እፎይታ ያገኙት የእንጦጦ ተራራ ባተሌዎች

ዜና ሐተታ

በአዲስ አበባ እንጦጦ ጫካ እንጨት እና ቅጠል ለቅመው በመሸጥ ቤተሰባቸውን የሚያስተዳድሩ ባተሌዎች ብዙ ናቸው። ሥራቸው በአደጋ የተከበበ ነው፤ መውደቅ፣ መነሳት፣ መሸከም፣ መጓዝ ይበዛዋል፤ እስከ አስገድዶ መደፈር የሚያደርስና ለድብደባም የሚያጋልጥ አደጋም የተጋረጠበት እንደሆነ ይነገራል፡፡

ወይዘሮ ዮርዳኖስ ሚዴቅሳ 14 ዓመታትን ከእንጦጦ ተራራ ቅጠል ለቅመው በመሸጥ ሕይወታቸውን መርተዋል፡ ፡ በእንጦጦ ተራራ ቅጠል እየለቀሙ ገበያ ወስደው ሲሸጡ ብዙ ፈተናዎችን አሳልፈዋል፡፡

የዕለት ገቢ በሚያገኙበት ቅጠል ለቀማም ጥቅጥቅ ያለውን ጫካ ተገን አድርገው ቅጠል የሚለቅሙ ሴቶችን የሚደፍሩና ገንዘብ አምጡ ባይ ቀማኞችን ጭምር ተጋፍጠው በሚያገኙት ገቢም አራት ልጆች አሳድገዋል፣ አስተምረዋል፡፡

ቅጠል እየለቀሙ በመሸጥ የሚገኝ ገቢ ሕይወትን የሚለወጥ አለመሆኑ ቢታመንም ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ሕይወትን ለመምራት ግን እንደአማራጭ ሆኗቸዋል። ሞራል የሚነካው የሰዎች ንግግርም ያስከፋቸው እና ያስተክዛቸው እንደነበር አልሸሸጉም፡፡

ልጆቻቸውም የእንጨት ተሸካሚ ልጅ እየተባሉ ይሰደቡ ነበር አሁን ግን ልጆቻችን ይኮሩብናል እኛም ሞራል አግኝተናል ይላሉ፡፡ ወይዘሮ ዮርዳኖስ፤ ‹‹እግዚአብሔር ይመስገን የጉለሌ እንጀራ ማዕከል ተሠርቶ መጠናቀቅ አሁን ለእኛ መልካም ዕድል ይዞልን መጥቷል›› ይላሉ፡፡

ከደረቀ ዛፍ ጭራሮ ሲያወርዱ፣ ቅጠል ሲለቅሙ ወድቀው ጤናቸው የተቃወሱ እናቶችና ወጣት ሴቶች ቁጥር ትንሽ እንዳልሆነም ይናገራሉ። 2016 ዓ.ም አዲሱ ሥራቸውን የጀመሩበት ቀን መሆኑን ነግረውናል፡፡ አዲሱ ሥራቸው በጉለሌ እንጀራ ማዕከል እንጀራ መጋገር እንደሆነ ገልፀውልናል።

የወደፊት ተስፋቸው ብሩህ መሆኑን የገለጹት ወይዘሮ ዮርዳኖስ፤ ሆኖም በዕለት ገቢ ሲተዳደሩ የነበሩ በመሆናቸው ለጊዜው ወርሐዊ ገቢ መጠበቅ ትንሽ ከበድ ቢልም መንግሥት የሚያደርገው ነገር ይበልጥ ይጠቅመናል እንጂ አይጎዳንም በሚል በትልቅ ተስፋ እየሠራን እንገኛለን ብለዋል፡፡

ቅጠል በመልቀም ሲተዳደሩ እንደቆዩ የገለጹልን ሌላዋ እናት ደግሞ ወይዘሮ ታደለች ሻጋ ይባላሉ፡፡ አስር ዓመታትን በእንጦጦ ቅጠል በመልቀም ቤተሰብ ሲያስተዳድሩ እንደነበር ነግረውናል፡፡

“በእንጦጦ ጫካ ቅጠል ሲለቅሙ ብዙ አደጋዎችንም ተጋፍጠህ ነው፡፡ ጫካው የሚገኝበት ቦታ ወጣ ገባ በመሆኑ የመውደቅና ለጉዳት የመጋለጥ ክስተትም ብዙ ነው“ የሚሉት ወይዘሮ ታደለች፤ ከቀድሞ የእንጨት ለቀማ ሥራቸው ያላቀቃቸው የጉለሌ እንጀራ ማዕከል መሆኑን ይናገራሉ።

‹‹መንግሥት ይህን ልፋታችንን አይቶ ከአስቸጋሪ ሕይወት ስለታደገን እናመሰግናለን ብለዋል፡፡››

የልጆቻቸውን ሕይወት ለማሻሻል ለስደት እየተዘጋጁ ባለበት ሁኔታ በጉለሌ እንጀራ ማዕከል የሥራ ዕድል ሰለተፈጠረላቸው ከሰው ሀገር ይልቅ በሀገራቸው መሥራትን መርጠዋል።

አሁን ላይ እንጀራ ቀንና ሌሊት በመጋገር ሕይወታቸውን ለማሻሻል እየሠሩ መሆናቸውን ተናግረው፤ እንጨት ከመሸከም ያዳናቸውን አምላክ አመስግነዋል። ልጆቻቸው የእንጨት ተሸካሚ ልጅ ከመባል መዳናቸው ደስታ እንደተሰማቸውም ገልፀዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተገነባው የጉለሌ እንጀራ ማዕከል በአካባቢው እንጨት በመልቀም ለሚተዳደሩ 551 እናቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታስቦ የተገነባ ነው። ለከተማዋ ሁለተኛው የእንጀራ ፋብሪካም ነው። 450 ዘመናዊ የእንጀራ መጋገሪያ ምጣድ ተገጥሞለታል፣ 551 እናቶች በሁለት ፈረቃ ተከፍለው ይሠሩበታል፡፡ ሁለት የእንጀራ መጋገሪያ ሕንጻዎች፣ የሕጻናት ማቆያ፣ የእህል ማከማቻና ወፍጮ፣ ልዩ ልዩ አገልግሎት የሚሰጡ ማዕከላትን ያካተተ ነው።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት በመዲናዋ እየተሠሩ ያሉ የወንዝ ዳር ፕሮጀክቶችን፣ የፍሳሽ ማስወገጃ ሥራዎች፣ የከተማ ግብርናን፣ የኮሪደር ልማት ሥራዎችን፣ የእንጀራ ማዕከላት እና ሌሎች የልማት ሥራዎችን በጎበኘበት ወቅት በእንጀራ መጋገሪያው ማዕከል የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸውን እናቶች አነጋግረን ያጠናቀርነው ዘገባ ነው፡፡

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 15 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You