
አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያን ከለላ ፈልገው የሚመጡ ስደተኞች ቁጥር ቢጨምርም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚያደርገው ድጋፍ እየቀነሰ መምጣት ተግዳሮት እንደሆነበት የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት አስታወቀ።
የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ብሩህተስፋ ሙሉጌታ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ስደተኞችን ተቀብላ በማስተናገድ የረጅም ጊዜ ታሪክ አላት። አሁን ላይም ሀገራዊና የዓለም አቀፍ ሕጎችን መሠረት በማድረግ ከአንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን በላይ ስደተኞችን ተቀብላ እያስተናገደች ትገኛለች።
የስደተኛ ቁጥር እየጨመረ ቢመጣም የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድጋፍ ከጊዜ ወደጊዜ እየቀነሰ መምጣቱ እንደሀገር ተግዳሮት መሆኑን ጠቁመዋል።
በ1951 ኮንቬንሽን መሠረት ለስደተኞች ድጋፍ የሚደረገው በተቀባይ ሀገራትና በለጋሽ ሀገራት ትብብር ነው ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ይህን ዓለም አቀፍ ድንጋጌ አክብሮ ስደተኞችን እየተቀበለና ከለላ እየሰጠ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል።፡ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም እነዚህን ስደተኞች በመደገፍ ግዴታውን መወጣት ይጠበቅበታል ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በሚሰጠው ከለላና ድጋፍ እንዲሁም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በሚያደርገው ድጋፍ ስደተኞችን ተቀብለን እያስተናገድን እንገኛለን ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ በዚህ ሂደት ውስጥ ዋንኛው ተዋናይ ተቀባዩ ማኅበረሰብ የሚያጋጥሙ ተፅዕኖዎችን ተቋቁሞ ስደተኞችን ለመቀበልና አብሮ ለመኖር የሚወስደው ኃላፊነትም ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው።
ስደተኞችን ተቀብሎ በማስተናገድ ሂደት የተለያዩ ተግዳሮቶች ቢኖሩም፤ ከአጋር አካላትና ከተቀባዩ ማኅበረሰብ ጋር በመሆን ከለላውን እስካሁን ማረጋገጥ ተችሏል።
ሰዎች በሀገራቸው ባጋጠማቸው ችግር ምክንያት ተሰደው ወደ እኛ ይመጣሉ ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ እንደሀገር የእነዚህን ስደተኞች ፍላጎት ለማሟላት ከፍተኛ ችግር ይስተዋላል።
ስለሆነም የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ግዴታውን እንደተወጣ ሁሉ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት ጠቁመዋል።
ይህን ችግር በዘላቂነት መፍታት እንዲቻል ኢትዮጵያ የስደተኞች አካታችነትን እየተገበረች ነው ያሉት አቶ ብሩህተስፋ፤ በዚህም ስደተኞችንና ተቀባይ ማኅበረሰቡን በዘላቂነት ማቋቋም የሚቻልበትን መንገድ ለመፍጠር እየሠራች ነው ብለዋል።
አካታችነትን በሙሉ አቅም መተግበር ከተቻለ ዓለም አቀፍ ርዳታ ቢቀንስም ስደተኞችን ተቀብሎ ማስተናገድ የሚያስችል አቅም እንደሚፈጥር ጠቅሰው፤ ይሁን እንጂ አካታችነትን ለመተግበር በራሱ ከፍተኛ ሀብት ይፈልጋል ነው ያሉት።
ስደተኞች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሲፈቀድ ሥራውን መፍጠር የሚያስችል ሀብት መኖር እንዳለበት በማሳያነት ያነሱት አቶ ብሩህተስፋ፤ በተጨማሪም የሚጋሩት የተቀባዩን ማኅበረሰብ ሀብት ስለሆነ የሚተገበሩ ፕሮግራሞች ተቀባይ ማኅበረሰቡንም የሚያካትት መሆን ይኖርበታል።
ይህን ከግምት በማስገባት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚያደርገውን ድጋፍ በማጠናከር ኢትዮጵያ ለስደተኞች የምታደርገውን ድጋፍና የምትሰጠውን ከለላ ሊያግዝ እንደሚገባ አመላክተዋል።
ኢትዮጵያ ስደተኞች ተገቢውን አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉ በብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ውስጥ እንዲካተቱ ማድረጓንም ምክትል ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል።
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን የካቲት 18 ቀን 2017 ዓ.ም