‹‹የትኛውም መሪ ይምጣ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ያላት አስተዋጽኦ ተመሳሳይነት ያለው ነው›› – አቶ ትዕግስቱ አወሉ

አቶ ትዕግስቱ አወሉ የምሥራቅ አፍሪካ የጂኦፖለቲካ ተንታኝ

ረጅሙን እድሜያቸውን ያሳለፉት በፖለቲካው ውስጥ ነው:: ከልጅነታቸው ጀምሮ በዘርፉ ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል:: በተለይም በተፎካካሪ ፓርቲ ውስጥ ረጅም ጊዜያት እንደማሳለፋቸው መጠን በአባልነት እና አመራርነት በርካታ ተሳትፎዎችን አድርገዋል:: በዚሁ በፖለቲካው ጉዳይ እስከ 2013 ዓ.ም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ታግለዋል:: ፓርቲያቸውን ይዘው በሌላ ተፎካካሪ ፓርቲ ውስጥ በመዋሃድም ተሳትፎ አበርክተዋል::

የዛሬው የዘመን እንግዳችን አቶ ትዕግስቱ አወሉ ሲሆኑ፣ የፖለቲካ እንቅስቃሴውን ለጊዜውም ቢሆን ያቆሙት አንድነት ፓርቲ ውስጥ በነበሩበት ወቅት ነው:: እንዲያም ሆኖ አሁንም ቢሆን ፖለቲካውን እርግፍ አድርገው አልተውትም፤ በቀጣይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ተሳትፎ ማድረግ እስኪጀምሩ ድረስ ለጊዜው በየትኛውም የተፎካካሪ ፓርቲ ውስጥ ተሳትፎ የላቸውም:: በአሁኑ ወቅት ሶስተኛ ዲግሪያቸውን በመማር ላይ ይገኛሉ::

የዛሬ የዘመን እንግዳችን የምስራቅ አፍሪካ የጂኦፖለቲካ ተንታኝ አቶ ትዕግስቱ፣ የተወለዱት አዲስ አበባ ይሁን እንጂ ያደጉት አሰብ ነው:: አንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተማሩትም እዛው አሰብ ነው:: ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ግን የቤተሰባቸው የሥራ ባህሪ አንዴ አሰብ ሌላ ጊዜ አዲስ አበባ እንደመሆኑ እርሳቸውም አንዴ አሰብ ሌላ ጊዜ አዲስ አበባ በመማር አጠናቀዋል::

የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በታሪክ ትምህርት የያዙ ሲሆን፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በትምህርት ምርምርና ልማት ለመሥራት ችለዋል:: እንግዳችን በአንድ ሁለተኛ ዲግሪ መወሰንን ስላልፈለጉ ሌላ ሁለተኛ ዲግሪም የተማሩ ሲሆን፣ በመካከለኛው ምስራቅ ጂኦፖለቲካ ጥናት ላይ በመሥራት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመርቀዋል:: በአሁኑ ወቅት ደግሞ በኮተቤ የሶስተኛ ዓመት የፒኤች.ዲ ተማሪ ናቸው::

እንግዳችን አቶ ትዕግስቱ፣ ቀደም ባሉት ጊዜያት በፖለቲካ ተሳትፎውም ሆነ በሥራ ደረጃ በተለይ በመምህርነት ብዙ አገልግለዋል:: በግል ኮሌጆችም ሆነ በመንግሥትም ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የታሪክ ትምህርትን አስተምረዋል:: በአሁኑ ወቅት የሚያስተምሩት በኮሌጆች ውስጥ ነው:: በአሁኑ ወቅት ሶስተኛ ዲግሪያቸውን እየሠሩ የሚገኙት በኢዱኬሽናል ፖሊሲ እና ስትራቴጂክ ማኔጅመንት ላይ ሲሆን፣ እየተማሩ ያሉትም በኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ነው:: እንግዳችን የተለያዩ መጣጥፎችን ይጽፋሉ::

አቶ ትዕግስቱ፣ በዚህች ሀገር ላደርግ የምችለው አበርክቶ ይኖረኛል ይላሉ፤ ይህንንም ማሳካት የሚችሉት በፖለቲካ ውስጥ ተሳትፎ በማድረግ እንደሆነም አጫውተውናል:: በየትኛው ፓርቲ የሚለውን ግን አሁን መግለጽ አልችልም ብለዋል:: በፖለቲካው ተሳትፈው የሃሳብ ትግል ማድረግን ይሻሉ:: ምክንያቱም የፖለቲከኛ ጡረተኛ ባለመኖሩ የኢትዮጵያን አንድነት ሊያጠናክር የሚችል አበርክቶ እንዳላቸው አልሸሸጉም:: መቼ የሚለውን በውል ባይናገሩም ወደፖለቲካው ዓለም የማይመለሱበት ምክንያት እንደሌላቸው አጫውተውናል:: አዲስ ዘመን አቶ ትዕግስቱ አወሉን በተለይ በባሕር በር ዙሪያና በቀጣናው ባለው እንቅስቃሴ ዙሪያ የዛሬው የዘመን እንግዳ አድርጎ አቅርቧቸዋል::

አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ምክንያታዊነቱን የሚገልጹት እንዴት ነው?

አቶ ትዕግስቱ፡- ኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄን ማንሳቷ ምክንያታዊ ስለመሆኑ አንዳች ጥርጥር የለውም:: ሀገራችን ቀደም ሲል ባሕር በር የነበራት ሀገር ነች:: በታሪክ አጋጣሚ ግን የአሰብ ወደብን አጥታለች:: የአሰብ ወደብን ያጣችበት ምክንያት ደግሞ ኤርትራን በማጣቷ ነው::

ሉዓላዊ የሆነች ሀገር ወደብ የላትም፤ የባሕር በር ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ባልተናነሰ ሁኔታ የደህንነት ዋስትና ነው:: ለምሳሌ አሰብ ወደብን ብንወስድ ሌላው ቀርቶ ለኤርትራም ጭምር የኢኮኖሚ ጠቀሜታ የለውም:: የአሰብ ወደብ ለኢትዮጵያ የደህንነት ችግር ነው:: ምክንያቱም ጣልቃ ገቦች በጥሩም በመጥፎም እየተጠቀሙበት ነው:: ስለዚህ የባሕር በር አንዱና ዋናው ነገሩ ከኢኮኖሚም ባለፈ የደህንነት ማስጠበቂያም ጭምር መሆኑ ነው::

ለምሳሌ የጂቡቲ ወደብን ብንወስድ ደግሞ በዚያ ዙሪያ የተሰባሰቡት ሀገራት አካባቢያቸው እዚያ ሆኖ አይደለም፤ ነገር ግን በዚያ ቦታ የደህንነት ጉዳይ በመኖሩ ነው:: በሶማሊያም በኩልም ያለው ሁኔታ ይኸው ነው:: በዚያ ቀጣና በተለይም በአፍሪካ ቀንድ በዓለም ደረጃ ስጋት ናቸው ተብለው የተለያዩ ፈተናዎች እንደመኖራቸው ስጋቱ ኢትዮጵያንም የሚመለከት ነው::

በአሁኑ ወቅትም የባሕር በር ጥያቄው መነሳቱ መልካም ነው:: በእኔ ግምገማ ከኢሕአዴግ ጋር ሰው ቂም የተያያዘው የባሕር በር ስላሳጣን ነው:: በሽግግሩ ሰሞን የነበሩት መፈክሮች የባሕር በር ጥያቄ እንደነበሩም የሚታወስ ነው::

የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት የኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ካድሬዎች ወደመጨረሻው ጊዜያቸው ሕዝቡን ይቀሰቅሱ የነበረው “ኤርትራን የምታጣ ከሆነ አንገትህ መቆረጡ ነው” በሚል ነበር:: ይህ ማለት የባሕር በር ታጣለህ ማለት ነው:: ስለዚህ በየሥርዓቱ ጥያቄው በተለያየ መንገድ ይገለጻል:: አሁንም መነሳቱ ትክክል ነው ማለት ብቻ አይደለም መብትም ጭምር ነው:: ምክንያቱም የመጠቀም መብት ስላለን ነው::

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ የባሕር በርን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ማግኘት አለባት ተብሎ ይታመናል፤ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው ይላሉ?

አቶ ትዕግስቱ፡- በእኔ አተያይ ኢትዮጵያ የባሕር በርን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ማግኘት እንዳለባት መገለጹ አግባብነት ያለው ነው:: በሰላም የማይገኝ ነገር የለም። ነገር ግን በመጀመሪያ ኢትዮጵያን በሰላሙ ረገድ ማጽናት አለብን:: የኢትዮጵያን ሰላም ማረጋገጥ አለብን:: አሁን ባለው ሁኔታ መጀመሪያ የራሳችንን የቤት ሥራ መወጣት አለብን:: ከዚያ በኋላ የውጭውን ማየት እንችላለን:: ምክንያቱም ምንም እንኳ የባሕር በር ጥያቄ መጠየቁ ተገቢ ቢሆንም በመጀመሪያ ግን እኛ እራሳችንን አንድ ማድረግና የጋራ ሃሳብ እንዲኖረን ያስፈልጋል::

ይህ የባሕር በር ጥያቄ የጋራችን መሆን አለበት፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የባሕር በር ጥያቄውን እኩል ላያዩት ይችላሉ:: ስለዚህ በመጀመሪያ የውስጥ ሰላማችን ችግር ያጋጠመው በመሆኑ መታከም አለበት:: ኢኮኖሚያችንም የተረጋጋ መሆን አለበት:: ዲፕሎማሲያችን ራሱ ጥሩ የሚሆነው ኢኮኖሚያችን ሲያድግ ነው:: ዲፕሎማሲያችን ደግሞ የመደራደር አቅም መፍጠር አለበት::

የመደራደር አቅም ለመፍጠር ደግሞ በእኔ አተያይ ሶስት ነገሮች መሟላት አለባቸው፤ እነዚህም የቁሳዊ (የዳበረ የኢኮኖሚ)ኃይል, የመደራደር ኃይል እና ሃሳባዊ ኃይል (material power, bargain power, ideational power) ናቸው:: እነዚህ ነገሮች ሳይሟሉ መንቀሳቀስ ለጠላቶች እድል የሚሰጥ ነው::

ልክ በጣሊያን ቅርሶቻችን እንደተወሰዱትና በኋላ ላይም እንደተመለሱ አይነት መንገድ መከተል አለብን:: ትልልቅና እውቀት ያላቸው ሰዎች አሉ፤ በመንግሥት ደረጃ ተደራጅተው አቅም መፍጠር አለብን:: ይህ በሚፈለገው መድረክ ሁሉ መነገር አለበት:: አንድ ብሔራዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ ስለ ጉዳዩ በያገባኛል ስሜት መንቀሳቀስ መልካም ነው:: ጉዳዩ በሕገ መንግሥትም ላይ ሊቀመጥ ይገባል:: ምክንያቱም የትኛውም መሪ ቢመጣ የማስፈጸም መለኪያው ይሆናል:: ዝም ብለን የምናነሳው የባሕር በር ጥያቄ ለፖለቲካ ፍጆታ ብቻ የምናነሳ መሆን የለበትም::

ግብጽ የዓባይ ወንዝን የሕገ መንግሥቷ አካል አድርጋ እንደምትንቀሳቀሰው ሁሉ እኛም የባሕር በር ጥያቄያችንን ሕገ መንግሥታዊ ማድረግ አለብን:: ስለዚህም መሪዎቹ ጥያቄውን የሕልውና ጥያቄ ሊያደርጉት ይገባል ባይ ነኝ:: ምክንያቱም ኢኮኖሚውን በገንዘባችንም ተከራይተንም ወደብ ልናገኝ እንችላለን:: ነገር ግን የደህንነት ጉዳያችንን በተመለከተ የባሕር በር ማግኘት ግድ የሚል ነው:: የሰላማችን ጉዳይ ቀዳሚ መሆን ይኖርበታል፤ ሰላም እስካልተረጋገጠ ድረስ ሌሎች ጥያቄዎች ሊመለሱ አይችሉም::

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት የሚያስችሏት አማራጮች ምን ምን ናቸው ?

አቶ ትዕግስቱ፡- ጥሩ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ካለ ዙሪያችን ወደብ ነው:: በዚህ ስጋት አይኖረንም:: እንዲያም ሆኖ ኢትዮጵያ የባሕር በር ሳይኖራትም ብትቆይ አልወደቀችም:: ይሁንና ከዚህ በላይ ኢኮኖሚያችን ሊያድግ ይገባል:: ምክንያቱም ሕዝባችን እያደገ ነው:: እንደሚታወቀው ደግሞ ምስራቅ አፍሪካ ላይ በሕዝብ ብዛት ኢትዮጵያ አንደኛ ነች:: ይህ እንደ ቀላል የሚታይ አይደለም::

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የዓባይ ግድብን በምትገነባበት ወቅት ብዙ ውጣ ውረድ ማሳለፏ የሚታወቅ ነው:: ከዓባይ የሚገኘውን ጥቅም ለዓባይ ተፋሰስ ሀገራት ማጋራት መልካም ነው:: ተጠቃሚ የሚሆኑበትን እድል መፍጠር ነው:: ይህ አንዱ ከጎረቤቶቻችን ጋር ለሚኖረን ግንኙነት አንዱ መንገድ ነው:: ይህ ሲሆን የድርድር አቅማችንን ማሳደግ እንችላለን ማለት ነው:: በአሁኑ ወቅት ለኬንያ፣ ሱዳንና ለሌሎችም ጎረቤት ሀገራት መብራት እየሰጠን ነው:: ከዚህ በላይ ደግሞ እያሰፋን ብንሔድ የየሀገሩ መንግሥታት ብቻ ሳይሆን መብራት መስጠት ጥቅም ስላለው ሕዝቡ ራሱ ለኢትዮጵያ ሊቆምላት ይችላል::

ለምሳሌ ጂቡቲ እኛ ወደቧን መጠቀም ብናቆም ለማን ይሆናል፤ የጁቡቲ ወደብ ላይ የሸቀጥ ገቢና ወጪ የኢትዮጵያ ነው:: በጥቅሉ ለእኛ ቀይ ባሕር ዋናው ሲሆን፣ በሶማሊያ በኩል ሰላሙ እምብዛም አስተማማኝ ስለማይሆን መተማመን አይኖርም:: አሰብን ብንወስድ አሰብ የአፋር ነው:: ሊኖሩን የሚችሉት ሶስት ወደቦች ናቸው:: ስለዚህ አንዱ ገልፍ ላይ ያለው ነው፤ ይህም እንደ በርበራ አይነቱ ነው:: ሌላው ደግሞ ሶማሌ ላንድ ሲሆን፣ ነገር ግን ሁሉም ነገር በዲፕሎማሲ ሊመጣ የሚገባው ነው:: በጥቅሉ ግን ሰላሙ ካለ እና ኃይል ካለን የትኛውም የባሕር በር አማራጭ የእኛ ነው ማለት ይቻላል:: ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ግን የመደራደር አቅማችን ማደግ አለበት::

አዲስ ዘመን፡- ግብጽ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ እንዳይሳካ የተለያዩ መሰናክሎችን ማስቀመጥ የጀመረችው ኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄዋን በግልጽ በጀመረች ማግስት ነው፤ ግብጽ በዚህ መጠን የኢትዮጵያ እድገት የሚያሳስባት ለምድን ነው ይላሉ?

አቶ ትዕግስቱ፡- ግብጽ ቀደም ሲልም ቢሆን የዓባይ ግድብንም ስትቃወም የነበረው የኢኮኖሚ ችግር ገጥሟት ሳይሆን የዓባይ ወንዝን መቆጣጠር ስለምትፈልግ ነው:: ኢትዮጵያ በፖለቲካውም ጠንካራ እንዳትሆን ከሚመጣ ስጋት የተነሳ ነው:: ምክንያቱም ኢትዮጵያ በሕዝብ ብዛቷም ሆነ በሥልጣኔዋ ተወዳዳሪ ሀገር ነች::

ስለዚህ የግብጽ ሩጫ ዋና ዓላማ የእርሷን ጥቅም ለማስከበር ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ እንዳታድግ በመፈለጓ ነው:: ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ካደገች በመጀመሪያ የምትቆጣጠረው የአፍሪካ ቀንድን ነው:: የአፍሪካ ቀንድ ሀገሮች የምንላቸው አራት ናቸው:: እነርሱም ኤርትራ፣ ሶማሊያ፣ ጂቡቲ እና ኢትዮጵያ ናቸው:: እነዚህ በድንበር ዙሪያ ያሉ ሀገሮች ናቸው::

ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አፋር፤ ጂቡቲም ኤርትራም ውስጥ አለ፤ ኢትዮጵያ ውስጥም ኤርትራ ውስጥ ትግራይ፤ ኢትዮጵያ ውስጥም ሶማሊያ ውስጥም ሶማሌ አለ:: ስለዚህ ኢትዮጵያን የማናጸና ከሆነ በወዲያኛው በኩል ለመሰለፍ የደምም የባህልም ትስስሩ ስላለ ይህ ሕዝብ ተጋላጭ ነው:: ስለዚህ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያም ነች፤ እንደገና የአፍሪካ ቀንድም ነች:: የአፍሪካ ቀንድ የተረጋጋ እና ውጤታማ መሆን የሚችለው ኢትዮጵያ የተረጋጋች ስትሆን ነው::

ኢትዮጵያ የምታድግ ከሆነ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሕዝብ ይኸኛው ይሻለኛል ብሎ ወደሌላው ሀገር አይሔድም:: ኢትዮጵያ ተፈጥሮ የቸራትም ሀብት ትልቅ ነው፤ ሕዝቡ በራሱ ደግሞ ትልቅ ሀብት ነው:: ስለሆነም ይህ ስላለ ግብጽ እየተከላከለች ያለችው የኢትዮጵያን እድገት ነው:: ይህን ተጽዕኖ ለመቋቋም ደግሞ ኢትዮጵያ ራሷን በኢኮኖሚ የበለጠ ማደርጀት አለባት::

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ከቀጣናው ሀገራት ጋር ያላትን ትስስር የበለጠ ለማሳደግ የሚጠበቅባት ምንድን ነው?

አቶ ትዕግስቱ፡- ኢትዮጵያ ብትፈልግም ባትፈልግም የቀጣናው አባል ነች፤ ሶስቱ ሀገራት በድምሩ 40 ሚሊዮን አይሆኑም:: የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ወደ 130 ሚሊዮን የሚገመት ነው:: ስለዚህ በመጀመሪያ መፈጠር ያለበት ሰላም ነው:: ሰላም የማይኖር ከሆነ ምንም ቢታሰብ ስኬታማ መሆን አይቻልም:: በ30 ዓመት የተገነባው ሥራ በ30 ደቂቃ ሊፈርስ ይችላል::

በመጀመሪያ ርዕይ ያላቸው መሪዎች መኖር አለባቸው:: አለመታደል ሆኖ የቀጣናው መሪዎች ከጁቡቲ በስተቀር ሁሉም በእልህ የተወጠሩ ናቸው:: ለምሳሌ የኤርትራው ፕሬዚዳንት በአገዛዝ ሒደቱ ረጅም ዕድሜ ያስቆጠረ ነው:: ሶማሊያም እንደሚታወቀው የተረበሸ ሀገር ነው:: አንጻራዊ ሰላም ያለው ምናልባት ወደብ ስላላትም ወይም ደጋፊ ስላላትም ሊሆን ይችላል ጅቡቲ ነች:: ሌላው ደግሞ ሶማሊያ እና ጂቡቲ የአረብ ሊግ አባል ሀገሮች ናቸው:: በመሆኑም ቀጣናው ላይ የአረብ ፍላጎት አለ::

ቀጣናው የቀጣናው ሀገራት ሀገር ብቻ አይደለም:: በተፈጠረው የደህንነት ክፍተት ሌሎች ገብተውበታል:: ቀጣናው ላይ ከነባሮቹ በተጨማሪ አዳዲሶችም ገብተዋል:: ከገቡት ውስጥ ቱርክን ብንወሰድ እሷ ሶማሊያ ላይ ፍላጎት ስላላት ነው:: አንዳንድ ሀገራት የቀጣናውን ሕዝብ በእውቀት፣ በጤና፣ በሌሎችም መሠረተ ልማት እንዲያገኝ የሚያስቡ ሳይሆኑ ሁሌም እየተዋጋ እንዲኖር የሚፈልጉ ናቸው::

በቀጣናው ትልቁ የችግር ምንጭ የሆነችው ደግሞ ሶማሊያ ናት:: በአሁኑ ወቅት ከሶማሊያ ጋር ተጎድተንም ቢሆን መልካም ነገር መፍጠር ያስፈልጋል:: ኢትዮጵያ አልሻባብ በሶማሊያ ስለነበር፤ አልሻባብ ደግሞ ለኢትዮጵያም ስጋት ስለነበር ከአሜሪካም ጋር በመተባበር ተከላክለነዋል:: ወጣም ወረደ ኢትዮጵያ ለቀጣናው አስፈላጊ ሀገር ነች:: አልሻባብን ለመከላከል ትልቁን ሚና የተጫወተችው ኢትዮጵያ ነች:: ስለዚህ የኢትዮጵያ አስፈላጊነት አይቀሬ ነው:: በመሆኑም ኢትዮጵያ በሰጥቶ መቀበል ስትራቴጂ ዲፕሎማሲዋን ማሻሻል አለባት:: በእርግጥ ይህ ይጠፋቸዋል ተብሎ አይታሰብም::

አዲስ ዘመን፡- እንደ አሕጉር የአፍሪካን ችግር በአፍሪካዊ መፍትሔ የሚለው ሃሳብ በአግባቡ ተግባር ላይ ውሏል ብለው ያስባሉ?

አቶ ትዕግስቱ፡- በሚፈለገው መልኩ ተግባራዊ አልሆነም:: ሆኖም አሁንም ቢሆን እነዚህ የአፍሪካ ሀገሮች ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ የሚለው መርህ መቀመጡም ሆነ ተግባራዊ መደረግ መጀመሩ ተገቢ ነው:: ምክንያቱም አፍሪካዊ የሆነ ችግር ከአፍሪካ ውጭ በሆነ አካል የሚታገዝ ከሆነ መብትን የሚነጥቅ ይሆናል::

በአሁኑ ሰዓት ትልቁ የአፍሪካ ችግር ከቅኝ ገዢዎቻቸው አስተሳሰብ ዛሬም አለመውጣታቸው ነው:: ዛሬም ሃሳባቸው በቅኝ ገዢዎቻቸው የተበረዘ ነው:: ለምሳሌ በአሁኑ ወቅት የምዕራብ አፍሪካ ሀገሮችን ስናይ እያበጣበጣቸው ያለው የፈረንሳይ ጣልቃ ገብነት ነው:: ወደ አፍሪካ ቀንድም ሲመጣ ተመሳሳይ ነው:: ስለዚህ በአፍሪካ ሕብረት መሪዎች ጉባዔ የጸደቀው የ2063 አጀንዳ ስኬታማ መሆን የሚችለው እቅዱ በየሀገሩ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ሲሠራበት ነው::

አፍሪካ የሚለው ስያሜ የሁሉም ሀገር ስብስብ እንጂ የአንድ ሀገር አሠራር ብቻ የያዘ አይደለም:: አጀንዳው በትምህርት፣ በጤና፣ በግብርናው ዘርፍ፣ በመሠረተ ልማት ትስስር፣ በፖለቲካው እና በብዙ እቅድ የታጨቀ ነው፤ እሱን በመጀመሪያ ሁሉም በየሀገሩ ሊሠራው ያስፈልጋል::

አፍሪካ በመፈንቅለ መንግሥት ጭምር እየተሰቃየች ያለች አሕጉር ነች:: የሱዳን ችግር ራሱን የቻለ ነው:: የሶማሊያም ችግር እንዲሁ የሚጠቀስ ነው:: ስለዚህም በበርካታ ችግሮች የተተበተበችው አፍሪካ ችግሮቿን በሙሉ በራሷ አቅም የመፍታት ብቃት ሊኖራት ይገባል::

አለበለዚያ አፍሪካ እርስ በእርስ እንዲጋጭ እና መፍትሔ ከሌላ ቦታ እንዲመጣ የሚደረግ ከሆነ እንዲሁም በኢኮኖሚ ተንኮታኩታ ድጋፍን ከሌላ ቦታ እንድታገኝ የሚደረግ ከሆነ ችግሩ ቀጣይነት ይኖረዋል:: አፍሪካ ለችግሯ መፍትሔ ከሌላ ቦታ ከጠበቀች ሀገራቱ የየራሳቸውን ባንዲራ አውለበለቡ እንጂ ከቅኝ ገዥዎቻቸው መዳፍ አልተላቀቁም ማለት ነው:: በአሁኑ ወቅት ቅኝ ገዥዎች ቀደም ሲል በቅኝ የገዛሁት ሀገር ነው በሚል እንደልባቸው የሚገቡበት አሕጉር ነው::

ስለዚህ ችግሮች ሲፈጠሩ መፈታት የሚገባቸው በአፍሪካውያን መሆን አለበት፤ የማስፈጸሚያ አቅሙ ደግሞ ለምሳሌ ችግር ፈጣሪውን ከኅብረቱ ማገድ ሊሆን ይችላል፣ ይህ ግን በቂ ላይሆን ችላል:: ለምሳሌ አፍሪካ ያሏት ተቋማት ጠንካራ መሆን አለባቸው፤ ለምሳሌ በምስራቅ አፍሪካ ያለው የምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) ጠንካራ ተቋም መሆን አለበት:: በተለይ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ያለውን ችግር ለመፍታት ኢጋድ መግባት አለበት::

ጤናማ የሆነ የፖለቲካ ሥርዓት ከሌለ የ2063 አጀንዳ ቀርቶ ራሳቸውም ሀገር ሆነው ለመቀጠል ያስቸግራቸዋል:: አጀንዳውን ለመተግበር የቸገራቸው ነገር ቢኖር የደህነት መታጣት ነው:: ደህንነታቸውን ማጠናከር አለባቸው::

ሀገራትን የሚያስተሳስረው ኢኮኖሚ ነው:: ኢትዮጵያ ከዚህ አኳያ ብዙ ሀብት ያላት ሀገር ነች፤ ከዚህ አንጻር ለመጫወት ሰፊ ሚና አላት:: አፍሪካ የጥይት ድምጽ የማይሰማባት አሕጉር መሆን አለባት ተብሎ የተቀመጠው በራሱ ትልቅ ግብ ነው::

ስለዚህ አፍሪካውያን በመጀመሪያ አቅም መፍጠር አለባቸው:: ችግሮች ሲፈጠሩ ደግሞ በዴሞክራሲያዊ መንገድ በሰላም የሚፈታበትን መንገድ ማፈላለግ የተገባ ነው:: ተኩስ ይቁም እንጂ ዘለቄታዊ መፍትሔ በአሕጉሪቱ የለም ማለት ያስደፍራል:: ሠብዓዊ መብት እንዲረጋገጥ መሥራት ያስፈልጋል::

አፍሪካ ለራሱ ችግር የራሱን መፍትሔ ለማስቀመጥ የሚያስችለው የራሱ የሆነ ዘዴ አለው፤ ሀብቱም አለው፤ ችግሮችን የሚፈታበት የዳበረ ባህል አለ:: ያንን አውጥቶ የመጠቀም ባህል ግን ገና የዳበረ አይደለም::

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ያላትስ አበርክቶ የሚገለጸው እንዴት ነው?

አቶ ትዕግስቱ፡- ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ያላት አበርክቶ በአንድ ቃለ ምልልስ የሚገለጽ አይደለም:: የኢትዮጵያ አበርክቶ ለአፍሪካ እንደ ርዕዮተዓለም የሚታይ ነው:: ኢትዮጵያ ለጥቁር ሕዝቦች የያደረገችው አበርክቶ እንደ ርዕዮተዓለም የሚታይ ነው:: ምክንያቱም ኢትዮጵያ ለነጻነት ያደረገችው ትግል ትልቅ ሥራ ነው::

ኢትዮጵያ ለነጻነት ሲባል የነጻነት ታጋዮችን ብቁ ያደረገችም ጭምር ነች:: ስለዚህም ኢትዮጵያ የአፍሪካ እናት ነች:: ምክንያቱም በቅኝ ግዛት ስም ተበታትነው የነበሩ ሀገራት ነጻ ወጥተው የየራሳቸውን እይታና ዓላማ እንዲከተሉ አርዓያ የሆነች ናት:: ስለዚህ ኢትዮጵያ የአሕጉሩ እናት ናት ማለት ይቻላል:: በተለይም በትግል፣ በስትራቴጂም የተጫወተችው ሚና የላቀ ሲሆን፣ ለፓን አፍሪካኒዝም ድርሻው ጉልህ ነው::

ስለዚህ አሁንም ቢሆን የትኛውም መሪ ይምጣ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ያላት አስተዋጽኦ ተመሳሳይነት ያለው ነው:: የኢትዮጵያ መሪ የራሱን ሕዝብ ችግር በተፈለገው መጠን ላይፈታና ችግር ሊሆንም ይችላል፤ ነገር ግን በአፍሪካ ጉዳይ ተመሳሳይ የሆነ አቋም ያለው ነው:: ኢትዮጵያውያን መሪዎች በየዘመኑ ለአፍሪካ በትጋት ሲሠሩ ይስተዋላሉ::

ለምሳሌ በቅርብ በሱዳን ግጭት ኢትዮጵያ የሠራችው ሥራ አለ፤ ሩዋንዳም ውስጥ እንዲሁ ሰላም እንዲሰፍን ተሳትፎዋ የጎላ ነበር:: በእርግጥ የኢትዮጵያ ተሳትፎ በአፍሪካ ብቻ የሚወሰን አይደለም:: በነገሥታቱ ጊዜም ቢሆን ኮሪያ ላይ ያደረገችው አጋርነት የሚታወስ ነው::

አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ማብራሪያ አመሰግናለሁ::

አቶ ትዕግስቱ፡- እኔም አመሰግናለሁ::

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 8 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You