
– ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከእንግሊዝ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር በሁለትዮሽ ጉዳይ ውይይት አደረጉ
አዲስ አበባ፡– ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ እንግዶቿን የማይረሳ ትውስታ፤ የማያረጅ ትዝታ እንዲኖራቸው አድርጋለች ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከእንግሊዝ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አንጄላ ሬይነር ጋር በዋና ዋና የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን ጉዳዮች ላይ ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ 38ኛው የአፍሪካ ኅብረት መደበኛ ጉባዔ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቅቋል። ሀገራችን ኢትዮጵያም እንደ ኅብረቱ መቀመጫ ሀገር የሚጠበቅባትን አከናውናለች፡፡ ኢትዮጵያ እንግዶቿን የማይረሳ ትውስታ የማያረጅ ትዝታ እንዲኖራቸው አድርጋለች ብለዋል፡፡
አቀባበሉ፣ መስተንግዶውና መርሐ ግብሮቹ እንግዶቻችንን ያስደመመ ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እንግዶቿ የማይረሳ ትውስታ፣ የማያረጅ ትዝታ እንዲኖራቸው አድርጋለች። በዚህ የተነሣ የቆይታ ጊዜያቸውን ያራዘሙ እንግዶች ብዙ እንደሆኑ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ለኅብረቱ ዓላማዎች እና መርሆች መሳካት ያላትን ቁርጠኝነት በጉባዔው ዝግጅትና መስተንግዶ በተግባር እንዳሳየች አመልክተው፤ የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወን ብዙዎች የሚቻላቸውን ሁሉ አድርገዋል ብለዋል።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወን ብዙዎች የሚቻላቸውን ሁሉ አድርገዋል። አዘጋጅ ኮሚቴው፣ የውጭ ጉዳይ ዲፕሎማቶች፣ የፕሮቶኮል ባለሙያዎች፣ የቴሌና የመብራት ተቋማት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የጸጥታ ተቋማት፣ የትራፊክ ፖሊሶች፣ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች፣ ሚዲያዎች፣ የኪነ ጥበብና የሰርከስ አባላት፣ ሆቴሎች፣ የአዲስ አበባ መስተዳድር የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች፣ የጽዳት ባለሙያዎች፣ እንደ አንድ ልብ ሰሚ፣ እንደ አንድ አካል ፈጻሚ ሆነው ሠርተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ሕዝብ ለእንግዶቹ ተገቢውን ክብርና መስተንግዶ በመስጠት፣ መንገዶች ሲዘጉ በትዕግሥት በመጠባበቅ፣ ለጉባዔው ስኬት የሚጠበቅበትን ሁሉ አድርጓል። ለሁላችሁም በኢትዮጵያ መንግሥት እና በራሴ ስም ላቅ ያለ ምስጋና አቀርባለሁ ሲሉ ገልጸዋል።
ሁላችንም በሀገር ፍቅር ስሜት በሥርዓት እና በዲሲፕሊን በመሥራታችን እንግዶቻችንን አስደምመናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ የሀገራችንን ከፍታ አሳይተናል። ከአንድ ሺህ በላይ የሚሆኑት የሚዲያ ሰዎች መልካም ገጽታችንን ለዓለም አሳይተዋል። ከአሥር ሺህ ዎች የሚልቁት እንግዶች እየበለጸገች ስለምትገኘው ሀገራችን ምስክሮች ሆነዋል ሲሉ አመልክተዋል።
ይህ ትብብራችንና ለሀገራችን ስኬት ያለን ቁርጠኝነት፣ ከጉባዔው በኋላም እንደሚቀጥል አምናለሁ። ኢትዮጵያ የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት መሆንዋ በአለት ላይ እስኪጻፍ ድረስ ጥረታችን ይቀጥላል ብለዋል።
በተያያዘ ዜናም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከእንግሊዝ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አንጄላ ሬይነር ጋር በዋና ዋና የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን ጉዳዮች ላይ ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል ፡፡
ኢትዮጵያ እና እንግሊዝ ረጅም ታሪክ እና ጥልቅ ግንኙነት እንዳላቸው ጠቁመው፤የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሯ ጉብኝትም ይሄንን ግንኙነት የበለጠ ያጠናክራል ነው ያሉት፡፡ ወደፊት ስንመለከት፣ አጋርነታችን ከፖለቲካ እና ከዲፕሎማሲ በላይ በመስፋፋት ከፍተኛ የንግድ እና የኢኮኖሚ ትብብርን ይጨምራልም ብለዋል፡፡
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ማክሰኞ የካቲት 11 ቀን 2017 ዓ.ም