ትውልዱ ዘመኑን የሚዋጅ የፖለቲካ ስብዕና መፍጠር ይጠበቅበታል!

በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ ያሉ ፖለቲከኞች እና ከእነርሱ የሚመነጨው የፖለቲካ እሳቤ በአንድም ይሁን በሌላ በማኅበረሰቡ ፍላጎት ላይ የተመሠረተ ፣ ለፍላጎቱም የተገዛ ሊሆን ይገባል። በተለይም ባለንበት ዘመን ካለው አጠቃላይ የማኅበረሰብ ንቃተ ሕሊና አኳያ ፤ለሕዝብ ፍላጎቶች ተገቢውን ትኩረት መስጠት የፖለቲካ “ሀ ሁ” ከሆነ ውሎ ሰንብቷል።

ለሕዝብ ፍላጎት ባዕድ በመሆን የራስን ፍላጎት በሕዝብ ላይ በመጫን የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚደረጉ ጥረቶች ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው እንደሚያመዝን የአደባባይ ምስጢር ነው። በተለይም ሰላም እና ልማት የሕልውና ያህል ጥያቄ በሆነባቸው ማህበረሰቦች ውስጥ እነዚህን የሕዝብ ጥያቄዎች ሰምቶ እንዳልሰማ መሆን ሊያስከፍል የሚችለው ያልተገባ ዋጋ ከግምት ያለፈ ነው።

በእርግጥ የሰላም እና የልማት ጥያቄ የተወሰነ ማህበረሰብ ብቻ ሳይሆን የሰው ልጆች ቀዳሚ መሻት ነው። ይህ መሻቱ የመነጨው የሰላም እጦት ፣ ድህነት እና ኋላቀርነት ካስከፈሉት እና እያስከፈለው ካለው መልከ ብዙ ፣ መጠነ ሰፊ ያልተገባ ዋጋ አንጻር ነው። ከእዚህ ባለፈም ይህንን መሸከም የሚያስችል ሰብዓዊ ማንነት ስለሌለው ነው።

ባለንበት ዘመን የሰው ልጅ አስተሳሰብ በዘመናት መካከል በተፈጠሩ ክስተቶች እና ክስተቶቹ በፈጠሯቸው መልካም አጋጣሚዎች በብዙ መገራት ችሏል፡፡ ከእዚህ የተነሳም ዘመኑ ከየትኛውም ጊዜ ይልቅ ለሰላም እና ለልማት ትልቅ ትኩረት እየሰጠ ይገኛል። ከእዚህም ባለፈ ሰላም እና ልማት ለአንድ ማህበረሰብ እና ሀገር ብቻ ሳይሆን እያደገ ለመጣው የሰው ልጆች ፍላጎት መሟላት ዋነኛ ጉዳይ ከሆኑ ውለው አድረዋል።

በተለይም በማደግ ላይ ያሉም ሆኑ “ዝቅተኛ የዕድገት ደረጃ ላይ የሚገኙ ” በሚባሉ ሀገራት ውስጥ የሚኖሩ ሕዝቦች ካሉበት አስከፊ ሕይወት ለመውጣት ለሚያደርጓቸው ጥረቶች ስኬት ሰላም እና ልማት የሚኖራቸው ፋይዳ ከግምት ያለፈ ነው። እነዚህ ሀገራት ያላቸውን አቅም አሟጥጠው ወደ ልማት መግባት ካልቻሉ አሁን ያለው ትውልድ ብቻ ሳይሆን የመጪ ትውልዶች እጣ ፈንታ በስጋት የተሞላ ሊሆን እንደሚችል ለመገመት አይከብድም።

በተለያዩ ፍላጎቶች እየተናጠች ባለችው ዓለማችን፤ ከድህነት እና ከኋላቀርነት ለመውጣት የሚደረግ የሕዝቦች ትግል የቱን ያህል በመልከ ብዙ ችግሮች እንደሚፈተን በዕለት ተዕለት ሕይወታችን የምናስተውለው ነው። በተለይ ከሰላም እጦት ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ ፈተናዎች የቱን ያህል መራር ዋጋ እንደሚያስከፍሉም በተጨባጭ የሚታይ ነው።

ለእዚህ ደግሞ እኛ ኢትዮጵያውያን ከትናንት እስከ ዛሬ ያለው ታሪካችን ከምንም በላይ ሊነግረን የሚችል ነው ። እንደ ሀገር ከድህነት እና ከኋላቀርነት ለመውጣት ያደረግናቸውን ጥረቶች ተከትለው ያጋጠሙን የሰላም እጦቶች የቱን ያህል ዋጋ እንዳስከፈሉን እናውቃለን። የነበረንን በብዙ የመለወጥ መሻት አክስመው ለከፉ ዛሬዎች እንደዳረጉን ነጋሪ የሚያስፈልገን አይደለም።

የለውጥ መሻታችንን ተከትለው የሚመጡ አለመደማመጦች፤ ከእዚያም አልፎ የሕዝቡን የለውጥ መሻት ለግል እና ለቡድን ፍላጎቶች ለማዋል የተደረጉ ያልተገቡ ሙከራዎች በዘመናት መካከል በግጭት አዙሪት ውስጥ እንድንዳክር አድርገውናል። በብዙ ከምንጠየፈው ድህነት እና ኋላቀርነት ጋር አብረን እንድንኖርም አስገድደውናል።

ብዙ ሕልመኛ ትውልዶችን እስከ ሕልማቸው ቀብረን እንድንቆዝም፤ ከእዚያም አልፈን በግጭት ታሪክ ድባቴ ውስጥ እንድንኖር አድርገውናል። ከትናንት በአግባቡ መማር ባለመቻላችን ዛሬም በተመሳሳይ የግጭት አዙሪት ውስጥ ለማለፍ ተገደናል። ከሁሉም የከፋው ደግሞ ከትናንት አለመማራችን ብቻ ሳይሆን፤ ሕዝባችን አብዝቶ በሚሻው ሰላም እና ልማት ላይ በአደባባይ ጠላት ሆነው በተነሱ ራስ ወዳድ ፖለቲከኞች ምክንያት ከእዚህ የግጭት አዙሪት መውጣት አለመቻላችን ነው ።

እነዚህ ኃይሎች ሕዝባችን በአደባባይ ስለ ሰላም እና ልማት ድምጹን ከፍ አድርጎ እየጮኸ ፤ ጦርነት በቃን እስከ ዛሬ ለጦርነት የከፈልነው ዋጋ ትናንታችንን ከማስወሰድ ፣ ዛሬያችንን ከማጨለም፣ ነገዎቻችንን ተስፋ አልባ ከማድረግ ባለፈ ምንም አልጠቀመንም እያሉ ባለበት ወቅት፤ ጦርነትን የሥልጣን መቆመሪያ ካርድ አድርገው እየወሰዱ ነው፡፡ ተስፈኛ በሆነው ትውልድ የደም ግብር ያልተገባ የሥልጣን መሻታቸውን እውን ለማድረግ ባልተገባ ድፍረት እየተንቀሳቀሱ ነው።

መላው ሕዝባችን በተለይም ወጣቱ ትውልድ የእነዚህ ኃይሎች መቆመሪያ ካርድ እንዳይሆን ራሱን ከየትኛውም የጥፋት መንገድ መቆጠብ ይኖርበታል። ሀገር እና ሕዝብን አክሳሪ የሚያደርግ የፖለቲካ አስተሳሰብ ሰለባ እንዳይሆን፤ በእዚህም ተስፋ እና ሕልሙን እንዳያጣ ከእራሱ ጋር ሊመክር ፤ለእዚህ የሚሆን ዘመኑን የሚዋጅ የፖለቲካ ስብዕና መፍጠር ይጠበቅበታል!

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 6 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You