«… ሸማኔው ደጉ … ጠንካራው ብርቱ
ኩሩ ባህልህ….. መለያ እምነትህ
‘ማያልቅ ፈጠራህ …
ሰርተህ በዓለም …ይታወስ ሞያህ
ድብቅ ውለታህ
ኦሆ ሸማ… ሸማ
ኦሆ ሸማ… ሸማ
…ወገን ሸማኔ … የወንዜ የአገሬ
የትውልድ ገጽታ አሻራ ታሪኬ …» እያለች ድምፃዊት ምንይሹ ክፍሌ ስታዜም የሸማኔዎች ውለታ ይሰማናል። የለበስነው ጥበብ የተከናነብነው ጋቢ እፊታችን ይደረደራል ። እናም ምስጋና እና ሙገሳ አያንሳቸው ይሆን? ውለታቸውን የምንመልስበት እንደ እነሱ ጥበብ ባይኖረንም ጥበበኞቹ ግን በመረዋው ድምጻቸው ስራቸውን አክብረዋል ፤አወድሰዋል።
በታቃራኒው ደግሞ “ባጎረስኩ እጄን ተነከስኩ” አይነት ጥበብ ባለበሱ ስም ሲሰጣቸው፣እንደ ሙያ እና ባለሙያ ሳይቆጠሩ መኖራቸውን ስናስታውስ ደግሞ ያሳዝናል። ይሁንና ለዛሬ የ“ህይወት እንዲህ ናት” አምዳችን እንግዳ የመረጥነው ወጣት አሳምነው አርባ ይህንን ምልከታ ከሚቋቋሙትና ትችቱን ወደጎን ትተው ለሙያው ክብር ከሚሰጡት መካከል አንዱ ነው። እርሱ ሽመና እና ሸማኔ በሚለው መጠሪያ አያፍርም።
ኑሮን ለመግፋት ብቻ ሳይሆን ሽመናን ጥበብን መቅጃ መንገድ አድርጎ ስለሚወስደውም ሙያዬና ማንነቴ ነው ይለዋል የሽመና ስራን። ሽመና ጥበብ ነው። ኑሮን ለመግፋት በአንድ መስክ ላይ መሰማራት ግድ በመሆኑ የሚሰራበት ብቻም አይደለም። ለመስራት ገንዘብ መሰረታዊ ነገር ቢሆንም ለእርሱ ግን የሥራው ፍቅር ይበልጥበታል። በዚህም ከ11 ዓመቱ ጀምሮ ዛሬ ድረስ ዘልቆበታል።
እናም የሙያ ፍቅሩን በሀይል ደግፎና ውጤታማነትን አጠናክሮ ትልቅ ቦታ እደርስበታለሁ ብሎ ያምናል፤ለዚህም ይጣጣራል ። ብዙ ተሞክሮዎች አሉኝ የሚልበት ሙያም ይኸው ሽመና መሆኑን ይናገራል። እኛም በዚህ ሙያ ያካበተውን ልምድና ፈተናዎቹን ያለፈበትን መንገድ ትምህርት ይሆነናል በሚል እንዲህ አቀረብነው።
ደጉ ልጅ
ወጣት አሳምነው አርባ የተወለደው አዲስ አበባ በተለምዶ ሽሮ ሜዳ 04 ቀበሌ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ቢሆንም እድገቱ ግን ከአርባምንጭ በትንሽ ርቀት ላይ በምትገኘው ጬንጫ ዞን ልዩ ስሟ ቢላላና ሻዬ በምትባል የገጠር ከተማ ውስጥ ነው። ጳጉሜን አምስት ቀን 1973ዓ.ም የአዲስ ዓመት መግቢያ ዋዜማ ለእነ አቶ አርባ ቤተሰብ አሳምነው በረከት የተቸረበት ጊዜ ነበር። እናት እና አባቱ የበኩር ልጃቸውን አሳምነውን አግኝተው ቤታቸው በመጀመሪያ ወንድ ልጅ ተባርኳል።
ይህ መሆኑ ደግሞ ቤተሰቡ በቤተሰብ ተከቦ እንዲያሳልፍ ሲባል እናትና አባቱ ልጃቸውን አንከብክበው ወደ ትውልድ ቀያቸው አቀኑ። አሳምነውም በአያትና ቅድመ አያት እንዲሁም በሞላው ቤተሰብ ውስጥ ተሞላቆ እንዲያድግ ሆነ። አዲስ አበባን ለቆም የቢላላና ሻዬን የተፈጥሮ አየር እየሳበ የልጅነት ቡረቃውን ቀጠለ። በዚህ ቦታ አሳምነው ልጅነቱን ሲያሳልፍ ቤተሰቡን ከብት በመጠበቅ ያግዝ ነበር። የእነአሳምነው ቤተሰብ በህብረት መኖርን የለመደ በመሆኑ አሳምነው ከከብት እገዳው ሲመለስ የቤት ውስጥ ሥራዎችንም ያከናውናል።
መቼም ብዙዎቻችሁ «አርባ» ማለት ምን ይሆን እያላችሁ የራሳችሁን ግምት ስትሰጡ እንደቆያችሁ ልገምት። ከቁጥር ጋር የሚያቆራኝ ይኖራል። ይህ ግን የተለየ ትርጓሜ ያለው ነው። በጋሞዎች ዘንድ ብዙ ጊዜ ስም የሚያወጣው አባት ነው። ስለዚህም የአሳምነው አባት አርባ የሚል መጠሪያ ተሰጥቷቸዋል። አርባ ማለት «ጀግና ወይም አርበኛ» ነው። አቶ አርባ ጀግና መሆን ባይችሉ በጣም ደፋርና የተጣላን አስታራቂ መሆን ችለዋል። ለሰላም ለሚሰራ ሰው ደግሞ ጀግና ቢባል ምን ይከፋል። እርሳቸውም አሳምነውን «ውዱጋ» ሲሉ ይጠሩታል። ይህ ማለትም በጋሞኛ “የአለቆች ሁሉ አለቃ ወይም ጀነራል“ እንደማለት ነው።
በእነአሳምነው ቤት ውስጥ ብዙ ቤተዘመድ ቢኖርም በቤት ውስጥ ማንም ሰው ተቀምጦ አይበላም። ሁሉም መስራት አለበት። ብዙ ጊዜ ሴቶች ድውር ሲያዳውሩ ወንዶቹ ይሸምናሉ። እናም አሳምነውም እድሜው ከፍ እስኪል ድረስ ድውር ያዳውር እንደነበር ያስታውሳል። ከአስር ዓመቱ በኋላ ግን የመጀመሪያ ልጅ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ወደ ሽመና ስራው ገብቷል።
ወጣት አሳምነውን ከልጆች ሁሉ ለየት የሚያደርገ ባህሪያት አሉት። የመጀመሪያው ለሰው ሁሉ በእኩል ደረጃ ታዛዥ ነው። ከታዛዥነቱ ብዛት የራሱን ሥራዎች ሁሉ ትቶ የሰዎችን ይሰራል። በዚህም «ደጉ ልጅ» የሚል ቅጽል ስም ወጥቶለታል። ሌላው መለያ ባህሪው የዋህነት ነው። ነገሮችን በውይይት መፍታት መቻሉ፤ ከሰዎች ጋር በቶሎ የመግባባት ችሎታና አቅሙም ለየት ያደርገዋል።
አሳምነው በልጅነቱ ብዙን ጊዜ መጫወት የሚወደው የበዓል ወቅት መጨፈር ሲሆን፤ በተለይ መስቀል ሲመጣ ከጓደኞቹ ጋር ወንዝ በመውረድ አዳራቸውን ሲጨፍሩና ሲዘፍኑ የሚያሳልፉት ጊዜ ልዩ ስሜትን እንደሚፈጥርለት ይናገራል። ከዚያ ውጪ የሚደሰተው በሽመናው ላይ በሚፈጥራቸው የጥበብ ሥራዎች ነው። በዚህም አባቱ ቶሎ ሥራዎችን የመረዳት ችሎታውንና የፈጠራ አቅሙን በጣም ያደንቁለት እንደነበር ያስታውሳል።
አሳምነው በ12 ዓመቱ ዳግም ወደ አዲስ አበባ ከአባቱ ጋር መጣ። ይህ ደግሞ ይበልጥ ብዙ ሀላፊነቶችን እንዲወስድ ያደረገበት ወቅት እንደነበር ይገልጻል። ምክንያቱም የሚኖሩት በዘመድ ቤት በመሆኑ ብዙ የሚያጨናንቁት ነገሮች ነበረና አባቱን መደገፍ ላይ ነው ትኩረቱን ያደረገው። ስለዚህ ብዙ የሥራ ጫና ወድቆበታል።
በእርግጥ ይላል እንግዳችን በእርግጥ «ጊዜው ደግና ሰውም ሩህሩህ ነበር። ስለዚህም የአባቴም ጓደኛ ቤቱ ውስጥ ሲያስጠልለው ምንም አይነት ክፍያ አይጠይቀውም። እንደውም በባህሉ ዘንድ«ገማ» በአማርኛ ገንዘብ እስኪይዝ ድረስ በነጻነት በቤቱ እየተጠቀመ እንዲኖር ረድቶታል። እኔም ብሆን ነጻ ሆኜ እንድማርና ቤተሰቤን እንዳግዝ አግዞኝ ነበር። ይሁንና አባቴን አለማገዝ ይከብዳልና ብዙ ሥራዎችን አከናውን ነበር» ይላል። በተለይ ደግሞ አባቱ ወደ ትውልድ ቀያቸው በተጓዙበት ወቅት ትልቅ ጫና ውስጥ ገብቶ እንደነበርና የልጅነት አቅሙን እንደፈተነው አይረሳውም።
የትምህርት ጥማት
አሳምነው ወቅቱ የደጎች ዘመን በመሆኑ አባቱ መታወቂያ ባይኖራቸውም በሌላ ዘመድ መታወቂያ አማካኝነት ነበር ትምህርት ቤት የገባው። እናም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን የተማረው ድል በትግል የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው። አሳምነው ጠዋት ትምህርት ቤት ይውልና ከሰዓት ሲመለስ ሸማ በመስራት ኑሮውን ቢገፋም ማታ ግን በምንም መልኩ የጥናት ጊዜውን የሚሻማበት አልነበረም። ስለዚህም የልጅነት የትምህርት ፍላጎቱ ታክሎበት በትምህርቱ ጎበዝ ተማሪ ነበር።
የአሳምነው አባት እስከስምንተኛ ክፍል የተማሩ በመሆናቸው ደግሞ ይበልጥ የትምህርትን ጥቅም ጠንቅቀው ያውቃሉና ለጨዋታ ጊዜ ሳይሰጥ ትምህርቱ ላይ ትኩረት እንዲያደርግ ይገፋፉታል። ሰው የሚለወጠው በትምህርትና በሥራ ነው ብለው ስለሚያምኑም ከዚህ ውጪ አልባሌ ቦታ ልጃቸው እንዲውል አያደርጉትም። በዚህም ጎበዝና የደረጃ ተማሪ ሆኖ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን እንዲከታተል ሆኗል።
«አባቴ መቼም ቢሆን በሽመና ሙያ እንድቀጥል አይፈልግም። ምክንያቱም ለሸማኔ የሚሰጠው ግምት ዝቅተኛ በመሆኑ ነው። ስለዚህ የሁልጊዜ ምኞቱ ተምሬ ራሴን ለውጬ የተሻለ የሚባለውን ሙያ እንድይዝ ነው።» የሚለው እንግዳችን፤ የአባቱ ለትምህርት ትኩረት መስጠት በትምህርቱ ውጤታማ እንዲሆን እንዳስቻለውና አባቱ ለትምህርት የሚሰጡት ዋጋ አባቱን በህይወት ካጣም በኋላ እንዲቀጥል እንዳስቻለው ይናገራል።
ወጣት አሳምነው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እስከ አስረኛ ክፍል የተከታተለው በቀድሞ ተፈሪ መኮንን ሁለተኛ ደረጃ በአሁኑ እንጦጦ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤት ነው። ከዚያ በኋላ ግን በተለያዩ ችግሮች ምክንያት አልገፋበትም። ሆኖም ከአስረኛ ክፍል አቋርጦ « በደረጃ ሶስት ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ» በዚያው በእንጦጦ ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ሰልጥኗል። በወቅቱ ምንም አይነት ገንዘብ በእጁ ላይ እንዳልነበረ የሚገልጸው ባለታሪኩ፤ ኑሮ ርካሽ ቢሆንም ብር ማግኘት ግን በጣም ከባድ ነው። በዚህም ቤተሰቡን መግቦ ለማደር ሥራ ላይ ማተኮር ነበረበትና ትምህርት ገትቶ ለቤተሰቡ መኖር ጀመረ።
በእርግጥ ይህ ብቻ አይደለም ለማቋረጤ መንስኤው የሚለው አሳምነው፤ ህንዶች በሽመና ሥራ ላይ የተሰማሩትን ለማሰልጠን መምጣታቸው ነው። ስለዚህ ውጤታማ የሚሆንበትን ጠንቅቆ የሚያውቀው አሳምነውም ትምህርቱን አቁሞ ወደ ስልጠናው እንደገባ ይናገራል። የአባት ሞትና ቤተሰቡን የማስተዳደር ሀላፊነት በእርሱ ጫንቃ ላይ ማረፉም አንዱ ለትምህርቱ መቋረጥ መንስኤ ነበር። ምንም እንኳን የትምህርት ፍቅሩ ቢኖረውም መቀጠል ግን አልቻለም።
የሽመና ውለታ
«በ11 ዓመቴ ሽመናን ባልጀምር ብዙ ነገሮች ዛሬ ላይ አጣ ነበር። በመጀመሪያ የማጣው ቤተሰቤን ይሆን ነበር» ይላል። ድር ከማዳወር የጀመረውን ስራ ያጠናከረው ሽመናን ከሚሰራው ሰው አጠገብ በመቀመጥ እነርሱ ሲለቅሙ አለቃቀሙን በመከተል ጀመረ። የተለያዩ ዲዛይኖችን እንዴት ማውጣት እንደሚቻልም በአይኑ እያማተረ ይከታተላል። መጨረሻ ለእነርሱ በሚመጥን መልኩ እንጨት ተዘጋጅቶለት ወደ ለቀማ ሥራ መግባቱን ይናገራል። ይህ ከታለፈ በኋላም በዚያው መልቀሚያ ልምምድ ጎን ለጎን ደግሞ ያግዛሉ። ፍጻሜው ጥበብ መስራት መቻል ነውና ጥበብ ሰሪነቱን ተካነው።ይህ ደግሞ ለእርሱ ቀላል እንደነበር ይገልጻል።
ብዙ ጊዜ የሽመና ሥራ የሚሰራው ከእርሻ በኋላ ነው። ከብቶች የሚጠብቁት ሌሎች ልጆች ከሆኑ በቤት ውስጥ ቀሪ የሆነው ቤተሰብ ሽመናውን ያከናውናል። ይህ ደግሞ በ11 ዓመቱ ሙያውን ለምዶ ቤተሰቡን አጋዥ እንዲሆን እንዳስቻለውና ከለቀማ አልፎ የተለያዩ የጥበብ ሥራዎችን መስራት እንዳበቃው ይናገራል። እንዳውም በአንድ ጊዜ ሦስት ስራ ይሰራል። ያዳውራል፤ ይለቅማል፤ ይሸምን እንደነበርም ያስታውሳል።
«አዲስ አበባን በስም እንጂ ምን እንደምትመስል አላውቃትም፤ መብራቷ ሲንቦገቦግና የመኪናው ትርምስ ሲበዛ እንዲሁም ሽሮ ሜዳ ገባን ሲባል ብቻ ነው የተገነዘብኩት። ይህ ደግሞ ብዙ አዲስ ነገሮች እንደሚያጋጥሙኝ አስገንዝቦኝ ነበር። ሆኖም ለመስራትና ለመለወጥ እንዲሁም እውቀቴን ከፍ ለማድረግ መጥቻለሁና መውደቅ እንደሌለብኝ አምኛለሁ። ችግሮችን ተጋፍጬ ማሸነፍም ፍላጎቴ ነው። በዚህም የማልቋቋመውን ተቋቁሜ አልፌያለሁ» ይላል።
የአባቱ ግፊት ምንም እንኳን ትምህርት ላይ ቢሆንም ያለባቸው ጫና ለመቋቋም ሽመናውን በስፋት እንዲሰራ እንዳደረጉት የሚያነሳው ባለታሪኩ፤ ክፍለአገር መሄዳቸውን ተከትሎ ብቻውን ለማደርም ሆነ እየሰራ የቤት ኪራይ ለመክፈል በእጅጉ ይከብደው እንደነበር ያስታውሳል። ግን በልቶ እንዲያድርም የሆነው በዚያ ሙያ በመሆኑ ሙያውን እንደሚያከብር ይናገራል።
«ሽመና ለእኔ ባለውለታዬ ነው። አያቴን ከሞት ታድጎልኛል። አያቴ ህመም ላይ እንዳለ ቶሎ ድረሱ ሲባል እጃችን ላይ ምንም ገንዘብ አልነበረም። ስለዚህም ማሳከምም ሆነ ለእርሱ መድረስ የሚቻልበት ሁኔታ አልነበረም። ግን አንድ ነገር በእጃችን ነበር ጥበብ ወይም ሙያ። እርሱን ወደ ገንዘብ በመለወጥ ሰው ማትረፍ እንደሚቻል ያየሁት ከዚያ በኋላ ነው። ሌሊት ሙሉ ስንሰራ አድረን ሁለት ጋቢ አደረስን። ከዚያ አባቴ በጠዋት ሸጦ ወደ አገር ቤት በመሄድ እርሱን ማትረፍ ቻለ።» ይላል።
አሳምነው የሽመና ሙያውን ውለታ ሲናገር በዚህ አላበቃም። በማግስቱም ቢሆን ሳይተኛ የቤቱን ጎዶሎ የሞላው በዚሁ በሽመና ስራው እንደነበር ያነሳል። ይህ ባይሆን ኖሮ ቤተሰቡ በረሃብ ያልቅ እንደነበርም ያስታውሳል። በእርግጥ እርሱ እየለፋ እኔ እንዴት እቀመጣለሁ በማለት እናቱ ከእንጦጦ ተራራ እንጨት ለቅመው በመሸጥ ቤቱን ይደጉሙ ነበር። ይህ ግን በቤት ውስጥ ላለው ስምንት ቤተሰብ ከባድ እንደነበር አይረሳውም። እናም ዛሬም ቢሆን «ሽመና ለእኔ ምግቤ፤ ህይወቴም ነው» ይላል።
ፈተናዎች
በህንዶች አማካኝነት የቀለም ውህደትን ተምሮ ለብዙዎች እንዳሰለጠነ የሚናገረው አሳምነው፤ እውነትም የትውልድ ገጽታ… እውነትም የታሪክ አሻራ… እውነትም የማንነታችን መታያ አለ ከተባለ ሸማኔዎች ጋር ነው። ነገር ግን ብዙ መሞላት ያለባቸው ችግሮች አሉ ይላል። ለአብነት እስከዛሬ 10 ብር ይገዛ የነበረ ክር ዛሬ 40 ብር ገብቷል። ከዚያም ይባስ ብሎ ጥሬ እቃነቱ ጥራትም ሆነ ብዛት ወርዷል። ይህ ደግሞ እኔም ሆንኩ መሰሎቼን በየጊዜው በምሬት ውስጥ እንድናልፍ እያደረገን ነው ይላል።
ከአንዱ አገር የሚመጣው ጥሬ እቃ ከሌላው አገር መለየቱም ዋጋ እያስከፈላቸው እንደሆነ የሚገልጸው አሳምነው፤ አገር ውስጥ የሚመረቱት ጥሩ ጥራት ያላቸውና ከኮተን የሚመረቱት በምን ምክንያት እንደቆሙ ባይታወቅም በዚህም እየተቸገሩ መሆኑን ይናገራል። የመስራትና ውጤታማ የመሆን አቅማቸውን እንዳዳከመባቸውም ያስረዳል።
ሌላው በሥራው ላይ ፈተና የሆነው ትዕዛዝ ሰጥቶ የሚጠፋው ሰው መብዛት ሲሆን፤ በሦስት መቶ ብር ቃብድ እስከ ሁለትና ሦስት ሺ ብር ኪሳራ ማጋጠሙን ይናገራል። የሌላን ሰው ፍላጎት ደግሞ መጥቶ የሚወስደው ሰው ቁጥር እጅግ አናሳ ነው። በዚህም ሳይሸጥ የሚቀመጠው ጥበብ ይበራከታል። ገንዘብ መያዙ ደግሞ ቶሎ ቶሎ ለመስራትና ሌሎች ጥሬ እቃዎችን ለማምጣት ያስቸግራል። በጥራትና በጊዜ ሌሎች ተጠቃሚዎችን ለማርካትም ፈተና ይሆናል። ሰራተኛም ቢሆን ገንዘብ አያገኝምና ይሸሻል። ስለዚህ የማንወጣው ችግር ውስጥ ነን ይላል።
ያለ ጥሬ እቃ ደግሞ ሽመናው አዋጭነትም ሆነ የመሰራቱ እድል አይኖረውም። ስለዚህም በቀጣይ ከጓደኛው ጋር በመሆን ፈቃድ አውጥተው ይህንን ዘርፍ ለማዘመንና ችግሮችን ለመፍታት እንዳሰበ አጫውቶናል።
ከዜሮ ወደ አንድ ሚሊየን
የወጣት አሳምነው ትልቁ ካፒታሉ ሰው መሆኑን ይናገራል። ደንበኞች ላይ በስፋት ሰርቻለሁ። እኔ ከ11 ዓመቴ ጀምሮ እንደዘለኩበት ቤተሰቤም ይህንን ሙያ እንዲወደው አድርጌያለሁ። በዚህም ዛሬ ላይ ከወንድሞቼ ጋር እንድሰራ ሆኛለሁ» ይላል። ትልቅ ማሳያ ሱቅ ከፍተን አብረን እንድሰራ የሆነው፤ ራሳችን እየሸመንን ለነጋዴው የምናከፋፍለው፤ በጋራ ተንቀሳቅሰን የገንዘብ አቅማችንን ከፍ ማድረግ የቻልነው በገንዘብ ሳይሆን በሙያው እና በደንበኞች ብዛት ነው ሲል ይናገራል።
«መነሻችን እጃችንና ሙያው ነው። ሱቃችንን የሞላው ከአንድ ሚሊዬን ብር በላይ የሚገመተው አልባሳትም በዚሁ ሙያ የመጣ ነው። አሁን ሁላችንም ራሳችንን የቻልነው፤ ቤት የገዛነውም በሙያው ጠንክረን በመስራታችን ነው። በትውልድ አገራችን ቤት ሰርተናል። ይህ ደግሞ ለማምረቻም ሆነ ምርታማነታችንን ለመጨመር ሰፊ እድል ይሰጠናል። እዚያ ተመርቶ እዚህ የሚሸጠው ብዙ ነው። የሰው ጉልበትና ሌሎች ነገሮች ደግሞ በብዛት የሚገኙት በዚያ ስለሆነ ይህንን ማድረጋችን ሀብት እንድናካብት አድርጎናል» ይላል። በዚያ ላይ በቅርቡ በትውልድ ቀዬአቸው ዳቦቤት የመክፈት እቅድ እንዳላቸው ነግሮናል።
ከአባቱ ጋር በነበሩበት ጊዜ ጠንክሮ በመስራት እስከመቼ ለቤት ኪራይ ተብሎ ባጠራቀሟት ገንዘብ የገዟት ቤትም ካፒታላቸው እንደሆነች የሚናገረው አሳምነው፤ ዛሬ «ደሬ» የሚባል አገር በቀል ድርጅት ላይ በመሳተፍ የበጎ አድራጎት አገልግሎት ይሰጣል። ከወንድሞቹ ውጪ በየዘርፉና በየችሎታቸው አስር ለሚሆኑ ሰራተኞች የሥራ እድል ፈጥሯል። በተመሳሳይ ለጥልፍና ለስፌትም እንዲሁ ሌሎች ሰራተኞችን በኮንትራትና በቋሚነት ቀጥሮ እያሰራ ነው። እንደ ወቅቱ ሁኔታ ደግሞ የሥራ እድል የፈጠረላቸውም ሰዎችም አሉ።
አምራች እንደመሆናቸው መጠንም የባነር ላይ ጽሁፎች፤ የሶፋና ለቲሸርት የሚሆኑ የተለያዩ ሎጎዎችንም ሆነ ጽሁፎችን ይሰራሉ። የተለያዩ ጋዎኖችንም እንዲሁ በፈለጉት ዲዛይን ሰርተው ያቀርባሉ። ይህ ደግሞ ካፒታሉ ላይ የሚደመር ነው ሲል አጫውቶናል።
ቤተሰብ
ልጅነቱ ያስተማረው የመግባባት አቅም ለዛሬ የትዳር አጋር የምትሆነውን ባለቤቱን እንዲያገኝ አስችሎታል። በሄደበት ማደር የሚወደው፤ የጓደኞቹ እህቶች ሳይቀሩ እንደወንድም የሚቀርቡት አሳምነው፤ አንድ ቀን ይህ የሚቀየርበት እድል ተፈጠረበት። መቼም የውሃ አጣጭ ከየት እንደሚመጣ አይታወቅም አይደል? ስለዚህ ከጓደኞቹ ሚስት እህት አንዷ ላይ አይኑ አረፈ። በፍቅርም ተመኛት። ስለዚህ ምን ማድረግ እንዳለበት ሲያወጣ ሲያወርድ ቆይቶ አንድ ቀን ድፍረት አገኘና ጠየቃት። እርሷም ብትሆን በፍቅሩ ተነድፋ ኖሮ ወዲያው እሽ አለችው። ግን ቤተሰብ ይህንን መቀበል በጣም ከብዶት ከረመ። ቤቱንም ሆነ የንግድ ሱቁን እስከመደብደብ ደርሰው እንደነበርም አይረሳውም። ግን ምን ያድርግ ፍቅር ነዋ! ታገሰ።
በወቅቱ የዛሬዋ ባለቤቱ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ነበረች። በዚህም ለአዲስ አበባ ተወላጅ ተማሪዎች ዶርም አይፈቀድምና ተከራይታ በምትማርበት ጊዜ ነበር ያወቃት። ከዚያ ምንም እንኳን ቤተሰብ አሻፈረኝ ቢልም እርሷ ግን ምርጫዋን እርሱን አድርጋለችና አብረው መኖርን መረጡ። ከዚያ ቤተሰቧን ወደ ጎን ትተው እርሱ በሚያደርግላት ድጎማ ትምህርቷን ተመርቃ ሥራ ያዘች። ትዳሩም ተጧጧፈ። መጨረሻ ላይ ቤተሰብ ከልጁ ርቆ መቆየት አይችልምና ባይወድም በግድ ጋብቻቸውን ተቀበለው። ዛሬ ግን ሁሉም በደስታ ተለውጦ የአንድ ልጅ አባትም ሆነዋል።
የሰዎች ነኝ
«እኔ የሰዎች ነኝ ብዬ ሁልጊዜ አስባለሁ። ምክንያቱም ለእኔ መኖር እነርሱ ናቸው መሰረቱ። ለእነርሱ ደግሞ እኔ አስፈልጋለሁ። ስለዚህ መተጋገዝና ለሰዎች ብሎ መኖርን ገንዘብ ማድረግ ይገባል። ዛሬ አንድነት የሌለውና ወንድም በወንድሙ መጨካከን የበዛው ለእራሴ የሚለው ስለበዛ ነው። ማንም በራሱ መኖር አይችልም። የሰውነት ክፍሎች እንኳን በአንድነት መስራት ካልቻሉ አንዱ ቢጎል አብሮ የሚጎለው ብዙ ነገር አለ። እናም ሰዎች ሲኖሩ እኔ እኖራለሁ ማለትን ልምድ ማድረግ ይገባል» ይላል።
ሰዎች በየዋህነትና ባለማወቅ ክፉ ነገር ያደርጋሉ። ከሁለት ሻንጣ በላይ የባህል ልብሶችን በእምነት በመስጠቴ ከ50 ሺህ ብር በላይ ያጣሁትም በእነዚህ አይነት ያለመታመን ህይወት ውስጥ ባሉ ሰዎች ነው። ዛሬም ቢሆን መታመንን ማጉደል አልፈልግም። ምክንያቱም ምንም አልጎደለብኝም። ከዚያ የበለጠ መወደድና አክብሮትን አክሎልኛል እንጂ። ስለዚህ ሰዎች ማድረግ ያለባቸው ብዙ ሰርቀን ከምናተርፈው ይልቅ ጥቂት ነገር አድርገን እንደሚበዛልን ማመን ላይ መጠንከር ነው ሲልም ይመክራል።
ለቀሪው እድሜያችን በረከት የሚሆነንን ለማግኘት ባለን መደሰትና በሰዎች ደስታና ማግኘት መርካት ነውም ይላል። እኛም መልዕክቱ ለህይወታችን መሰረት ይሁን በማለት አባይን በጭልፋ እንዲሉ ታሪኩን በዚህ ቋጨን። ሰላም!
አዲስ ዘመን ሀምሌ 14/2011
ጽጌረዳ ጫንያለው