ለሁለተኛ ግዜ አሜሪካንን ለማስተዳደር ይሁንታ ያገኙት ፕሬዚዳንት በመጀመሪያዎቹ ቀናት ካስተላለፏቸው ውሳኔዎች አንዱ አሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስ ኤይድን) ይሰጠው የነበረውን እርዳታ አገልግሎት ማቋረጥ ነው፡፡ ይህ የትራምፕ ውሳኔ ብዙዎችን ከማስደንገጡም በላይ በዩኤስ ኤይድ ላይ ተንጠልጥለው ለኖሩ ሀገራት ከፍተኛ መረበሽን ፈጥሯል፡፡
በ1960ዎቹ በጆኔፍ ኬኒዲ የተቋቋመው ዩኤስ ኤይድ በእርዳታ ስም በሚሰራው ደባዎቹ ብዙ ጊዜ ይታማል፡፡ ሀገራት በርዳታ ስም ጥገኛ ሆነው እንዲኖሩ እና በተጓዳኝም አሜሪካ እና አጋሮቿ ለሚያወጧቸው ፖሊሲዎች ታዛዥ ሆን እንዲኖሩ ማሰሪያ መንገድ ተደርጎ ይወሰዳል። በዚህም ላለፉት 60 ዓመታት የአፍሪካ ሀገራት በዩኤስ ኤይድ ከሚጣልላቸው እርጥባን አልፈው ራሳቸውን በኢኮኖሚ ለመቻል ተስኗቸው ቆይተዋል። በዩኤስ ኤይድ ሲሰጥ የቆየውም ርዳታ ስንፍናን የሚያበረታታ እና የሥነ ልቦና ጥገኝነትን በሚፈጥር መልኩ ስለተቃኘ ብዙዎች የአፍሪካ ሀገራት በራሳቸው ሀብት ሰርተው ከመለወጥ ይልቅ የዩኤስ ኤይድን ርዳታ እየለመኑ መኖርን ምርጫቸው አድርገው ኖረዋል፡፡
ብዙ ምሁራን እንደሚያምኑትና ከበርካታ ተረጂ ሀገራት ነበራዊ ሁኔታ መገንዘብ እንደሚቻለው ርዳታ ለሰጪው ሀገር እንጂ ለተቀባዩ ሀገር ይዞት የሚመጣ ዘላቂ ጥቅም የለም፡፡ ላለፉት 60 ዓመታት የአፍሪካ ሀገራት ኑሯቸውን ርዳታ ላይ አድርገው የቆዩ ሲሆን ከዚህም የተረፋቸው ግጭት፤ ጦርነት፤ አለመረጋጋት፤ ስደት እና መፈናቀል ብቻ ነው። ጥናቶች እንደሚያሳዩትም በርዳታ የተለወጠ አንድም ሀገር የለም፡፡
እርዳታ ከላይ ሲታይ ጠቃሚ ይምሰል እንጂ ይዞት የሚመጣው መዘዝ ብዙ ነው፡፡ ርዳታ ጠባቂነት ከክብርም በላይ የሥነልቦናም ጦስ ይዞ ይመጣል። የተረጂነትን ባሕል ያስፋፋል፤ ምርታማነትን ይቀንሳል፤ ምጽዋት ጠባቂነትን ያስፋፋል፡፡
ምጽዋት ጠባቂ ማኅበረሰብ ደግሞ ተሸናፊ ነው፤ የሥነልቦና የበላይነት አይኖረውም፡፡ ከሰው ፊትም መቆም አይቻለውም፡፡ እንደ ሀገርም ሉአላዊነትን ሙሉ ለሙሉ ማረጋገጥ አይችልም፡፡
የድህነት ከበርቴዎች ‹‹LORDS OF POVERTY›› ደራሲ ግርሓም ሓንኮክ እንደጻፈው ርዳታ መዘዙ ብዙ ነው፡፡ ሀገራትን ያሽመደምዳል፤ የሀገርን ኩራት ይነጥቃል፤ ጠባቂነትን ያስፋፋል፡፡
ርዳታ ለተረጂዎቹ የሚደረግ ሰናይ ተግባር ይምሰል እንጂ የርዳታ መጨረሻው ግን የረጂዎችን ኪስ ማደለብ ነው፡፡ ከተረጂዎች ይልቅ በበጎ አድራጎት ድርጅት ስም የሚንቀሳቀሱ ተቋማት ከእርዳታ በእጅጉ ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡
ስለዚህም የፕሬዚዳንት ትራምፕ ውሳኔ ለግዜው ድንጋጤ ቢፈጥርም ወደፊት ግን ይዟቸው የሚመጣቸው ጥቅሞች አሉት፡፡ ሀገራት በራሳቸው እንዲተማመኑ እና ባላቸው ሀብትም መበልጸግ እንደሚችሉ መተማመንን ይፈጥራል፡፡ ራስን ከመቻል የተሻለ አማራጭ እንደሌለ ይገነዘባሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ ጥሩ ምሳሌ ነች፡፡
የአስተሳሰብ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ኢትዮጵያ ለሌላው ለመትረፍ እና ለማበደር የሚያንሳት ምንም ነገር የለም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚጨበጥ፣ የሚታይ፣ ለውጥና እድገት አለ። በዚህ በያዝነው ዓመት 8.4 በመቶ እድገት ለማስመዝገብ ጠበቅ ያለ እቅድ ተይዟል። ባለፉት ሶስት ወራት የታዩት አፈጻጸሞች የሚያመላክቱት ኢትዮጵያ በአጭር ግዜያት ከራሷ አልፋ ለሌሎችም መብቃት እንደምትችል ነው፡፡
ግብርናን ብንወስድ፤ ግብርና ባለፉት ዓመታት ከፍተኛ ውጤት የታየበት ዘርፍ ነው፡፡ ቀደም ሲል ክረምት እና ዝናብ ተጠብቆ ሲሰራበት የነበረው የግብርና እንቅስቃሴ አሁን ወቅት የማይገድበው ሆኗል፡፡ በዚህም ምክንያት ሰብል፣ ጥጥ፣ ሆርቲካልቸር ተደምሮ ክረምት ከበጋ ሰላሳ ሚሊዮን ሔክታር መሬት በማረስ 1.4 ቢልዮን ኩንታል ምርት እንደሚሰበሰብ ይጠበቃል፡፡
በቡና የተገኘውም ውጤት የኢትዮጵያ መጻኢ ግዜ ብሩህ መሆኑን የሚያመላክት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከብራዚልና ከቬትናም ቀጥሎ ሶስተኛዋ ትልቅ ቡና አምራች ሀገር ለመሆን በቅታለች፡፡። ባለፈው ዓመት 1.4 ቢልዮን ዶላር ከቡና ኤክስፖርት አግኝተናል። በዚህ ዓመት ሁለት ቢሊዮን ዶላር ገደማ ይጠበቃል።
ዘንድሮ ከአራት መቶ ሀምሳ እስከ አምስት መቶ ሺህ ቶን ድረስ ለውጪ ገበያ ለማቅረብ እቅድ ተይዟል። አራት መቶ ሀምሳ ሺ ቶን ማለት የዛሬ አምስት ዓመት አጠቃላይ የኢትዮጵያ ምርት አራት መቶ ሀምሳ ሺህ ቶን አይሞላም ነበር። ይህ እድገት በቡና ብቻ ሳይሆን በሻይም ምልክት መታየት ተጀምሯል። ሻይ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በስፋት ተተክሏል በጣም አስደናቂም ውጤት እየተገኘበት ነው።
ስንዴን በሚመለከት ሶስት መቶ ሚሊየን ኩንታል ስንዴ በዚህ ዓመት እንደሚመረት ይጠበቃል፡፡ ጤፍ ከ600 ሚሊዮን ኩንታል በላይ እንደሚመረት መሬት ላይ ያለው የማሳ አያያዝ ያስታውቃል፡፡
በርካታ ኢንዱስትሪዎች በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ወደ ምርት መግባታቸው እና አንዳንዶቹም በአፍሪካ ገበያ የማፈላለግ ሥራ ውስጥ መግባታቸው የኢትዮጵያ ምርቶች በቀጣይ የአፍሪካን ገበያ እንደሚያጨናንቁት ይጠበቃል፡፡
ማዕድን በሚመለከት በወርቅ፣ ብረታ ብረት፣ የድንጋይ ከሰል አዳዲስ ፋብሪካዎች ሥራ ይጀምራሉ። በርካታ የወርቅ ፋብሪካዎችም ወደ ሥራ ይገባሉ፡፡ ወደ ውጭ ከተላከ ወርቅ በሦሥት ወራት ብቻ ከ500 ሚሊዮን ዶላር በላይ መገኘቱ ብዙዎችን ወደዚህ ዘርፍ እንዲገቡ እንደሚያበረታታቸው ይጠበቃል፡፡
ሲሚቶን ብንወስድ የለሚ ሲሚንቶ ብቻ በዓመት 450 ሺህ ቶን ሲሚንቶ ያመርታል፡፡ አሁን ያለውን የሲሚንቶ ምርት 16 በመቶ እድገት ሀገር ውስጥ ያመጣል፡፡ እነዚህ ፋብሪካዎች በተሟላ አቅም እየሰሩ ሲሄዱ የኢንዱስትሪው እና የማዕድን ዘርፉ ተደምሮ ከፍተኛ እምርታ ያመጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የአገልግሎት ዘርፉም ቢሆን እድገቱ በጣም አመርቂ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ብቻ ብንወስድ አሁን ያለውን አቅም በብዙ እጥፎች የሚያሳድጉለትን ሥራዎች እያከናወነ ነው፡፡ በአፍሪካ ትልቁ አየር መንገድ ብቻ ሳይሆን፤ በአፍሪካ ሁለተኛ የሆነውን አየር መንገድ በእጥፍ የሚበልጥ አቅም እየፈጠረ ነው፡፡ 124 አውሮፕላን ማዘዝ ብቻ ሳይሆን አሁን ያለን ኤርፖርት ከ20 እስከ 25 ሚሊዮን ተሳፋሪዎች በዓመት ማስተናገድ የሚችል ቢሆንም፤ በቂ ስላልሆነ ከ100 እስከ 130 ሚሊዮን ተሳፋሪዎች ማስተናገድ የሚችል ኤርፖርት ለመገንባት ጥናት ተጠናቋል፡፡ ይህም በአፍሪካ ግዙፉ ኤርፖርት ያደርገዋል፡፡
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ለመስጠት እንጂ ለመቀበል የተፈጠረች ሀገር አይደለችም፡፡ ኢትዮጵያ ቡናን ለዓለም የሰጠች፤ ሉሲን ለዓለም ሕዝብ ያበረከተች፤ በዓለም ላይ አንዲትም ቅንጣት ታክል ውሃ ሳትወስድ ለጎረቤቶቿ 12 ወንዞችን የምታበረክት፤ ስልጣኔን ያስተማረች፤ ሕይወታቸውን በየጊዜው በሚሰው ጀግኖች አማካኝነት ለጥቁር ሕዝቦች ፋና ወጊ የሆነች ሀገር ነች፡፡ ስለዚህም ኢትዮጵያ በተፈጥሮዋ ሰጪ እንጂ ተቀባይ ልትሆን አትችልም፡፡
እነዚህ ተስፋ ሰጪ ተግባራት ኢትዮጵያ በአጭር ግዜ ውስጥ ከተረጂነት ተላቃ ራሷን በምግብ እንደምትችል አመላካቾች ናቸው፡፡ መንግሥት ‹‹ተረጂነት ይብቃ›› በሚል መርህ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ኢትዮጵያን ሙሉ ለሙሉ ከተመጽዋችነት ለማላቀቅ አዲስ ዕቅድ ይዞ መጥቷል፡፡
በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ውስጥ እስከ 250 ሺ ሄክታር በማረስ ኢትዮጵያ በቂ እህል ለማምረትና ከርዳታ ተቀባይነት ለመላቀቅ አቅዳለች፡፡
በዚሁ ተነሳሽነት ውስጥ – ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመቻል ታስቦ በ110 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተዘራው ምርት መሰብሰብ ጀምሯል፡፡ ከ600 እስከ 700 ሺ ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) ጉዳዩን አስመልከተው ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለፁት ሰብአዊ ድጋፍ በራስ አቅም በሚመለከት በየጊዜው የሚኖሩንን የሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎቶች በእያዳንዱ ክልል ላይ የተለያዩ ጥናቶችን መነሻ በማድረግ ወደ ሁለት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎት ለማሟላት እየሠራች ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ 500 ሺህ ሜትሪክ ቶኑ መጠባበቂያ፣ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶኑ ደግሞ የዕለት ደራሽ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህንን ለማሳካትም ወደ 253 ሺህ ሄክታር መሬት ማረስን የሚጠይቅ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ በክረምት ጊዜ እስከ መኸር ያለው ተጠቃልሎ የተያዘ መሆኑን አመልክተው፤ እስካሁን 110 ሺህ ሄክታር መሬት ታርሶ ምርቱ እየተሰበሰበ ነው። ከዚህም ከ600 እስከ 700 ሺህ ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል። ኮሚሽነሩ እንደተናገሩት፤ ሰብዓዊ ድጋፍ በራስ አቅም በሚል ተነሳሽነት፤ ደቡብ ምዕራብ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ሲዳማ፣ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ሐረሪ፣ ድሬዳዋና አዲስ አበባ ራሳቸውን እየቻሉ ስለሆነ ከኮሚሽኑ የሚላክ ሰብዓዊ ድጋፍ የሚባል የለም።
ከዚህ በፊት ሲላክ የነበረውን ሰብዓዊ ድጋፍ ክልሎች አሁን በራሳቸው አቅም እየሸፈኑ ነው። ለተቀሩትም ክልሎች ቢሆን የሚላክላቸው በ30/70 መስፈርት ሲሆን፣ እንዲህም ሲባል 70 ከመቶ በራሳቸው አቅም፤ 30 በመቶ ደግሞ ኮሚሽኑ የሚደግፈው ነው። የምግብ ሉአላዊነትን ለማስጠበቅ ፖሊሲ ተነድፎ እየተሠራ ነው ያሉት አምባሳደር ሽፈራው (ዶ/ር)፤ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ይህንኑ ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
በጋ ላይና ክረምትን ጨምሮ 2017 እና 2018 ዓ.ም በአመዛኙ እንደሀገር ራስን ለመቻል የተያዘ ሲሆን፤ እቅዱ እንደሚሳካ ጅምሮቹ ማሳያዎች ናቸው ብለዋል። የምግብ ሉዓላዊነት ማምረትንና ያመረትነውን ለራሳችን ፍጆታ ማዋልን የሚጠይቅ ነው ያሉት ኮሚሽነሩ፤ በቅርቡ በተጀመረው የሌማት ትሩፋት ተነሳሽነት ሀገራዊ የምግብ ሉዓላዊነት ማረጋገጫ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።
የውጭ ርዳታ ፈላጊነት፣ ጥገኝነትና ተረጂነት እየከፋ ሲሄድም ወደ ልመና የሚወስድ አባዜ እንዳይኖር የሚያደርግ በመሆኑ ለማስቀረት ውጤታማ ሥራ እየተሠራ ስለመሆኑ አስገንዝበዋል። ‹‹ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመቻል ከቤተሰብ እስከ ክልሎች ድረስ ሁሉም በጋራ መረባረብ ካልቻለና ሚናውን ካልተወጣ ሌላ አማራጭ የሌለበት ነው። ራሳችንን መቻል የክብራችን፣ የነጻነታችንና የሉዓላዊነታችን መገለጫ ነው” ሲሉ አምባሳደር ሽፈራው (ዶ/ር) አመልክተዋል። ሰብዓዊ ድጋፍ በራስ አቅም ለመቻል ፖሊሲና ስትራቴጂ ተቀርጾ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ለሰብዓዊ ድጋፍ በሀገራችን ያለው አቅም ሕዝባችን ነው። ብዙ አጋሮችና የመንግሥት አቅሞች ተሰባስበው የሚፈጥሩት ነገር ቢኖርም፤ ሕዝባችን ውስጥ ያለው የአይበገሬነትና የመደጋገፍ ሥራው ከምናስበው በላይ ጠንካራ ነው ያሉት ኮሚሽነሩ፤ በየአካባቢው ባለው እንደ እድርና እቁብ ያሉ አደረጃጀቶች የሚሠራው ሥራ ከፍ ያለ ነው። ሕዝቡ በባሕላዊም ሆነ በሃይማኖታዊ መንገድ ያለው የመረዳዳት ልምዱ የሚበረታታ እንደሆነ ተናግረዋል።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ራሷን በምግብ ለመቻል እያደረገችው ያለው ጥረት የሚበረታታ ነው፡ ፡ ከእርዳታ ጠባቂነት ለመውጣት የተቀየሰው መንገድም ተስፋ ሠጪ ነው፡፡ ስለዚህም አርሶ አደሩ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከርዳታ እሳቤ እራሱን ማውጣትና ራስን በምግብ ለመቻል የሚደረገውን ጥረት ሊያግዝ ይገባል፡፡ ሁሉም ርዳታ መቀበልን ከተጸየፈ ኢትዮጵያ ከተረጂነት ወደ ሰጪነት የምትሸጋገርበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፡፡
አሊሴሮ
አዲስ ዘመን ሐሙስ የካቲት 6 ቀን 2017 ዓ.ም