በኢትዮጵያ እድሜ ጠገብ ከሆኑ ሆስፒታሎች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ የሃገሪቱ ትልቁ ሪፈራል ሆስፒታልም ነው፡፡ በነባር ህንፃዎቹ ልዩ ልዩ የህክምና አገልግሎቶችን ለበርካታ አመታት ለዜጎች ሲሰጥ የቆየ ቢሆንም፣እነዚህ ህንጻዎች በአሁኑ ወቅት እርጅና ተጫጭኗቸዋል፤ የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል።
ሆስፒታሉ ከቅርብ አመታት ወዲህ ተጨማሪ ህንፃዎችን በመገንባት የህክምና አገልግሎቱን ለማስፋት ጥረት እያደረገ ይገኛል። ይሁንና አብዛኛዎቹ ህክምናዎች አሁንም የሚሰጡት እርጅና በተጫጫናቸው የሆስፒታሉ ህንፃዎች ላይ በመሆኑ አገልግሎቱን በተሻለ ጥራት መስጠት አልተቻለም፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የግል ባለሃብቶችንና ሌሎች ተቋማትን በማሳተፍ ሆስፒታሉን ለማሳደስ በቅርቡ በገባው ቃል መሰረት የሆስፒታሉ ችግር በመጠኑም ቢሆን ይቃለላል ተብሎ ተገምቷል፡፡
አዲስ ዘመን ጋዜጣም የሆስፒታሉን አጠቃላይ እድሳት ሂደት በተመለከተና ከእድሳቱ በኋላ በተለይ ለተጠቃሚው ሊያበረክተው በሚችለው አስተዋፅኦ ዙሪያ የሆስፒታሉን ክሊኒካል ሰርቪስ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶክተር ይርጉ ገብረህይወትን አነጋግሯል፡፡ እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡
ለእድሳቱ የመንግስትና የግል ባለሃብቶች ቁርጠኝነት
ሆስፒታሉን በማሳደስ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን ጨምሮ በመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ዘንድ ከፍተኛ ቁርጠኝነት ተይዟል፡፡ የግል ባለሃብቶችም በሚችሉት አቅም በሆስፒታሉ በሚካሄዱ የተለያዩ የእድሳት ስራዎች ለመሳተፍ ቃል ገብተዋል። ባለሀብቶቹ ተሳታፊ የሚሆኑበት አሰራርም በሆስፒታሉ በኩል ተመቻችቷል። ይህም ለሆስፒታሉ ሰራተኞችና በተለይም ለተገልጋዮች ብሩህ ተስፋ ሰጥቷል፡፡
ሆስፒታሉ በህዝብ የተሰራ እንደመሆኑ መጠንና በአሁኑ ወቀት ደግሞ ለእድሳቱ በመንግስትና በግል ባለሃብቶች ቃል መገባቱ ከሆስፒታሉ ሃምሳኛ አመት ምስረታ በኋላ ሰዎች ባላቸው አቅም ሆስፒታሉን ዳግም ለማሳደስ ያላቸውን ቁርጠኝነት ያሳያል፡፡ ይህም በበጎ የሚታይና በበጎ ፍቃድ መስራት እንፈልጋለን ያሉ ሰዎችም ጭምር ለማገዝ ዝግጁነታቸውን ያረጋገጡበት ነው፡፡
የሆስፒታሉ እድሳት ሂደት
የግል ባለሃብቶችና በጎ ፍቃደኞች ሆስፒታሉን ለማሳደስ ቃል መግባታቸው በበጎ የሚታይ ቢሆንም አብዛኛው የሆስፒታሉ እድሳት የሚካሄደው ሆስፒታሉ ሳይዘጋና ስራዎችም ሳይቆራረጡ ነው፡፡ ለዚህም ከፍተኛ ዝግጅት ተደርጓል፡፡ በሆስፒታሉ የሚገኙ አንዳንድ የህክምና ክፍሎች ከሚሰጡት ወሳኝ አገልግሎት አኳያና በክፍሎቹ ያሉ ህሙማንን በትክክለኛ መንገድ ወደ አማራጭ ቦታ መውሰድ የሚያስፈልግ በመሆኑ እድሳቱን በቶሎ ማስጀመር አይቻልም፡፡ በመሆኑም የሆስፒታሉ አጠቃላይ የእድሳት ስራዎች ደረጃ በደረጃ የሚከናወኑ ይሆናል፡፡
በአሁኑ ወቅትም እድሳቱ የሚመለከታቸው የህክምና ክፍሎች የዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ ናቸው፡፡ ለአብነትም የህፃናት ፅኑ ህሙማን፣ የአዋቂ ፅኑ ህሙማንና፣ የማዋለጃ ክፍሎች አማራጭ ናቸው ያሏቸውን መንገዶች ወስደው በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡
በሆስፒታሉ የሚካሄዱ እድሳቶች
ሆስፒታሉ የጤና ተቋም እንደመሆኑ መጠን እድሳቱ እንዲሁ በቀላሉ የሚከናወን አይደለም። ከሁሉ በፊት በሆስፒታሉ ውስጥ መሰረታዊና ትልቅ የሚባሉ አስራ ሶስት ችግሮች ተለይተዋል። መሰረታዊ የሆስፒታሉን ችግሮችን ለመቅረፍ የእድሳት ስራው የቀለም ቅብ፣ የኤሌክትሪክና መሰል ስራዎችን ያካትታል፡፡
ከትላልቅ የሆስፒታሉ ችግሮች ውስጥ በዋናነት የሚጠቀሰው የውሃ እጥረት ነው። ውሃው በከፍተኛ ግፊት ወደ እያንዳንዱ የሆስፒታሉ ወለሎች ሲወጣ ቧንቧዎች ይፈነዳሉ። በዚህም ምክንያት የውሃ መቆራረጥ ያጋጥማል። በመሆኑም ውሃ ለሁሉም የሆስፒታሉ ወለሎች እንዲዳረስ ማድረግ በእድሳቱ ቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቶ የሚሰራበት ጉዳይ ይሆናል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በቂ ውሃ ባለመኖሩ ምክንያት የተወሰኑ የሆስፒታሉ መፀዳጃ ቤቶች ተገቢውን አገልግሎት እየሰጡ ባለመሆናቸው የውሃ አቅርቦቱን በማሻሻልና መፀዳጃ ቤቶቹን በማስተካከል አገልግሎት አንዲሰጡ ይደረጋል፡፡ በተጨማሪም ከአንዱ የህንፃ ወለል ወደ ሌላኛው ወለል ውሃ እንዳያልፍ የማድረግ ስራዎችም አብረው ይሰራሉ፡፡ ሆስፒታሉን የማስዋቡም ስራም ከዚሁ ግን ለጎን የሚከናወን ይሆናል፡፡
የሆስፒታሉን የፍሳሽ ስርአት ማስተካከልም በእድሳት ሂደቱ የሚከናወን ሌላኛው ስራ ሲሆን ከሆስፒታሉ የሚወጣው ፍሳሽ በተለይ በአካባቢ ላይ ጉዳት እንዳያስከትል ፍሳሹን አክሞና አጣርቶ የማስወገድ ስራዎችም ይሰራሉ፡፡ የሆስፒታሉን እድሳት የማስጠናት ስራም በተባበሩት መንግስታት የህፃናት አድን ድርጅት ይሰራል። በአሁኑ ወቅት በአጭር ጊዜ የሚሰሩ ስራዎች እንደማሳያ የሚሆኑና ነገርግን በረጅም ጊዜ ሂደት ተቋሙን የሚቀይሩ ናቸው ተብሎ ይታሰባል፡፡
እድሳቱ የሚከናወንበት አግባብ
የግል ባለሃብቶች፣ ተቋማትና ግለሰቦች ልባቸው በፈቀደው መጠን እንሰራለን ብለው በሆስፒታሉ እድሳት የሚፈልጉ ክፍሎችን ተረክበዋል፡፡ ለዚህም ሆስፒታሉ ለእድሳት አነስተኛ ያለውን ደረጃ /standard/ አስቀምጧል፡፡ እያንዳንዱን የሆስፒታል ክፍሎች ለማሳደስ የሚጠይቀው የራሱ ደረጃና ቴክኖሎጂ በመኖሩ በእድሳቱ ሂደት ይህም ከግምት ውስጥ አንዲገባ ተደርጓል፡፡
በእድሳቱ የሚሳተፉ ሰዎች የፈለጉትን ክፍል በራሳቸው መንገድ በተቀመጠው የሆስፒታሉ አነስተኛ የእድሳት ደረጃና ከዛ በላይ ባለው እንዲሳተፉ የሚቻልበት መንገድ ይመቻቻል፡፡ ለእድሳቱ ቃል የገቡ የግል ባለሃብቶችና ተቋማትም በርካታ በመሆናቸው እድሳት የሚፈልጉ ክፍሎች ተለይተው በቀጣይ የሚሰጣቸው ይሆናል። ባለሀብቱና ተቋማቱ ሆስፒታሉን ለማሳደስ በመንግስት ፊት ቃል የገቡ ከመሆናቸው አኳያ ቃላቸውን በመጠበቅ የእድሳት ስራውን ይሰራሉም ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የጤና ሚኒስቴር የኢንጂነሪንግ ትምህርት ክፍል እድሳቱን ለማከናወን በቅድሚያ የክፍሎቹን ጉድለት ለይቷል፡፡ በቀጣይም ክፍሎቹ የሚፈልጉትን የእድሳት አይነት ካወቀ በኋላ ለእድሳቱ የሚፈጀውን የዋጋ ግምት የሚያወጣ ይሆናል፡፡ ለእድሳቱ የሚያስፈልጉ ሃብቶችን ደግሞ ቃል የገቡ ባለሃብቶችና ተቋማት ማበርከት ይጠበቅባቸዋል፡፡
እድሳቱ ከፍተኛ እውቀትና ክህሎት የሚጠይቅ በመሆኑና የጤናውን ዘርፍ ፍላጎት ያሟላ መሆን ስለሚጠበቅበት በተጠና መልኩ የሚከናወን ይሆናል፡፡ ሰዎች የሆስፒታሉን ክፍሎች እየመጡ ለማሳደስ ቃል ገብተዋል፡፡ ይሁንና የእድሳት ስራው በትክክልና በማያዳግም መልኩ ለማከናውን እንዲቻል ቃል የገቡ የግል ባለሃብቶችና ተቋማትን አቅም መነሻ በማድረግ አነስተኛ የእድሳት ደረጃ /standard/ ሆስፒታሉ አስቀምጧል፡፡ በመሆኑም ከትንሹ ደረጃ በታች የሚሰራ ስራ አይኖርም፡፡
የእድሳቱ ጠቀሜታ በሆስፒታሉ እይታ
ሆስፒታሉ ሰዎች የራሳቸውን ገንዘብ አውጥተው የሰሩት ትልቅ ተቋም እንደመሆኑ መጠን የአሁኑ ትውልድም በተመሳሳይ ተቋሙን ወደፊት የማስተላለፍ ሃላፊነት አለበት፡፡ ከዚህ አኳያ በተቋማትና በግል ባለሃብቶች ሆስፒታሉን ለማሳደስ ቃል መገባቱም ተገቢና አስፈላጊ ነው፡፡
ባለው ውስን የበጀት አቅም ሆስፒታሉን ወደፊት ለማራመድ ከዚህ በፊት ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡ ይሁንና እነዚህ ጥረቶች በቂ ባለመሆናቸው ሆስፒታሉን ማደስ የግድ ይላል። ይህም ለጤና ባለሞያው ንፅህ ቦታ ላይ መስራት እንዲችልና ህዝቡም ንፁህና ጥራት ያለው የጤና የህክምና አገልግሎቶችን እንዲያገኝ ያስችለዋል። የሚቀጥለውን ትውልድ የጤና አገልጋይ የሚፈጥር በመሆኑና መለኪያውን ከፍ ማድረግ ስለሚገባ የእድሳቱ ፋይዳ የጎላ ነው፡፡
ዜጎች የጥቁር አንበሳ ድጋፍ ያስፈልገኛል በሚል የእኔነት ስሜት ሆስፒታሉን ለማሳደስ ተነሳሽነት ማሳየታቸውም የሚደነቅና ወደፊትም ሊበረታታ የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ በመንግስት በኩል ሆስፒታሉን ለማሳደስ ቃል መገባቱም እንደ ትልቅ እድል የሚታይና ሆስፒታሉንና አካባቢውን ፅዱ፣ ብሩህና ደማቅ ለማድረግ የሚያስችል ከመሆኑም በላይ ሆስፒታሉ ከሃምሳ አመት በላይ የተነፈገውን እድል እንዲያገኝ የሚያስችል ነው፡፡
እድሳቱ መቼ ይጠናቀቃል?
በሆስፒታሉ የሚከናወኑ የእድሳት ስራዎች አንዳንዶቹ ቀላል ቢሆኑም የውሃና ፍሳሽ ስራዎቹ ግን ከባድ በመሆናቸው ከፍተኛ ጥንቃቄ ይሻሉ፡፡ ዋነኛ ጉዳይ መሆን ያለበትም ሰላሳ ሁለት ወለሎችን በጥቂት ወራቶች ውስጥ እድሳታቸውን ማጠናቀቅ ሳይሆን፣ ትክክለኛውን ሂደት በመከተል የህክምና አገልግሎቱ ሳይቋረጥ የእድሳት ስራውን ማከናወን ነው፡፡ በመሆኑም የእድሳት መጠናቀቂያው ጊዜ ብዙ የሚያሳስብ አይደለም፡፡
ባላሀብቶች በገቡት ቃል መሰረት የሚሸፈኑ ሰላሳ ሁለት የሆስፒታሉ ወለሎች ያሉ ቢሆንም ሌሎች እድሳት የሚፈልጉ ተጨማሪ የሆስፒታሉ ተቋማትና ክፍሎችም አሉ፡፡ እነዚህንም መንግስት፣ ህዝቡና የግል ባለሃብቱ በገንዘቡ፣ በእውቀቱ እንዲሁም በጉልበቱ ተረባርቦ የተፈጠረውን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ወደሚቀጥለው ከፍታ አብሮ ለመሄድ በጋራ መስራት ይጠበቅበታል፡፡
አዲስ ዘመን ሐምሌ 16/2011
አስናቀ ፀጋዬ