
ፑቲን ከዩክሬን ጋር ለሚደረግ የተኩስ አቁም ከበድ ያሉ ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀመጡ፡፡የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከዩክሬን ጋር እንዲደረስ የታቀደውን የተኩስ አቁም ሃሳብ እንደሚስማሙበት ቢገልጹም፤ በርካታ “ጥያቄዎች” የጫሩ ከባድ ቅድመ ሁኔታዎችን ማስቀመጣቸው ተገልጿል።
የሩሲያው ፕሬዚዳንት በጉዳዩ ዙሪያ ምላሽ የሰጡት በእዚህ ሳምንት መጀመሪያ ዩክሬን ከአሜሪካ ጋር ባደረገችው ውይይት የቀረበውን የ30 ቀናት የተኩስ አቁም ዕቅድ መቀበሏን ተከትሎ ነው። የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ በዕቅዱ ዙሪያ ፑቲን የሰጡትን ምላሽ “የማይጨበጥ” ከማለት ባለፈ በሩሲያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ እንዲጣል ጠይቀዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አሜሪካ በሩሲያ የነዳጅ፣ የጋዝ እና የባንክ ዘርፎች ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ ጥላለች።ፑቲን ሐሙስ ዕለት በሞስኮ በተካሄደ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተኩስ አቁም ሃሳቡን “ትክክለኛ ሲሆን እኛም እንደግፈዋለን። ነገር ግን ልንወያይባቸው የሚገቡ ጥያቄዎች አሉ” ብለዋል።
የተኩስ አቁም ስምምነቱ ወደ ዘላቂ ሰላም ሊያመራ እና የእዚህን ቀውስ መንስኤ ማስወገድ ሊኖርበት ይገባል ብለዋል ፑቲን።“ከአሜሪካውያን አጋሮቻችን ጋር መደራደር አለብን። ምናልባትም ወደ ዶናልድ ትራምፕ ስልክ እደውላለሁ” ሲሉ ገልጸዋል።
“ለዩክሬን ወገን ለ30 ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት መደረጉ ጥሩ ነው” ሲሉ ፑቲን አክለዋል።“እኛ ብንደግፈውም ግን ልዩነቶች አሉን።” ብለዋል።ዩክሬን ባለፈው ዓመት ወታደራዊ ዘመቻ በማድረግ የተወሰነ አካባቢ የተቆጣጠረችበት የኩርስክ ግዛት አንደኛው ርዕሰ ጉዳይ መሆኑን ፑቲን ተናግረዋል።
ሩሲያ ኩርስክን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥራለች ከማለት ባለፈ በስፍራው ያሉት የዩክሬን ወታደሮች “ተቆራርጠዋል” ብለዋል።“ለመውጣት እየሞከሩ ቢሆንም እኛ ግን ተቆጣጥረናል። መሣሪያቸውን በየቦታው ጥለዋል።” “ኩርስክ ውስጥ ለዩክሬናውያን ሁለት አማራጮች ብቻ አሉ፤ እጅ መስጠት ወይም መሞት” ሲሉ ገልጸዋል።
ፑቲን የተኩስ አቁም እንዴት እንደሚሠራ የቀረቡ አንዳንድ ጥያቄዎችን ሲገልጹም “እነዚያ 30 ቀናት እንዴት ጥቅም ላይ ይውላሉ? ዩክሬን እንድትደራጅ ነው? እንድታጠቃ ነው? ሰዎችን ለማሠልጠን ነው? ወይስ እነዚህ ነገሮች አይሆኑም? እንዴትስ ቁጥጥር ይደረግበታል?” ሲሉ ጠይቀዋል።
“ትግሉ እንዲቆም ማነው ትዕዛዙን የሚሰጠው? ምን ዋጋስ ያስከፍላል? ከሁለት ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ በሚሆን ስፍራ ማን የተኩስ አቁሙን እንዳፈረሰ ማን ነው የሚወስነው? እነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች ከሁለቱም ወገን ጥንቃቄ የተሞላበት ሥራ ይጠይቃሉ። ማንስ ይቆጣጠረዋል?” ሲሉ በርካታ ጥያቄዎችን ወርውረዋል።
ፑቲን “በቀጥታ አልቀበለውም አላለም” ነገር ግን “በተግባር ውድቅ ለማድረግ እያዘጋጀ ነው” ሲሉ ዘለንስኪ በምሽት በሚያስተላልፉት የቪዲዮ መልዕክታቸው ላይ ተናግረዋል።“ፑቲን በእርግጥ ይህን ጦርነት መቀጠል እና ዩክሬናውያንን መግደል እንደሚፈልግ በቀጥታ ለፕሬዚዳንት ትራምፕ ለመናገር ይፈራል።” ሲሉ ዜሌንስኪ ተችተዋል።የሩሲያው መሪ ብዙ “ምንም የማይሠራ” በርካታ ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጠዋል ሲሉ ዜለንስኪ ተናግረዋል።
ከፑቲን አስተያየት እና ከዜለንስኪ ምላሽ በኋላ በሁለቱም ወገኖች አቋም መካከል ግልጽ የሆነ መለያየት መኖሩ ታይቷል። ዩክሬን ባለ ሁለት ሂደት እንዲኖር ትፈልጋለች፤ አስቸኳይ የተኩስ አቁም እና ቀጥሎም የረጅም ጊዜ እልባት እንዲኖር።
ሩሲያ በበኩሏ ሁለቱን ሂደቶች መለየት እንደማትችል ከመግለጽ ባለፈ ሁሉንም ጉዳዮች በአንድ ስምምነት ውስጥ መወሰን አለባቸው የሚል አቋም አላት። ሁለቱም ወገኖች አቋማቸውን ለማንጸባረቅ የቆረጡ ይመስላሉ።
ሩሲያን ለሰላም ጥሪው እምቢተኛ እንደሆነች አድርጋ በማቅረብ ዩክሬን በሩሲያ ላይ ጫና እንደምትፈጥር ታምናለች። ሩሲያ በበኩሏ ስለኔቶ መስፋፋት እና ስለዩክሬን ሉዓላዊነት ያሏትን መሠረታዊ ስጋቶቿን ለማቅረብ አሁን ዕድል እንዳላት ታምናለች።
ይህ ደግሞ ለዶናልድ ትራምፕ ችግር ይፈጥራል። አፋጣኝ ውጤት እንደሚፈልጉ ግልጽ በማድረግ ጦርነቱን በቀናት ውስጥ ለማቆም ቃል ገብተዋል።
የፑቲንን አስተያየት ተከትሎ በዋይት ሃውስ ንግግር ያደረጉት ፕሬዚዳንት ትራምፕ በበኩላቸው፤ ከሩሲያው መሪ ጋር ለመገናኘት “እንደሚፈልጉ” እና ለ30 ቀናት የሰላም ስምምነቱ ሩሲያ “ትክክለኛውን ነገር ታደርጋለች” የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።“ ከሩሲያ የተኩስ አቁምን ማየት እንፈልጋለን” ብለዋል።
ቀደም ብለው ከኔቶ ዋና ጸሐፊ ማርክ ሩት ጋር በኦቫል ኦፊስ ባደረጉት ስብሰባ ላይ ቀደም ሲል ከዩክሬን ጋር በዝርዝር ጉዳዮች መወያየታቸውን ትራምፕ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።“ከዩክሬን ግዛት ስለሚጠበቁ እና ስለሚነጠቁት እንዲሁም ደግሞ ስለሌሎች የመጨረሻ ስምምነት ጉዳዮች እየተነጋገርን ነበር” ብለዋል።
“የመጨረሻ ስምምነት ብዙ ዝርዝሮች ጉዳዮች ላይ ውይይት ተደርጓል።” ዩክሬን ኔቶ ስለሚቀላቀልበት ጉዳይ ትራምፕ በሰጡት አስተያየት “መልሱ ምን እንደሆነ ሁሉም ሰው ያውቀዋል” ብለዋል።
በሩሲያ ነዳጅ እና ጋዝ ላይ የተጣለው አዲስ ማዕቀብ የትራምፕ አስተዳደር የአሜሪካን የክፍያ ሥርዓት የበለጠ በመገደብ ለሌሎች ሀገራት የሩሲያን ነዳጅ መግዛት አስቸጋሪ እንዲሆንባቸው አድርገዋል።
በሌላ በኩል ፑቲን ከአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ ጋር በሞስኮ በዝግ መክረዋል።ቀደም ብሎ የክሬምሊን ረዳት ዩሪ ኡሻኮቭ በአሜሪካ የቀረበውን የተኩስ አቁም ሃሳብ ውድቅ አድርገውታል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 6 ቀን 2017 ዓ.ም