
“በማህበራዊ ሚዲያ አማካኝነት ሃይማኖትን ሽፋን አድርገው የክብረ-ነክ፣ የትንኮሳ፣ የጥላቻና ጸብ ቀስቃሽ መልዕክቶችን በሚያስተላልፉ አካላት ላይ አፋጣኝ ሕጋዊ ርምጃ እንዲወሰድ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጠየቀ” የሚለው የሰሞኑ የመገናኛ ብዙኃን ዜና-ዘገባ የእዚህ ጽሑፍ መነሻ ሲሆን፤ በተለይ “ሽፋን” የምትለዋ ዘወትራዊ መሸሸጊያ ለአንዴ (እና ለመጨረሻ ጊዜ) ከፖለቲካ አይሉት ማህበራዊ ሰፈር መንግሎ ለመጣል እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ማበረታታትና መደገፍ የጽሑፉ ንኡስ አላማ ነው።
“ሽፋን” ሌላው ዓለምም ሊኖር ይችል ይሆናል። እንደ እኛ ሀገር ግን ቅጡን ባጣ ሁኔታ ሥራ ላይ እየዋለ ያለበት ሀገር ያለ አይመስልም። ይህንን በጣም በርካታ በሆኑ ማሳያዎች ማሳየት የሚቻል ሲሆን፤ ለጊዜው የተወሰኑትን በመውሰድ የ“ሽፋን”ን መጠነ-ስፋት፣ መጠነ-ርዝመትና ጥልቀት፤ እንዲሁም ህሊና ቢስነት እንመልከት።
እርግጥ ነው የአስተሳሰብ ድህነት በነገሠ ቁጥር መሸሸጊያ ፍለጋ መኳተን የሚጠበቅ ነው። ማህበራዊ ፋይዳ ያለው ተግባር መሥራት ሳይቻል ሲቀር ወይ ብሔርን፣ ወይ ፆታን፣ ወይ ሃይማኖትን ሽፋን አድርጎ ሕዝብን ከሕዝብ በማጋጨት ከልማትም ይሁን ከሰላም መልክአ-ምድር ማራቅ፤ ተግባሩን ለመፈፀምም ምሽግ እየፈለጉ መመሸግና እዛ ምሽግ ውስጥ ሆኖ የፖለቲካ ትርፍን ማስላት እየተለመደ የመጣ የዘቀጠ ተግባር ነው።
ርዋንዳን ለዛ ሁሉ ያበቃት፣ ለመጥፎ ምሳሌነት የዳረጋት፣ ማስተማሪያነት ትሆን ዘንድ ላስተማሪዎች ያቀበላት አንድ እዚህ ግባ የማይባል፤ ምንም አይነት የረባና ተቀባይነት ሊያስገኝለት የሚችል ሃሳብ የሌለው ግለሰብ (ዛሬ እንዲህ ከመሸገበት አንገቱ ተይዞ ለፍርድ ሊቀርብ) ነው።
ወደ ራሳችን ተመልሰን ጥያቄዎችን እናንሳ እስኪ። ለመሆኑ እስከ ዛሬ ስንትና ስንት ደም ነው የፈሰሰው። በእውነት የሕዝብን ችግር ለመቅረፍ ተብሎ ነውን? ስንትና ስንት የማጨራረስ ሙከራዎች (አብዛኞቹ መክሸፋቸው በጀ እንጂ) የተደረጉት እውነት ለሀገር ታስቦ ነው? የእኔ ብሔር እንዲህ ሆነ/ደረሰበት፣ ሃይማኖታችን እንዲህ እንዲህ ሊደረግ ነው ወዘተ እየተባለ ስንትና ስንት ደም የፈሰሰውና የንፁሀን ህይወት የተቀጠፈው በ“መጤ” እና “ነባር” ምሽጎች ውስጥ በመመሸግ (ሽፋን በማድረግ) አይደለምን? ታዲያ እነዚህን ሁሉ ያለፈ ሰው እንዴት እንደገና “በሃይማኖት ሽፋን” ሌላ ዙር እልቂት ይደግሳል? ለምን?? ለምንስ ከመንፈሳዊነትና ከሃይማኖት መሠረታዊ ዕሴቶች ጋር የሚቃረን ተግባር ይፈፅማል፤ ለምን? “አንድ ያለኝ አንጡራ ሀብት ሃይማኖቴ ነው” የሚልን ሕዝብስ በእዚህ መልኩ ለማጋጨት መሞከር ለምን አስፈለገ፤ ለምን? እስከ ዛሬ የተገደሉት ንፁሃን፣ የተቃጠሉት የሃይማኖት ተቋማት • • • አይበቁም??
የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጠቅላይ ፀሐፊ ሊቀ ትጉሀን ቀሲስ ታጋይ ታደለ “በማህበራዊ ሚዲያ በተለይም አንዳንድ የኦርቶዶክስ ክርስትና አማኝ ነን የሚሉ ግለሰቦች፣ የእስልምና ሃይማኖት ነቢይ በሆኑት በነቢዩ መሐመድ ላይ ድፍረት የተሞላበት ክብረ ነክና ጸያፍ ንግግር ሲያደርጉ ታይተዋል” በማለት ነው ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ የሰጡት።
በማህበራዊ ሚዲያው ይህንን የሚሉ ሰዎች እውነት እነዚህ ሁለት ታላላቅ ሃይማኖቶች አብረው፣ ትከሻ ለትከሻ ተደጋግፈው መኖራቸውን አያውቁ ይሆን? እውነት እነዚህ የሃይማኖት ተቋማት ዛሬ በእዚህ ደረጃ ሊገለፁ የሚገባቸው ናቸውን? ይህ የማህበራዊ ሚዲያው ባለሟሎች እኩይ ተግባር የሁለቱን ሃይማኖት ምእመናንስ ይመጥናልን? የተደረገው ነገር እውነት እንኳን ቢሆን ከግለሰብ ጥፋትና ወንጀል ባለፈ ሃይማኖቶቹን ይወክላል ማለት ይቻላል? እንደማይመጥንና እንደማይወክላቸው እየታወቀ እነሱን ሽፋን ማድረጉ ለምን አስፈለገ? ለምንስ ሃይማኖትን ሽፋን ማድረግ ፋሽን ሆነ? ፋሽን ማድረጉስ እስከ መቼ ነው የሚቀጥለው፣ እስከ ስንተኛው ክፍለ ዘመን???
በተለይ በአሁኑ ሰዓት የሁለቱ ታላላቅ ሃይማኖቶች የተቀደሰ የጾም፣ የጸሎትና በከፍተኛ ደረጃ መንፈሳዊ እነፃ ላይ ሆነው (ቀሲስ ታጋይ እንዳስታወሱት) ሳለ፤ ይህንን እንደ ፀጋና የአምላክ በረከት አድርጎ በመውሰድ ለሀገርና ለሕዝብ በሚበጅ መልኩ መጠቀም እየተገባ በፈረደበት ማህበራዊ ሚዲያ “ክብረ-ነክ፣ የትንኮሳ፣ የጥላቻ እና ጸብ ቀስቃሽ ዘመቻዎችን” ማካሄድ የግል ዓላማን ለማሳካትና ድብቅ አጀንዳን ለማራመድ ሃይማኖትን ሽፋን ከማድረግ የተለየ ምንም አይነት ምክንያት ሊኖረው አይችልም። በተለይ በሃይማኖት ሰበብ የሚመጣው ጦስ ከወዲሁ የሚታወቅ ከመሆኑ አኳያ ተግባሩ በምንም መንገድ ተቀባይነትን ሊያገኝ ከቶም አይቻለውም።
በመግለጫው ላይ እንደተገለጸውም ሆነ እኛም አጥብቀን እንደምናምነው፣ ይህ ዓይነቱ ኢ-ሥነምግባራዊ እና ሕገ ወጥ ተግባር የትኛውንም የሃይማኖት ተቋም የማይወክል፣ ይልቁንም የሚወገዝ፣ ውጉዝ ከመአሪዎስ ሊባል የሚገባው ተግባር ነው። በጉባኤው “አንዳንድ ወንድሞችና እህቶች የግለሰቡን ሕገ-ወጥ ተግባር ተቋማዊ ለማድረግ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ መለስ ብለው እንዲያጤኑትና ግለሰብንና ተቋምን እንዲለዩ” መገለፁም አግባብነትና ትክክለኛ ስለሆነ ሁላችንም ከእዚህ አቋም ጎን ልንቆም፤ የእኩይ ተግባሩን ሽፋን ግልጥልጥ አድርገን ማንነቱን ልናጋልጥ ግድ ይሆናል።
ይህ ድፍረት የተሞላበትና ፍፁም ኢትዮጵያዊ ያልሆነ ተግባር ከስሩ ይነቀል ዘንድ የሁሉም (እኔ ሃይማኖት የለኝም የሚል እንኳን ቢኖር) የተባበረ ጥረት ያስፈልጋልና የጥቂቶችን ጥቃት በጋራ መመከት ተገቢ ይሆናል። “ድርጊቱ የሚወገዝና በወንጀል የሚያስጠይቅ” መሆኑን የሕግ ባለሙያዎች እየተናገሩ ነውና በሕግ መጠየቅ ያለበት ይጠየቅ ዘንድ ግድ ይሆናል። የኢትዮጵያ ሕዝብ በብልህነቱ ዓለም ያውቀዋል፤ ስለ አስተዋይነቱ ምስክርነት የተሰጠው ሕዝብ ነው። በመሆኑም፣ ሁሌም በእዚህ መለያው መቀጠል እንጂ የተለያዩ ነገሮችን ሽፋን እያደረጉ፤ ብሔር ከረጢት ውስጥ እየተወሸቁ ወዘተ ሊያጫርሱት ለሚፈልጉ እድል ሊሰጣቸው አይገባም። ለሕግ አሳልፎ መስጠት ግን የግድ ይሆናል።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 6 ቀን 2017 ዓ.ም