
መንግሥት ለሳይንስ ትምህርት ዘርፎች ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በሀገሪቱ ባሉት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለዚህ አገልግሎት የሚውሉ የሳይንስ ማዕከላት እንዲስፋፉ ምክንያት ሆኗል። የማዕከላቱ መስፋፋት ተማሪዎች በንድፈ ሃሳብ የተማሩትን በተግባር እየፈተሹ እንዲማሩና በቀላሉ እንዲረዱ ለማድረግ የሚያስችል ነው።
በዚህ ላይ ሌሎች መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት እየሠሩ ይገኛሉ። ለአብነትም ‹‹ስቴም ሲነርጂ›› የተሰኘው ግብረ ሰናይ ድርጅት ይጠቀሳል። ድርጅቱ ተማሪዎች ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድረስ በሳይንስ፣ በምህንድስና፣ በቴክኖሎጂ፣ በሒሳብ ትምህርቶች የዳበረ እውቀት እንዲኖራቸው ለማድረግ ይሠራል፤ ከታች ጀምሮ የሚማሩት ትምህርት በተግባር የተደገፈ እንዲሆን ለማድረግ እየሠራ ነው። ድርጅቱ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር ጭምር አብሮ ይሠራል።
ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዲሁ በስቴም ማዕከሎቻቸው አማካይነት ይሠራሉ። ተቋማቱ ደረጃቸውን የጠበቁ የሳይንስ ትምህርት ዘርፍ ቤተሙከራዎች ስላላቸው በሳይንስ ትምህርት ዘርፎች ልዩ ተሰጥኦና ሃሳብ ያላቸው ተማሪዎችን በመቀበል መርሃ ግብሮችን በማዘጋጀት ሥልጠናዎች እየተሰጡ ይገኛሉ።
ከዩኒቨርሲቲዎቹ ማዕከላት መካከል አንዱ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ስቴም ማዕከል ነው። ማዕከሉ ከተቋቋመበት 2006 ዓ.ም አንስቶ በርካታ ተማሪዎችን በማሰልጠን ለሳይንስ ዘርፍ ትምህርቶች የበኩሉን አበርክቶ እያደረገ ይገኛል። በዚህም ማዕከሉ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጀምሮ እስከ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ያሉ ተማሪዎችን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን ከማዕከሉ የተገኙ መረጃዎች ያመላክታሉ።
የስቴም ማዕከሉ አስተባባሪ አቶ ግርማ ወርቄ ማዕከሉ ከተቋቋመበት ጊዜ በሳይንስ ዘርፎች በርካታ ተማሪዎችን እያሰለጠነ እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ ዘንድሮ ብዙ ተማሪዎች እያሰለጠነ መሆኑን አመላክተዋል።
ማዕከሉ የተቋቋመበት ዋና ዓላማም ተማሪዎች ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ድረስ በሳይንስ፣ በምህንድስና፣ በቴክኖሎጂ፣ በሒሳብ ትምህርቶች በተግባር የተደገፈ የዳበረ እውቀት እንዲኖራቸው ማድረግን ያለመ መሆኑን አስታውቀዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ስቴም ማዕከሉ የተለያዩ ፕሮግራሞችን አዘጋጅቶ ሥልጠናዎች ይሰጣል። ሥልጠናውም ተማሪዎች በንድፈ ሃሳብ የተማሩትን ወደ ተግባር በመቀየር በተግባር እንዲለማመዱና እንዲፈተሹ የሚያስችል ነው። በተጨማሪ ሁሉም ተማሪዎች ወደ ማዕከሉ መጥተው መጠቀም ስለማይችሉ በየሳምንቱ ሐሙስ የተንቀሳቃሽ ቤተሙከራ አገልግሎት በመስጠት ለሁሉም ተማሪዎች ተደራሽ እንዲሆን ያደርጋል።
የተንቀሳቃሽ የቤተሙከራ አገልግሎቱ በጎንደር ከተማና በዙሪያው ባሉ ሁሉም ትምህርት ቤቶች በመንቀሳቀስ አገልግሎት በመስጠት ተደራሽ እየሆነ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ በየሳምንቱ ዓርብ ለወርክሾፕና ለጉብኝት ለሚመጡ ተማሪዎች አገልግሎቶች ይሰጣል።
እንደ ደባርቅ፣ ደብረ ታቦር፣ ኢንጅባራ፣ ደብረ ብርሃን የመሳሰሉት ዩኒቨርሲቲዎች በቡድንም ሆነ በግል ማዕከሉን ለመጎብኘት ለሚመጡ ተማሪዎች አገልግሎት እንደሚሰጥ ጠቅሰው፤ በተለይ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በየዓመቱ ለጉብኝት ወደ ማዕከሉ እንደሚመጡ አመላክተዋል።
ማዕከሉን ለመጎብኘትና ተሞክሮ ለመቅሰም በግልም ሆነ በቡድን ወደ ዩኒቨርሲቲው ማዕከል በየዓመቱ የሚመጡ ሌሎች ተማሪዎች እንዳሉም ጠቅሰው፤ አብዛኛዎቹ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች መሆናቸውንም ተናግረዋል።
በማዕከሉ ልዩ የፈጠራ ዝንባሌ ላላቸው ተማሪዎች የወርክሾፕ ፕሮግራም እየሰጠ መሆኑን የሚገልጹት አቶ ግርማ፤ ተማሪዎች በቤተ ሙከራዎቹ የሚሰጣቸው ትምህርት መፍታት፣ መበየድ፣ ማሰር እና የመሳሰሉት በማድረግ በተግባር እየሞከሩ፣ በእጆቻቸው እየነካኩ የሚሠሩበትና የሚለማመዱበት መሆኑን ይገልጻሉ። ይህም ከተግባር ትምህርት ጎን ለጎን የማኅበረሰቡን ችግር ሊፈቱ የሚችሉ የፈጠራ ሥራዎችን እንዲሠሩ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርም ያመላክታሉ።
እስካሁን ማዕከሉ በሚሰጠው አገልግሎት ተጠቃሚ ከሆኑ ተማሪዎች ብዙዎቹ ትልቅ የሚባል ደረጃ ላይ የደረሱበት ሁኔታ እንዳለም ጠቅሰው፣ የራሳቸውን ስታርትአፕ የከፈቱ እንዳሉም ተናግረዋል። ከእነዚህ ባሻገርም የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢንሳ) ተወካዮች ወደ ማዕከሉ በመምጣት ማዕከሉን መጎብኘታቸውንም አስታወሰው፣ ይህም ተከትሎም የማዕከሉን 24 ተማሪዎች በመውስድ በአስተዳደሩ እንዲሠሩ ያደረጉበት ሁኔታ እንዳለም ተናግረዋል።
አስተባባሪው እንዳብራሩት፤ ማዕከሉ ዘንድሮም የአጭር ጊዜ ሥልጠና እና የተንቀሳቃሽ ቤተሙከራ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። በተያዘው በጀት ዓመት 206 ተማሪዎች የተንቀሳቃሽ ቤተሙከራ አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓል። እሴት በመጨመር ለማኅበረሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችሉ ሥልጠናዎችም ተሰጥተዋል።
እሴት የመጨመር ሥልጠና ሲባል በአንድ ጥሬ እቃ ላይ እሴት መጨመር የሚያስችሉ ሥልጠናዎች መሆናቸው ጠቅሰው፣ ለአብነት ሳሙና፣ ዘይት፣ ወረቀት እና የመሳሰሉትን እንዴት መሥራት እንደሚቻል የሚያሳይ በተግባር የተደገፈ ሥልጠና በመስጠት ብዙ ተማሪዎች እውቀት እንዲያገኙ ተደርጓል። በዚህም ሦስት መምህራንና 23 ተማሪዎች ሥልጠናውን እንዲወስዱ መደረጉን ጠቅሰው፤ ይህም ሰልጣኞቹ ያገኙትን በተግባር የተደገፈ ሥልጠና ወደ ትምህርት ቤታቸው ሲመለሱ ሳሙናም ሆነ ሌሎች ምርቶችን በቀላሉ እንዴት ማምረት እንደሚቻል ማስተማርና ማሳየት ያስችላቸዋል ብለዋል።
በተጨማሪም በዚህ በጀት ዓመት መስከረም ወር ብራይተር ጀነሬሽን ከተሰኘ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ጋር በመተባበር 18 ተማሪዎችን በቋንቋ፣ በአመራርነት፣ በጊዜ አጠቃቀምና በመሰል ርዕሰ ጉዳይ ላይ ከቴክኖሎጂ ጋር የተገናኙ ሥልጠናዎች በመስጠት የእውቅና ሰርተፊኬት እንደተሰጠም አመላክተዋል።
ሥልጠናው በተለይ ተማሪዎች ራሳቸውን የሚመሩበት መንገድ እንዲኖራቸው በራስ መተማመንን እንዲያዳብሩ ያደርጋል የሚሉት አቶ ግርማ፤ ለዚህም ከሥልጠናው በኋላ ብዙ ተማሪዎች ራሳቸውን እንዴት መምራት እንዳለባቸው ትምህርት እንዳገኙበት፣ በራስ መተማመናቸው እንዲጨምር እንዳደረገላቸውና ከዚያ ያለፈ ብዙ እውቀት እንደገኙበት ከሚሰጡት አስተያየት መደመጡንም ተናግረዋል።
የማዕከሉ አስተባባሪ እንዳብራሩት፤ ማዕከሉ ከትምህርት ቤቶች በሳይንስ ትምህርቶች ዝንባሌና ተሰጥኦ ያላቸው ተማሪዎች ተመልመለው ሲመጡለት ተቀብሎ ሥልጠናው ይሰጣል። ሥልጠናው ከሰባተኛ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ላሉ ተማሪዎች የተዘጋጀ ነው። ማዕከሉ ተመራቂ ተማሪዎችንም ለብቻቸው በልዩ ሁኔታ ያስተናግዳል። በልዩ ሁኔታ የሚመጡለትን ተማሪዎችም እንዲሁ ያሰለጥናል።
ማዕከሉ የኤሌክትሮኒክስ፣ የመካኒክስ፣ የኦብቲ ክስ እና የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ቤተሙከራዎች እንዳሉት ጠቅሰው፣ አንዱ ቤተሙከራ በአንድ ጊዜ አገልግሎት መስጠት የሚችለው ከሃያ ተማሪ እንደማይበለጥ ይገልጻሉ። በእነዚህ ሁሉም ቤተሙከራዎች በአንድ ጊዜ ለሦስት ሰዓት ያህል 80 ተማሪዎች ማስተናገድ የሚቻልበት ሁኔታ እንዳለም ገልጸዋል።
በማዕከሉ ከሰባተኛ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ያሉ ተማሪዎች እንደሚሰለጥኑ ጠቅሰው፣ እነዚህን ተማሪዎች የሚመጥኑ ሥልጠናዎች እንደሚሰጡ ያመላክታሉ። ተማሪዎችም እንደየደረጃቸው የሳይንስ ትምህርቶችን በተግባር በተደገፈ መልኩ እንዲያገኙ እንደሚደረግ ይገልጻሉ። ይህንንም አብነት ጠቅሰው ሲያብራሩ በኦብቲክስ ዙሪያ የሚሰጠው ሥልጠና ስለ ብርሃን ምንነትና ጥቅም እንዲሁም በዘርፉ ዓለም ከደረሰበት ቴክኖሎጂ እና አብርክቶችን እያዛመዱ የሚመለከቱበት መሆኑን አብራርቷል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ተሰጥኦቸውን ተጠቅመው እንዴት መፍጠር እንደሚችሉ ለማሳየት እንደሚረዳ ተናግረዋል።
እሳቸው እንዳስታወቁት፤ ተማሪዎች እንደ የክፍል ደረጃቸው የሚማሩት ትምህርት የተለያየ ስለሆነ በክፍል በንድፈ ሃሳብ የቀሰሙትን እውቀት በተግባር እየፈተሹ እንዲማሩ ይደረጋል። ስለ ብርሃን እንዲሰለጥኑ ሲደረግ ተማሪዎቹ ስለ ብርሃን በንድፈ ሃሳብ የተማሩትን በምን ዓይነት ሂደት ወደ ተግባር መቀየር እንዳለባቸው በተግባር እንዲያዩት ይደረጋል። ይህም ሕግጋገቶችን ተከትለው በቀላሉ ለመሥራት ያስችላቸዋል።
የማዕከሉ የኤሌክትሮኒክስ፣ የመካኒክስ፣ የኦብቲክስ እና የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ቤተሙከራዎች ተማሪዎች በፈለጉት የትምህርት ዘርፍ ያላቸውን ተሰጥኦ እንዲፈትሹና በደንብ እያወጡ እንዲያሳዩ ለማድረግ እንደሚረዳቸው ጠቁመዋል።
በተመሳሳይ ማዕከሉ እየሰጠ ያለው የተንቀሳቃሽ ቤተሙከራዎች አገልግሎት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንዳሉት አቶ ግርማ አስታውቀው፣ ይህም በየትምህርት ቤቱ የተደበቁ የፈጠራ ችሎታና ተሰጥኦ ያላቸው ተማሪዎች ካሉበት ቦታ ድረስ በመሄድ ተሰጥኦቸውን እንዲያወጡ ያግዛቸዋል ብለዋል።
‹‹ተንቀሳቃሽ ቤተ ሙከራውን በየትምህርት ቤቱ በምናሳይበት ጊዜም ሃሳብ ያላቸውን ብዙ ተማሪዎች ማገዝ እንደምንችል እየነገርናቸው በምን መንገድ መጓዝ እንዳለባቸው እናሳያቸዋለን፤ በዚህም መልኩ ጭምር ወደ ማዕከሉ እንዲመጡ እያደረግን እንገኛለን›› ይላሉ። በዚህም ብዙ ተማሪዎችን ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲደርሱ ማድረግ የተቻለበት ሁኔታ እንዳለም ይገልጻሉ።
በተንቀሳቃሽ ቤተሙከራ ተገኝተው ተጠቃሚ ከሆኑት ተማሪዎች መካከል የተወሰኑት በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ተመርጠው የተወሰዱበት ሁኔታ እንዳለም ጠቅሰው፤ ተጨማሪ ሥልጠና አግኝተው በሀገር ውስጥ ዩኒቨርሲቲዎችና በውጭ ሀገር ሥራ ላይ የተሠማሩ እንዳሉም አመልክተዋል።
‹‹ተማሪዎች በንድፈ ሃሳብ ከተማሩት ትምህርት ይልቅ በተግባር የተማሩትና ሠርተው ያዩትን በቀላሉ አይረሱትም›› የሚሉት አስተባባሪው፤ ይህም በእጃቸው ነክተው ፈተናውና ገጥመው ስለሚሠሩ ውስጣቸው ያለውን ሃሳብ ለማውጣትም ሆነ አዲስ ሃሳብ ለማፍለቅ እንደሚያስችላቸው አስታውቀዋል።
እሳቸው እንዳብራሩት፤ ማዕከሉ እንደ ሮቦቲክስ እና 3ዲ ዓይነት ተጨማሪ ሥልጠናዎችንም ይሰጣል። ሮቦቲክስ ላይ የተለያዩ የሮቦት ዓይነቶች ስላሉ በእያንዳንዱ ላይ ሥልጠናዎች ይሰጣሉ። ተማሪዎች የተለያዩ ፕሮጀክቶች ሲሠሩ እገዛ የሚያደርጉላቸው የ3ዲ ቴክኖሎጂ ሥልጠናዎችንም እንዲወስዱ ይደረጋል።
ወደ ማዕከሉ የሚገቡ ተማሪዎች ሁሉም መጀመሪያ ላይ በተመሳሳይ መልኩ የጥንቃቄ ሥልጠናዎች እንዲወሰዱ እንደሚደረግ አስተባባሪው አመልክተው፣ ቀጥሎም የሰባተኛና ስምንተኛ ክፍል ተማሪዎችን በአንድ ላይ እንዲሁም የዘጠነኛና የአስረኛ ክፍል ተማሪዎችን በአንድ ላይ እንዲሆኑ በማድረግ ሥልጠናው እንደሚሰጣቸው አስታውቀዋል።
የአስራ አንደኛና የአስራ ሁለተኛ ክፍልም ተማሪዎችም እንዲሁ በአንድ ላይ እንዲሰለጥኑ እንደሚደረግ ጠቅሰው፤ የዘጠነኛና የአስረኛ ክፍል ተማሪዎች እንዲሁም የአስራ አንደኛና የአስራ ሁለተኛ ክፍል ተማሪዎች በአንድ ቤተ ሙከራ የሚሰጣቸው ሥልጠና ርዕሰ ጉዳይ አንድ ይሆን እንጂ ይዘቱ ግን የተለያየ ነው ሲሉም አብራርተዋል።
ማዕከሉ እየሰጠ ያለው አገልግሎት ተማሪዎች በሳይንስ ትምህርቶች ያላቸውን ተሰጥኦ አውጥተው እንዲጠቀሙ እንደሚያስችል ጠቅሰው፣ ይህም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው አስተባባሪው ገልጸዋል፤ ለሳይንስ ትምህርቶች ትኩረት ተሰጥቶ ቢሠራና በመላ ሀገሪቱ የስቴም ማዕከላት ማብዛትና ማስፋፋት ቢቻል መልካም እንደሆነም እንደሆነም አስገንዝበዋል።
የሳይንስ ትምህርት ዘርፍ መንግሥትም ሆነ የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ሰጥተው መደገፋቸውን ሊቀጥሉ እንደሚገባም አስታውቀዋል። ስቴም (ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢንጂነሪንግ እና ሒሳብ ዘርፍ) የሚመለከት መሆኑን ጠቅሰው፣ በደንብ ሊሠራበት እንደሚገባም አስገንዝበዋል፤ እነዚህ የትምህርት ዘርፎች በሁሉም ዘርፍ ውስጥ የሚገኙ ከመሆናቸውም በላይ ያደጉት ሀገራት ተሞክሮም በእነዚህ ዘርፎች ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ውጤታማ መሆን እንደሚያስችል ያስገነዝባል ሲሉም ጠቁመዋል። በተለይ የስቴም ማዕከላት ሥራዎች ብቁ ተማሪዎች ለማውጣት እንደሚያግዙ ተናግረው፣ ሚዲያውም ሆነ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላትም እንዲሁ ትኩረት ሊሰጡት ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል።
በሳይንስ ትምህርት ዘርፎች የተለየ ተሰጥኦ ያላቸው ተማሪዎች በልዩ ሁኔታ ወደ ማዕከሉ መጥተው ሥልጠናውን መከታተል እንደሚቸሉም አስተባባሪው አመላክተዋል። ሌሎች በትምህርት ቤታቸው አማካኝነት የሚመጡ ሰልጣኞችም ሥልጠናውን መውስድ የሚችሉበት ሁኔታ የተመቻቸ መሆኑንም ይጠቁማሉ።
በቀጣይ ማዕከሉ አሁን ከሚሰጣቸው ሥልጠናዎች በተጨማሪ ሌሎች ሥልጠናዎችንም እያዘጋጀ መሆኑን ይገልጻሉ። በተለይ ለሕፃናት፣ ማየትና መስማት ለተሳናቸው ወገኖች እና ሌሎችንም ያካተተ ሥልጠና ለመስጠት ታቅዶ እየተሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ማክሰኞ የካቲት 11 ቀን 2017 ዓ.ም