
የአስተዳደግ ማንነቷ እንደ ማንኛውም ልጅ የሚወሳ ነው። እንደ እኩዮቿ በሰፈሯ ቦርቃ ተጫውታለች። እንደ ልጅ ለእናት ለአባቷ በወጉ ታዛለች። ዕድሜዋ ሲደርስ ደግሞ ደብተር ይዛ ትምህርት ቤት ገብታ ነበር። ደብረ ማርቆስ ‹‹አብማ ማርያም›› ላይ ብዙ ትዝታዎች አሏት። ያደገችበትን የ‹‹ድብዛ››መንደር ዙሪያም ዘንግታው አታውቅም፡፡
ዛሬ ኑሮና ሕይወት አርቆ ቢነጥላትም ልጅነቷ ውል ባላት ጊዜ የኋሊት በትዝታ ትጓዛለች። ንግስት ደባሱ የኖረችበት ዕድሜ በብዙ የፈተናዎች ጥግ አመላልሷታል። ክፉ ደግ ባየችበት የሕይወት ጉዞም ዕንባና ሳቅ፣ ደስታና መከራ ጓዶኞቿ ነበሩ። በዚህ ሁሉ መሀል ትናንት አልፎ ዛሬ መተካቱ ደግሞ የምስጋናዋ ምክንያት ሆኗል። ሁሌም ፈጣሪዋን የምታስበው የሚገባውን ክብር አብዝታ በመስጠት ነው፡፡
እሷ የሕይወት መንገዷ በተለየ አቅጣጫ ሲራመድ ቆይቷል። በርካታ ሴቶች ሊደፍሩት በማይቻላቸው የሙያ ግዴታ ተሰልፋ ማንነቷን አስመስክራለች። እውነታው ጥሎባት ያለፈው ጠባሳ ግን ለእሷ የክፉ ቀን ምልክት ብቻ አይደለም። ውስጧ ሁሌም ስለ ሀገርና ወገን ሲባል ያኖረችው ደማቅ ዐሻራ መሆኑን ይነግራታል፡፡
1984 ዓ.ም ደብረማርቆስ
ይህ ጊዜ በሀገሪቱ አዲስ የለውጥ ምዕራፍ የተከሰተበት፣ መንግሥት በመንግሥት የተተካበት ነበር። በወቅቱ የሥራ ፈላጊውን ያህል፣ ከሥራው የሚፈናቀለው፣ ከነበረበት ርቆ የሚሰደደው ጥቂት አልነበረም። በዚህ ፈታኝ ጊዜ ላይ የቆመችው ንግስትም ራሷን የምትችልበት አማራጭ መፈለግ ይዛለች። የዛኔ ዕድሜዋ መሥራትና መሮጥ የሚያስችላት አፍላ ጊዜ ላይ ነበር። ይህ ብርታት ደግሞ ከማንም ባላነሰ በልዩ ሞራል ተገንብቷል።
ሥራ ፈላጊዋ ንግስት በአንድ አጋጣሚ የሰማችው እውነት ሙያዋ ሆኖ ይዘልቅ ዘንድ ከውሳኔ አደረሳት። በወቅቱ የሀገር መከላከያ ወታደሮችን ለማሰልጠን በምልመላ ላይ ነበር። ወጣቷ ንግስት ስለጉዳዩ ደጋግማ ማዳመጥ አላሻትም። ተገቢውን ሁሉ አሟልታ በአጭር ጊዜ ከወታደሮች ማሰልጠኛ ግቢ ተገኘች፡፡
ውትድርና በባህሪይው ፈታኝ የሚባል ነው። ‹‹ወታደር›› ተብሎ በብቃት ለመቆም በሥርዓት የታነጸ በቂ ሥልጠና ያስፈልጋል። ይህ ሥልጠና በዋዛ የሚያልፉት፣ በቀላሉ የሚሻገሩት አይደለም። ወታደራዊ ሥልጠና ማለት በውስጡ የሀገርን ጉዳይ ያዝላል። የወገንን ኃላፊነት ይሸከማል። እያንዳንዱ ሰልጣኝ ወታደርም ይህን እውነታ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡
አሁን ንግስት ምልምል ወታደር ሆና ከማሰልጠኛ ገብታለች። በስፍራው እንደ ሴትነቷ ብዙ ጉዳዮች ይፈትኗታል። እሷ ግን በዋዛ እጅ አልሰጠችም። ከወንዶች እኩል ወታደራዊ ጓዟን ተሸክማ ተራራውን ወጥታ ትወርዳለች። ጠዋት ማታ ራሷን አካል በሚፈትን፣ ሰውነትን በሚያዝል ከባድ ስፖርት መሀል ታገኘዋለች፡፡
ጊዚያት የፈጀው ሥልጠና እንዳበቃ ንግስት ሙሉ ወታደር ሆና በክብር ምርቃት ግቢውን ለቀቀች። ከእርሷ ጋር ሥልጠናውን የተጋሩ ባልንጀሮቿ ዛሬም አብረዋት ናቸው። ከዚህ በኋላ ሀገር ከእሷ የምትጠብቀውን ግዴታና ኃላፊነት ለመቀበል ዝግጁ ሆናለች። ንግስት ወታደር ከሆነች በኋላ ስለ ሀገሯ ያላት ጥልቅ ፍቅር ጨመረ። ጠዋት ማታ ለወገኗ ክብር ማሰብ፣ መጨነቅ ልምዷ ሆነ። ይህን ዕውነት ይዛ በምትሰማራበት የግዳጅ ውሎ ሁሉ ወታደር የመሆኗ ሀቅ በተግባር ይመሰከር ያዘ፡፡
ውትድርና …
በውትድርና ዓለም ስለነገ ይሉት ዕቅድ የለም። ሁሌም ዛሬን መኖር፣ አሁንን ብቻ ማሰብ አይቀሬው ልማድ ነው። መቼውኑም የጠዋቱ ሰላም ለረፋድ ውሎ ዋስትና ሆኖ አያውቅም። ምሽቱን በቸር ማጋመስም ለለሊቱ አዳር እፎይታ አይሰጥም። በዚህ ቦታ የማንነት ዓላማ የሚቃኘው በሀገር ፍቅርና በጋለ ወታደራዊ ስሜት ነው፡፡
ንግስት ወታደር ሆና መሳሪያ ካነገተች ወዲህ ሕይወቷ በነዚህ እውነታዎች ተቃኝቷል። ሁሌም ቢሆን የምትኖረው ዛሬን ብቻ እንደሆነ ታስባለች። ነገን አሻግራ ለማየት የቆመችበት ሀቅ አርቋት አያውቅም። በዋለችባቸው አውድ ውጊያዎች በርካታ ጓዶቿን ከጎኗ አጥታለች። ትናንት አጋር የሆኗት፣ ድምጻቸውን ሰምታ በእኩል ያወጋች ያጫወተቻቸው በጦርነት ክፉ አጋጣሚ ተነጥቃቸዋለች፡፡
እንዲህ መሆኑ እሷን መሰል ወታደሮች ዛሬን ብቻ በድል ተራምደው እንዲያልፉ አስገድዷቸዋል። አዎ! ዛሬን በሰላም ካደሩ ለነገ ዓለም ይተርፋሉ። ዛሬን ያለ ችግር ከተሻገሩ ‹‹ነበር››ን በነበር ያወሳሉ፡፡
ንግስት በውትድርና ዘመኗ ስለንብረት ማፍራትና ገንዘብ መያዝ አስባ አታውቅም። ልክ እንደሌሎቹ ዛሬን በሰላም ማለፏ ብቻ የሕይወቷ ትርፍና ሽልማት አድርጋ ተቀብላዋለች። አሁን ንግስት ቆፍጣና ወታደር ነች። በተገኘችበት የግዳጅ ውሎ ኃላፊነቷን በብቃት ልትወጣ ዝግጁ ነች፡፡
ትዳር …
ወታደሯ ንግስት ከሥልጠናዋ ማግስት አብሯት ከነበረ አንድ ሰው ጋር ህጋዊ ጋብቻ ፈጸመች። ይህ ሰው እንደ እሷ ቆፍጣና ወታደር ነው። በብዙ ውጣ ወረዶች አልፏል። በጠነከረ የትግል ጉዞም እንደ ወርቅ ተፈትኗል። በሁለቱም ልቦና ውሎ ያደረው ፍቅር በቁም ነገር መታሰሩ አልቀረም። ነገ ሀገር በሰላም ውሎ ሲያድር ሕይወት በአማን ሲቃኝ ቤት ጎጆ የመቀለስ ህልማቸው ዕውን ይሆናል፡፡
ሁለቱም በሕይወት ካሉ ሕይወትን በአዲስ መልክ ይቀበላሉ። ምናልባት ጦርነት ይሉት መቅሰፍት በሞት ቢለያቸው አንዳቸው ለሌላቸው የልብ ማስታወሻ ይሆናሉ። ይህ የማይፋቅ እውነት የማንኛውም ወታደር የሕይወት ተሞክሮ ነው። ሕይወት በወታደር ቤት በዚህ መልኩ ሊቃኝ ግድ ይላል፡፡
ጦርነቱ …
1992 ዓ.ም። የኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት ተቀስቅሷል። ሁሉም ስለእናት ሀገሩ ዳር ድንበር መደፈር ከልቡ እየተቆጨ ነው። ይህ ቁጭት በርካቶችን በሞራል አንቀሳቅሶ ወደ ጦር ሜዳ ማዝመት ጀምሯል። ዕለት በዕለት የሚሰማው ደማቅ ድል በየአፍታው አዲስ ብስራት እየደረበ ዜናውን አድምቆታል። ይህ እውነት በተለይ በጦርሜዳ ለተሰለፉ ወታደሮች ትርጉሙ ይለያል፡፡
ከቀናት በአንዱ ደግሞ እነ ንግስት በተሰለፉበት የጦር ሜዳ ግንባር ጦርነቱ አይሎ ተሰማ። በድንገትም እንዲህ ሆነ። ንግስትና የትግል ጓዶቿ ‹‹ዓዲኣላ›› ከተባለችው የትግራይ ድንበር ከጠላት ኃይል ጋር ሲዋጉ ዋሉ። ጦርነቱ ፋታ የማይሰጥና ወታደራዊ ስልትን የሚጠይቅ ነበር፡፡
ሁለቱም ወገኖች በልዩ ብርታት ራሳቸውን ለመከላከል ይታኮሳሉ። ሽፋን እየሰጡ፣ ኃይል እያከሉ ያጠቃሉ። በርካቶች የሕይወት መስዋዕትነት እየከፈሉ ነው። በክብር የወደቁት ዛሬን ኖረው አልፈዋል፡። ‹‹ዓዲኣላ›› በከባድ ጦር መሳሪያ መናወጥ ይዛለች። ደረቁ አፈር ስፍራውን በቀይ አቧራ ሸፍኖታል። እዚህም እዚያም የሚሰማው የጣር ድምጽ አይሏል፡፡
ከቁስለኞች መሀል …
አሁን ምድር አዝና ተከፍታለች። በደምና አጥንት፣ በሕይወት መስዋዕትነት የተከፈለው ዋጋም ዕለቱን አክብዶት ውሏል። ጦርነቱ ጋብ እንዳለ የተጎዱት ወታደሮች ከሞቱት ተለይተው ታወቁ። ከነዚህ ጉዳተኞች መሀል ንግስት ደባሱ አንዷ ነበረች። ግራ እግሯን ተመታ ቆስላለች፡፡
ቁስለኞች ተለይተው ወደ ሕክምና ሲላኩ ንግስት ወደ ጎንደር ሆስፒታል የመሄድ ዕድል አገኘች። በስፍራው ተኝታ ሕክምና እያገኘች ቆየች። ብዙ አልቆየችም። የነበረችበት ጉዳት በሠራዊቱ የሚያዘልቃት አልሆነም። ስለጉዳቷ፣ ስለሀገሯ ስለከፈለችው መስዋዕትነት በክብር መሰናበት ነበረባት፡፡
ሁሉም ጉዳይ በሂደት ተጠናቀቀ። ንግስት ደንብና ሕጉ በሚፈቅደው አግባብ ከመከላከያ ሠራዊት በቦርድ ስንብት ለቀቀች። አስራ አንድ ዓመታት ያገለገለችበትን ሠራዊት ለቃ ስትሰናበት ለውድ ሀገሯ ያበረከተችው ድርሻ ኩራቷ ነበር። በእሷ መቁሰልና መድማት የተመዘገበው ድልም የታሪኳ ደማቅ ዐሻራ ሆኖ ተመዝግቧል።
አሁን ንግስት ወታደር አይደለችም። የቤት እመቤት ወይዘሮ ልትሆን ግድ ብሏል። ቀድሞ ወደነበረችበት የክፍለ ጦር ዕዝ አመራች። ባለቤቷም ጦሩ ከሰፈረበት ስፍራ ላይ ይገኛል። ወደ ዝዋይ ስትመጣ አባወራዋ በክብር ተቀበላት። ሁለቱም ጥንዶች በሕይወት አሉ። አሁን የጋራ ጎጇቸውን የሚያጸኑበት ጊዜው ደርሷል። ባልና ሚስቱ በአንድ ቤት መኖር ጀመሩ። ወይዘሮዋ ትናንትን ረስታ ‹‹ቤቴን፣ ትዳሬን›› ማለት ያዘች። ወታደሩ ባሏ ስለ ሀገር ግዳጁን መወጣት ቀጠለ፡፡
ነበርን በነበር …
አሁን ንግስት እንደ ትናንቱ አይደለችም። ሕይወትን ስለ ‹‹ዛሬ ብቻ›› አትልም። ስለነገም አርቃ ታስባለች። ቀድሞ ተስፋ የሚያስቆርጣት፣ የምትተክዝበት ሀቅ አሁን በውስጧ የለም። ይህ እውነት ከትዳሯ ማግስት ልጆች ወልዳ እንድታቅፍ ምክንያት ሆኗል። ቤት ሰርታ በወጉ እንድትኖር ሰበብ ፈጥሯል፡፡
ወይዘሮዋ ትናንት የሆነውን ስታስብ ለፈጣሪዋ ምስጋናዋ ይለያል። ዛሬ በሕይወት መኖሯ መልካም ሆኖ ብዙ አይታለች። ቀድሞ ከእሷ ጋር በግንባር የተሰለፉ ጓደኞቿ ሞተው ተረስተዋል። ጥቂት የማይባሉትም ከአካል ጉዳት ጋር ኑሮን እየገፉ ነው። የጦርነት ክፋት ብዙ ነው። ከሰላም ያጣላል፣ ከዓላማ ያስታል፡፡
ሕይወት ከጦር ሜዳ ማግስት ለንግስት መልካም ሆኗል። በሰላም፣ በእፎይታ በትዳሯ እየኖረች ልጆች ታሳድጋለች። ያቋረጠችውን ትምህርት የመቀጠል ፍላጎት ቢኖራትም ቅድሚያውን ለልጆቿ ሰጥታለች። የእነሱ መማር ለእሷ ክብር ነው። ሁሉንም በክብር ቁምነገር ማድረስ ዓላማዋ ሆኗል። 2000 ሚሊኒየም ደግሞ ለወይዘሮ ንግስት አዲስ ዕድልን ይዞ ደረሰ። በዝዋይ ከተማና አካባቢው የተቋቋመው የአበባ እርሻ ልማት በያዘችው ልምድና አገልግሎት በወር ደመወዝ ሊቀጥራት ፈቀደ፡፡
ንግስት ሌላው አዲስ የሕይወት ምዕራፍ መከፈቱ በገባት ጊዜ ዳግም ፈጣሪዋን አመሰገነች። በዝዋይ ሮዝስ ካምፓኒ በጥበቃ ሙያ ተቀጥራ ሥራ ስትጀምር የወታደር ማንነቷን እንደተላበሰች ነበር። ዛሬ ሕይወት በሌላ መንገድ ላይ አቁሟታል። እንዲያም ሆኖ ያለፈችበት መስመር ሙያዋን በወጉ ለመወጣት የሚያግዛት ሆኗል።
እንደ ወታደር …
ይህ ሥፍራ የጦር ሜዳ ግዴታ የለበትም። እሷ ግን ሁሌም በቦታው እንደ ወታደር ነች። ለሙያዋ የተለየ ፍቅር አላት። ዕለት በዕለት የምትቆምበትን ስፍራ እንደ ግንባር ግዳጅ ቆጥራ ኃላፊነቷን በብቃት ትወጣለች። በጦር ሜዳ ያገኛት የእግሯ ላይ ጉዳት ብርድ በሆነ ጊዜ ያስነክሳታል። እሷ ግን ለዚህ ስሜት ፊት አትሰጥም። ይህ እውነት የማንነቷ ምልክት፣ የግል ታሪኳ ማስታወሻ ነው። እንዲያም ሆኖ የእሷ ትኩረት ትናንትና ሆኖ አያውቅም። ዛሬ ላይ ቆማ ስለ ነገ ታስባለች፡፡
በካምፓኒው በቆየችባቸው አስራ ሰባት ዓመታት ብዙ የሕይወት ልምድ ቀስማለች። በተለይ ልጆቿን አሳድጋ ለማስተማር፣ ቤት ትዳሯን ለመምራት ተረጋግታ መኖሯ መልካም ሆኗል። ዛሬ ሁለት ወንድ ልጆቿ ከቁምነገር ደርሰዋል። የትናንቷ ምክትል የሃምሳ አለቃ ንግስት አሁንም ለቤትና ለሥራዋ ወታደር ነች፡፡
የመጀመሪያ ልጇ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቆ ራሱን ችሏል። ሁለተኛውም ባለው የዲዛይን ልምድና ችሎታ በኩባንያው የሠራተኞችን የደንብ ልብስ ሰፍቶ ያቀርባል። ወታደሩ ባለቤቷ ዛሬ በጡረታ ላይ ነው። እንዲያም ሆኖ ሥራን አልተወም። ቤት ጎጆውን ለመደገፍ በጥበቃ ሙያ ተሰማርቷል፡፡
ከደብረ ማርቆስ ዝዋይ የከተመችው ንግስት ያለችበትን ቦታ ከልብ ትወደዋለች። በድርጅቱ ጣራ ሥራ የሚገኙ ሴቶች ለእሷ ሁሌም እንደ ቤተሰብ ናቸው። በፍቅር ተሳስበው ያድራሉ። በክፉ ደግ ይጠያየቃሉ። ዛሬ ንግስት በበርካታ የሕይወት ውጣ ውረድ አልፋ ትናንትን በነበር የምታወጋበት ዘመን ላይ ደርሳለች። ከምንም በላይ ስለ ሰላም የምትሰጠው ግምት ይለያል፡፡
ይህ ሀቅ ለእሷ ከቃል በላይ ሆኖ ይተረጎማል። ንግስት የጦርነትና የሰላም ዋጋን በሚዛን አስቀምጣ መዝናዋለች። ጦርነት በእሷና በሌሎች ላይ ያሳረፈው ክፉ ጠባሳ አሁን ድረስ ቁስሉ ይሰማታል። በሰላም ቀን ደግሞ ያገኘችውን ታላቅ በረከት ከእሷ በላይ የሚናገር አይኖርም፡፡
ዛሬን…
ንግስት አሁን ትናንትናን አይደለችም። ነገን ስታስብ ፍጹም ደስታ ይሰማታል። ነገን ስታልም ህልሞቿ የተዋቡ የደመቁ ናቸው። ዛሬን በሕይወት ቆማ በሙሉ አካል ለሥራ መብቃቷም እንደ ሕይወት ሽልማት ትቆጥረዋለች። አረንጓዴው የሥራ ልብሷ በደማቆቹ ውብ አበቦች መሀል መታየቱ ለእሷ ውበቷ ነው፡፡
እነዚህ አበቦች ለእሷ ከውበትም በላይ ተስፋ ናቸው። ሕይወቷ ከእነሱ ይመስላል። በክፉ ቀን ክፉ አጋጣሚ ተቀንጥሳ አልቀረችም። በውሎዋ ባየች፣ ባሰበቻቸው ጊዜ ህብራዊ ድምቀታቸው ነገዋን ያሳምሩታል። በእነሱ መኖር ሕይወቷ ዳግም አብቧል። ማንነቷ በአዲስ ለምልሟል። የትናንቷ ወታደር የዛሬዋ ወይዘሮ ንግስት ደባሱ።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 6 ቀን 2017 ዓ.ም