ሀገሪቱን ባለ ዘመናዊ ግብይት ያደረገ፣ አርሶ አደሩን ከደረቅ ቼክ እና ከደላላ የታደገም ነው፡፡ በዚህ ስራውም 11 አመታትን በስኬት ተጉዟል። ስራውን ሲጀምር ከነበረው ቁመና በአሁኑ ወቅት በሁሉም መስኩ በከፍተኛ ሁኔታ አድጓል-የኢትዮጵያ ምርት ገበያ፡፡
የልህቀት ማእከል ለመሆን በመብቃቱም ሀገሮች ልምድ እየቀሰሙ የራሳቸውን ምርት ገበያ ማቋቋም የቻሉበትም ነው ሲሉ የገበያው የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ስራ አስኪያጅ አቶ ነጻነት ተስፋዬ ይናገራሉ፡፡ ከአቶ ነጻነት ጋር በምርት ገበያው አጠቃላይ ቁመና ላይ ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አቅርበነዋል
አዲስ ዘመን፡,- ምርት ገበያው ስለሚያገ በያያቸው ምርቶች ጠቅለል ያለ ማብራሪያ ቢሰጠኝ ?
አቶ ነጻነት፡– የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተቋቋመ 11 አመታትን አስቆጥሯል፡፡ የተቋቋመውም በሀገራችን ዘመናዊ የንግድ ስርአት ለመገንባት ታስቦ ነው፡፡ በአባላት የተመሰረተ ተቋም ነው፡፡ የህብረት ስራ ማህበራት፣ ኩባንያዎችና የመንግስት ተቋማት የተካተቱበት 347 አባላት አሉት፤
በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ አስተማማኝ የክፍያ ስርአት እንዲኖረው ታስቦ እና በመረጃ ላይ የተመረኮዘ ዘመናዊ የግብይት ስርአት የመገንባት ሃላፊነት ተቀብሎ ነው የተቋቋመው፡፡
በአሁኑ ወቅት ቡና፣ ሰሊጥ፣ ነጭና ቀይ ቦሎቄ፣ አረንጓዴ ማሾ፣ አኩሪ አተር እና ሽንብራ ያገበያያል፡፡ ስራውን የተጀመረውም በቆሎና ስንዴ በማገበያየት ነው፡፡
ከዚህ በፊት ገዥና አቅራቢ በድምጽ የሚገበያዩበት የግብይት ስርአት የነበረው ሲሆን፣ ሁለቱ አካላት ፊት ለፊት እየተገናኙ ይገበያዩም ነበር፡፡ ይህም ለሰባት አመታት ያህል አገልግሎት ሰጥቷል፡፡
አሁን የኤሌክትሮኒክ የግብይት ስርአት እየተከተለ ነው፡፡ ይህን አሰራር በቅድሚያ በዋናው መስሪያ ቤት ከጀመርን በኋላ በቅርቡ ወደ አካባቢያዊ የግብይት ማእከላት አውርደነዋል። ከአዲስ አበባ ውጪ የመጀመሪያውን የአሌክትሮኒክ የግብይት ስርአት ሀዋሳ ላይ ባለፈው ጥር ወር ከፍተናል፡፡ ሁለተኛውን ደግሞ በቅርቡ ሁመራ ላይ አስመርቀናል፡፡
አዲስ ዘመን፡– የዚህ ግብይት ፋይዳ ምንድን ነው ?
አቶ ነጻነት፡– በዚህ አሰራር ተገበያዮች የግድ አዲስ አበባ መምጣት አይገባቸውም ባሉበት ስፍራ ሆነው መገበያየት ይችላሉ፡፡ ግብይታቸውን በኤሌክትሮኒካል መንገድ ማስኬድ ያስችላቸዋል፡፡ ለምሳሌ የሁመራ ሰሊጥ አቅራቢዎች እና ገዥዎች
አዲስ አበባ ወይም ሀዋሳ ካለው ጋር ኔትወርክ ውስጥ በመግባት ግብይት መፈጸም ይችላሉ፡፡
አዲስ ዘመን፡– ምርት ገበያው ምን ያህል ተስፏፍቷል ?
አቶ ነጻነት፡– የሰለጠነ እውቀት ያለው በህግ የሚመራ የግብይት ስርአት መፍጠር ችሏል። የቅርጫፎቹም ብዛት 23 አድርሷል፡፡ ከእነዚህ ቅርንጫፎች 11ዱ ቡና አብቃይ አካባቢ የተቋቁሙ ሲሆን፣ በዋናነት ቡና ተረክበው/ሌሎች ምርቶችም ይረከባሉ፤ ጥራቱን መርመረው ዋናው መስሪያ ቤት መረጃውን ልከው ግብይት እንዲፈጸም የሚያደርጉ ናቸው ፡፡
ሌላው ምርት ገበያው ትልቅ የክፍያ እና የርክክብ ስርአት ፈጥሯል፡፡ ቀደም ሲል አቅራቢዎች ምርታቸውን ለላኪዎች ካስረከቡ በኋላ በወቅቱ ገንዘባቸው አይከፈላቸውም ነበር፡፡ በርካታ ሰዎች ገንዘባቸውን በደረቅ ቼክ ያጡ ነበር፡፡ ገንዘባቸውን ለመቀበል እንግልት ይደርስባቸውም ነበር፡፡ በዚህ የተነሳም ገንዘባቸውን እያገላበጡ እንዳይሰሩበት አርጓቸዋል፡፡ በቤተሰባቸውም በኑሯቸውም ላይ ችግር ፈጥሮ ቆይቷል፡፡
ይህን ችግር ለመፍታት ገበያ ከ16 ባንኮች ጋር ውል ፈጽሟል፡፡ በአይቲ እና ኤሌክትሮኒክ ሲስተም የተገናኘ የባንክ የክፍያ ስርአት ዘርግቶ እየሰራም ነው፤ በዚህም ማንኛውም ገዥ ወደ ኢትዮጵያ ምርት ገበያ የሚመጣው ገንዘብ ባንክ አስገብቶ ይሆናል ፤ ገንዘብ ሳያስቀምጥ መገበያየት አይችልም፡፡
ለእዚህ ተብሎ የተከፈቱ ከ5 ሺ በላይ የባንክ አካውንቶች አሉ፡፡ እነዚህ የባንክ አካውንቶች ምርት ገበያውና ባንኮቹ በጋራ የሚያንቀሳቅሷቸው እና የሚቆጣጠሯቸው ናቸው ፡፡
አዲስ ዘመን፡– ግብይቱ እንዴት ነው የሚፈጸመው ?
አቶ ነጻነት፡- አቅራቢ ምርቱን ወደ ኢትዮጵያ ምርት ገበያ መጋዘን አቅርቦ ናሙና ተወስዶ ተመርምሮ ደረጃ ይሰጠዋል፡፡ ቅርንጫፎች ኤሌክትሮኒካሊ መረጃውን ይልካሉ፤ እኛ የግብይት የጊዜ ሰሌዳ እናወጣለን፤ ይህንንም ተገበያዮች እንዲያውቁት ይደረጋል፤ በዚህም መሰረት መጥተው ይገበያያሉ፤ የሚገበያዩት ኤሌክትሮኒክ የግብይት ስርአቱ ላይ ነው፡፡ በዋጋ ሲስማሙ ስምምነቱ ህጋዊ ስምምነት ነው፤ መቀየር አይችሉም፡፡
በማግስቱ ከእኩለ ቀን በፊት ከገዥ የባንክ ሂሳብ ገንዘቡን ቀንሰን ወደ አቅራቢው አካውንት እናስገባለን፡፡ ለገዥው ደግሞ ምርቱን የሚረከብበትን ሰነድ እንሰጠዋለን፤ ኤሌክትሮኒካሊም ወደ ቅርንጫፉ ይላካል፡፡ ወዲያውኑ የዚያኑ ቀን ምርቱን መረከብ ይችላል፡፡
አሁን ገበሬው ገንዘቤን አጣሁ ብሎ አያዝንም፤ገዥውም በዚህ ደረጃ ምርት እፈልጋለሁ ካለ ለዚያ ደረጃ ዋስትና የሚሰጠው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ነው፡፡ የገዛሁት የይርጋጨፌን ደረጃ አንድ ነው ካለ ደረጃ አንድ የይርጋ ጨፌን ቡና ይረከባል፡፡
ገበሬው ምርቱን ወደ ገበያ ሲያወጣ ዋጋውን የሚወስኑለት ደላላዎች ነበሩ፡፡ ገበሬው የዋጋ መረጃ ያገኝ ስላልነበረ ደላላ እና ገዥ ጫና ይፈጥሩበት ነበር፡፡ ስለዚህ ይህን ለመከላከል እና ገበሬው ራሱ ዋጋ የሚሰጥ እንዲሆን በሁለት የስልክ መስመሮች / 929 እና 934 / በጽሁፍ መልዕክትና በድምጽ ዕለታዊ የገበያ መረጃ ወዲያውኑ ማግኘት የሚችልበት ስርአት ተፈጥሯል፡፡
አንድ ግብይት ሲፈጸም ከ12 እስከ 15 ደቂቃ ብቻ የሚወስደው፤ይህ ግብይት ከተፈጸመ ከሁለት እስከ አራት ሰከንድ ውስጥ የገበያ መረጃው
ይለቀቃል፡፡ ስለዚህም የትም ቦታ ያለ ኢትዮጵያዊ ገበሬ፣ የውጪ ዜጋም ሆነ ማንኛውም ሰው የገበያ መረጃውን ማግኘት ይችላል፡፡
እኔና አንተ እየተነጋገርን ባለበት በአሁኑ ወቅት የሀገር ውስጥ ቡና ግብይት እየተካሄደ ነው። ቀጥሎ የሰሊጥ ግብይት ይፈጸማል፡፡ ስለዚህ የሀገር ውስጥ የቡና ግብይት የይርጋ ጨፌ በስንት ዋጋ እንደተገበያየ ወዲያውኑ የትም ቦታ ያለ አቅራቢና ገዥ መረጃውን ማግኘት ይችላል፡፡ መረጃው በአማርኛ በትግሪኛ፣ በኦሮምኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋ ይሰራጫል፡፡
ገበሬው ይህን ካወቀ በሚቀጥለው ምርቱን ይዞ ሲወጣ ያለውን ዋጋ ማዕከላዊ ገበያ ላይ ያውቃል። በዚህ ዋጋ ነው የምሸጠው ሲል እዚህ ያለውን ዋጋ አውቆ ነው ማለት ነው፡፡ ይህ አሰራር ገበሬው በራሱ እንዲተማመን፣ እውቀት ኖሮት ወደ ገበያ እንዲወጣ፣ ተገቢውን ክፍያ ለምርቱ እንዲያገኝ አስችሎታል፡፡
ምርት ገበያው የልህቀት ማእከል/ሴንተር ኦፍ ኤክሰለንስ/ መሆን ችሏል፡፡ በህግ፣ በእውቀት፣በቴክኖሎጂ እና በመንግስት ቁርጠኝነት መሰረት የተገነባ የግብይት ስርአት ስለሆነ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገሮችም እንደ ምሳሌ የሚታይ ለመሆን በቅቷል፡፡ በርካታ የአፍሪካ ሀገሮች እኛ ዘንድ መጥተው ልምድ ቀስመው መሪዎቻቸውም ገበያውን መጥተው ጎብኝተው በሀገራቸው ተመሳሳይ የልውውጥ ተቋም/ኤክስቼንጅ/ ከፍተ ዋል፡፡
ለአብነትም ጋና ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በመላክ ልምድ እንዲቀስሙ አርጋለች፡፡ ሀገራቸው ሄደው የኤሌክትሮኒክስ የግብይት ስርአት ዘርግተዋል፡፡ ኬንያም ከፍታለች፡፡ የታንዛኒያ ፕሬዚዳንት ምርት ገበያውን ጎብኝተው በሀገራቸው ገበያው እንዲቋቋም አርገዋል። ናይጄሪያ እና ማሊ ተመሳሳይ ስራ ሰርተዋል፡፡ በቅርቡም ሞዛሚቢኮች ይመጣሉ፡፡ በዚህም የልህቀት ማእከልነቱን ለአፍሪካም አትርፏል፡፡
ይህ ብቻም አይደለም፤ የኢኮኖሚክስና የመሳሰሉት መስኮች ተማሪዎች መመረቂያቸውን ሲሰሩ ምርት ገበያው የመረጃ ምንጫቸው እያረጉ ናቸው፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎች ምርት ገበያውን ይጎበኛሉ፡፡ ይህም እውቀት የሚሸጋገርበት የልህቀት ማእከልነቱን ያመለክታል፡፡
ጠንካራ ዳታ ቤዝ አለን፡፡ ምንኛውም በምርት ገበያው በኩል የሚገበያይ ምርት መረጃ ለሚመለከታቸው የመንግስት መስሪያ ቤቶች ይተላለፋል፡፡ የዘመናዊነት አንዱ መገለጫ በህግ ማእቀፍ ውስጥ የሆነ የግብይት ስርአት መገንባት
እንደመሆኑ ምርት ገበያው ይህን እያረገ ነው። ለምሳሌ ብሄራዊ ባንክ ፣ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣የገቢዎች ሚኒስቴር፣ ጉሙሩክ እኛን የሚቆጣጠረው መስሪያ ቤት በመሉ ከምርት ገበያው የእያንዳንዱን ግብይት መረጃ ያገኛሉ።
ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ለውጭ ገበያ ብለው ምርት ከወሰዱ በኋላ ሀገር ውስጥ እንዲሁም በኮንትሮባንድ መሸጥ አይችሉም። በዚህም የውጭ ምንዛሬ በአስተማማኝ መንገድ እንዲገኝ ሙሉ መረጃ መስጠት አስችሏል። ሁለተኛ ማንኛውም በምርት ገበያው ግብይት የፈጸመ ላኪ ተገቢውን ታክስ የመክፈል ግዴታ ያለበት በመሆኑ ለግብር ሰብሳቢው መስሪያ ቤት አስተማማኝ የመረጃ ምንጭ መሆን ተችሏል። ስለዚህ ለታክስ ክፍያም አስተዋጽኦ አርጓል ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡– ደላላ የሚፈጥረውን ችግር ምርት ገበያው አስቀርቷል ማለት ይቻላል?
አቶ ነጻነት፡– ምርት ገበያው ይህን የማስቀረት ሃላፊነት /ማንዴት /የለውም። ይህ ሊፈታ የሚችለው በቀበሌ እና በወረዳ ደረጃ ነው። ምርት ገበያው እዚያ ድረስ ሊሄድ አይችልም።
ቡናን ብንመለከት ከቡና ምርት አጠቃላይ ግብይት ውስጥ 40 በመቶው በመሀል ላይ ባሉ የእሴት ሰንሰለቶች ውስጥ አካላት ይባክናል። የደላላው ሁለት ሶስት እርከን አለው። መጓጓዣ፣ ገበሬው የሚሸጥበት የአካባቢ ገበያ፣ ከአካባቢ ገበያ ወደ ዋና አቅራቢዎች ሰንሰለቶች አሉ፤ እዚህም ደላላ አለ።
ሌሎች ለምርቱ እና ለግብይቱ ማደግ ምንም አስተዋጽኦ የማያደርጉ ክፍሎች ገንዘቡን ይበሉታል። ይህን መስበር የሚቻለው ከቀበሌ አንስቶ አስከ ወረዳ ባሉት እርከኖች ብቻ ነው። በመጀመሪያ የግብይት ማዕከላት ደረጃ መስበር ያስፈልጋል። ይህ ካልተሰበረ ገበሬው የምርቱ ተጠቃሚ አይሆንም። ሌሎች ሀገሮች ብናይ እነ ብራዚል እና ኮሎምቢያ ላይ ከ10 እስከ 13 በመቶ ነው በግብይት ሰንሰለት ላይ የሚባክነው። እነ ቤትናም ዘንድ 7 በመቶ ነው። ለምንድን ነው
ገበሬው ይህን የሚያጣው።
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የሚያደርገው የገበያ መረጃ መስጠት ነው። ገበሬው መረጃውን ካወቀ በዚህ ዋጋ ነው የምሸጠው ብሎ ይወስናል። ሁለተኛው ገበሬዎች ቡናቸውን ቀጥታ ለአቅራቢም ለሌላም ሳይሸጡ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ አምጥተው የሚሸጡበት ስርአት ዘርግተናል። ይህም በመሀል ያለውን ደላላ ምናምን የሚባለውን አሰራር ይሰብራል ማለት ነው።
ሌላው የምናበረታታው የህብረት ስራ ማህበራትን ነው። ማህበራቱ የአባሎቻቸውን ምርት አምጥተው እንዲገበያዩ። ትልቁ ስራ መሰራት ያለበት ታች ላይ ነው።
አዲስ ዘመን፡–የምርት ገበያው እንቅስቃሴ ሲጀመር ከነበረው ወይም የገበያው መስራች ዶክተር አሊ ከነበሩበት ጊዜ አንጻር ሲታይ አሁን በምን ላይ ይገኛል? በቀድሞ ቁመናዬ ነኝ ብሎ ያምናል?
አቶ ነጻነት፡– የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ሲጀመር የነበረው አቅም አይደለም አሁን ያለው። የእጥፍ እጥፍ አድጓል። ገበያው ከዛሬ አስራ አንድ አመት ቁመናው ጋር ሲወዳደር በተሻለ ቁመና ላይ ይገኛል። በተሻለ አቅም ላይ ነው። ቀላል ምሳሌ ላንሳልህ፤ እንደተመሰረተ 138 ሺ ሜትሪክ ቶን ምርት ነበር ያገበያየው። ሁሉንም አይነት ምርቶች በአጠቃላይ ማለት ነው። አሁን ወደ 630 እና 640 ሜትሪክ ቶን እያገበያየ ይገኛል። ይህ ቀላል ነገር አይደለም።
ስራውን የጀመረው ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ዳሸን ባንክ ጋር ነበር። አሁን የባንኮቹ ቁጥር 16 ደርሷል። በእነዚህ ባንኮች ከ5 ሺ በላይ የባንክ አካውንቶች አሉ። 5 ሺ የባንክ አካውንት ማንቀሳቀስም ማለት ቀላል ነገር አይደለም።
ግብይት ሲጀመር በሳምንት አንድ ቀን ነበር የሚካሄደው። አሁን ከሰኞ እሰከ አርብ ግብይት አይቋረጥም፤ በየቀኑ ግብይት አለ። በኛ አገበያይ አካላት በኩል የሚገበያዩ 20 ደንበኞች /ክሊያንት/ ነበሩ። አሁን ደንበኞቹ ከ20 ሺ በላይ ሆነዋል። ከሶስት ሚሊየን በላይ ቀጥተኛ ተጠቃሚዎች አሉን፤ ገበሬዎች ማለት ነው። በቀጥታ እና ቀጥታ ባልሆነ መንገድ የሚጠቀም ከ25 ሚሊዮን በላይ ህዝብ አለ። የአርሶ አደሩ ቤተሰብ.፣ ትራንስፖርተሮች፣ በየቅርንጫፉ የሚገኙ ተሸካሚዎች፣የጉልበት ሰራተ ኞች፣ የጥበቃ ሰራተኞች የገበያው ተጠቃሚ ናቸው።
ሲጀመር የነበረው ቅርጫፍ የሳሪሱ ብቻ ነበር። ምርት መቀበያ የነበረው። አሁን የቅርንጫፎቹ ብዛት 23 ደርሷል።
በየቀኑ የሚካሄደው ግብይት/ትራንዛክሽንም/ እንደዚያው ነው። ባለፉት አስር አመታት ብቻ ወደ 5 ቢሊዮን ሜትሪክ ቶን አገበያይተናል። ይህም ወደ 203 ቢሊየን ብር ዋጋ አለው።
በርካታ ሰዎች አገልግሎቱን እየተጠቀሙ ናቸው። አሁን ቀጥታ መጥተው እንዲገበያዩ ፈቅደናል። በፊት ቡና ነበር የተፈቀደው፤ አሁን ለሰሊጥም ተፈቅዷል። ሰሊጥ ተገበያዮች በአገናኞች ብቻ ሳይሆን በራሳቸውም በቀጥታ በምርት ገበያው የሚገበያዩበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
ሰሊጥ ያለው ገበሬ ራሱ መገበያየት ይችላል። ሰሊጥ አምራቾች የሚጠቀሙት ሜካናይዜሽን ነው። በጣም ብዙ ያመርታሉ ማለት ነው። ስለዚህ አርሶ አደሩ የራሱን ምርት አምጥቶ መገበያየት ይችላል።
ገበያው ሲጀመር ጥቂት ምርቶች ነበሩ ግብይት የሚካሄዳባቸው። አሁን የምርት አይነቱ ዘጠኝ ደርሷል። ኑግ በቅርብ ጊዜ ይገባል። ጥጥ እና ሌሎችም ምርቶች ወደ ምርት ገበያ ስርአት እንዲገቡ ጥናት እየተካሄደ ነው።
እድላችን ሰፊ ነው፤የሄድንበት መንገድም ሰፊ ነው። በጣም ብዙ ሰው በጣም ብዙ አርሶ አደር ተጠቃሚ አርገናል።
የገበያ ስርአታችንም ልክ እንደዚያው ነው። የአገር ውስጥ የማስተገባት ግብይት የዛሬ አራት አመት ወደ ኤሌክትሮኒክ ትሬድ ተቀይሯል። በአዲስ አበባ ግብይቱ በኤሌክትሮኒክ መንገድ ሲካሄድ ቆይቶ አሁን ወደ ታች ወርዷል። ኤሌክትሮኒክ ግብይቱ በሀዋሳ እና ሁመራ ተከፍቷል። በሚቀጥለው አመት ነቀምት፣ ጎንደር እና ጂማ እንከፍታለን። ይህም የሀገር እሴት ነው። ለእያንዳንዱ ቅርንጫፍ ከ10 ሚሊየን ብር በላይ ይወጣል።
አዲስ ዘመን፡– ይህን ጥያቄ ያነሳሁበት ምክንያት ምርት ገበያው ቀደም ሲል መገናኛ ብዙሃንን በስፋት ይጠቀም ስለነበርና አሁን ግን ያንን ስላላየሁ ነው። ያኔ ያን ያህል ሚዲያ የተጠቀመው አዲስ ስለሆነ ሊሆን ይችላል። ከሰጡኝ መግለጫ መረዳት እንደቻልኩት አዳዲስ ነገሮች ብዙ አላችሁ፤ ይሁንና መገናኝ ብዙሃን ላይ ብዙም አይስተዋሉም። ይህ ለምን ሆነ፤ ከሚዲያ ጋር ያላችሁ ግንኙነት እንዴት ይገለጻል ለማለት ፈልጌ ነው።
አቶ ነጻነት፡– ሲጀመር አዲስ ስለነበር ሚዲያውን በጣም ይጠቀም ነበር። አሁን የምንሰራበት መንገድ በፊት ያልነበረ ነው። አሁን የውጪ ሀገር ግብይቶች የገበያ መረጃ በየወሩ እንለቃለን። በፊት የገበያ መረጃ በየቀኑ የምንለቀው በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ላይ ብቻ ነበር። አሁን ግን በአራቱም ክልሎች የቴለቪዥን ጣቢያዎች የገበያ መረጃዎችን እንለቃለን። በየቀኑ መረጃ ይቀርባል። የሳተላይት ቴሌቪዥኖችም ከኛ እየወሰዱ ያሰራጫሉ፤ ለዚህም ከኛ ጋር ውል ተፈራርመዋል። በአጠቃላይ 14 መገናኝ ብዙሃን ስለ ምርት ገበያው በየቀኑ ያወራሉ።
ከዚህ ውጪ ምረቃ ሲኖር፣ ጉብኝት ሲኖር ሚዲያ እንጋብዛለን። የእናንተም ጋዜጠኞች ይመጣሉ። የሚዲያ ቱር እናዘጋጃለን። ጋዜጠኞች ይዘን እንዞራለን።
ሌላው ማህበራዊ ሚዲያ ነው። በማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀሙ ከመንግስት መስሪያ ቤት በአብነት የሚጠቀሰው ምርት ገበያው ነው። በተቋሙ ማኅበራዊ ሚዲያ በኩል በየቀኑ ወዲያውኑ የገበያ መረጃዎቻችንን እንለቃለን። የግድ ሜይን ስትሪም ሚዲያውን/ብሄራዊ የመገናኝ ብዙሃንን/ አንጠብቅም። ትናንት የተካሄደው የግብይት መረጃ ማታውኑ ተለቋል። ሚዲያ ላይ ይነገራል። የሚፈልግ ሰው ዌብ ሳይታችን፣ትዊተር ገጻችን፣ፌስቡክ ገጻችን ላይም ማግኘት ይችላል። አያመልጠውም።
ያኔ የነበረው የሚዲያ አካሄድ እና የአሁኑ ልዩነት አለው። አሁን እስከታች ድረስ ሰው ሊያገኝ በሚችለው መንገድ መልቀቅ ነው ያለብን። ቡሌ ሆራ ከተማ ላይ የሚገኝ አርሶ አደር ከፍቶ የገበያ መረጃውን ማግኘት ይችላል። የግድ ቲቪ መጠበቅ የለበትም፤ ከፈለገም በቋንቋው በኦቢኤን ማግኘት ይችላል።
አዲስ ዘመን፡– ይህ ከአይቲ ጋር የተገናኘው ስራችሁ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በተያያዘ በተለይ አንዳንዴ በሚፈጠሩ ችግሮች የኮኔክሽን ችግር አይገጥማችሁምን ?
አቶ ነፃነት፤ እርግጥ ነው ተጽእኖ ያረጋል። አዲስ የቡና ግብይት ስርአት ከጀመርን ወዲህ ሁሌም ጧት ላይ ፍሪ ትሬድ ኢንፎርሜሽን በሚል መረጃዎችን ለተገበያዮች እናሰራጫለን። ይህ ማለት ዛሬ የምናገበያየው ቡና የማን የማን ይሆናል የሚለውን ያካትታል። ተገበያዮችም ይህን አውቀው ነው ለግብይቱ የሚመጡት። ያንን መረጃ በቴሌግራም እንለቅላቸዋለን፤ በኛ ስም ኢሜይልም ከፍተንላቸዋል።
ኢንተርኔት ሲታገድ ግን ሌላ መስሪያ ቤት ላይ ያለው ችግር እኛም ዘንድ ይመጣል። እሱ ብቻ የጸጥታ መደፍረስ ሲከሰት መስሪያ ቤቶች የሚዘጉበት ሁኔታ ያጋጥማል። ባለፈው ጊምቢ ላይ ችግር አጋጥሟል።
እኛ ግን አማራጮች አሉን። የኢንተርኔት መስመር ሲዘጋ በሀርድ ኮፒ እንለጥፋለን። ሁለተኝ በኢሜይል እንልክላቸዋለን። መረጃውን አንዱ ካንዱ ይቀባበላል። ያ ክፍተት በዚህ አይነት መንገድ ሸፍኗል። አንዱ ቅርጫፍ ላይ ባይኖር ሌላው ጋ ስለሚኖር ግብይቱ ይቀጥላል። አይቋረጥም።
የኢንተርኔት መስመራችን ጠንካራ ነው። ግብይት የሚካሄድበት ኔትወርክ የኛ ባለለሙያዎች በዘረጉት ሎካል ኔትወርክ ነው የሚሰራው። ስለዚህ ኔትወርክ ውጪ ቢቋረጥ መስሪያ ቤት ውስጥ አይቋረጥም። የሀዋሳና ሁመራ ኢንተርኔት ከተቋረጠ የኤሌክትሮኒክስ ግብይቱ ይቋረጣል። ይህ ግን ሀገራዊ ችግር ነው።
አዲስ ዘመን ፡– ለትብብርዎ እናመሰግናለን።
አቶ ነጻነት፡– እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 16/2011
ኃይሉ ሣህለድንግል