ቦቢቾን – በአፕል ምርት

ዜና ሀተታ

የቅጥር ግቢውን መግቢያ በር እልፍ እንዳሉ የሚመለከቱት በቁመት አጫጭር፤ በያዙት ምርት ደግሞ ብዛት ካለው የአፕል ዛፎች ጋር ነው። መካከለኛ የሰው ቁመት ባለው የአፕል ዛፍ ላይ ‘ቢያንስ ከ70 እስከ 100 የአፕል ፍሬዎች ተንዠርግገው ይታያሉ። መኖሪያ ቤቱን አልፈው ወደ ጓሮ ዞር ሲሉም የሚያጋጥምዎ ተመሳሳይ የአፕል ዛፎች ናቸው። ወርሃዊ የካቲት፤ ምርቱ የሚደርስበት እንደመሆኑ ግመጡኝ ግመጡኝ የሚያሰኙ የአፕል ፍሬዎች ተመልክተናል።

ሥፍራው ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ሃድያ ዞን፣ ሆሳዕና ከተማ ነው። በቅጥር ግቢያቸው ውስጥ ተፍ ተፍ እያሉ ያገኘናቸው በከተማ ግብርና ሥራ የሚተዳደሩትን አቶ ታገሰ መሎሮን ነው፤ አፕል አምራችና ባለሙያ ናቸው። በሃድያ ዞን፣ በሆሳዕና ከተማ ቦቢቾ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው።

እኚህ አርሶ አደር በዋናነት ትኩረት አድርገው የሚያመርቱት አፕል ነው። አፕል ሲያመርቱ አንድ አይነት ዝርያ ያለውን ሳይሆን ምርት መስጠት የሚችሉ የተለያዩ አይነቶችን ነው። እያመረቱ የሚገኙት በቤተሰብ ደረጃ ተደራጅተው ሲሆን፣ ከአፕል በተጨማሪ አቮካዶና ማንጎም በቅጥር ግቢያቸው ከሚያመርቷቸው የፍራፍሬ አይነት የሚጠቀሱ መሆናቸው ይገልጻሉ።

አቶ ታገሰ፣ ፍራፍሬውን በማምረት ላይ የሚገኙት በሆሳዕና ከተማ አስተዳደር በከተማ ግብርና ውስጥ በመካተት ነው። በዚህ ሁሉ ከተማ አስተዳደሩ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይም የቀበሌያቸው የግብርና ባለሙያ ክትትል በማድረግ ሙያዊ ድጋፋቸው እንዳልተቋረጠባቸው ያስረዳሉ።

አፕል አምራቹ አቶ ታገሰ፣ ምርቱን የሚሸጡት በአብዛኛው በመንግሥት ቢሮዎች አካባቢ ሲሆን፣ የገበያ ችግር እንደሌለባቸው ይናገራሉ። ሽያጩን የሚያከናውኑት በመንግሥት ቢሮዎች ብቻ ሳይሆን ለማኅበረሰቡም ጭምር እንደሚያቀርቡ ያስረዳሉ።

እርሳቸው እንደሚሉት፤ አምና በተመሳሳይ ወቅት ከአመረቱት የአፕል ምርት ያገኙት ወደ 13 ኩንታል የሚጠጋ ምርት ነው። በዚህ ዓመት የሚያገኙት የአምናውን ያህል ምርት አይደለም። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ በጥቅምት ወር ሲዘንብ የነበረው ዝናብ የአፕሉን አበባ በማራገፉ ነው ይላሉ።

በ2012 ዓ.ም አንድ ኪሎ አፕል ሲሸጡ የነበረው በ50 ብር ነው። የገበያው ዋጋ ከፍ እያለ ሲሄድ በ75 ብር መሸጥ እንደነበረ ይናገራሉ፤ በአሁኑ ወቅት ግን የአንድ ኪሎ አፕል ዋጋ 150 ብር ነው ይላሉ። አምና ከአፕል ምርት ብቻ ያገኙት ወደ 50 ሺህ ብር አካባቢ ነው። ዘንድሮ ግን በዝናቡ ምክንያት አበባው በመርገፉ ወደ 100 ሺህ ብር ዝቅ ሊል እንደሚችል ይናገራሉ። የገንዘቡ መጠን የመጨመሩ ምስጢር ደግሞ የመሬት ሽፋኑ ሰፊ በመሆኑ ነው ሲሉ የገለጹት።

አቶ ታገሰ እንደልብ እንዳያመርቱ የውሃ ችግርና የመሬት ጥበት ተግዳሮት እንደሆነባቸው ይናገራሉ። ቀደም ሲል ሰፊ መሬት ሊሰጣቸው ከጫፍ ደርሶ እንደነበር አስታውሰው፤ በመካከሉ ኮቪድ 19 በመከሰቱ ጉዳዩ በዚያው መቅረቱንም ያስታውሳሉ።

ሐረገወይን ዓለሙ በሆሳዕና ከተማ ግብርና ጽሕፈት ቤት የግብርና ባለሙያ ናቸው፤ መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት የሌማት ትሩፋት ሥራዎች ላይ ሙያዊ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ይናገራሉ። እርሳቸው ሙያዊ ድጋፍ በሚያደርጉበት ቀበሌ፣ የዶሮ እርባታ፣ ጥምር ግብርና እና ሌሎችም የከተማ ግብርና እንዳለ ያስረዳሉ።

እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ የአፕል ማሳ ያለ ሲሆን፣ እየለማ የሚገኘው በግለሰብ ደረጃ ነው። ግለሰቡ በኢንተርፕራይዝ ተደራጅተው የሚሠሩት ነው። አፕል በዓመት ሁለቴ ምርት የሚሰጥ የፍራፍሬ አይነት ሲሆን፣ የካቲት ወር እና ሐምሌ ወር መጨረሻ ላይ ይለቀማል፤ ከምርቱ አሰባሰብ ጋር ተያይዞ እንደከተማቸው ድጋፍ የሚሰጡበት ጊዜ ነው።

ድጋፋቸው በከተማ ግብርና ላይ ተሠማርተው በጥምር ግብርና ላይ የተሠማሩትንም ሆነ እንደየፍላጎታቸውና እንደየአካባቢያቸው ሁኔታ በተሠማሩበት የከተማ ግብርና ዘርፍ ሙያዊ ድጋፍ የሚያደርጉላቸው እንደሆነም ባለሙያዋ ተናግረዋል። ድጋፋቸውም ነዋሪዎች ባላቸው በትንሽ ቦታ ላይ እንዴት ማምረት እንደሚቻል ሙያዊ ድጋፍ ይሰጧቸዋል። ነዋሪውም ቀድሞ ከነበረው ባህላዊ የሆነ የጓሮ አትክልት አመራረት ዘዴ ዘመናዊ ማድረግ በመጀመሩ ተጠቃሚ በመሆን ላይ ይገኛል ይላሉ። ሁለትም ሆነ ሶስትም ከብት ላላቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ለከብቶቻቸው መኖ ይሆን ዘንድ የመኖ ዝርያ ይሰጣቸዋል። ያም በመሆኑ ከብቶቻቸው በወተቱ ረገድ ምርታማ እየሆኑላቸው ይገኛሉ ብለዋል።

እርሳቸው እንደሚሉት፤ እንደ ሆሳዕና ከተማ የሚቸግራቸው ውሃ ነው። ይሁንና ብዙዎች የውሃ ጓድጓድ በመቆፈር ለጊዜው በአማራጭነት እየተጠቀሙ ይገኛሉ። በከተማው ደረጃ ክረምት ላይ ነዋሪው የሚጠቀመው የዝናብ ውሃን ነው። በጋ ላይ ሲሆን ደግሞ የተለያዩ የውሃ አማራጮችን ለምሳሌ የጉድጓድ ውሃ በመቆፈርም እንዲጠቀሙ ያደርጓቸዋል። ይሁንና በጋ ላይ የቆፈሩት የጉድጓድ ውሃ እስከመጥፋት ደረጃ ይደርሳል። ችግሩን ለመፍታትም የዝናብ ውሃ በማቆር የመሥራት እቅድ አለ። እስካሁንም ማቆር ያልተቻለው ውሃ ለማቆር የሚያስፈልገው ግብዓት ባለመኖሩ ነው ብለዋል።

አቶ ጌታቸው ዮሐንስ የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ግብርና ጽህፈት ኃላፊ ናቸው። ሆሳዕና ከተማ የዞኑ ሃድያ፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር መቀመጫ እንደመሆኗ ወደ 500 ሺህ ገደማ ሕዝብ የሚኖርባት ከተማ መሆኗን ያስረዳሉ። ይህን ሕዝብ መመገብ የሚያስችል ሥርዓት በመፍጠሩ ረገድ ሥራ በመሠራት ላይ እንደሚገኝም ያመለክታሉ።

እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ በመሠረቱ ግብርና አራት አራት ዋና ዋና ተግባራት የሚከናወኑበት ዘርፍ ነው። አንደኛው የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ነው፤ ሁለተኛው የውጭ ምንዛሬን ለማስቀረት ታስቦ የሚሠራበት ዘርፍ ነው። ሶስተኛ በሥራ እድል ፈጠራ ላይ በሰፊው የሚገባበት ነው። አራተኛ በውጭ ምንዛሬ ከውጭ የሚገቡ ጥሬ እቃዎችን በሀገር ውስጥ ለመተካት የሚያስችል ነው።

ግብርናን ማዘመን ስንችል የሀገራችንን ሕዝብ መመገብ የሚያስችል አቅም የሚፈጠርበት ነው ያሉት አቶ ጌታቸው፣ ይህም የሚረጋገጠው በትንንሽ ማሳዎች ብዙ ምርት ማምረት ሲቻል ነው ብለዋል። በጣም ጥቂት በሆነ መሬት ላይ የተለያዩ ፍራፍሬን ማምረትና ተጠቃሚ መሆን እንደሚቻልም ያመለክታሉ።

በተመሳሳይ መልኩ አትክልትን በውስን ቦታ በማምረት የከተማ ነዋሪው በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል። በከተማ ጥምር ግብርና ውስጥ ላሉ የከተማው አምራቾች ወደዚህ ዘርፍ በመቀላቀል የዕለት ፍጆታ ባለፈ ለገበያም ጭምር ማምረት እንዲያስችላቸው ሙያዊ ድጋፍ እንደሚሰጡም ነው የተናገሩት።

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 12 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You