ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የሴት አመራሮችን ቁጥር ለማሳደግ እየሠራ ነው

ድሬዳዋ ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የሴት አመራሮችን ቁጥር ለማሳደግ በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ አስታወቀ።

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዑባ አደም (ዶ/ር ) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ ዩኒቨርሲቲው ሴቶች በአመራርነት ደረጃ ያላቸው ተሳትፎ ከፍ እንዲል በርካታ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል።

በዩኒቨርሲቲው በመጀመሪያ ደረጃ አመራር ቦታ ላይ ለሚወዳደሩ ሴቶች በአወንታዊ ድጋፍ (አፈርማቲቭ አክሽን) 10 በመቶ ነጥብ እንደሚጨምርላቸው የጠቆሙት ፕሬዚዳንቷ፤ መካከለኛ አመራር ለመሆን ለሚወዳደሩ ሴቶች ሰባት ነጥብ አምስት በመቶ አወንታዊ ድጋፍ ይጨመርላቸዋል፡፡ከእዚህ አኳያ አንድ ሴት ለአመራርነት ከተወዳደረች ቦታውን የማግኘት ዕድሏ በጣም ሰፊ ይሆናል ብለዋል።

የሲቪል ሰርቪስ አዋጅ ላይ የተቀመጠው አወንታዊ ድጋፍ ሦስት በመቶ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሴቶች በየደረጃው በአመራር ደረጃ እንዲሳተፉ ለማበረታታት የበለጠ ድጋፍ ለማድረግ መወሰናቸውን ገልጸዋል።

በዩኒቨርሲቲያችን በአመራር ደረጃ ያለው የሴቶች ተሳትፎ 23 በመቶ ደርሷል ያሉት ፕሬዚዳንቷ፤ ከተቻለ ይህን ቁጥር ወደ ሃምሳ በመቶ ለማሳደግ ነው ጥረት የምናደርገው።የእኛ ዩኒቨርሲቲ በሴት የሚመራ ተቋም ስለሆነ ትንሽ ለየት ባለ ሁኔታ ሴቶችን ማብቃት ላይ አተኩረናል ብለዋል።

እንደ ዑባ (ዶ/ር )ገለጻ፤ በዩኒቨርሲቲው የሴት መምህራን ቁጥር 16 በመቶ ነው።በምርምር ዙሪያና በሌሎችም ዘርፎች ሴቶች የሚያደርጉት ተሳትፎም ዝቅተኛ ነው።ሁኔታውን ለመለወጥ በአጠቃላይ የሴቶች ተሳትፎን ከማጉላት አንጻር ሴቶች በአመራርነት፣ በምርምር እና ዩኒቨርሲቲው በሚሠራቸው በሁሉም ሥራዎች ውስጥ እንዲሳተፉ ከፍተኛ ድጋፍ ይደረግላቸዋል፡፡

አወንታዊ ድጋፍ የሚባለው ነገር ሁሉም ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ቢሆንም፤ አንዳንድ ጊዜ እንደሚረሳ ገልጸው፤ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በየትኛውም ቦታ ላይ ጨርሶ የማይታለፍ ትልት አጀንዳ መሆኑን ተናግረዋል።

አያይዘውም በሴቶች የአመራርነት ተሳትፎ አሁን በሀገራችን ብዙ ለውጦች አሉ።ከፓርላማ ጀምሮ በካቢኔ ደረጃ በርካታ ለውጦች ተደርገዋል።እነዚህን ማጠናከር አለብን።በሁሉም ነገር ብንመለከታቸው ሴቶች ነገሮችን በጥንቃቄ ከመሥራት አንጻር የተሻለ ቁርጠኝነት አላቸው።የማህበረሰቡ ግማሽ አካል ስለሆኑ ያለሴቶች ተሳትፎ የምንፈልገውን ነገር ማሳካት አንችልም።በየትኛውም ቦታ ላይ አሁን ካለው በተሻለ መንገድ መደገፍ አለባቸው ብለዋል።

ሴቶች ወደ ኃላፊነት ቦታ መምጣት ያለባቸው እንዲሁ ዝም ብሎ ሳይሆን በቂ የሆነ የአቅም ግንባታ ሥልጠና ተሰጥቷቸው አብቅተናቸው መሆን አለበት ሲሉ ያሳሰቡት ፕሬዚዳንቷ፤ ሴቶችን ካበቃናቸው ተፈጥሮ ከለገሳቸው ጥንካሬ ጋር ተዳምሮ ምንም ነገር ያስቸግራቸዋል የሚል እምነት እንደሌላቸው ገልጸዋል።

ተስፋ ፈሩ

አዲስ ዘመን መጋቢት 6 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You