ባለፈጠራ ሀሳቦችን በፋይናንስ የመደገፍ አበረታች ተግባር

በሀገሪቱ የፈጠራ ሀሳብ ማመንጨትና በዚህ የፈጠራ ሀሳብ ሥራ መፍጠር ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ ሆኗል። ሥራ ጠባቂነት በሥራ ፈጠራ እየተተካ ነው።

ሥራ ከመንግሥት ይገኛል ብሎ መጠበቅ ጊዜው ካለፈበት ዓመታት ተቆጥረዋል። የግሉ ዘርፍ ሌላው ሰፊ የሥራ እድል የሚያስገኝ ዘርፍ እየሆነ ቢመጣም፣ ያለውን የሥራ ፈላጊ ብዛት ጥያቄ መመለስ የሚችል አይደለም።

ለእዚህ አንዱ መውጫ እየሆነ የመጣው በራስ አቅም ሥራ መፍጠር ነው። ለእዚህ ደግሞ የፈጠራ ሀሳብ ማመንጨትና ያንን ወደ ሥራ መለወጥ ያስፈልጋል። በርካታ ወገኖች የፈጠራ ሀሳብ በማመንጨትና ሥራ በመፍጠር ባለሥራ ከመሆናቸው በተጨማሪ ለሌሎች በርካታ ሰዎች የሥራ እድል እየፈጠሩ ናቸው። የማኅበረሰብንም ሆነ የሀገርን ችግር በመፍታት በኩል የራሳቸውን ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ፡፡

በዚህ የወድድር ዓለም የፈጠራ ሀሳቦች ተወዳዳሪ ሆነው መቅረብ እንዳለባቸውም ይታመናል። ለእዚህም ሥራ ፈጣሪዎች አዳዲስ የፈጠራ ሀሳቦቻቸው ችግር ፈቺ እንዲሆኑ ለማድረግ በተለይ የግድ በሳይንስና ቴክኖሎጂ መታገዘ ይኖርባቸዋል።

መንግሥት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የፈጠራ ሀሳብ ያላቸውን ወጣቶች በተለያየ መንገድ እየደገፈ መሆኑ ይታወቃል። ባለተሰጥኦዎችን መሰረት በማድረግ በቡራዩ የተከፈተው ማዕከል እንዲሁም በመንግሥትና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በመሆን የሚያከናውናቸው ሥራዎች ለእዚህ በአብነት ሊጠቀሱ ይችላሉ።

ይህን ሁሉ ጥረት ተከትሎ የባለተሰጥኦ ወይም የፈጠራ ሀሳቦችን ይዘው የሚመጡ ወጣቶች ቁጥርም እየጨመረ ይገኛል። ይህንንም ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ጋር ተያይዘው ከሚካሄዱ ባዛርና ኢግዚቢሽኖች፣ ስልጠናዎችና የተለያዩ የድጋፍ አማራጮች መረዳት ይቻላል። የእነዚህ ድጋፎች ተጠቃሚ የሆኑ ወጣቶችም በቴክኖሎጂ የተደገፉ፣ ችግር ፈቺ የፈጠራ ሀሳቦችንና ውጤቶችንም እያበረከቱ ናቸው።

የሥራ ሀሳባቸው ግን በጥናት ላይ የተመሰረተና ችግርን የሚፈታ፣ ማምረትን ወይም ምርትና ምርታማነትን ማሳደግን ማዕከል ያደረገ ሊሆን ይገባል። ለእዚህ ደግሞ ተጨማሪ ድጋፎች ያስፈልጓቸዋል፡፡

ባለ ተሰጥኦዎች የፈጠራ ሀሳባቸው ሰሚና ተመልካች ማግኘቱ ወደ ሥራ ተለውጦም ጥቅም የሚያስገኝበት ሁኔታ መፈጠሩ አንድ ነገር ነው፤ ይህ በእንዲህ እንዳለ በተለያዩ ችግሮች ሳቢያ የፈጠራ ሀሳባቸውንና ሥራቸውን መሬት ላይ ለማውረድ ሲቸገሩ የሚስተዋሉ ባለፈጠራ ሀሳቦችም አሉ።

ይህም ሁኔታ ተጨማሪ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ያመላክታል። ድጋፉ የተወሰነ ደረጃ ድረስ መዝለቅ ይኖርበታል። ድጋፉ በሌሎች የተለያዩ ምክንያቶችም አስፈላጊ ነው፡፡

ሌሎች ዜጎችም የፈጠራ ሀሳብ ያላቸው ወይም ሥራ የፈጠሩ ሰዎችን ሲመለከቱ በርካቶችም ያላቸውን እምቅ አቅም ለማውጣት እንደሚጥሩ ይታወቃል። በሀገሪቱም በሥራ ፈጣሪዎች ሊፈቱ የሚችሉ በርካታ ችግሮች ይታያሉ።

መንግሥት የፈጠራ ሀሳብ ያላቸውን ሰዎች በስልጠናና በፋይናንስ ለመደገፍ እያከናወነ ካለው ተግባር በተጨማሪ የግሉ ዘርፍ ድጋፍ ወሳኝ ነው። የግሉ ዘርፍም በተለያዩ ጊዜያት በባለተሰጥኦዎች መካከል ውድድር እያካሄደ የተሻለ ውጤት ያገኙትን ብድር በማመቻቸት ጭምር የሚደግፍበት ሁኔታ እየታየ ነው፡፡

ለእዚህም አዋሽ ባንክ ‘’ የታታሪዎቹ’’ እና ‘’የቀጠሌወን’’ የተሰኙትን የሥራ ፈጠራ ውድድሮች እና የኢትዮጰያ ንግድ ባንክ የሚያዘጋጀውን ‘’ነጋድራስ’’ የሥራ ፈጠራ ውድድሮችን በአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በእነዚህ ውድድሮች ላይ በመሳተፍ በርካታ ሥራ ፈጣሪዎች የፈጠራ ሥራዎቻቸውን እያቀረቡ ይገኛሉ። ተወዳዳሪዎቹ ይዘዋቸው የሚቀርቡት የፈጠራ ሥራዎች በሳይንስና ቴክኖሎጂ ተደግፈው ለማኅበረሰቡ ችግር ፈቺ ሊሆኑ የሚችሉ ናቸው፡፡

አዋሽ ባንክ በተለያዩ ጊዜያት የፈጠራ ሥራ ያላቸውን ዜጎች ወደ ፊት ለማውጣት በርካታ ሥራዎችን በመስራት ላይ ይገኛል። ባንኩ የፈጠራ ሀሳብ ያላቸው ዜጎች ሀሳባቸውን በስልጠና በማጎልበት ወደ መሬት እንዲያወርዱና የፋይናንስ ድጋፍ አግኝተው የፈጠራ ሥራዎቻቸውን እንዲያስፋፉም የበኩሉን አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው።

ባንኩ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ከፍተኛ በጀት በመመደብ ሥራ ፈጣሪዎችን ለማበረታታትና ተገቢውን የፋይናንስ ድጋፍ እንዲያገኙ ለማድረግ ሲያካሂድ የቆየውን ሁለተኛውን ምዕራፍ ‘’ የታታሪዎቹ’’ እና ‘’የቀጠሌወን’’ የሥራ ፈጠራ ውድድር የመዝጊያ ፕሮግራም ባለፈው ሳምንት አካሂዷል፡፡

ይህ የሥራ ፈጠራ ውድድር በርካታ ወጣቶች ተሳትፈውበታል፤ ውድድሩ ለአንድ ዓመት ያህል ብርቱ ፉክክር ሲደረግበት የቆየና ሰፊ የቴሌቪዥን የስርጭት ሽፋንም ያገኘ ነው። ወጣቶቹ በውድድሩ ላይ በናሙና (prototype) የተደገፉ ሥራዎቻቸውን አቅርበዋል፤ ብርቱ ፉክክር አድርገዋል፤ በዳኞች ውሳኔ መሰረት ከ1ኛ–5ኛ ደረጃ ለወጡ ተወዳዳሪዎች ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ባንኩ ከ200 ሺህ ብር እስከ አንድ ሚሊየን ብር የገንዘብ ሽልማት ያበረከተላቸው ሲሆን፣ በተጨማሪም ፕሮጀክታቸውን እውን የሚያደርጉበት እስከ አምስት ሚሊየን ብር ብድር ያለዋስትና እንደየፕሮጀክታቸው ሁኔታ አመቻችቶላቸዋል።

በመዝጊያ ፕሮግራሙ ላይ ንግግር ያደረጉት የአዋሽ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ፀሐይ ሽፈራው እንደገለፁት፤ ባንኩ ላለፉት 30 ዓመታት የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት እንዲያስመዘግብና የኅብረተሰቡ ኑሮ እንዲሻሻል አስተዋፅኦ የሚያደርጉ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን ሲሰራ ቆይቷል፡፡

አነስተኛና ጥቃቅን ቢዝነሶች የወደፊቷን ኢትዮጵያ ለማሳደግ የራሳቸው ድርሻ አላቸው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ባንኩ ይህን በመረዳት በአደረጃጃት ረገድ ለጥቃቅን፤ አነስተኛና መካካለኛ ቢዝነሶች ልዩ ትኩረት በመስጠት እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የታታሪዎቹ’’ እና ‘’የቀጠሌወን’’ የሥራ ፈጠራ ውድድር ወቅቱን የጠበቀና ፍላጎት ተኮር ስልጠናዎችን በየዓመቱ ለበርካታ ባለራዕይ ሥራ ፈጣሪዎች በመስጠት ወደ ሥራ ለማስገባት የታለመ መርሃ ግብር መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ እንደዚህ አይነት የሥራ ፈጠራ ውድድሮች የሥራ ፈጣሪዎች የሚያጋጥሟቸውን ሶስት ዋና ዋና ችግሮች ለመቅረፍ ይረዳሉ። እነሱም የክህሎት፤ የሥራ መነሻ ካፒታል፣ ሥራው ከተጀመረ በኋላ የሚያስፈልገውን የሥራ ማስኬጃ ፋይናንስ ችግር ለመቅረፍ ይጠቅማሉ፡፡

በእነዚህ ውድድሮች ከ1ኛ- 5ኛ ደረጃ የወጡ ከ200 ሺህ ብር እስከ አንድ ሚሊየን ብር የሚደርስ የገንዘብ ሽልማት እንደተበረከተላቸው የገለፁት አቶ ፀሐይ፣ ፕሮጀክታቸውን እውን የሚያደርጉበት የአምስት ሚሊየን ብር ብድር ያለዋስትና እንደየፕሮጀክታቸው ሁኔታ ተመቻችቶላቸዋል ብለዋል፡፡

በዚህ የሥራ ፈጠራ ውድድር ላይ ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የተወጣጡ አምስት ሺህ ሥራ ፈጣሪዎች ተመዝግበው ከአንድ ሺህ 600 በላይ የሚሆኑ ሥራ ፈጣሪዎች ተለይተው በአስር ቋንቋዎች የክህሎት ስልጠና እንደተሰጣቸውም ገልፀዋል፡፡

የባንኩ ፕሬዚዳንት እንዳብራሩት፤ በመጀመሪያና በሁለተኛ ምዕራፍ ተሳታፊ ለነበሩ ሁሉም ሰልጣኞች መሰረታዊ የቢዝነስ ንድፈ ሀሳብ አዘገጃጃት፣ የቢዝነስ ፕላን አቀራረፅ፣ የተግባቦት ክህሎትና መሰል መሰረታዊ ዕውቀት የቀሰሙበት ስልጠና ተሰጥቷቸዋል። በአጠቃላይ 134 የሥራ ፈጠራ ሀሳቦች፣ 80 የታታሪዎቹ ተወዳዳሪዎች በአማርኛ ስልጠና ተከታትለው ዳኞች በሰጡት ውጤት 12ቱ ለመጨረሻ ዙር አልፈው ባሳለፍነው ሳምንት ለፍፃሜ ደርሰዋል፡፡

በተመሳሳይም 54 ቀጠሌወን ከኦሮሚያ ክልል ተመርጠው በአፋን ኦሮሞ ስልጠና እንዲከታተሉ ተደርጓል፤ የፈጠራ ሀሳባቸውንም በአፋን ኦሮሞ አቅርበዋል። ከ54 ቀጠሌወን ውስጥ ስምንቱ ለፍጻሜ ውድድር አልፈዋል።

በቀጠሌወን ውድድር ላይ ተሳትፈው ከ1ኛ- 5ኛ ደረጃ ለያዙ ተወዳዳሪዎች ከ200 ሺህ ብር እስከ አንድ ሚሊየን ብር የገንዘብ ሽልማት እና ከዋስትና ነፃ የሆነ አምስት ሚሊየን ብር ብድር ተመቻችቶላቸዋል። ከ6ኛ- 8ኛ ለወጡ ተወዳዳሪዎች ከ80 ሺህ ብር እስከ 100 ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ቀጠሌወን የሥራ ፈጠራ ውድድር በኦሮሚያ ክልል ያለውን የሥራ አጥነት ለመቅረፍ ለሚደረገው ርብርብ አስተዋፅኦው የጎላ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ጠቅሰው፣ በቀጣይም መሰል ውድድሮች እንደሚካሄዱ ጠቁመዋል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዳንኤል ተሬሳ እንደገለፁት፤ በሀገሪቱ በርካታ የሥራ ፈጠራ ሀሳብ ያላቸው ዜጎች አሉ፤ እነዚህ የፈጠራ ሀሳብ ባለቤቶች ወይም ሥራ ፈጣሪዎች በቂ ስልጠናና የፋይናንስ ድጋፍ ካላገኙ የፈጠራ ሥራዎቻቸውን ሙሉ በማድረግ ወደ ገበያው ለመውጣት ይቸገራሉ። እንደዚህ አይነት ውድድሮች ሥራ ፈጣሪዎች ወደ ፊት እንዲወጡና የፈጠራ ሀሳባቸውን ወደ መሬት እንዲያወርዱ ዕድል እንደሚፈጥሩላቸውም ገልፀዋል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው እንዳስታወቁት፤ ለኢኮኖሚ ዘርፉ ጉልህ ሚና ያላቸው ሀሳቦችን በውስጡ ለያዘው ለእዚህ የሥራ ፈጠራ ዘርፍ ትኩረት ሳይሰጠው ቆይቷል። እንደዚህ አይነት ሥራ ፈጣሪዎችን የሚያበረታቱ ውድድሮች መካሄዳቸው አዳዲስ የሥራ ሀሳቦች ያላቸው ዜጎች ወደፊት እንዲወጡ ያደርጋቸዋል፡፡

አዋሽ ባንክ ባዘጋጃቸው የሥራ ፈጠራ ውድድር ላይ ያየናቸው ሥራ ፈጣሪዎችም ለሀገር የሚጠቅሙ አዳዲስ የሥራ ፈጠራ ሀሳቦችን ይዘው የመጡ ናቸው ያሉት አቶ ዳንኤል፣ እነዚህ የሥራ ፈጣሪ ወጣቶች የፋይናንስ ድጋፍና ስልጠና እንዲሁም የመስሪያ ቦታ ካገኙ ችግር ፈቺ የፈጠራ ሥራዎችን መስራት ይችላሉም ሲሉ ገልፀዋል፡፡

መንግሥት ትኩረት አድርጎ እየሰራበት ያለው ስታርትአፕ ቴክኖሎጂ ኢትዪጵያ ለበርካታ ሥራ ፈጣሪዎች መፍለቂያ እንድትሆን እንደሚረዳ ጠቅሰው፣ እንደዚህ አይነት ውድድሮች ወጣቶች የሥራ ፈጠራ ሀሳባቸውን ይበልጥ ይዘው ወደፊት እንዲቀርቡ እንደሚያስችልም ጠቁመዋል፤ አዳዲስ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ውጤቶች እንዲመጡ የሥራ ዕድሎችም እንዲፈጠሩ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አላቸው ብለዋል፡፡

ውድድሮቹ ከወጣቶች ባሻጋር ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎችንም እንደሚያበረታቱም ተናግረዋል። አዳዲስ ሀሳቦች እንዲመጡና እነዚህ ሀሳቦችም ወደ ሥራ ሲለወጡም የማኅበረሰቡን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮች እንደሚፈቱም ጠቅሰዋል፡፡

በሀገራችን አዳዲስ የሥራ ፈጠራ ሀሳቦች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው ሲሉ ተናግረው፣ በርካታ ኢንተርፕራይዞች እየተደራጁ መሆናቸውንም ገልጸዋል። መንግሥትም ትኩረት አድርጎ እየሰራ የሚገኘው ክህሎት እንዲቀድምና እያንዳንዱ ሥራ በክህሎት እንዲመራ ለማድረግ ነው ሲሉም ጠቅሰው፣ በዚህም ውጤት እየተገኘ መሆኑን አመልክተዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው እንዳሉት፤ ተወዳዳሪዎች ይዘውት የቀረቡትን የፈጠራ ሀሳብ በይበልጥ እንዲያጎለብቱ ስልጠናዎችን መውሰዳቸው ያላቸውን የፈጠራ ሀሳብ በክህሎት እንዲደግፉት ይረዳቸዋል። ባንኩም ለተወዳዳሪዎች ስልጠና መስጠቱ ለክህሎት ቅድሚያ እየተሰጠ እንዳለ የሚያመላክት ነው።

እንደዚህ አይነት የፈጠራ ሥራዎች የፋይናንስ ድጋፍ እንዲያገኙና የመስሪያ ቦታ በማመቻቸት ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት በጋራ በመስራት እነዚህን የሥራ ፈጠራ ሀሳቦች ወደ መሬት በማውረድ ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋፅኦ ኢንዲያበረክቱ ማድረግ ይገባቸዋል:: ሀሳብ ብቻ ሆነው መቅረት እንደሌለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡

መንግሥት ሥራ አጥነትን ለመቀነስ የሪፎርም ሥራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ የጠቆሙት አቶ ዳንኤል፣ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴርም የዜጎችን አዳዲስ የሥራ ዕድል ፈጠራ ሀሳቦች ወደ መሬት ለማውረድና ክህሎት ተጨምሮባቸው ለሌሎችም የሥራ ዕድል እንዲሆኑ ለማድረግ እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡

‹‹መንግሥት ብቻውን የሥራ ዕድል መፍጠር አይችልም›› ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣ የሥራ ፈጠራ ሀሳቦችን በፖሊሲና በተለያዩ ሕጎች እንዲጠናከሩ በመስራትና ለሥራ ፈጣሪዎች ድጋፍ በማድረግ ዘርፉን ማሳደግ ይገባል ብለዋል፡፡

በዚህ አዋሽ ባንክ ባዘጋጀው የ’’ቀጠሌወን ‘’ የፈጠራ ሥራ ውድድር አንደኛ ወጥቶ የአንድ ሚሊየን ብር ተሸላሚ የሆነው ከሰላሌ ፊቼ የመጣው ተወዳዳሪ ወጣት አብረሃም እሸቱ ነው፤ ወጣቱ ይዞት የቀረበው የፈጠራ ሥራ በጸሀይ ኃይል የሚሰራ ተሽከርካሪ ነው።

ሁለተኛ የወጣው ደግሞ የ700 ሺህ ብር ሽልማት ያገኘው ፊሮምሳ ገረመው ይባላል፤፤ ፊሮምሳ ይዞት የቀረበው የፈጠራ ሥራም ለግብርናው ዘርፍ ችግር ፈቺ የሆነ ድሮን ነው። ይህ ድሮን ለሰብል ተባይ መከላከያ ኬሚካል ለመርጨት የግብርና መሳሪያዎችን ከቦታ ቦታ ለማድረስም ይጠቅማል፡፡

ሐይማኖት ከበደ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ የካቲት 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You