይን ኮርሶች አስተምራለች፤ ከኢትዮጵያ ወጣት የቴክኖሎጂ ፈጣሪዎች መካከል አንዷ ሆናለች። ዛሬ ላይ በአዲስ አበባ የሚገኘው አይኮግላብስ የተሰኘው አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እና ሮቦቲክስ ኩባንያ ውስጥ ቁልፍ ሰው ነች። የእርሷ ስኬት በርካታ ኢትዮጵያውያንን በቴክኖሎጂ እና በፈጠራ ሥራ እንዲሠማሩ ምክንያት ሆኗል። ለመሆኑ አንተስ? ከቤተልሔም የዲጂታሉ ዓለም ስኬት ምን ትማራለህ?
እርግጥ ነው በሀገራችን በኢንተርኔት አማካኝነት የሚደረግ ትምህርት ውስን ነው። የኢንተርኔት አገልግሎት፣ ከፍተኛ የዳታ ወጪ እና የዲጂታል እውቀት እጥረትን ጨምሮ በርካታ ተግዳሮቶች አሉ። በመንግሥት በኩል እነዚህን መሰናክሎች ለመፍታት በመሠረተ ልማት፣ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ እና በወጣቶች መካከል የዲጂታል ክህሎቶችን ለማስፋፋት የሚያስችሉ ፕሮጀክቶችን መደገፍ ያስፈልጋል። እስከዚያው ድረስ ግን የግል ጥረትህን አታቋርጥ። ለቲክቶክ ያልጠፋ ዳታ እራስህን በእውቀት ለማስታጠቅ ጥቂት ጊዜና ጥቂት ገንዘብ አታጣም መቼም።
በዓለም አቀፍ የሥራ ገበያ ውስጥ ተወዳደር
የፍሪላንሲንግ (በርቀት ሆኖ በቤት ውስጥ መሥራት) በዲጂታሉ ዓለም መስፋፋት መልክዓ ምድር የሚፈጥረውን የጊዜ ገደብና እንቅፋቶችን በማስወገድ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሥራ እንዲወዳደሩ ዕድል እየከፈተ ነው። እንደ (Upwork,Fiverr,Toptal) ያሉ መድረኮች ፍሪላንሰሮችን በዓለም ዙሪያ ካሉ ደንበኞች ጋር ያገናኛሉ። ለመሆኑ ስለነዚህ ፕላትፎርሞች ምን ያህል ታውቃለህ? ሶፍትዌር ልማት፣ የይዘት ጽሑፍ እና ዲጂታል ግብይት ባሉ የሙያ መስኮች ላይ እራስህን ማሠልጠንህ የርቀት ሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንደሚያደርግህ ታውቅ ይሆን?
የርቀት ሥራ ለአንተና ለመሰል ወጣቶች ጠቃሚ ልምድ እንድትቀስሙና ዓለም አቀፍ ምርጥ ተሞክሮዎችን እንድትማሩ ያስችላችኋል። በተጨማሪም ቋሚ የገቢ ምንጭ ይሆናል። ፍሪላንሲንግ ቀጣይነት ያለው የመማር እና የክህሎት እድገትን ያስገኛል። እያደገ ከመጣው የሥራ ገበያ ውስጥ ክህሎትህን መሠረት አድርገህ ብቻ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ መሆን ትችላለህ።
እዚህ ጋር አንድ ሌላ ስኬታማ ወጣትን በምሳሌነት ላንሳልህ። ዮዳሔ ዘሚካኤል ይባላል። የኦንላይን ትምህርቶችን በመውሰድ የርቀት ሥራ (ፍሪላንሲንግ) ፕላትፎርሞችን በመጠቀም ስኬታማ ሆኗል። ዛሬ ዮዳሔ ታዋቂ ኢትዮጵያዊ የሶፍትዌር ገንቢ ነው። አንተስ የዮዳሔን እና የቤተልሔምን ፈለግ መከተል አትፈልግም?
የዲጂታል ዘመን ንግዶችን ተቀላቀል
ቴክኖሎጂ ሥራ ፈጣሪነትን ያበረታታል። አንተም በዚህ መድረክ ላይ ቀዳሚ ሁን። ዲጂታል አብዮቱ የኢትዮጵያ ወጣቶች በአነስተኛ ሀብት ሥራ እንዲጀምሩ መንገድ እየፈጠረ ነው። እንደ ኢንስታግራም እና ፌስቡክ ያሉ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች እንዲሁም እንደ Shopify እና Jumia ያሉ የኢ-ኮሜርስ መድረኮች ለገበያው ትልቅ ዕድል ይዘው መጥተዋል፤ በእነዚህ መድረኮች ያንተ ድርሻ ምንድነው። መፍጠንና ራስህን ተወዳዳሪ ማድረግ አለብህ።
አብዮቱ ለኢትዮጵያውያን ወጣቶች ምርቶችን በሀገር ውስጥ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በኦንላይን መደብሮች እንዲሸጡ ዕድል ይሰጣል። ይህ ብቻ አይደለም ሥራ ፈጣሪነትን ያበረታታል።
በወጣት ኢትዮጵያውያን አልሚዎች የተፈጠሩ ንግዶችን በምሳሌነት ማንሳት ይቻላል። ለምሳሌ ተጠቃሚዎች ባሉበት ሆነው ምግብ የሚያዙበት መተግበሪያ (BeU Delivery) አንዱና ዋነኛው ነው። መተግበሪያው በአዲስ አበባ የምግብ አቅርቦት አገልግሎት ላይ ለውጥ በማምጣት ለደንበኞች ምቹ እና ለአሽከርካሪዎች የገቢ ዕድሎችን የፈጠረ ነው። አንተም ይህንን መሰል የቴክኖሎጂ በረከት ለሀገርህ ማበርከት ትችላለህ።
ፈጠራ እና ማኅበራዊ ተፅዕኖ
በርካታ የኢትዮጵያ ወጣቶች ከግል ስኬት ባሻገር የኅብረተሰቡን ችግሮች ለመፍታትና ለውጦችን ለመፍጠር ቴክኖሎጂን በመጠቀም ላይ ናቸው። ከጤና እስከ ግብርና፣ በቴክኖሎጂ የተደገፉ መፍትሔዎች ማኅበረሰቦችን እየለወጡ እና ሕይወትን እያሻሻሉ ነው። አንተም የዚህ አካል መሆን አለብህ። የቴክኖሎጂውን አብዮት መቀላቀል ይኖርብሃል። ከራስ የተሻገረ ብሔራዊ ጀግና ለመሆን የግዴታ ድንበር መጠበቅ አይጠበቅብህም። በተሠማራህበት ሙያ ላይ ለውጥ ካመጣህ አርበኛ ነህ። ለምሳሌ የሚከተሉት የቴክፈጠራዎች በወጣት አርበኞች የተፈጠሩ ናቸው።
ለአብነት በግብርና ላይ እንደ ሄሎ ትራክተር ያሉ መተግበሪያዎች እንዲፈጠሩ ምክንያት የሆኑ ወጣቶች ናቸው፤ ቴክኖሎጂው አርሶ አደሮች በተመጣጣኝ ዋጋ ማሽነሪዎች በማገናኘት የግብርና ምርታማነትን ያሳድጋል። ሌላም ልጨምርልህ በጤናው ዘርፍ እንደ ቴሌሜድ ያሉ ፕላትፎርሞች የርቀት የሕክምና አማራጭ በመስጠት እፎይታን ፈጥረዋል። በትምህርት ዘርፍ እንደ ኩራዝቴክ ያሉ መተግበሪያዎች የኢትዮጵያን የትምህርት ጥራትን እንደሚያሳድጉ ታምኖባቸዋል። አንተም በተማርከው የኦንላይን ትምህርት (ክህሎት) አንዳች ጠቃሚ ነገር ማበርከት ትችላለህ።
ቀደም ሲል በምሳሌነት ያነሳኋት ወጣት ቤተልሔም ደሴ ቴክኖሎጂን ለማኅበራዊ ተፅዕኖ በማዋል ረገድ ፈር ቀዳጅ ነች። በ iCog Labs ውስጥ በምትሠራው ሥራ የጤና አጠባበቅ አቅርቦትን ማሻሻል እና የትምህርት መሣሪያዎችን ማቅረብን የመሳሰሉ ችግሮችን ለመፍታት ሞክራለች፤ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ለሚጠቀሙ ፕሮጀክቶች ክህሎቷን ተጠቅማ የተቻላትን አድርጋለች። ጥረቷ አዲሱ ትውልድ ኢትዮጵያዊ የፈጠራ ባለሙያዎች ቴክኖሎጂን ለበጎ ዓላማ እንዲጠቀም አነሳስቷል። ለዚህ ነው አንተም የዘመኑን አብዮት መቀላቀል የሚኖርብህ።
እንደ መውጫ
የዲጂታል አብዮቱ የኢትዮጵያ ወጣቶች የወደፊት ሕይወታቸውን እንዲቀርጹ እና ለሀገራዊ እድገት የበኩላቸውን አስተዋፅዖ እንዲያበረክቱ ልዩ ዕድል ይዞ እንደመጣ አምናለሁ። የኦንላይን ትምህርትን፣ የርቀት ሥራን (ፍሪላንሲንግ)፣ ሥራ ፈጠራን በማበረታታት ወደር የለውም። የኢትዮጵያ የወደፊት ዕጣ ፈንታ በዲጂታል ልማት እንደሚወሰን ማመን አለብህ። የኢትዮጵያ ወጣቶች ደግሞ የዚህ ለውጥ መሐንዲሶች ናቸው። አንተም የዚህ ትውልድ አባል ነህ!! ለዚህ ነው ስኬትን ለማግኘት እና ነገን የበለጠ ብሩህ ለማድረግ ቴክኖሎጂን ገንዘብህ አድርግ የምልህ። እንደ ቤተልሔም ደሴ፣ ዮዳሔ ዘሚካኤል፣ ቤኢዩ ዴሊቬሪ እና አፍሮ ሞባይል ያሉ ምሳሌዎች ቴክኖሎጂን በቅርበት እና በእውቀት ለበጎ ዓላማ ከተጠቀምክ ማለቂያ የሌለው እድሎችን እንደምታገኝ አትጠራጠር። ሰላም!!
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 6 ቀን 2017 ዓ.ም