ዕለቱ ሰኔ 29 ቀን 2012 ዓ.ም ነው። በታሪካዊቷ ጎንደር ከተማ ተገኝተናል። የታላላቅ ነገሥታት መቀመጫ በነበረችው በዚህች ድንቅ ከተማ የመገኘታችን ምስጢር ደግሞ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሚያስመርቃቸው የነገዋ ኢትዮጵያ ብሩህ ተስፋ የሆኑት ወጣቶች ምርቃት ስነ ስርዓት ላይ ለመታደም ነበር። በያዝነው ዓመት ከስምንት ሺ በላይ ተማሪዎችን በተለያዩ የትምህርት መስክ ያስመረቀው ዩኒቨርሲቲው እንደ ባለታሪኮቹ ነገሥታት ለአገር አለኝታና ኩራት መሆኑን ተያይዞታል።
ለቤተሰብና ለአገር የደስታ ቀን በሆነው በዚያች ዕለት ዩኒቨርሲቲው ለተመራቂዎች በክብር እንግድነት የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር የሆኑትን አቶ አወል አርባን ጋብዞ የማነቃቂያ መልክት አስተላልፈው ነበር። በመልክታቸውም የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እና ተመራቂዎች ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና እና ዕድገት ለመምራት ከማንኛውም ጊዜ በላይ በአንድነት እና በፍቅር በጋራ መተባበር እንደሚኖርባቸው መልክታቸውን አስተላልፈዋል።
ርዕሰ መስተዳደሩ ለተመራቂዎች መልዕክታቸውን በማስተላለፍ ብቻ ወደ ክልላቸው አልተመለሱም። የዩኒቨርሲቲውን የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ተመልክተዋል። ይህ ብቻ አይደለም ለክፍለ ዘመናት የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ሳያስደፍሩ በአንድነት ነገሥታት የጣሉትን የኪነ ሕንፃ አሻራ እና ታሪክ ወደያዘው መሀል የጎንደር ከተማ በማቅናት የአፄ ፋሲል ቤተመንግሥትን ጎብኝተዋል።
በዚህ ስነ ስርዓት ላይ የታደመው የዝግጅት ክፍላችን የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድሩ የያኔውን የኢትዮጵያ ርዕሰ መንግሥት ታሪክ እና የስልጣኔ ምልክት መመልከታቸው የፈጠረባቸውን ስሜት በቃለ መጠይቅ አስቀርቷል። ይህን መልዕክታቸውን ሰፋ ባለ መልኩ ከማንሳታችን አስቀድመን ግን የጉብኝቱ ዋና አካል የሆነው የአፄ ፋሲል ቤተ መንግሥትን በወፍ በረር ለመመልከት እንሞክር።
የታሪካዊቷ ጎንደር አሻራ
የአፄ ፋሲል ቤተመንግሥት ወይንም የነገሥታት ግቢ በጎንደር ከተማ የሚገኝ ምሽጎችና የቤተመንግሥታት ድንቅ የኪነ ሕንፃ ግንብ ስብስብ ነው። ግቢው የተመሰረተው በ1628 ዓ.ም በዓፄ ፋሲል ደስ እንደነበር የታሪክ አዋቂዎች እና ድርሳናት ይገልጽሉ። ማቀባበያ የሚሰኘው የግቢው አጥር 900 ሜትር ርዝመት ሲኖረው በውስጡ 70 ሺ ስኩየር ሜትር የመሬት ይዞታ ያካልላል። አጼ ፋሲለደስ የመጀመሪያውንና ታላቁን ግንብ ያሠሩ እንጂ፣ ከእርሳቸው በኋላ የተነሱት ነገሥታትም ለ220 ዓመታት የየራሳቸውን ሕንፃ በመሥራት ቦታው በቅርስ እንዲዳብር አድርገዋል። በግቢው የመጨረሻውን ሕንፃ ያሠራችው ንግሥት ብርሃን ሞገስ ትባላላች።
የነገስታቱ ቤተ መንግሥት እና የርዕሰ መንግሥት መቀመጫ ገናና በነበረበት ዘመን በሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶችና ሱቆችን በውስጡ ያቅፍ ነበር። በጥንቱ ዘመን የአስተዳደር ስርዓት ተቀርጾለት በጥንቃቄ የሚመራ እንደነበርም ታሪክ ያስገነዝበናል። ስርዓቱም ‹‹ስርዓተ መንግሥት›› በመባል ሲታወቅ በመጽሐፍ መልኩ በግዕዝና በድሮው አማርኛ የተመዘገበ ነበር።
ፋሲል ግቢ፣ የውሃ እጥረት እንዳይገጥመው በማሰብ ‹‹በአንገርብ እና ቃሃ›› በተሰኙ ሁለት ምንጮች መካከል ነበር የተመሰረተው። ከግቢው በስተደቡብ የጎንደር አደባባይ ሲገኝ፤ ቦታው ለገበያነት፣ ለአዋጅ መንገሪያነት እና ለወንጀለኛ መቅጫነት ያገለግል ነበር። በአሁኑ ወቅት የጎንደር ከተማ መናፈሻ በመሆነ ያገልግላል። ማቀባበያ የሚሰኘው የግቢው አጥር ግንብ በዙሪያው 12 በሮች ሲኖሩት፤ እነዚህ በሮች ግልጋሎታቸውን የሚወክሉ ስያሜ ነበሯቸው። አንዳንዶቹ በሮች ከውጪኛው ዓለም ጋር ይገናኙ የነበሩት በትላልቅ ድልድዮች ነበር። ምንም እንኳ አብዛኞቹ የግቢው ቤቶች በጦርነትና እሳት ቢወድሙም ዋና ዋናዎቹ ሕንፃዎች ግን እስከ አሁኑ ዘመን ዘልቀው ይታያሉ። ከነዚህ ጉልህ ሕንፃዎች መካከል የፋሲለደስ ግንብ፣ ትንሹ የፋሲል ግንብ፣ የታላቁ እያሱ ግንብ፣ የዳዊት 3ተኛ ዙፋን ቤት፣ ምንትዋብ ግንብ፣ የምንትዋብ ቱርክ መዋኛ፣ የፈረሶች ቤት፣ የፈረሰኞች አለቃ ቤት፣ አንበሶች ቤት፣ የበካፋ ግንብ፣ የበካፋ ሰገነት፣ የቀዳማዊ ዮሐንስ ጽሕፈት ቤት፣ ዮሐንስ ቤተ መጻሕፍት፣ አዋጅ መንገሪያን፣ ክረምት ቤት፣ ቋል ቤት (የሠርግ ቤት) እና ግምጃ ቤት ማርያም እንዲሁም አጣጣሚ ሚካኤል የሚሰኙ አብያተ ክርስቲያናት ይግኙበታል። በተጨማሪ ከፋሲል ግቢ ወጣ ብሎ በስተሰሜን ራስ ግንብ ይገኛል።
የርዕሰ መስተዳድሩ ምልከታ
የአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳደር አቶ አወል አርባ የጎንደር ዩኒቨርሲቲን በጎበኙበት ወቅት የከፍተኛ ትምህርት ቤቱ እንደ ታሪካዊው የአፄ ፋሲል ቤተ መንግሥት ሁሉ የታሪክ አሻራ ለመጣል እና የስልጣኔ ምልክት ለመሆን የሚያደርገውን ጥረት አድንቀዋል። ይህ ጥረት ለአማራ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ለመላው ኢትዮጵያ ትልቅ ዕድል የሚፈጥር እንቅስቃሴ መሆኑንም በልምድ ልውውጥ ጉብኝታቸው ወቅት ተናግረዋል።
‹‹የአፄ ፋሲል ቤተመንግሥት ታሪካዊ ቅርስ እና የታሪክ አሻራን ከዚህ ቀደምም ጎብኝቼዋለሁ። ነገር ግን እንደአሁኑ ሁሉንም ስፍራ እና ኪነ ሕንፃ አላየሁትም ነበር›› የሚሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ይህ ድንቅ የኪነ ሕንፃ ጥበብ ትናንት ኢትዮጵያ ምን ላይ እንደነበረች ማሳያ እንደሆነ ይገልጻሉ። የትላንቱን ታሪክ ጠብቆ ማቆየት ብቻ ሳይሆን መድገም እንደሚቻልም ይገልጻሉ። ከዚህ ተምሳሌት መነሻ ሌላ ፋሲል፤ሌላ የስልጣኔ መገለጫ መሥራት እንደሚቻልም ይናገራሉ።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የጀመራቸው መማሪያ ክፍል ሕንፃዎች የዚህ ማሳያ መሆናቸውን የሚያነሱት ርዕሰ መስተዳደሩ ይህን በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ ይናገራሉ። የአፄ ፋሲል ግንብ እንዲሁም በውስጡ የሚገኙት ቤተ መንግሥቶች በዓለም ቅርስነት መመዝገባቸው እና የቱሪስት መዳረሻ መሆናቸው ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ኩራት መሆናቸውንም ያነሳሉ። ይህን እንቁ ጠብቆ ለመጪው ትውልድ በአደራ ማስተላለፉ ደግሞ የዚህ ዘመን ትውልድ ድርሻ መሆኑን ያሳስባሉ።
በአፄ ፋሲል ቤተመንግሥት ግቢ ውስጥ ስድስት ቤተመንግሥት እንደሚገኝና ሁሉንም የመጎብኘት አጋጣሚውን በማግኘታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ይናገራሉ ርዕሰ መስተዳደሩ። ይህ ቅርስ የሚያስተላልፈው የራሱ ድንቅ መልዕክት እንዳለው ይጠቅሳሉ። አፄ ፋሲል የራሱን አሻራ በቅድሚያ ካስቀመጠ በኋላ የእርሱን እግር ተከትለው ተጨማሪ ቤተ መንግሥቶችን በግቢው ውስጥ ያሳነፁት ነገስታት አገር ግንባታ የትውልድ ቅብብሎሽ መሆኑን የተረዱ መሆናቸው እንዳስደነቃቸው ሳይገልጹ አላለፉም። ከዚህ ታሪክ አዲሱ ትውልድ አንድነትን ጥንካሬን እና ጥበብን ወርሶ አሁን ያለችውን ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና መምራት እንደሚገባው ተናግረዋል። ታሪክን አቆይቶ ለመጭው ትውልድ ማስተላለፍ ራሱን የቻለ ታሪክ ነው የሚል ጠንካራ መልዕክትም በታሪካዊቷ ጎንደር በመገኘት የአደራ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 14/2011
ዳግም ከበደ