የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስ ቲክስ አገልግሎት ድርጅትን የመሠረቱት ድርጅቶች ሦስት ነበሩ፡፡ ከቀደምት መስራቾቹ መካከል በ1956 ዓ.ም የተመሠረተው የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ አክሲዮን ማኅበር እንዲሁም በ1960 ዓ.ም. የተመሠረተው የባህር ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት በቀደምትነት ይታወቃሉ። በ1999 ዓ.ም የተመሠረተው የደረቅ ወደብ አገልግሎት ድርጅት ታክሎበት፣ በ2004 ዓ.ም በሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት እንዲመሰረት ተደርጓል፡፡
ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ዋናው መሥሪያ ቤትና በጂቡቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት፣ ከአምስት በላይ የደረቅ ወደብ አገልግሎት መስጫዎች፣ ባህር ላይ (በመርከቦች) እና በትራንስፖርት አገልግሎት ብዙ ሠራተኞች ያሉት ሲሆን፣ የአገሪቱ የወጪና ገቢ ምርት የጀርባ አጥንት ሆኖ የሚያገለግል ነው፡፡ ድርጅቱ በየዓመቱ በሚያገኘው ትርፍ ምክንያት ከልማት ድርጅቶች በቀዳሚነት ተርታ እንዲሠለፍ አድርጎታል፡፡
በኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የቃሊቲ የየብስ ትራንስፖርትን ማዕከል በማድረግ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የካይዘን ፍልስፍና በቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ አገልግሎት መስጠት ያቆሙ የተለያዩ ማሽኖች ወደ ስራ እንዲገቡ በማስቻል እና ምቹ የስራ አካባቢን በመፍጠር የሰራተኞችን ምርታማነት የጨመረ ሲሆን በአጭር ጊዜ ውስጥ አሰራሩን ቀልጣፋ እና ወጪ ቆጣቢ እንዲሆን አስችሏል። ባለፉት ስምንት ወራት ባከናወናቸው የለውጥ ተግባራት የሎጂስቲክ ጊዜን ከማሳጠር በተጨማሪ የካይዘን ፍልስፍና ተግባራዊ እንቅስቃሴ አድርጎ የተሻለ አፈፃፀም በማስመዝገቡ በቀጣይም ተቋሙ ያስመዘገበውን ውጤት በማስፋፋት ጠንክሮ እንዲሰራ ማበረታቻ ሆኖለታል፡፡
የቃሊቲ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት የየብስ ትራስፖርት ዳይሬክተር አቶ ተሰማ ፎቴ እንደሚናገሩት፤ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ቃሊቲ ቅርንጫፍ የንብረት አጠቃቀም፣ አያያዙ ብክነቱ ከፍተኛ ነበር፡፡ በዚህም የተወሳሰበ ነገር እንዲፈጠር አድርጓል። የሰራተኛ ተነሳሽነት በዛው ደረጃ ዝቅ ያለ ነበር፡፡ የካይዘን ትግበራው በአራት አቅጣጫ እየተፈፀመ ይገኛል፡፡ የመጀመሪያው ማሽን ሾፕና የጥገና ማዕከል፣ ሁለተኛው የመለዋ ወጫ ግምጃ ቤቶች ሲሆኑ ሶስት ትላልቅ የመለዋወጫ ግምጃ ቤቶች አሉት፣ ሶስተኛው የመኪና ማቆሚያ አካባቢን ሲያካትት የግቢው ማዕዘን በጣም ተጣቦ መኪና የሚቆምበት ቦታ ክፍት ለማድረግ ተሞክሯል፡፡ አራተኛው የቢሮ ካይዘን ሲሆን በዚህ ሁሉም ቢሮዎች እንዲቀየሩ ተደርጓል፡፡
እንደ አቶ ተሰማ ገለፃ፤ በቃሊቲ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ካይዘን ስራው ተጠናቋል፡፡ ይህን ተግባራዊ ለማድረግ የተደረጉ ቅድመ ዝግጅቶች አሉ፡፡ ለትግበራው ሶስት ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል። የመጀመሪያው ስልጠና መስጠት ሲሆን ለውጥን የሚመራው አመራር እንደመሆኑ 27 የሚደርሱ የዋና መስሪያቤት ሰራተኞች በካይዘን ኢንስቲትዩት አማካኝነት ስልጠና እንዲሰጥ ተደርጓል፡፡ ለሰራተኞችም በተመሳሳይ ለ275 ሰራተኞች ሶስት ቀን ስልጠና እንዲወስዱ የተደረገ ሲሆን ቀሪዎቹ ተከታታይ የሆኑ ስልጠናዎች ተሰጥቷቸዋል፡፡ ሌላው አደረጃጀት እንዲፈጠር ማድረግ ሲሆን ከዋና ስራ አስፈፃሚ ጀምሮ የጭነት አስተላላፊ እና የካይዘን አብይ ቡድን የሚባል እና የካይዘን ማስተባባሪያ ቡድን እንዲፈጠር ተደርጓል፡፡
ወደ ካይዘን አሰራር ሲገባ በድርጅቱ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ምን ይመስላል የሚለው ቅድሚያ እንዲታይ ተደርጓል፡፡ ቀደም ብሎ በማሽን ሾፕ ውስጥ ካርቶኖችና ቤቶች ተሰርተውበት ነበር፡፡ ተሰርተው የነበሩ ቤቶችን በማፈራረስ እና በማፅዳት ማሽን ሾፑ ለስራ ምቹ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ዋና ጋራዥና የእጥበት ክፍል ለእረጅም ዓመታት መስኮቶቹ በሻተር የተዘጉ በመሆናቸው በመብራት ነበር ጥገና የሚካሄደው፡፡ አሁን ሻተሮቹ ጠቅላላ ተነስተው ብርሃን በመገኘቱ የኤሌክትሪክ ወጪ መቀነስ ተችሏል፡፡ በፊት በቀን አምስት መኪና ይጠገን ነበር፡፡ በአሁን ወቅት ግን ወደ 29 መኪና መጠገን ተችሏል፡፡ በጋራዥ ውስጥ የተለያዩ የተቃጠሉ ዘይቶች የያዘ በርሜልም እንዲወገድ ተደርጓል፡፡ በእጥበት ክፍል ደግሞ የመሬቱ ሴራሚክ ጠቅላላ ጥላሸት ሆኖ ነበር፡፡ የእቃ አቀማመጥ ስርዓት ያለው አልነበረም፡፡ የእቃ ግምጃ ቤቶች በአግባቡ የተደራጁ ስላልነበሩ እንዲደራጁ ተደርጓል። መኪናዎች መቆሚያዎች እና የመኪና ስፖንዳዎች በየቦታው ተዝረክርከው ይታዩ ነበር፡፡ የማስጠገኛና የማስወገጃ በተመሳሳይ የሚጠገኑትም የሚወገዱትም ሳይለዩ ትርምስምስ ብሎ የተቀመጠበት አግባብ እንደነበር አቶ ተሰማ ያመለክታሉ፡፡
ብዙ አይነት የብክነት አይነቶች እንዲለዩ ተደርጓል፡፡ የመጀመሪያው ከሚገባው በላይ ማምረት ሲሆን ይህ ሲባል በመጋዘን ውስጥ እቃ እያለ ተመሳሳይ እቃዎች መግዛትና የሚወገዱ ደረሰኞች መብዛት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የክምችት ብክነት ሲታይ በየቀኑ የመኪና ክምችት እየበዛ መምጣት፣ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት ሳይሰጡ የሚቀመጡ ማሽኖች መኖር፣ አገልግሎታቸውን የጨረሱ ተሽከርካሪዎች ውሳኔ ሳያገኙ ቆሞ መቆየት እንዲሁም መወገድ የሚገባው እቃ አለመወገድ በቃሊቲ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ይስተዋል እንደነበር ይጠቅሳሉ፡፡
እንደ አቶ ተሰማ ማብራሪያ፤ በስራው የተገኙ ውጤቶች ሲታይ ሃያ ዓመት የሞላቸው አስራ ስምንት የሚሆኑ ማሽኖች ተጠግነው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ ከሰባት ዓመት በላይ የቆሙ ሁለት መኪናዎች እንዲሁም 63 ሼልፎች በባለሙያዎች ተጠግነው ጥቅም ላይ እንዲውሉ ተደርጓል፡፡ ከዚህ ስራ አጠቃላይ ሰባት ነጥብ አራት ሚሊዮን ብር ማትረፍ ተችሏል፡፡ለመኪና እጥበት የውሃ ማጣራት ስራ በማከናወን ሶስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ከወጪ ማትረፍ ተችሏል፡፡ ሶስት መቶ ሺ ብር ለጥገና የሚጠይቅ የእቃ ማንሻ ክሬን በድርጅቱ አቅም እንዲጠገን ተደጓል፡፡ በካይዘን ትግበራ የተገኘ ነፃ ቦታ 3 ሺ 975 ነጥብ አምስት ካሬ ነው፡፡ በተጨማሪም ሰራተኛው ላይ ስራ ተነሳሽነት በመፍጠር ከፍተኛ ውጤት ተገኝቷል። የመጋዘን ድምፅ ብክለት እንዲቀንስ ተደርጓል፡፡በጥገና ጋራዥ ማዕከል 19 መግቢያ ብቻ የነበረው ወደ 54 እንዲያድግ ተደርጓል፡፡ የጋራዥ እቃዎች ክምችት ከ86 እስከ 103 አማካይ ከነበረው አሁን 33 ሆኗል፡፡ ከማያገለግሉ እቃዎች ሽያጭ 11 ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ብር ተገኝቷል፡፡ በአጠቃላይ የተገኘው ወደ 27 ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ነው፡፡ በግምጃ ቤት ውስጥ 223 እቃዎች እያሉ እንዲገዛ ተጠይቆ ነበር፤ እንዲቀር ተደርጓል፡፡
የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስ ቲክስ አገልግሎት ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሮባ መገርሳ እንደሚናገሩት፤ የቃሊቲ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ለሃያ ዓመታት ተፈትሾ የማያውቅ ቦታ ነው። ታይተው የማይ ታወቁ እቃዎችና አዳራሾች ተገኝተዋል። በግቢ ውስጥ ህገወጥ ግንባታ እስከመባል የደረሰ መኖሪያ ቤት ተሰርቶበት ነበር። ከዚህ ለመውጣት ትክክለኛው አሰራር ካይዘን በመሆኑ በቅድሚያ ቃሊቲ ቅርንጫፍ እንዲመረጥ ነው የተደረገው፡፡ ከመጡ ለውጦች ዋና ዋናዎቹ የቃሊቲ ቅርንጫፍ እንደአሁኑ አልነበረም አገልግሎት የሚሰጠው፤ አሁን በተሻሻለ አሰራር ውስጥ ገብቷል፡፡ የእቃ ቆጠራ ሂደት ስድስት ወር የሚፈጀው በአስራ አምስት ቀን ውስጥ እንዲጠቃለል ተደርጓል፡፡
ቀደም ብሎ የካይዘን አሰራርን ተግባራዊ ለማድረግ የቁርጠኝነት ችግሮች ነበሩ የሚሉት አቶ ሮባ፤ ከተጀመረ በኋላም ብዙ ጥርጣሬዎች እንደነበሩ ጠቅሰዋል፡፡ የመጀመሪያው ትልቁና ዋናው የበላይ አመራር ትኩረት ሰጥቶ በለውጥ መሳሪያ ተጠቅሞ የአገር ሀብት እንዳይባክን ማድረግ አለመቻል ነው ያሉት አቶ ሮባ፤ ስራው ሲጀመር የሰው ጥርጣሬ የስራው ውጤቱ እንደታሰበው ላይሆን ይችላል የሚል ፍራቻ እንደነበርም ጠቅሰዋል፡፡ በተከታታይ በተሰሩ ስራዎችም ለውጥ መምጣቱንና በስራው ወጪ ሳይወጣ ገንዘቦችን ማዳን መቻሉንም ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን ሀምሌ 15/2011
መርድ ክፍሉ