የቴክኖሎጂ ልማትና ሽግግር ሥራዎች

የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ለቴክኖሎጂ ሽግግር ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል። ይህም ተቋማቱ ችግር ፈቺና አዳዲስ የፈጠራ ሃሳቦች እንዲፈልቁና ከውጭ የሚመጡ ቴክኖሎጂዎችም እንዲላምዱ ምቹ ሥነ ምህዳር በመፍጠር ብዙ የፈጠራ ሥራዎች እንዲፈጠሩና እንዲሸጋገሩ አስችሏል።

በተለይ የፈጠራ ሥራዎችንና አዳዲስ ሃሳቦችን ማበረታታት የሚያስችሉ ፕሮግራሞች በመቅረጽ የፈጠራ ሥራና ሃሳብ ያላቸውን በመደገፍና በማበረታታት ለነገ የሀገሪቱ የቴክኖሎጂ መሠረት የሚጥሉ የፈጠራ ውጤቶች ለማፍራት የተሰጣቸውን ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ይገኛሉ፡፡

በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት በሥልጠና እና በፈጠራ ሥራዎች ላይ በትኩረት እየሠሩ ናቸው። ከእነዚህ ተቋማት መካከል አንዱ የፌዴራል የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት ሲሆን፣ ለኢንስቲትዩቱ በተቋቋመበት አዋጅ ከተሰጡት ሥልጣኖች አንደኛው ሥልጠና መስጠት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ ትኩረት መሥራት ነው፡፡

ኢንስቲትዩቱ በትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ ላይ በተቀመጠው መሠረት እስከ ደረጃ ስምንት ድረስ ሥልጠናዎችን የሚሰጥ ሲሆን፣ ከታችኛው የኮሌጁ አደረጃጀት ጀምሮ እስከ ፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ኢንስቲትዩት ድረስ እነዚህን ሥልጠናዎች እንደሚሰጥ ከኢንስቲትዩቱ የተገኙ መረጃዎች ያመላክታሉ።

የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር (ዶ/ር) እንደሚሉት፤ ኢንስቲትዩት ከሥልጠና ባሻገር ተልዕኮ አለው። ይህም የቴክኖሎጂ ሽግግር ወይም ቴክኖሎጂዎችንና አዳዲስ የሚፈጠሩ ቴክኖሎጂዎችን በመሥራት በስፋት (በማስ) እንዲመረቱና ለኅብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆኑ ለማድረግ ይሠራል። በዚህ መሠረት በቴክኖሎጂ ልማትና ሽግግር ሥራዎች ላይ ቆይቷል፡፡

ቀደም ሲል በሀገር ደረጃ የክህሎት ውድድሮች ከተካሄዱ በኋላ የገንዘብ ወይም የሰርተፊኬት ሽልማቶች ተሰጥተው ቴክኖሎጂዎች የሚያስታውሳቸው እንዳልነበር ጠቅሰዋል። የፈጠራ ሥራዎች በአውድ ርዕይ እንዲቀርቡና ፕሮቶታይፕ ወይም ማሳያዎች እንዲሠሩ ይደረግም እንደነበር ጠቁመው፤ ምርቶቹ በብዝሀነት(በማስ) የሚባዙበት አሠራር ግን እንዳልነበረ ያመላክታሉ።

ይሁን እንጂ ከባለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በፌዴራል ደረጃ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴርና የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ኢንስቲትዩት በጋራ የክረምት ካምፕ/ሰመር ካምፕ/ እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ገልጸዋል። ይህም ‹‹እስኪል ኢትዮጵያ›› የሚል ስያሜ ተሰጥቶት በርካታ ፈጠራዎች ማውጣት ማስቻሉን ተናግረዋል፡፡

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ የዚህ የክህሎት ውድድር አሸናፊዎች ወደ አንድ ማዕከል እንዲገቡ ተደርጎ ከመኝታ አገልግሎት ጀምሮ ያሉ ሌሎች አገልግሎቶችና ሥልጠናዎች እንዲያገኙ ይደረጋል። በማዕከሉ ቆይታቸውም የፋብሪካ ጉብኝት እንዲያደርጉ እና ለሽልማት ያበቃቸውን የፈጠራ ሥራ ለማሻሻል እንዲሠሩ ይበረታታሉ። ተቀራራቢ የሆነ የፈጠራ ቴክኖሎጂዎች ያላቸውን ወደ አንድ በማምጣት በአንድነት እንዲሠሩ የሚደረግበት አሠራርም አለ።

‹‹በእስኪል ኢትዮጵያ›› በመጀመሪያው ዓመት በ2016 በጀት ዓመት 85 የሚሆኑ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ወጥተዋል። በ2017 በጀት ዓመት ደግሞ ይህ አሃዝ ወደ 99 ከፍ ብሏል፤ በድምሩ 184 አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ማግኘት ተችሏል። እነዚህ ቴክኖሎጂዎች አምስቱ የእድገት ዘርፎች በሚባሉ ግብርና፣ ቱሪዝም፣ ማዕድን፣ ኢንዱስትሪ፣ ኢንፎርሜሽን፣ ኮሙኒኬሽንና ቴክኖሎጂ ላይ ትኩረት ያደረጉ ናቸው።

ዋና ዳይሬክተሩ ይህንንም ግብርናን አብነት ጠቅሰው ሲያብራሩ ግብርናን የሚያሻሽሉ ቴክኖሎጂ ብዙ ዓይነት ፈጠራዎች መሥራታቸውን ጠቁመዋል። ‹‹እስኪል ኢትዮጵያ›› የተሰኘው እንቅስቃሴ በፌዴራል ብቻ ሳይሆን በክልሎች እንዲስፋፋ እየተደረገ መሆኑን አመላክተዋል።

የፈጠራ ሥራዎችን ለመደገፍ ከሚያጋጥሙ ማነቆዎች መካከል ዋነኛው የፋይናንስ አቅርቦት ችግር መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል። የፈጠራ ሥራዎች የፋይናንስ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረው፣ የሀገሪቱ ፋይናንስ አቅራቢ ተቋማት ጀማሪ የፈጠራ ቢዝነሶችን/ ስታርትአፕ/ ለመደገፍ የሚያደርጉት ጥረት ቢኖርም በቂ አይደሉም ብለዋል፡፡

እሳቸው እንዳብራሩት፤ የፈጠራ ሥራዎች እንዲሰፉ ካልተደረገ አንደኛ ሀገሪቱ በቴክኖሎጂ ራሷን አትችልም፤ ሁለተኛም በሀገር ውስጥ በቀላሉ ሊሠሩ የሚችሉ ነገሮች ከውጭ እንዲገቡ የሚደረግበት ሁኔታ ሊቀጥል ይችላል። የፋይናንስ አቅርቦት ችግር መፍታት እስካልተቻለ ድረስ ውጤት ማምጣት ይቻላል የሚል እምነት የለኝም ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ አስገንዝበዋል።

እነዚህ 184 የፈጠራ ሥራዎች ከተለያዩ የሀገሪቷ አካባቢዎች ጥብቅ መስፈርትና ልየታን አልፈው ወደ ማዕከሉ መግባታቸውን ጠቅሰው፣ የፈጠራ ሥራዎቹ የተለያዩ ደረጃዎች የተቀመጠላቸው መሆናቸውንና እነዚህም ደረጃዎችን ጠብቀው እንደሚሄዱ ገልጸዋል።

እንደ እሳቸው ገለጻ፤ የመጀመሪያዎቹ ሥልጠናዎች፣ በኢንዱስትሪ ጉብኝት የልምድ ልውውጥ ማድረግ፣ የቢዝነስ እቅድ ማዘጋጀት፣ ዲዛይኖችን ማሻሻልና የመሳሰሉት ሲሆኑ፣ እነዚህን ደረጃዎች ካለፉ በኋላ የመጨረሻው ደረጃ የሚሆነው የፋይናንስ ድጋፍ አግኝተው የፈጠራ ቴክኖሎጂዎችን በብዛት ወደ ማምረት የሚገቡበት ነው።

አሁን አንዳንዶቹ የፈጠራ ሥራዎች በፋይናንስ ድጋፍ ፍለጋ ላይ ሲሆኑ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ የፋይናንስ ድጋፍ አግኝተው ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችና ከክልሎች ጋር በተሰጣቸው ትዕዛዝ መሠረት በብዛት እያመረቱ ይገኛሉ። ለአብነት መስኖን የሚያሻሽሉ ቴክኖሎጂዎችን ከመስኖና ቆላማ ሚኒስቴር ጋር በመሆን እንዲባዙ ተደርጓል። አንዳንድ ፍላጎት ያላቸው ክልሎችም ቴክኖሎጂዎቹ እንዲባዙ አዘዋል።

ሁሉንም ቴክኖሎጂዎች በብዛት ወደ ሥራ ለማስገባት ግን የፋይናንስ አቅርቦት ማነቆ መሆኑን ጠቅሰው፣ እነዚህ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች የፋይናንስ ድጋፍ አግኝተው ወደ ማምረት ሥራ ከገቡ በኋላ በግላቸው አቅም እየፈጠሩ ወደ ኩባንያ ደረጃ እንዲያድጉ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡

የሌሎች ሀገራት ተሞክሮ እንደሚያሳየው ለተሳኩ የቢዝነስ ሙከራዎች በመንግሥት በኩል ሁኔታዎች እንደሚመቻቹ ጠቅሰው፤ ለፈጠራ ባለቤቶች ድጋፍ በመስጠትና እየተደጋገፉ እንዲሠሩ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ያመላክታሉ።

ዋና ዳይሬክተሩ እንዳብራሩት፤ የፋይናንስ ማነቆዎችን ችግር ለመፍታት ጥረቶች እየተደረጉ ናቸው። አንደኛ እንደ ሀገር የስታርትአፕ አዋጅ እንዲሻሻል እየተደረገ መሆኑን ነው። ሁለተኛው ተቀናጅቶ መሥራት ነው። ሥራው በሚመለከታቸው መንግሥታዊ ተቋማት መካከል በደንብ ተቀናጅቶና ተናቦ መሥራትን ይጠይቃል። ሦስተኛው ደግሞ የድጋፍ ማሕቀፎችን በተሟላ መልኩ ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል።

‹‹ያሉት ጅምሮች ለሀገር ትልቅ ተስፋ ናቸው። ኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ይኖርባታል። ለዚህ የሚረዳ ሥራ ተጀምሯል፤ ግን ደግሞ የድጋፍ ማሕቀፎች በተሟላ ሁኔታ ተግባራዊ በማድረግ በኩል የሚታዩ ጉድለቶች ለመሙላት መሠራት ይኖርበታል›› ሲሉ አስገንዝበዋል።

ከሚመለከታቸው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ጋር አብረን የምንሠራባቸው የጋራ ፕላት ፎርሞች አሉን ሲሉም ጠቅሰው፣ ይህንንም ከሚጠበቀው ውጤት አንጻር ይበልጥ ማቀናጀት እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል።

የፈጠራ ቴክኖሎጂዎች በማዕከሉ ለአጭር ጊዜ /አንድና ሁለት ዓመታት/ የሚቆዩበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል ጠቅሰው፤ የሚቆዩበት ጊዜ በሚያገኙት የድጋፍ ማሕቀፍ የጊዜ ገደብ ላይ እንደሚወሰን ያመላክታሉ። በአጭር ወራት የሚወጡ እንዳሉ ሁሉ ለአንድ ዓመትና ሁለት ዓመት የሚቆዩ እንዳሉም ይገልጻሉ።

እሳቸው እንዳሉት፤ ለስታርትአፕ የሚደረገው ድጋፍ ወደተሟላ ትግበራ መገባት አለበት። አንደኛ ጀማሪ ቢዝነሶች እስካልተበረታቱ ድረስ ተኪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ የማምረት አቅም አይጠናከርም። ሁለተኛ ኢትዮጵያ የብዙ ተስፋዎችና ከ70 በመቶ በላይ የሚሆን አምራች የወጣት ኃይል ያላት ሀገር እንደመሆኗ ወጣቶችን በመጠቀም ብዙ ፈጠራዎችን ማፍራት ይቻላል። እነዚህን ማሻሻልና ለዚህ እንዲረዳ ማነቆዎችን መፍታት የግድ ያስፈልጋል፡፡

ስታርትኦፖችን መደገፍ እንደ ቀላል ሥራ መታየት የለበትም። እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ታዳጊ ሀገራት ይቅርና በኢኮኖሚ ደረጃቸው የተሻለ ቦታ ላይ ባሉት ዘንድም ቢሆን ስታርትአፖች በፈተናዎች ውስጥ ነው የሚያልፉት። በተቻለ መጠን ያለውን አቅም በመጠቀም ጀማሪ ቢዝነሶችን በማበረታታት የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችና ፈጠራዎች እንዲወጡ ማድረግ ላይ መሥራት ይገባል፤ በዚህ ይበልጥ ውጤታማ መሆን ይቻላል። ይህ ሥራ በሀገር ደረጃ የተያዙ እድገት ተኮር ዘርፎችን የበለጠ ለማሳደግም ይረዳል፡፡

በመጀመሪያው ዓመት ‹‹እስኪል ኢትዮጵያ›› ውድድር 400 ኢኖቬተሮች፣ በሁለተኛው ዙር 200 አካባቢ ኢኖቬተሮች በየክልሉ በተካሄዱ የክህሎት ውድድሮች ማሸነፋቸውንም አስታውሰዋል። ይህ ብዙ ቁጥር መሆኑንም ያመለክቱት።

እሳቸው እንዳብራሩት፤ በቴክኖሎጂና አዲስ ፈጠራ ለማውጣት ባለተሰጥኦዎች ያስፈልጋሉ፤ ዛሬ በጥቂቶች ጥቅም ላይ የዋሉ ቴክኖሎጂዎች ነገ ሚሊዮኖች ሊጠቀሙባቸው ይቻላሉ። ሥራው በአንድ ወይም በሁለት ሰዎች ሊሠሩ ይችላሉ።

ኢኖቬተሮችን በማፍራት በኩል ያለውን ተሞክሮ ወደ ክልሎች ማስፋት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፣ በኢንስቲትዩቱ በኩል ከኮሌጅ ጀምሮ በቴክኒክና ሙያ ተቋማት እየተሠራ ያለውን ሥራ በማብዛት ለክልሎች ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

‹‹እስኪል ኢትዮጵያ›› ውድድር ይቀጥላል›› ያሉት ብሩክ ከድር(ዶ/ር) ፣ በሚቀጥለውም ዓመት ውድድሩ እንደሚካሄድ ጠቁመዋል። ይህንኑ መሠረት በማስያዝ ራሱን የቻለ በጀት ኖሮት በፕሮግራም ደረጃ እንዲያዝ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል። ይህም ፕሮግራሙ በሀገር ደረጃ የሚመራበት ራዕይ እንዲኖረው ማድረግን እንደሚጠይቅም ገልጸዋል።

በተመሳሳይ ተወዳዳሪዎች የሚመለመሉበትን መንገድ በጥንቃቄና በተሟላ መልኩ እንዲፈጸም በማድረግ እንዲሁም ቴክኖሎጂዎች ድጋፍ እንዲያገኙና ወደ ብዝሀ ምርት(ማስ ፕሮዳክሽን) ደረጃ እንዲወጡ እንደሚደረግም ጠቁመዋል። በዚህ መነሻነት የኢትዮጵያ ምርቶች እንዲበዙ ማድረግ ላይ መሥራት እንደሚያስፈልግ አስታውቀው፣ በሀገር ውስጥ በተለያዩ ዘርፎች ችግር ፈቺ ምርቶች እንዲባዙ ማድረግ ላይ እንደሚሠራ ገልጸዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ እንዳብራሩት፤ በተለይ ትኩረት በተሰጣቸው ዘርፎች ሊሻሻሉ የሚችሉና ችግር የሚፈቱ የፈጠራ ውጤቶች ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት ከውጭ የሚገባውን መተካት ያስፈልጋል። ይህንን በሀገሪቱ አቅም እያሳኩ ለመምጣት ኢንስቲትዩቱ ትልቅ ራዕይ እንዳለው ጠቁመው፣ እነዚህ የፈጠራ ሥራዎች ቁጭት የወለዳቸው መሆናቸውንም አስታውቀዋል፡፡

ትንሹንም ትልቁንም የቴክኖሎጂ ውጤት ከውጭ ከማስመጣት በሀገር ውስጥ በማምረት ራሳችንን የማንችለው የሚለው ጥያቄ በሁላችንም አእምሮ ሊመጣ ይገባል ሲሉ ተናግረው፣ እንደ የእህል ፕሮስስ ማድረጊያ ትናንሽ የግብርና ማሽነሪዎች፣ ሶፍትዌሮችንና ማዕድን ለማውጣት የሚውሉ ቴክኖሎጂዎችን የግድ ከውጭ ማስገባት ላይጠበቅብን ይችላል ሲሉም አስገንዝበዋል።

‹‹እነዚህን ቴክኖሎጂዎች ያሉንን ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም መሥራት የምንችልበትን መንገድ መቀየስ ያስፈልገናል›› ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ እነዚህን ዓይነት ማሽነሪዎችን፣ አካል ጉዳተኞችን የሚረዱ ቴክኖሎጂዎችንና የመሳሰሉትን የግድ ከውጭ ማምጣት የለብንም፤ ባለን አቅምና ፈጠራ ተጠቅመን መሥራት ይጠበቅብናል›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ በሀገር ውስጥ በተገኙ ፈጠራዎችና አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ለችግሮች መፍትሔዎች ማምጣት ሲቻል፣ በቴክኖሎጂ ራስን ወደ መቻል ይመጣል። ኢትዮጵያውያን ለኢኮኖሚ ነፃነት ጥረት እያደረጉ እንደመሆናቸው፣ በሀገሪቱ ልጆች እውቀትና አቅም በመጠቀም የቴክኖሎጂ ሉዓላዊነትንም እያረጋገጡ መምጣት ይቻላል።

የሌሎች ሀገራት ተሞክሮ የሚያሳየው ይሄንኑ መሆኑን ጠቅሰው፣ በዚህ በኩል ብዙ ልምድ ካላቸው ሀገራት መካከል የምስራቅ ኤዥያ አካባቢ ሀገራት እንደሚጠቀሱም አስታውቀዋል። ሀገሮቹ ከታች ጀምሮ በታዳጊነት እድሜ ክልል ውስጥ ባሉ ወጣቶች ላይ በመሥራታቸው የኢኮኖሚ ሉዓላዊነታቸውን በማረጋገጥ ዛሬ ትልልቅ ኩባንያዎች አፍርተዋል ሲሉም አብራርተዋል።

‹‹ትልልቅ ኩባንያዎች የትንንሽ ሃሳብ ውጤቶች ሲሆኑ፣ መጀመሪያ ከትንሽ ልምምድ የተነሱ ናቸው፤ በእኛም ሀገር እንደዚህ ዓይነቱን ነገር እያሰፋን መሄድን ይኖርብናል›› ብለዋል፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ የስታርትአፕ አዋጁ ብዙ ፋይዳዎች ይኖሩታል። ከእነዚህም መካከል በቅድሚያ ጀማሪ ቢዝነሶችን ለማበረታታት የሚደረገው ጥረት ትኩረት እንዲያገኝ፣ ሁለተኛው የድጋፍ ማሕቀፎችን ተንተርሶ ለተቋማት ድጋፍ እንዲደረግ እንዲሁም ስታርታአፖች ለረጅም ጊዜ ሲጠይቋቸው የነበሩ ተግዳሮቶች እንዲፈቱ ማድረግ ማስቻል የሚሉት ይገኙበታል።

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 14 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You