በፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የተመራ ልዑክ በሶማሊያ የሥራ ጉብኝት አደረገ

አዲስ አበባ፦ በጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የተመራ ልዑክ በሶማሊያ የሥራ ጉብኝት አድርጓል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ መሃሙድ ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ባደረጉት ውይይት፤ በቀጣይ በሞቃዲሾ የቴክኒክ ውይይት እንዲደረግ ባስቀመጡት አቅጣጫ መሠረት ነው ልዑኩ ጉብኝቱን ያደረገው፡፡

በጉብኝቱ ላይ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡

የሶማሊያ ብሔራዊ ጦር ኃይሎች የመከላከያ ሠራዊት አዛዥ ሜጀር ጀነራል ኦዳዋ ዩሱፍ ራጌ እና የሀገሪቱ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ኤጀንሲ (NISA) ዳይሬክተር አምባሳደር አብዱላሂ መሀመድ አሊ ለልዑኩ ደማቅ አቀባበል አድርገዋል፡፡

የመከላከያ ሠራዊት አዛዡ እና ዳይሬክተሩ በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል እየጠነከረ የመጣውን ግንኙነት አድንቀዋል፡፡ ኢትዮጵያ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት እና ለቀጣናዊ ሰላም እያበረከተች ያለችውን አስተዋጽኦም አጠናክራ እንደምትቀጥል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት የሚከተለውና ለጎረቤት ሀገራት ቅድሚያ የሚሰጠው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲም ለአፍሪካ ቀንድ ብሎም ለአህጉሪቱ ሰላም የላቀ ፋይዳ እንዳለው አንስተው፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በአፍሪካ ኅብረት የሶማሊያ ሰላም አስከባሪ ኃይል (አሚሶም) ተልዕኮ ላይ ያለውን የላቀ ሚናም አውስተዋል፡፡

እ.አ.አ ከ2007 ጀምሮ ለሶማሊያ መረጋጋት መስዋዕትነት ለከፈሉ በአፍሪካ ኅብረት የሶማሊያ ሰላም አስከባሪ ኃይል (አሚሶም) ፣ አትሚስ እና ሌሎች የጸጥታ ኃይሎችም ዕውቅና እና ክብር ሰጥተዋል።

በአሚሶም እና አትሚስ የተመዘገቡ ድሎችን አጽንቶ ማስቀጠል ለሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም እና ልማት ያለውን ፋይዳም አመላክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ የጦር ኃይሎች እና የመረጃና ደኅንነት ተቋማት አመራሮች በሶማሊያ እና በቀጣናው ስላለው የጸጥታ ሁኔታ በመምከር፤ በአፍሪካ ቀንድ ሰላም፣ ደኅንነት እና መረጋጋትን ማስጠበቅ እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በውይይቱ ላይ ኢትዮጵያ ለቀጣናው መረጋጋት ያላት ሚና በአድናቆት የተነሳ ሲሆን፤ የአንካራው ስምምነት ተጨባጭ ውጤት እያመጣ መሆኑም የሀገራቱ ጥምር ኮሜቴ መረጃ ያመላክታል፡፡

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን የካቲት 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You