
የሰው ልጆች ከቴክኖሎጂ ጋር ያላቸው ቁርኝት በእጅጉ እየጨመረ መጥቷል፤ ያለቴክኖሎጂ የተቀላጠፈ አገልግሎት ማግኘት አይቻልም፤ በሥራ ውጤታማ መሆንም አይታሰብም። ቴክኖሎጂ የሰው ልጆች የዕለት ተዕለት ኑሮ እና የአኗኗር ዘይቤ እንዲቀየርና እንዲዘመን እያደረገ ያለበት ሁኔታ፣ ለሰው ልጅ መሠረታዊ ከሆኑት ነገሮች መካከል አንዱ ቴክኖሎጂ እንዲሆን እያደረገው ይገኛል።
ለኢትዮጵያ ሩቅ የነበሩት የቴክኖሎጂ ውጤቶችና አሠራሮች በሚገርም ፍጥነት ወደ ሀገሪቱ እየገቡ ይበልጥም እየተስፋፉ ይገኛሉ። በዲጂታል ቴክኖሎጂ በመታገዝ የሚሰጡ የኦንላይን አገልግሎቶች እየተስፋፉና እየተበራከቱ የመጡበትን ሁኔታም ለእዚህ በአብነት መጥቀስ ይቻላል። የትራንስፖርት፣ የምግብ እና የመሳሰሉት አገልግሎቶች አቅርቦት ሳይቀር በዲጂታል አገልግሎት ተደራሽ እየተደረገ ይገኛል። በዚህም ወጪ፣ ጊዜና ጉልበት እየተቆጠበ ነው፤ምርትና ምርታማነት እያደገ፣ አቅርቦት እየተቀላጠፈ ነው።
ኢትዮጵያ እነዚህን ቴክኖሎጂዎች በስፋት እየተጠቀመች ነው፤ በቀጣይም ይበልጥ በስፋት እንደምትጠቀም ይጠበቃል። ቀደም ሲል እነዚህ ቴክኖሎጂዎች ከውጭ እንዲመጡ ወይም በውጭ ኩባንያዎች እንዲሠሩ ይደረግ ነበር፤ ያም ሁኔታ እየተቀየረ ነው። አሁን በርካታ የዘርፉ የፈጠራ ሥራዎች በሀገር ልጆች ልጆችና ድርጅቶች ቴክኖሎጂዎች እየተተኩ ናቸው።
እነዚህ በሀገር ውስጥ ሀብትና አቅም እየተፈጠሩና እየለሙ ወደ ሥራ የገቡ የፈጠራ ሥራዎች በማህበረሰቡ የዕለት ተዕለት ኑሮ ውስጥ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመለየት መፍትሔ ይዘው የመጡ ናቸው። እነዚህን አይነት የፈጠራ ሥራዎችን የማፍለቁና ወደ ሥራ የማስገባቱ ሥራም በስፋት ይታያል።
ከእነዚህ መካከል ለወላጆች እፎይታ ለመስጠት ታልሞ የተሠራውን ‹‹ለልጄ ሶልሽን ›› የፈጠራ ውጤትን በዚህ ጹሁፍ ይዘን ቀርበናል። አብዛኛቹ ወላጆች ብዙ ጊዜያቸውን በሥራ የሚያሳልፉ እንደመሆናቸው ልጆቻቸው በሰርቪስ ትራንስፖርት እንዲመላለሱ በማድረግ እነሱ ሥራ ሥራቸውን ይላሉ። ይህን የሚያደርጉት የልጆቻቸው እንዲጠበቅ በማሰብ ነው።
ወላጆች የሰርቪስ አገልግሎት ከሚሰጡ ድርጅቶች ወይም ግለሰቦች ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ይታወቃል። በዚህም ትምህርት ቤቶችና የትራንስፖርት (ሰርቪስ) አገልግሎት በሚሰጡ ግለሰቦችም ሆኑ ተቋማት ላይ እምነት የሚያሳድሩበት ሁኔታ ቢኖርም፣ ልጆቻቸው ወደ ትራንስፖርት ሲገቡም ሆነ ከትራንስፖርቱ ሲወርዱ እንዲሁም በጉዞ ወቅት ስለሚያጋጥማቸው ችግር የሚያረጋግጡበት መንገድ ከስልክ ያልዘለለ ነበር ማለት ይቻላል።
ተሽከርካሪዎች የቴክኒክ ችግር አጋጥሟቸው ወይም አደጋ ደርሶባቸው ተማሪዎች ከትምህርት ሲስተጓጎሉ ወይም አደጋ ሲደርስባቸው መረጃ የማግኛዎቹ መንገዶች አሽከርካሪዎች ወይም ተማሪዎችና ህብረተሰቡ እንደሆኑ ይታመናል። አንዳንዴ ቤተሰብ ካልደወለ በስተቀር ወላጆች መረጃ በፍጥነት የማያገኙበት ሁኔታ ያጋጥማል።
በሀገራችን ይህን ችግር ለመፍታት የሚረዱ፣ ወላጆች የልጆቻቸውን ደህንነት ባሉበት ሆነው ማረጋገጥ የሚያስችሏቸው ቴክኖሎጂዊዎች ወደ ሥራ እየገቡ ናቸው። ከእነዚህ የቴክኖሎጂ ውጤቶች መካከል አንዱ ‹‹ለልጄ ሶልሽን ›› የተሰኘው የሞባይል መተግበሪያ ነው።
የሞባይል መተግበሪያው ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ሲልኩና ልጆቹ ከትምህርት ቤት ሲመለሱ ከትራንስፖርት ጋር ተያይዞ የሚያጋጥማቸውን የደህንነት ችግር ለመፍታት ታልሞ የተዘጋጀ ነው።
ጸደንያ ፋሲል (ዶ/ር) ከ ‹‹ለልጄ ሶልሽን›› መሥራቾች አንዷ ናት። ቴክኖሎጂውን ከሁለት ጓደኞቿ ጋር በመሆኑም ነው እውን ያደረገችው። ዶክተር ጸደንያ የህክምና ትምህርቷን ተከታትላ ከጨረሰች በኋላ ወደ ሥራው ዓለም ተሰማርታ በአንድ ሆስፓታል ተቀጥራ የህክምና አገልግሎት በመስጠት ህብረተሰቡን ስታገለግል ቆይታለች።
በሥራ አጋጣሚ በተማሪዎች ላይ የተፈጠረ አንድ አደጋ ግን ይህን ሃሳብ እንድታመነጭ ምክንያት እንደሆናት ትናገራለች። እሷ እንዳለችው፤ ያ አደጋ የተከሰተው ተማሪዎች ከትምህርት ቤት ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ነው። መኪናው አደጋ ይደርስበታል፤ ሹፌሩም ጭምር ይጎዳል፤ በዚህ የተነሳ አደጋ መድረሱን የሚጠቁም መረጃ ለወላጆች የሚያደርስ ሰው አልነበረም።
በአካባቢው የተገኘው ህብረተሰብ ልጆቹ ሆስፒታል እንዲገቡ ቢያደርግም፣ ጥቂት ወላጆች መረጃው ቢደርሳቸውም፣ አብዛኛዎቹ ወላጆች ግን ስለልጆቻቸው የሚያውቁበት መንገድ አልነበራቸውም፤ በዚህ የተነሳም ለጭንቀትና ስጋት ተዳርገው፤ ሆስፒታሉም እንዲሁ በውጥረት ተሞልቶ እንደነበር ታስታውሳለች።
‹‹አብዛኛዎቹ ወላጆች ልጆቻቸው የት እንዳሉ የማያውቁ ሲሆን ወሬውን የሰሙ ጥቂቶች ደግሞ ወደ ሆስፒታሉ ይደውሉ ነበር፤ በዚህም ሳቢያ ትልቅ ውጥረት ተፈጥሮ ነበር›› ስትል ሁኔታውን አስታውሳ፣ ይህንን የወላጆች መረበሽና ጭንቀት ከተመለከተች በኋላ ውስጧ እረፍት እንዳጣ ትገልጻለች። መፍትሔ ፍለጋ ስባዝንም ትቆያለች፤ ሁኔታው ‹‹ለልጄ መተግበሪያ›› እውን መሆን ምክንያት ሆነ።
ጸደንያ (ዶ/ር) ከህክምና ሥራው ጎን ለጎንም ለዚህ ያግዙኛል ያለቻቸውን የተለያዩ ተያያዥ ሥልጠናዎች ወስዳለች። ይህም ሁኔታ በአእምሯዋ ስታወጣና ስታወርድ የቆየችውን ሃሳብ ተግባራዊ እንድታደርግ እድሉን ከፈተላት። ወላጆች ባሉበት ቦታ ሆነው የልጆቻቸውን ደህንነት የሚያረጋግጡበት ዲጂታል ፕላትፎርም ተግባር ላይ እንዲውል ለማድረግ ጠቅሟታል።
እሷ እንዳለችው፤ ለእዚህም ‹‹ለልጄ ሶልሽን›› የተሰኘውን ድርጅት በመክፈት መተግበሪያው ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ ተችሏል። ‹‹ለልጄ ሶሉሽን›› ብዙ የመፍትሔ ሃሳቦችን ይዟል። ከእነዚህ መካከል የመጀመሪያው ለልጄ የተሰኘው የትራንስፖርት ፕላትፎርም ነው። ይህ ፕላትፎርም በተለያዩ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ተማሪዎች ከቤታቸው ወጥተው ወደ ትምህርት ቤት የሚሄዱበትና ከትምህርት ቤት ወደ ቤት የሚመለሱበት ሁኔታ ደህንነቱ የተጠበቀ መሆኑን ወላጆች እንዲያውቁ የሚያደርግ ሥርዓት የተዘረጋለት ነው።
ፕላትፎርሙ ወላጆችንና የትራንስፖርት (የሰርቪስ )አገልግሎት ሰጪዎችን ያገናኛል። ለእዚህም የተማሪዎቹን ሙሉ መረጃ መዝግቦ ይይዛል። ተማሪዎች ወደ መኪናው ሲገቡም ሆነ ሲወርዱ መረጃ የሚይዝና ያሉበትን ሁኔታ አስመልክቶም ለወላጆች መልዕክት የሚያስተላልፍም ነው።
ቴክኖሎጂው አደጋ ቢከሰት ለወላጆች መልዕክት በማስተላለፍ ስለጉዳዩ እንዲያውቁ እንደሚያደርግ ታስረዳለች። ‹‹መተግበሪያው አደጋው እንዳይከሰት ማድረግ ባይችልም፣ በተቻለ መጠን የትራንስፖርት ሥርዓቱ ዲጂታል በሆነ መንገድ እንዲከናወን በማድረግ አደጋውንና የደህንነት ስጋቱን ለመቀነስ ያስችላል ብዬ አምናለሁ›› ብላለች።
ጸደኒያ (ዶ/ር) ሃሳቡ የፈጠራ ሥራውን የማልቱ ሥራ የተጀመረው በ2016 ሲሆን፣ ወደ ሥራ የተገባው ግን ባለፈው መስከረም ነው ስትል ጠቅሳ፣ ሥራው አዲስ እሳቤ ስለሆነ ህብረተሰቡ አምኖ ለመጠቀም ድፍረት አልነበረውም ብላለች፤ በዚህ የተነሳም ሥራው የተጀመረው በጥቂት ሰዎች እንደሆነም ትናገራለች። ድርጅቱ ሥራውን መስከረም ላይ ሲጀመር ሰባት ደንበኞች እንደነበሩት አስታውሳ፣ የማስተዋወቅ ሥራዎች መጀመራቸውን ተከትሎ ግን ሥራው እየታወቀና የደንበኞች ቁጥር እየጨመረ መጥቶ አሁን 30 መድረሱን አስታውቃለች።
በቅርቡም ማለዳ የተሰኘ ፕሮጀክት በማዘጋጀት በማህበራዊ ሚዲያ ላይ እያስተወወቁን ነው ስትል ገልጻ፣ ተደራሽነቱ እየሰፋ መጥቶ ከ120 በላይ ወላጆችና ከ180 በላይ ሹፌሮች መመዝገባቸውንም ገልጻለች። ሥራውን ከጀመርን አንስቶ ያሉት አራት ወራት ቢዝነሱን በምን መልኩ ማስኬድ ይቻላል የሚለውን እንድናውቅ ረድቷል ስትል አመልክታ፣ የትራንስፖርት አገልግሎቱ በምን መልኩ መስጠት እንዳለበትና ከትምህርት ቤቶችና ከወላጆች ጋርም እንዴት መሥራት እንዳለብን በደንብ እንድንረዳ እድል ሰጥቶናል ስትል ታብራራለች።
ይህ ሥራ በቀጣዩ የምንሰጠው የትራንስፖርት አገልግሎት የተሳለጠ እንዲሆን ይረዳናል ትላለች፤ አሁን ፕላትፎርሙን በማስተዋወቅና ሊንኩን አብሮ በመላክ ወላጆችም ሆኑ ሹፌሮች በሊንኩ አማካኝነት የተጠየቁትን ሙሉ መረጃ በመሙላት እንደሚመዘገቡም አመልክታለች።
የመረጃውን ትክክለኛነት ለማጣራት የሚፈልጉ አካላት በስልክ ደውለው ማጣራት የሚችሉበት መንገድ መኖሩን ትገልጻለች። ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ ድርጅቱ የተመዘገቡትን ሹፌሮች ማንነት የማጣራት ሥራ እንደሚያካሄድ ጠቅሳ፣ አስፈላጊ መረጃዎች ከተወሰዱ በኋላም ውል እንዲገቡ እንደሚያደርግ ተናግራለች። ወላጆችም ሆነ ሹፌሮች ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ በዚያው መሠረት ሥራው እንደሚጀመር አስታውቃለች።
አንዳንድ ሹፌሮች ሥራውን በራሳቸው ፈቃድ የሚያቋርጡበትና በመሃል የሚቀሩበት ሁኔታም እንዳለ ጠቁማ፣ እንደዚህ አይነት ነገሮች እንዳይፈጠሩ ሥራውን ከመጀመራቸው በፊት ተረድተውና አምነውበት እንዲሠሩ እንደሚደረግ አመላክታለች።
ጸደንያ (ዶ/ር) እንደ ዶልፊንና፣ ሚኒባስ ባስ አይነት ሰርቪሶች ሞግዚቶች እንዲኖራቸው እንደሚያስፈልግ ጠቅሳ፣ ከተማሪዎች ጋር ግንኙነት ላላቸው ለእነዚህ ሞግዚቶችና ሾፌሮች ድርጅቱ ሥልጠናዎች ይሰጣል ብላለች። ሞግዚቶች መኖራቸው ሹፌሩ ከመኪና እየወረደ ተማሪዎችን መንገድ ማሻገርና ቤት ማስገባት ውስጥ እንዳይገባ ያደርጋል ስትል አብራርታ፣ ይህ ሁኔታ የሚባክነውን ጊዜ ለመቀነስና ተማሪዎቹ በሰዓቱ ወደ ቤታቸው እንዲደርሱ እንደሚያስችል አስታውቃለች። ሞግዚቶቹም በሚሰጣቸው ሥልጠና መሠረት ተማሪዎቹን እንደሚቆጣጠሩም ጭምር ተናግራለች።
እሷ እንዳብራራችው፤ የክፍያ ሥርዓቱ ኪሎ ሜትርና የተለያዩ ሁኔታዎችን (የነዳጅ ዋጋ፣ የመንገድ ላይ ቆይታ ጊዜ፣ የመንገድ ሁኔታ እና የመሳሳሉትን/ ከግምት ውስጥ ያስገባ ነው። በዚህ ክፍያ ሥርዓት መሠረትም ወላጆች ክፍያ ይፈጽማሉ፤ የሹፌሮችም ክፍያ በወሩ መጨረሻ ይከናወናል። የድርጅቱ ገቢ ከሰጠው አገልግሎት የሚያገኘው ኮሚሽን ብቻ ይሆናል።
አገልግሎቱ በአያት፣ ሰሚት፣ ሜክሲኮ፣ ጀሞ፣ ፒያሳ መጀመሩን ጠቅሳ እየተሠራ ባለው የማስታወቂያ ሥራ ከየቦታው ደንበኞችን ማግኘት መቻሉን ገልጻለች።
አገልግሎቱን የሚፈልጉ ሰዎች ሞባይል መተግበሪያውን በማውረድ በተቀመጠው ሊንክ ሊመዘገቡ እንደሚችሉም ተናግራ፣ አገልግሎቱ አዲስ እንደመሆኑ ሰዎች እውነተኛነቱን ለማረጋገጥ እንደሚፈልጉ አመልክታለች። ‹‹ሰዎች የማስታወቂያዎቹን እውነተኛነት እየተጠራጠሩም ለማጣራት እኛ ጋ ይደውላሉ፤ በሊንኩም ገብተው የሚመዘገቡም አሉ›› ስትልም አብራርታለች።
ድርጅቱ በተቋቋመ አጭር ጊዜ ውስጥም ለ180 ሹፌሮችና ከሰባት በላይ ለሚሆኑ ሠራተኞች የሥራ እድል መፍጠሩንም አስታውቃለች፤ በቀጣይ ተደራሽነቱ እየሰፋና ሌሎች አገልግሎቶችን መስጠት እየጨመረ ሲሄድ ለብዙ ዜጎች የሥራ እድል ሊፈጥር እንደሚችል ጠቁማለች።
ድርጅቱ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከኮሪያ ዓለም አቀፍ ትብብር ኮይኮ ጋር በመተባበር ባዘጋጀው የአምስት ወራት ሥልጠና እድል ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል እንደነበር የምትገልጸው ዶክተር ጸደንያ፤ በሥልጠናው ከአንድ እስከ አራተኛ ደረጃ ከያዙት መካከል መሆኑን ትገልጻለች።
እሷ እንዳለችው፤ ከሥልጠናው አማካሪ ተመድቦላቸው እገዛ ተደርጎላቸዋል፤ ይህም ክፍተቶቻቸውን በደንብ ማየት በማስቻል ወደ ቢዝነሱ ለመግባት ማድረግ ያለባቸውን በተለይ በገበያ ወይም በገቢ ላይ መሥራት ያለባቸውንም አመላክቷቸዋል። ‹‹ሥልጠናው የደንበኞች ቁጥር እንዲጨምር በማድረግና በምናደርገው ስምምነትና በምናገኘው ገቢ ላይም ትልቅ ለውጥ እንድናመጣ አስችሎናል›› ብላለች ።
ጸደኒያ (ዶ/ር) እንዳለችው፤ ድርጅቱ መጀመሪያ ወደ ሥራው ሲገባ ብዙ ወላጆች አገልግሎቱን ለመጠቀም ፍቃደኛ አልነበሩም። ቀስ በቀስ ለልጆቻቸው የሚሰጠው አገልግሎት ደህንነቱ የተጠበቀ መሆኑ ሲገባቸው ብዙዎች አገልግሎቱን ለመጠቀም ፍቃደኛ እየሆኑ መጥተዋል። የወላጆች ዋንኛ ፍላጎት ‹ልጄ ደህንነቱ በተጠበቀ መንገድ ወጥቶ በሰላም ተመልሏል ወይ › የሚለው ነው ስትል ጠቅሳ፣ ከዚህ አንጻር የቀረበው አገልግሎት ለወላጆች እረፍት እንደሚሰጥ ተናግራለች።
እሷ እንዳስታወቀችው፤ ድርጅቱ ጀማሪ ስታርትአፕ እንደመሆኑ በብዙ ሙከራዎች ውስጥ አልፎ አሁን ላለበት ደረጃ ደርሷል። በቀጣይ ድርጅቱ ያለውን አሠራር አጠናክሮ ተደራሽነቱን በማስፋት የደንበኞችን ቁጥር ለመጨመርና ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በክልል ከተሞችም አገልግሎቱን ለማስፋት አቅዶ እየሠራ ነው።
ጀማሪ ስታርትአፕ መሆን በብዙ ተግዳሮቶች ውስጥ ማለፍ የግድ ሊል ይችላል፤ እንደኛ አይነት ጀማሪዎች ይህንን ከግንዛቤ ማስገባት አለባቸው። ‹‹ወደሥራው ሲገቡ ብዙ ተግዳሮቶች እንደሚያጋጥማቸው በማሰብ ተስፋ ሳይቆርጡ ችግሩን እንዴት ሊሻገሩት እንደሚችሉ እያሰቡ መጓዝ ይጠበቅባቸዋል›› ስትልም መክራለች።
በሌላ በኩል ድርጅቱ በቀጣይ መስከረም አዲስ አገልግሎት እንደሚጀምርም ጸደንያ (ዶ/ር) ጠቁማለች። ይህ አገልግሎት ‹‹ዋን ታይም›› ሰርቪስ አገልግሎት የሚባል መሆኑን ጠቅሳ፣ ይህም የሰርቪስ አገልግሎት የሚፈልጉ ተማሪዎች በሙሉ ምዝገባ ሲያካሂዱ ዲጂታል መታወቂያ የሚሰጥበት መሆኑን አስታውቃለች።
ተማሪዎች ዲጂታል መታወቂያ እንዲኖራቸው መደረጉ ሰርቪስ ቢያመልጣቸው በሌላ የድርጅቱን ሎጎ በለጠፈ ማንኛውም የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪ ዲጂታል መታወቂያቸውን ስካን በማድረግ ብቻ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ እንደሚያስችላቸውም ጠቁመዋል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ማክሰኞ የካቲት 18 ቀን 2017 ዓ.ም