«ሕገወጥ ግንባታን ሲያካሂዱ በተገኙ 2ሺ 454 ግለሰቦች ላይ ርምጃ ተወስዷል»ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ

ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ

ሀገር የምትመራው በሕግ እና በሥርዓት ነው፡፡ በተደራጀ ማኅበረሰብ ውስጥ ሕጎች እና መመሪያዎች የማኅበራዊ እና የአስተዳደር ሥርዓት የጀርባ አጥንት ሆነው ያገለግላሉ።

ሕግ ግለሰቦች እና ድርጅቶች ከኅብረተሰባዊ እሴቶች እና ደንቦች ጋር በሚጣጣም መንገድ እንዲሠሩ የአተገባበር ማሕቀፍ ናቸው። መንግሥታት ሕጎችን የሚያወጡት እንደ ፓርላማ ወይም ኮንግረስ ባሉ የሕግ አውጪ አካላት አማካኝነት ነው። በእነዚህ አካላት የሚወጡ ሕጎች ለደንቦች መሠረት ይሆናሉ፡፡

ሕጎች መደበኛ የሆኑ እና መደበኛ ያልሆኑ (ማህበራዊ ደንቦች) በመባልም ይከፈላሉ፡፡ መደበኛ ሕግ የሚባለው ሕጎች ከሚቀዱበት ሕገ መንግሥት ጀምሮ እስከ ፖሊሲ ማስፈጸሚያ የሚደርሱትን ደንቦች የሚያጠቃልል ነውአዋጆችም ሕገ መንግሥቱን መሠረት አድርገው የሚወጡ ሲሆን መመሪያዎች ደግሞ ከአዋጆች ይቀዳሉ፡፡ መመሪያዎችን መሠረት በማድረግም የማስፈጸሚያ ደንቦች ይወጣሉ፡፡

ለምሳሌ፣ አንድ ሕግ የካርበን ልቀትን ለመቀነስ የሚያስችሉ ሕጎችን ሊይዝ ይችላል፡፡ ይህም ሕግን መሠረት በማድረግ ተቆጣጣሪ ኤጀንሲዎች መመሪያዎችን ያዘጋጃሉ።

ሕጎች እና መመሪያዎች ለሥርዓት፣ ለፍትህ እና ለደህንነት ዋስትና ናቸው። እነዚህን ደንቦች በማውጣት፣ በማስፈጸም እና በማስተካከል የኅብረተሰቡን እሴትና ፍላጎት የሚያንፀባርቁ ሆነው እንዲተገበሩም መንግሥት ወሳኝ ሚና ይጫወታል።

ደንቦች መመሪያዎችን ግልጽ በማድረግ ለአተገባበር ምቹ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ የግለሰቦችን መብቶችን እና ነፃነቶችን ለማስጠበቅም ወሳኝ ናቸው። ይህም ሲባል ሕገ ወጦች በሚሄዱት አካሄድ ሕጋዊ የሆኑ ግለሰቦች መብቶቻቸው እንዳይጣስ ለማድረግም ጉልህ ሚና አለው፡፡

በመዲናችን አዲስ አበባ ሕግን የሚተላለፉ፤ አሠራር የሚጥሱ አካላትን ለማስተማር በከተማ አስተዳደሩ በአዋጅ የተቋቋመው የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን፤ ሕገ ወጥ ንግድ፤ ሕገ ወጥ ግንባታና መሰል ከአሠራርና ከሥርዓት ውጭ የሚከናወኑ የሥራ እንቅስቃሴዎች ሥርዓት እንዲይዙ የሚሠራ ተቋም ነው፡፡

ሕጎችን እና ደንቦችን ለማስከበር 2003 . ጀምሮ የተቋቋመው የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን የሥራ አፈጻጸም፤ ከሕገ ወጥ ንግድ ጋር እና ተቋሙ ሕግን በሚያስከብርባቸው ጉዳዮች ግንዛቤ ከመስጠት ባለፈ ምን ሠራ? አዋኪ የሆኑ ተግባራት ላይ በሚሰማሩ ተቋማት ላይ ምን ዓይነት ርምጃ ተወሰደ? የባለሥልጣኑ ስያሜው እና ተግባሩ ደንብን እና ሕግን ማስከበር ሆኖ ሳለ አንዳንድ የተቋሙ ሠራተኞች ሕግን ሲተላለፉ ምን ዓይነት የእርምት ርምጃ ይወሰዳል? በሚሉና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ ባለሥልጣኑ እያከናወናቸው ባሉ ተግባራት ዙሪያ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራን የተጠየቅ ዓምዳችን እንግዳ አድርገን እንደሚከተለው አጠናቅረነዋል፡፡

አዲስ ዘመን፡የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን የተደራጀበት ዋና ዓላማ ምንድን ነው?

ሻለቃ ዘሪሁን፡የደንብ ማስከበር ባለሥልጣን በ2003 ዓ.ም የተቋቋመ ተቋም ነው፤ ለደንብ ማስከበር ባለሥልጣኑ የጸደቁ፤ ለደንብ ማስከበር አፈጻጸም መደላደልን የሚፈጥሩ አዋጆች እና ደንቦች አሉት፡፡

ተቋሙ በ2003 ዓ.ም በከተማ አስተዳደሩ ቡድን መሪ ስር የተደራጀ እና ከዚያም በአዋጅ ቁጥር 37/2005 ራሱን ችሎ ለከንቲባው ተጠሪ እንዲሆን ተደርጎ የተቋቋመ ነው፡፡ በወቅቱም ተቋሙ በጽሕፈት ቤት ደረጃ የተዋቀረ በመሆኑ የራሱ ሥልጣን፤ ኃላፊነቶች እና ተግባራቱም በዝርዝር በደንብ ቁጥር 54/2005 ተቀምጠውለታል፡፡

በአዋጅ ቁጥር 64/2011 ዘርፍ ሆኖ ከሰላምና ጸጥታ ቢሮ ጋር በመቀናጀት እንዲሠራ በአዋጅ ቁጥር 74/2014 በድጋሚ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት ሆኖ ተዋቅሯል፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ ተቋሙ በተለያየ ጊዜ በተለያየ አደረጃጀቶች በሕግ ተቋቁሟል፡፡

ባለሥልጣን ሆኖ ከተደራጀ በኋላ በከተማ አስተዳደሩ ጸድቆ ወደ ተቋሙ የመጣ ቁጥር 150/2016 ደንብ አለ፡፡ ይህ ደንብ ለተቋሙ በርካታ ኃላፊነቶችን ይዞ የመጣ ነው፡፡ የመጀመሪያው ተቋሙ ከተቋቋመበት አላማ አንጻር ምን ምን ሥራዎችን ማከናወን አለበት? ምን ዓይነት ርምጃዎችን ይወስዳል? ምን ኃላፊነት አለበት? የሚለውን በዝርዝር ይዟል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከተማዋን ንጹህ፤ ጽዱ እና ዘመናዊ ለማድረግ በርካታ ተግባራቶችን ያከናውናል፡፡ ከዚህም ውስጥ የልማት ኮሪደር ሥራ አንዱ እና ዋነኛው ነው፡፡ የመጀመሪያው የልማት ኮሪደር ሥራ ተጠናቆ ለሕዝብ ክፍት ተደርጓል። ከዚህ ጋር በተያያዘ የደንብ ማስከበር ተቋሙ ሊያከውናቸው የሚገቡ ሥራዎችን በኃላፊነት እየሠራን ነው፡፡ ይህንንም ለማከናወን የመጀመሪያው ደንብ ቁጥር 150/2016 ተሻሽሎ በደንብ ቁጥር 167/2016 መሠረት ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡

ከከተማዋ እድገት ጋር ተያይዘው የሚወጡት ደንቦች ከጊዜ ወደ ጊዜ የተቋሙን የሥራ አፈጻጸም ያጠናከሩ ናቸው፡፡

አዲስ ዘመን፡ተቋሙ የተቋቋመበትን ተልዕኮ ለማሳካት ምን ዓይነት ሥራዎችን እየሠራ ነው?

ሻለቃ ዘሪሁን፡ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ 18 የሚሆኑ ተልዕኮዎች አሉት፡፡ ከነዚህ ውስጥ ዘጠኙ በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ተልዕኮው ኅብረተሰቡን በማሳተፍ እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት የደንብ መተላለፎችንና ተያያዥ ሕገ ወጥ ተግባራትን መከላከል፤ መቆጣጠር፤ ርምጃ መውሰድ፤ እንዲሁም የኦፕሬሽንን ሥራን ማስተባበርን ያካትታል፡፡

ሁለተኛ ተልዕኮው ሕብረተሰቡ ከደንብ ማስከበር ጋር በተያያዘ የወጡ ሕጎችና ደንቦች ዙሪያ በተለያዩ ግንዛቤ እንዲጨብጥ ይሠራል፡፡ ለዚህም የተለያዩ መድረኮችን ይፈጥራል፤ ሚዲያዎችን ይጠቀማል፤ በብሎክ እና በቡና ጠጡ አደረጃጀቶች ግንዛቤ ይፈጥራል፡፡

ሶስተኛ ተልዕኮው ከሚመለከተው አካል ጋር በጋራ በመሆን የተለያዩ ሕገወጥ ግንባታዎችን፤ የመሬት ወረራን እና በሕገ ወጥ መንገድ የመሬት ማስፋፋት ተግባራትን የመከላከል፤ የመቆጣጠር እና ሕጋዊ ርምጃን የመውሰድ ሥራ ይሠራል፡፡

አራተኛው ሕገ ወጥ የመንገድ ላይ ንግድን መቆጣጠር ነው፡፡ ይህም ሲባል መንገድ ላይ ብቻ የሚደረገውን ሳይሆን የበረንዳ ላይ (ከሱቅ ውጭ) ንግድንም ይጨምራል፡፡ ተቋሙ ሕጋዊ ሥርዓትን ሳይከተል የታረደ የእንስሳት ሥጋ እና ሕገ ወጥ የቁም ከብት ዝውውርን የመከታተል እና የመቆጣጠር ኃላፊነት አለበት፡፡

አምስተኛ ተልዕኮው በክፍት እና ዝግ የመናፈሻ ቦታዎች፤ በመንገድ አካፋዮች ዳርቻ እና አደባባዮች የሚከናወኑ ሕገወጥ ተግባራትን ይከላከላል፤ ይቆጣጠራል፤ እንዲሁም ርምጃ ይወስዳል፡፡

ስድስተኛ ደረጃ በትራፊክ እንቅስቃሴ እና ደህንነትን ላይ ሁከት የሚፈጥሩ በመንገድ ወይም በትራፊክ መብራት ላይ የሚከናወኑ ልመና፤ ንግድ እና እቃዎች በመደርደር መንገድ የመዝጋት አካሄዶችን የመከላከል፤ የመቆጣጠር እና ርምጃ የመውሰድ ኃላፊነት አለበት፡፡

ሰባተኛው ተልዕኮው ያለ ከተማ ፕላኑ የመንገድ ላይ ዛፍ ወይም አትክልት መትከል እና ድንኳን መትከል፤ ተረፈ ምርቶችን በመንገድ ላይ መጣል ለምሳሌም የህንጻ ግንባታ አሸዋ እና ድንጋዮችን በአጠቃላይ ለህንጻ ግንባታ አስፈላጊ በሆኑ ግብዓቶች በመንገድ ዳር በመጣል የትራፊክ እንቅስቃሴውን የሚያውኩ ግለሰቦች እና ተቋማት ላይ ርምጃ ይወስዳል፡፡

ሌላው ተልዕኮው ስምንተኛው ተልዕኮው፤ መንገዶችን ማሻሻል፤ መቀየር፤ መቀየስ፤ መዝጋት እና ማጠር የመሳሰሉ ተግባራት ላይ የእርምት ርምጃ ይወስዳል፡፡

ዘጠነኛው በመንገድ መብራት ምሶሶ እና ድልድይ ላይ፤ በመንገድ ምልክት እና በእግረኛ መንገድ ማካለያ ሕገ ወጥ ማስታወቂያዎችን መለጠፍን ይከላከላል፡፡

በተጨማሪም በሕገ ወጥ መንገድ ከድርጅት፤ ከፋብሪካ እና ከመኖሪያ ቤት የሚለቀቁ ደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻዎችን ይከታተላል፤ ይቆጣጠራል ርምጃ ይወስዳል፡፡

በመኖሪያ ቤት አካባቢ አዋኪ ተግባራትን የሚያከናውኑ ግለሰቦች ላይ ርምጃ ይወስዳል፡፡ ለምሳሌ በጋራ መኖሪያዎች አካባቢ ሺሻ ማጨስ፤ ጫት መቃም፤ ቁማር፤ ጆተኒ እና ሌሎችንም አዋኪ ተግባራት የሚያከናውኑትን ይቆጣጠራል፡፡

በትምህርት ቤቶች አካባቢ ላይ በተመሳሳይ ከሕግ እና ከባሕል ያፈነገጡ ተግባራትን ይቆጣጠራል። ለምሳሌም በትምህርት ቤቶች ዙሪያ የመማር ማስተማር ሂደቱን የሚያውኩ እንደ መጠጥ ቤት ያሉ እና ፔንሲዮኖች (አልጋ ቤቶች) ላይ እስከ መዝጋት የሚደርስ ርምጃ ይወስዳል፡፡

ከተልዕኮ አንጻር የደንብ መጣሶች ላይ ጥናት ያደርጋል፡፡ በጥናቶቹ በመመሥረትም እቅዶችን ያቅዳል፡፡ የትኞቹ ደንቦች ላይ ከፍተኛ ጥሰት ይከሰታል? የሚለውንም መነሻ በማድረግ ለኅብረተሰቡ የተለያዩ የግንዛቤ መድረኮችን አዘጋጅቶ ጥሰቶችን አስቀድሞ ለመከላከል ሥራዎችን ይሠራል።

ተቋሙ በሥሩ 6ሺ012 የደንብ አስከባሪ ኦፊሰሮች አሉት፡፡ አሁንም ተጨማሪ 2ሺ ኦፊሰሮችን ለማሰልጠን ማስታወቂያ አውጥተናል፡፡ ኦፊሰሮቹ ሥልጠናውን ሲጨርሱም ስምሪቶችን በመስጠት ደንብ የማስከበር ሥራውን አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡

አዲስ ዘመን፡ተቋሙ 2017 . በዋናነት አሳክቼዋለሁ የሚለው ተግባሩ የትኛውን ነው?

ሻለቃ ዘሪሁን፡ተቋሙ በየዓመቱ እቅዶችን ሲያቅድና ወደ ተግባር ሲገባ ከኅብረተሰቡ እና ከሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ጋር ውይይት በማድረግ ነው፡፡ በ2017 ዓ.ም ሊያከናውናቸው ያቀዳቸው በርካታ እቅዶች አሉት፤ ከእነዚያ ውስጥ በመጀመሪያ ግማሽ ዓመት ያሳካነው ዋናው ነገር የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ ነው፡፡

ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ አንዱ የቅድመ መከላከል ሥራ ነው፡፡ ይህንንም ሁለት ሚሊዮን ለሚገመት የከተማዋ ነዋሪ በተለያየ ዘዴ በመጠቀም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ሠርተናል፡፡ በሕጎቻችን እና በደንቦቻችን ላይም ተመሳሳይ ሰፊ ሥራ አከናውነናል፡፡

አዲስ ዘመን፡የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎቹ በምን መንገድ ለኅብረተሰቡ ደረሱ? ሁለት ሚሊዮን የተባለው ቁጥርስ በምን ታወቀ?

ሻለቃ ዘሪሁን፡ግንዛቤውን ተቋሙ ለኅብረተሰቡ የሰጠው ቤት ለቤት በመሄድ፤ በየትምህርት ቤቶቹ ለተማሪዎች እና ለመምህራን፤ በቡና ጠጡ መድረኮች እና ሕዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች በሞንታርቦ (በድምጽ ማጉያ) በመጠቀም የተሰጡ ናቸው፡፡ በወረዳና በክፍለ ከተማዎች መድረኮችን በማዘጋጀት ግንዛቤ ተፈጥሯል፡፡

አዲስ ዘመን፡የሰጣችሁት ግንዛቤ ምን ውጤት አምጥቷል?

ሻለቃ ዘሪሁን፡በስድስት ወራት ውስጥ በሠራነው የግንዛቤ መፍጠር ሥራ ከባለፈው ዓመት በተሻለ ውጤት አምጥተናል፡፡ ኅብረተሰቡ በሰጠነው ግንዛቤ እና ከተቋሙ ጋር አብሮ ለመሥራት ባሳየው ፍላጎት የወንጀል ተግባር ወይም የደንብ መተላለፍን በ58 ነጥብ 6 በመቶ መቀነስ ተችሏል፡፡

አዲስ ዘመን፡ከመሬት ጋር ተያይዞስ ተቋሙ ምን ያህል ካሬ ሜትር እየጠበቀ ነው? ምን ውጤትስ አምጥቷል?

ሻለቃ ዘሪሁን፡ከመሬት ጋር በተያያዘ ተቋሙ ያሳየው አፈጻጸም ከፍተኛ ነው፡፡ 5ሺ915 መሬት ባንክ የገቡ መሬቶችን እየጠበቅን ነው፡፡ 10 ሚሊየን 413ሺ 598 ካሬ መሬት ቦታ ተቋማችን ይጠብቃል። ከነዚህም ውስጥ ባለፉት ስድስት ወራት ምንም ዓይነት መሬት ከሕግ አግባብ ውጭ ሳይወረርም ሆነ ሕገ ወጥ ግንባታ ሳይካሄድበት ማቆየት ችለናል፡፡

በአርሶ አደር ቦታ ላይ የግንባታ ፈቃድ ሳያወጡ ሕገ ወጥ ግንባታን ሲያካሂዱ የተገኙ 2ሺ 454 ግለሰቦች ላይ ርምጃ ወስደናል፡፡ ሕገ ወጥ የመሬት መስፋፋት ሲያደርጉ ማለትም ከነበራቸው ካሬ ውጭ አጠገባቸው ያለውን መሬት ወደ ራሳቸው ይዞታ የቀላቀሉ 11 ግለሰቦች ላይ ርምጃ ተወስዷል፡፡

አዲስ ዘመን፡ግንዛቤ ከመስጠት ባለፈ ባለፉት ስድስት ወራት ተቋሙ ምን ተጨባጭ ሥራ ሠርቷል?

ሻለቃ ዘሪሁን፡በመንገድ ላይ ንግድ እና በበረንዳ ላይ ንግድ 27ሺ 163 ግለሰቦች በተደጋጋሚ ድርጊቱን ሲፈጽሙ ተገኝቶ ርምጃ ተወስዶባቸዋል። በደረቅ እና ፈሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ላይ ኅብረት ሥራ ሽርክና ማህበራትን (ቆሻሻ ለማንሳት የተደራጁ) ጨምሮ በ6ሺ665 ግለሰቦች ላይ አግባብ በሌለው ቆሻሻ አያያዝ ምክንያት ርምጃ ወስደናል፡፡

በሕገ ወጥ እንስሳት እርድ 821 ግለሰቦች፤ በመንገድ አጠቃቀም ጉድለት 5ሺ859 ግለሰቦች፤ በትምህርት ቤት ዙሪያ አዋኪ ድርጊቶችን በመንግሥት ትምህርት ቤት ዙሪያ ሲፈጽሙ በተገኙ 310 ግለሰቦች እና በግል ትምህርት ቤቶች ዙሪያ አዋኪ ድርጊትን በፈጸሙ 103 ተቋማት እና ግለሰቦች ላይ ርምጃ ወስደናል፡፡

936 በትምህርት ቤት አካባቢ በሚገኙ ፔንሲዮን (አልጋ ቤቶች)፤ ሺሻ ቤቶች፤ ቁማር ቤቶች፤ ቪዲዮ ቤቶች፤ ጆተኒና እና ከረንቡላ ቤቶችን የማሸግ ሥራ ሠርተናል፡፡ ከትምህርት ቤት ውጭ በተገኙ አዋኪ ድርጊቶችን በሚፈጽሙ 1ሺ984 ተቋማት ላይ ርምጃ  ተወስዷል፡፡

በአጥር፤ በድልድይ እና በግድግዳ ላይ በተሰቀሉ ደረጃቸውን ባልጠበቁ 88ሺ029 ሕገ ወጥ ማስታወቂያዎች ላይ ርምጃ ተወስዷል፡፡ በአጠቃላይ ከባለፈው ዓመት አንጻር 58 ነጥብ 6 በመቶ ወንጀሉ (ደንብ መተላለፉ)ቀንሷል፡፡

በደንብ እና በመመሪያው መሠረት ከጥፋተኞች ንብረትን በመውረስ እና በገንዘብ መቀጮ ባለፉት ወራት ለመንግሥት ገቢ ያደረግነው 153 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ የተሰበሰበውም ብር ተመልሶ ለሕዝብ ልማት እና ጥቅም የሚውል ነው፡፡ መንግሥት ከቅጣት በተሰበሰበው ብር አካባቢዎች ያጸዳል መሠረተ ልማት ይዘረጋል፡፡

አዲስ ዘመን፡ከመሬት አስተዳደር ውጭ ከሌሎች መንግሥታዊ ተቋማት ጋር ምን እየሠራችሁ ነው?

ሻለቃ ዘሪሁን፡ተቋሙ ከ27 መንግሥታዊ ሴክተሮች ጋር በትብብር ይሠራል፡፡ ከመሬት ጋር ባሉ ተያያዥ ጉዳዮች ከመሬት አስተዳደር እና ከግንባታና ፈቃድ ቁጥጥር ባለሥልጣን ጋር በጋራ እንሠራለን፡፡ በዚህም መሬት ላይ የነበረው የመሬት ወረራ ቀንሷል። በተለይም መሬት አስተዳደር የሚጠቀመው ሲስተም በቴክኖሎጂ የታገዘ በመሆኑ የቁጥጥር ሥራውን ቀላል አድርጎታል፡፡ አሁንም ከመሬት አስተዳደር ጋር በጋራ በመሆን የመሬት አስተዳደር ሥርዓት በመዘርጋት፤ የቁጥጥር ሥርዓቱን ለማዘመን እየተሠራ ነው፡፡

የኮሪደር መሠረተ ልማት ጋር በተያያዘ፤ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ፤ ከግንባታ ፈቃድ እና ቁጥጥር ባለሥልጣን፤ ከትራፊክ ማኔጅመንት እና ከኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር በጋራ በመሆን ሥራዎችን እየሠራን ነው፡፡

ወደፊት ለሕዝቡ ይፋ የሚደረገው በአዲስ አበባ ከተማ የወንዝ ዳርቻዎች እና አካላት ላይ የሚፈጸሙ ሕገ ወጥ ተግባራትን ለመቆጣጠር ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የቁጥጥር ሥራውን ለማከናወን የሚረዳ መመሪያ እና ደንብ አዘጋጅቷል፡፡ እነዚህ መመሪያ እና ደንቦች ወደ ሥራ ሲገቡ የደንብ ማስከበር ሥራውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን ያከናውናል፡፡

አዲስ ዘመን፡ከኮሪደር ልማቱ ጋር በተያያዘ ደንብ የማስከበር ሥራው ያዝ ለቀቅ ሲል ይስተዋላል፤ ይህ ለምን ሆነ?

ሻለቃ ዘሪሁን፡የኮሪደር ልማት ሥራ የእግረኛ  መንገዶችን፤ የሳይክል፤ የአካል ጉዳተኞች እና የመኪና መንገዶችን በአግባቡ እንዲለይ ተደርጎ የተሠራ ነው፡፡ ሥራው በሚካሄድበትና ለሕዝብ ክፍት በሚደረግበት ሰዓት ከመንገዱ አዲስ መሆን ጋር ተያይዞ በርካታ ሕዝብ የአጠቃቀም ግንዛቤ አልነበረውም፡፡

በዚህም የደንብ ማስከበር ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራውን ተሠርተዋል፡፡ እያንዳንዱ የኮሪደር ልማት በተሠራባቸው መንገዶች ላይ የደንብ አስከባሪ ኦፊሰሮችን በመመደብ እና የማስተካከያ ርምጃዎችን በመውሰድ ሰፊ ውጤታማ ሥራዎችን አከናውነናል፡፡

ተቋማችን ሥራዎችን ያዝ ለቀቅ አያደርግም ነገር ግን በተፈጠረው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ሕዝቡ ተገቢውን ደንብ እያከበረ በመሆኑ እንደ መጀመሪያው ቁጥጥር አናደርግም፡፡ ለምሳሌ በቦሌ መስመር አንዳንድ አዳዲስ የከተማዋ ነዋሪ ካልሆነ በስተቀር ሁሉም መንገዱን ይዞ ነው የሚሄደው፡፡

አልፎ አልፎም ቢሆንም አሁንም በእግረኛ መንገድ ላይ መሄድ ሲኖርባቸው በሳይክል መንገድ ላይ የሚሄዱ እና ያለ አግባብ የአካል ጉዳተኞችን መንገድ የሚጠቀሙ ግለሰቦች ላይ ቁጥጥር እናደርጋለን። በኮሪደር ልማቱ ሥራ ላይ ሕግን የማስከበር ተግባርን ጠንክረን እየሠራን ነው፤ ወደፊትም ይሄንኑ እናስቀጥላለን፡፡

አዲስ ዘመን፡የተለያዩ የእንጨት እና የብረት ሥራ የሚሠሩ ዜጎች ከልክ ያለፈ ድምጽ የሚያወጡ ማሽኖችን በቀን በመኖሪያ ቤቶች አካባቢ ይጠቀማሉ፡፡ አንዳንድ መጠጥ ቤቶችም በተመሳሳይ በማታ መኖሪያ ቤቶችን ይረብሻሉ፤ እንደዚህ ዓይነት ተግባራትን ለማስቆም ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ለምን አልቻለም?

ሻለቃ ዘሪሁን፡ይሄ የሚወሰደው እንደ አዋኪ ተግባር ነው፡፡ መጠጥ ቤቶች፤ ጋራዥ እና ሌሎችም ከልክ በላይ የሆነ ድምጽ የሚለቁ ተቋማት ላይ በየደረስንበት ከኅብረተሰቡ ጋር በመነጋገር ርምጃ እየወሰድን ነው ፡፡

አዲስ ዘመን፡ነዋሪዎች ንብረት እንዴት እንደሚወረስ እና የተወረሰው ንብረት ለማን ገቢ እንደሚደረግ ጥያቄ ያነሳሉ፤ እዚህ ጉዳይ ላይ ምን ምላሽ አለዎት?

ሻለቃ ዘሪሁን፡– ከመንገድ ላይ የሚወረሱ ንብረቶች ጋር በተያያዘ ፤ ማንኛውንም ሕገ ወጥ ንግዶች በመንገድ ዳር ላይ የሚያከናውኑ ግለሰቦች ንብረት ይወረሳል፡፡ አልባሳት፤ ጫማዎች፤ ፍራፍሬ እና ማንኛውም ለምግብነት የሚውሉ ፍራፍሬዎችን በመንገድ ዳር ላይ ሲነግዱ የታዩ ግለሰቦች ንብረት ላይ ርምጃ ይወሰዳል፡፡ ንብረቶቹ ከተወረሱ በኋላ እዛው ባለ ወረዳ ውስጥ ይቀመጥ እና በጨረታ ይሸጣል፡፡ ገንዘቡም ለመንግሥት ገቢ ይደረጋል፡፡

አዲስ ዘመን፡አንዳንድ የተቋማችሁ ሠራተኞች ሕግ ተላልፈው ሲንቀሳቀሱ ይስተዋላል፤ አመራሩ ይህንን በምን መልኩ እያስተካከለ ነው?

ሻለቃ ዘሪሁን፡እውነቱን ለመናገር ከዚህ በፊት የደንብ ማስከበር ባለሥልጣን ከሥነ ምግባር እና ከብልሹ አሠራር ጋር ተያይዞ ጥሩ ስም አልነበረውም፡ ፡ ይህንን ተቋማዊ ገጽታ ለመቀየር በርካታ ሥራዎች ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ ሥራው የተሳካ እንዲሆን ለአባሎቻችን ትጥቅ፤ ሥልጠና እና ግንዛቤ ሰጥተናል።

ከዚህም በተጨማሪ የሥነ ምግባር ግድፈት በተገኘባቸው ሠራተኞች ላይ አስተማሪ የሆነ ርምጃ እየወሰድን እና የማስተካከያ ሥራዎችን እየሠራን ነው። ነገር ግን ሙሉ በሙሉ ንጹህ ነን ማለት አይቻልም፡ ፡ የሚያጠፉትን በመቅጣት ብቻ ሳይሆን ሰዎች ወደ ጥፋት እንዳይገቡ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እንሠራለን።

የሕዝቡም ግንዛቤ እያደገ በመምጣቱ የደንብ ማስከበር ሥራው የተሳካ እንዲሆን እያገዘን ነው፡፡ ደንብ እንዲከበር የሚፈልግ ማኅበረሰብም እየተፈጠረ ነው፡፡ ሕግ ሲጣስ ሕብረተሰቡ ጥቆማ ይሰጣል፡፡

አሠራራችን የተሻለ እንዲሆን ለማድረግም ከኅብረተሰቡ አስተያየቶችን እንቀበላለን፡፡ በጥቅሉ አሁን ላይ የደንብ ማስከበር ባለሥልጣን እንደ ከዚህ በፊቱ አይደለም፡፡

አዲስ ዘመን፡የደንብ ማስከበር ተቋም ባለፉት ወራት በመልሶ ማልማት ሥራ ላይ ምን ዓይነት ሚና ተጫወተ? ለማኅበረሰቡስ ምን ዓይነት አገልግሎት ሰጠ?

ሻለቃ ዘሪሁን፡ተቋሙ ከማህበረሰቡ ጋር በቅርበት ይሠራል፡፡ የማዕድ ማጋራት ሥራ ላይ በንቃት ይሳተፋል፡፡ 11 ቤቶችን ለአቅመ ደካሞች ገንብቶ አስረክቧል፡፡ 75 ሕፃናትን ያሳድጋል፡፡ ከነዚህ ውስጥም ከመዋዕለ ሕፃናት ጀምሮ እስከ 12ኛ ክፍል አስተምሮ ዘንድሮ የሚያስፈትናቸው ተማሪዎች አሉት፡፡

በኮሪደር ልማት እና በመልሶ ማልማት ሥራ ላይ ከአካባቢያቸው ተነስተው ወደ ሌላ ሥፍራ የሚሄዱ ዜጎች ያለ ምንም ክፍያ የጫኝ እና አውራጅ ሥራም ሠርተናል፡፡ በሚያርፉበትም ቦታ እቃቸውን አውርዶ ሥፍራ የማስያዝ ሥራ አከናውናል፤ በዚህም ከኅብረተሰቡ ምስጋናን አትርፈናል፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩም ልዩ የእውቅና ሰርተፍኬት ተሰጥቶናል፡፡ አሁን ላይ ተቋማችን እንደ ከዚህ በፊቱ ስሙ በመጥፎ የሚነሳ አይደለም፡፡

አዲስ ዘመን፡ስለሰጡን ጊዜ እጅግ አድርገን እናመሰግናለን፡፡

ሻለቃ ዘሪሁን፡– እኔም አመሰግናለሁ፡፡

መክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 12 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You