ኢኮኖሚ ከዛሬ አርባና ሃምሳ አመት በፊት ልጅነታቸውን ያሳለፉ ሰዎች ትዝታቸውን ሲያወሩ ኮሽም፣ ሾላ፣ ዋንዛ፣ አጋምና ቀጋ ብቻ ከመንደራቸው ከሚገኝ ዛፍ ላይ አውርደው የሚበሉት የፍራፍሬ አይነት ዛሬም በምናባቸው ትውስ እንደሚላቸው በየጨዋታቸው ብቅ ያደርጉታል።
ለጥላ የሚውለው ዋርካም ለማረፊያ ብቻ ሳይሆን፣ የተጣላ ማስታረቂያ፣ የጓደኛሞችና የፍቅረኛሞች መቀጣጠሪያም ጭምር ነው ሲሉ ይደመጣሉ።የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው የተፈጥሮና በሰው የሚተከሉ የተለያየ ዝርያ ያላቸው የዛፍ አይነቶችም እንዲሁ ብዙ ናቸው።የደን ሀብታችን ‹ያልተዘመረለት› እንደሚባለው አይነት ነው፡፡
በአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን በደን ዘርፍ የኢንዱስትሪና ገበያ ልማት ዳይሬክተር ጀነራል ወይዘሮ አብረኸት ገብረህይወት እንደሚሉት የደን ሀብት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዳለው አልተነገረለትም።ትኩረትም አልተሰጠውም ባይ ናቸው።የደን ሀብት ለግንባታ፣ ለኢንዱስትሪና ለማገዶ አገልግሎት ይውላል።በተገባደደው በጀት አመት ለሀገር ውስጥ የማገዶ ፍጆታ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን፣ ለግንባታ ሁለት ነጥብ ሁለት ሜትሪክ ኩብ ጥቅም ላይ ውሏል።ይሄ በመረጃ የተገኘው ብቻ እንጂ ከዚህም በላይ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።የደን ሀብቱ በአብዛኛው ለሀገር ውስጥ ነው የሚውለው
ከተፈጥሮ ደን ከፍተኛ የእጣን ምርት ይገኛል።ለአብነት እንደጠቀሱት ለዕጣን የሚውል የደን ሀብት በኢትዮጵያ በሰሜን አካባቢ በስፋት የሚገኝ ሲሆን፣ ምርቱ ዛፉን በማድማት ነው የሚከናወነው።ምን ያህል ጊዜ መድማት እንዳለበትና አመታዊ የምርት መጠኑም ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ መከናወን ከቻለና በደን አስተዳደር ከተመራ ዘላቂ የሆነ ገቢ ማግኘት ይቻላል።ይሁን እንጂ ከመጠን በላይ በመመረቱና የእጣን ምርት በሚፈልገው ስህነምህዳር ባለመጠበቁ ችግኝ እየተተከለ እንኳን ማገገም አልቻለም።
የተፈጥሮ ሃብት የሆነው ቀርክሃም በዓለም ላይ እጅግ ተፈላጊና የዕንጨት ውጤቶችን የሚተካ ሲሆን፣ የምድር ውሃን በመጨመርና አፈርን በመጠበቅ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያለው ተክል ነው።የቀርከሃ ተክል በኦሮሚያ፣ ሀዊ ዞን፣ በቤንሻንጉልጉሙዝ እና በደቡብ ክልልሎች የሚገኝ ሲሆን፣ በቤንሻንጉልጉሙዝ ክልል ግን በስፋት ይገኛል።ቀርከሃ ተገቢው እንክብካቤ ካልተደረገለት ከተተከለ ከ50 አመታት በኃላ ይሞታል።ወይም ይጠፋል።ለጣውላ ምርት የሚውለው ደግሞ በኦሮሚያ፣ ደቡብ፣ አማራ ክልሎች በስፋት የሚመረት ሲሆን፣ በትግራይ ክልል የሚገኘው የእንጨት ውጤቶች ማምረቻ ፋበሪካም ከአካባቢው አርሶአደሮች ምርቱን እንደሚያገኝ ዳይሬክተር ጀነራሏ አስረድተዋል።
ከተለያዩ ዛፎችም መአዛማ ዘይቶች ይመረታሉ።የከሰል ፍላጎት ማቆም ስለማይቻል የዛፍ ልማቱ ሳይጎዳ በአግባቡ በማምረት ከሀገር ውስጥ ፍጆታ ባለፈ የውጭ ምንዛሪ ማግኛ ማድረግም ይቻላል።ለጣውላ የሚውለው የባህርዛፍ ምርትም የደን ውጤት በመሆኑ ደን ጥቅሙ ዘርፈብዙ ነው።በዚህ ረገድ አርሶአደሩ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውን በመረዳቱ ለኢንደስትሪ ግብአት የጣውላ ዛፍ በብዛት በማልማት ይጠቀማል።በቀጥታም ለውጭ ገበያ በማቅረብ ተጠቃሚነቱን እያሳደገ ይገኛል፡፡
እንደ ዳይሬክተር ጀነራሏ ገለጻ የደን ውጤቶችን ለሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች በማቅረብና በማምረት ኦሮሚያና አማራ ክልሎች የደን ኢንተርፕራይዞች ቢኖሩም በተገባደደው በጀት በሁለት ምክንያቶች ቀደም ካሉ አመታት ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ ውጤት ነው የተመዘገበው።ኢንዱስትሪዎች በውጭ ምንዛሪ እጥረት ኬሚካሎች ከውጭ ማስገባት ባለመቻላቸው ብዙ ምርት አልተቀበሉም።በጸጥታና በተለያየ ምክንያትም ግብአት አልቀረበም።የግብአት አቅርቦትና ገቢን በተመለከተ የተደራጀ መረጃ ማግኘትም በዘርፉ ከሚስተዋሉ ችግሮች መካከል ይጠቀሳል።ክፍተቶች ቢኖሩም በዘጠኝ ወራት ጊዜ ከአጣና፣ ከቀርከሃ እና ከዛፍ ላይ ከሚገኝ ዕጣን ብቻ 26 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ገቢ ተገኝቷል።የወጪ ንግዱ የብቃት ማረጋገጫ ፍቃድ ይዘው በሚንቀሳቀሱ ቢከናወንም ህገወጥ ንግድ ዘርፉን እየጎዳው መሆኑን ዳይሬክተር ጀነራሏ ያስረዳሉ።ገቢ የሚሰበሰበው ለውጪ ንግድ ከሚላከው ብቻ ሳይሆን፣ ባለንብረቱ ዛፉን ሲቆርጥ የሚፈጽመው ክፍያ መኖሩንና ገቢውም ተመልሶ ለልማት እንደሚውል አመልክተዋል፡፡
ከዘርፉ የበለጠ ተጠቃሚ መሆን እንዲቻል አርሶአደሩም ሆነ ሌሎች አልሚዎች እሴት ጨምረው ለገበያ እንዲያቀርቡ የሥራ ክፍሉ በበጀት አመቱ ከጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ጋር በጋራ በመሆን በጣውላ፣ በመአዛማ ዘይት፣ በእጣንና ከሰል አመራረት ዙሪያ የሙያ ማጎልበቻ ሥልጠና ተሰጥተዋል፡፡
በሥራ ክፍሉ የደን አመራርት፣ አጠቃቀም፣ ግብይት፣ በአጠቃላይ ከወጪና ገቢ ጋር በተያያዘ በደን ውጤቶች ግብይት ላይ እየተሰራ ይገኛል።የሥራ ክፍሉ ከኢንደስትሪዎች ጋር የተገናኘ ተግባር ቢያከናውንም የተፈጥሮ ደን ሳይባክን በሰው የሚተከሉ ደኖች ጥቅም ላይ የሚውሉበት አሰራር ወጥ በሆነ ዕቅድ ባለመመራቱ በአግባቡ ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም።በመሆኑም በውድ ዋጋና በውጭ ምንዛሪ የሚገቡትን የደን ውጤቶች በሀገር ውስጥ መተካት ባለመቻሉ የውጭ ምንዛሪ ወጭን ማዳን አልተቻለም፡፡
የሚተከሉ ችግኞች ለኢንዱስትሪ፣ ለማገዶና ለሥነምህዳር መጠበቂያ ተለይተው በዓላማ ቢከናወኑ በዘርፉ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በማስቀረት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ማሳደግ እንደሚቻል ዳይሬክተር ጀነራሏ ይናገራሉ።የስዊድንና የደቡብ ኮሪያ ሀገሮችን የደን ልማት ተሞክሮ የማየት እድሉ የገጠማቸው ጀነራል ዳይሬክተሯ ለደናቸው የሚያደርጉት እንክብካቤ መንፈሳዊ ቅናት እንዳሳደረባቸው በመግለጽ ኢትዮጵያ ምቹ የአየር ንብረትና መሬት እያላት ባለመንከባከቧና ተጠቃሚ ባለመሆኗ ቁጭት አሳድሮባቸዋል፡፡
‹ኢትዮጵያ ተራሮችዋን በደን የሸፈነች ቀን በኢኮኖሚ ብልጽግና መሰረቷን ጣለች ማለት ነው› ያሉት በኮሚሽኑ የብሄራዊ ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶክተር አይተብቱ ሞገስ ለጣውላና ለአጣና የሚውሉ ባህርዛፍ፣ የፈረንጅ ጽድና ፓይን የተባለ የዛፍ ዝርያ የሚለማበት አንድሚሊዮን ሄክታር መሬት መኖሩንና ከዚህ ውስጥም የመንግሥት ድርሻ ከአንድ አራተኛ የበለጠ አለመሆኑን አመልክተዋል፡፡
ባህር ዛፍ በስፋት አምርተው ለኢንዱስትሪ ግብአት በማቅረብ ከእርሻ ሥራ ከሚያገኙት በላይ ውጤታማ የሆኑ አርሶአደሮችን በሀገር ደረጃ ማፍራት መቻሉን የሚያስታውሱት ዶክተር አይተብቱ ከሰሊጥና ከቡና ቀጥሎ የባህር ዛፍ አጣና የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት የኢኮኖሚ ምንጭ መሆኑን መረጃዎች እያሳዩ መሆናቸውን ተናግረዋል።የረጅም ጊዜ የደን ልማት ዕቅድ እየተያዘ ቢሰራና በአንድ ሚሊየኑ ሄክታር መሬት ላይ የሚለማውን በሶስት እጥፍና ከዛ በላይ ማሳደግ ቢቻል ኢኮኖሚውን ለመደገፍ አቅም ይፈጠራል።ለብዙ ዜጎችም የሥራ ዕድል መፍጠር ይቻላል፡፡
የደን ልማት የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ እንደሆነ በብዙዎች ግንዛቤ አለመኖሩን የሚናገሩት ዶክተር አይተብቱ እንዳስረዱት የደን መመናመን የኢኮኖሚ አቅጣጫን እስከማስለወጥ ጉዳት ያደርሳል።ከአንድ መቶ ሚሊዮን ህዝብ በላይ ያላት ሀገር የደን ሽፋኗ 15 ነጥብ አምስት በመቶ ብቻ ነው።በዚህ ከቀጠለ እንደ ሀገር የሚታቀደው የኢኮኖሚ እድገት ብቻ ሳይሆን፣ የመኖር ህልውናንም ይፈታተናል።ስነ ምህዳሯ የተስተካከለ፣ ጎርፍ የማያጠቃት፣ ግድቦችዋ በደለል የማይሞሉ፣ ውሃ ማስረግ የሚችሉ ተራሮች ያሏት፣ የውሃ ማማዋ የተስተካከለ ሲሆን፣ ዘላቂ የሆነ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ ይቻላል፡፡
ዶክተር አይተብቱ የደቡብ ኮሪያ የደን ልማት ተሞክሮ የማየት ዕድል አግኝተዋል።እርሳቸው እንዳሉት ደቡብ ኮሪያ እኤአ 1950ዎቹ አካባቢ ከኢትዮጵያ ያነሰ የደን ሽፋን ነበር ያላት ከአምስት በመቶ ያልበለጠ።አሁን 65 በመቶ ላይ ደርሳለች።ተራሮችዋ ሁሉ በደን ተሸፍነዋል።ዜጎችና መሪ እጅና ጓንት ሆነው መስራታቸው ነው ለውጤት ያበቃቸው።ህዝቡ ለደን የሚሆን መሬት ለመስጠት ፈቃደኛ መሆኑ ለደን ልማቱ እድገት አስተዋጽኦ አበርክቷል።ኢትዮጵያም ውስጥ የደቡብ ኮሪያ ተሞክሮ እንዲተገበር ነው ፍላጎታቸው።በክረምቱ አራት ቢሊየን ችግኝ ለመትከል የተያዘው መርሃ ግብር ቀጣይነት ካለውና የተተከለው ከጸደቀ በአጭር ጊዜ ውጤት ማስመዝገብ ይቻላል፡፡
መናገሻ፣ ጭልሞ፣ ወፍ ዋሻ፣ ሐረና በተባሉ አካባቢዎች የሚገኙት የተፈጥሮ ደኖች መመናመን የሚያሳስባቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአካባቢ ሳይንስ መምህር ፕሮፌሰር ተሾመ ሶሮምሳ እስከነ ውበታቸውና ጥንካሬያቸው ጥቅም ላይ ይውሉ የነበሩ ቀረሮና ኮሶና ሌሎችም ሀገር በቀል ዛፎች በእጅጉ ቀንሰው በውጭ ምንዛሪ እየተገዛ በፈረንጅ ዛፍ የእንጨት ውጤቶች አገልግሎት ላይ መዋላቸው አስቆጭቷቸዋል።
የደን ልማቱ ተጠናክሮ ባለመቀጠሉ ከኦስትሪያና ከሌሎች ሀገሮች በውጭ ምንዛሪ የሚገባው ጣውላ እንዲሁም በግዥ ለቢሮ፣ ለቤት እና ለተለያዩ አገልግሎት የሚውሉ ቁሳቁሶችን በሀገር ውስጥ መተካት አለመቻሉን በማሳያነት ይገልጻሉ።‹የካርቦን ፋይናንስ› አጀንዳ ሆኖ የሚነሳው የደን መመናመን አሳሳቢ እየሆነ በመምጣቱ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
የዘርፉ ባለሙያ እና መምህርም እንደመሆናቸው አበርክቶአቸውን እንዲነግሩን ላቀረብንላቸው ጥያቄ ፕሮፌሰር ተሾመ በሰጡት ምላሽ ከአራት አመት በፊት 10ሺ የዩኒቨርሲቲውን ተማሪዎች በማሳተፍ ሰበታ ላይ ችግኝ ተክለዋል።የጥበቃና የእንክብካቤውን ሥራም ለኦሮሚያ ክልል ደንና ጥበቃ አደራ በመስጠት ያከናወኑት ተግባር ውጤት ማፍራቱን አረጋግጠዋል።ምዕራብ ሸዋ አካባቢም ከአርሶ አደሮች ጋር በመመካከር ሀገር በቀል ዛፍ እንዲተክሉ ማድረጋቸውንም አስታውሰዋል፡፡
በጥናት በኩልም በ‹ካርቦን ፋይናንስ› ላይ እየሰሩ ይገኛሉ።እርሳቸው እንዳሉት የእያንዳንዱ ዝርያ ካሮቦን የመምጠጥ አቅም በማጥናት ወደ ገንዘብ በመቀየር ያለውን ውጤት ማሳየት ነው።እያንዳንዱ ገበሬ ማሳ ላይ የሚገኝ ዛፍ የካርበን ዋጋ እንዳለውና የጥናት ውጤቱ ሲጠናቀቅም መረጃው ለሚፈልጉ አካላት እደሚያገለግል ገልጸዋል።
የችግኝ ተከላ በትውልድ ቅብብሎሽ ባለመቀጠሉ አሁን ላይ ጉዳቱ እየታየ ይገኛል።በኢትዮጵያ የተፈጥሮና በሰው የሚተከል ዛፍ በመመናመኑ የደን ሽፋኑ አስደንጋጭ በሚባል ደረጃ እየቀነሰ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።ጉዳቱ ከቀጠለና ቶሎ መተካት ካልተቻለም አሳሳቢነቱን ይገልጻሉ።በክረምቱ የተጀመረው የአራት ቢሊየን የችግኝ ተከላ መርሃግብር ተጠናክሮ ከቀጠለ ከቁጭት መውጣት ይቻላል፡፡
አዲስ ዘመን ሀምሌ 18/2011
ለምለም መንግሥቱ