
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ በተደጋጋሚ ከሚናገሯቸው ጉዳዮች አንዱ የውጭ ባንኮች ወደ ሀገር ውስጥ መግባትን በተመለከተ ነው:: የባንክ ኢንዱስትሪው ከዓለም የፋይናንስ ሥርዓት ጋር ተወዳዳሪ እንዲሆን እና ሀገሪቱም ከዘርፉ ተጠቃሚ እንድትሆን በማሰብ የውጭ ባንኮች ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ተጋብዘዋል::
የውጭ ባንኮች ወደ ሀገር ውስጥ ከመግባታቸው በፊትም የሀገር ውስጥ ባንኮች በቂ ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርጉ በጠቅላይ ሚኒስትሩ በተደጋጋሚ ምክር ተለግሷቸዋል:: የሀገር ውስጥ ባንኮች ያለባቸውን የፋይናንስ አቅም እንዲያጠናክሩ፤ አሠራራቸውን እንዲያዘምኑ እና ተወዳዳሪ የሰው ኃይል እንዲገነቡ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ተነግሯቸዋል:: አለፍ ሲልም ትናንሽ አቅሞቻቸውን አሰባሰበው እና ተዋሕደው ጠንካራ ባንክ እንዲመሠርቱ በርካታ ምሑራን ጭምር ምክር ሲለግሷቸው ቆይቷል::
ሆኖም ባንኮቹ ከተለያዩ አካላት የሚሰጣቸውን ምክር ሰምተው ወይም በራሳቸው ተነሳስተው ተወዳዳሪ ባንክ ለመሆን ዝግጅት ሲያደርጉ ብዙም አይታዩም:: በቴክኖሎጂ፤ በሰው ኃይል በአገልግሎት አሰጣጥ በሌሎች የመወዳደሪያ ዘርፎች ራሳቸውን ሲያበቁ አይታዩም:: ወይንም እየተዘጋጁ እንደሆነ እንኳን ፍንጭ አላሳዩም::
የውጭ ሀገር ባንኮች ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው እንዲሠሩ የሚያስችለውን ‹‹የባንክ ሥራ አዋጅ ቁጥር 1360/2017›› ያለፈው ታኅሣሥ ወር በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማፅደቋ የሚታወቅ ነው:: ይህ ደግሞ የውጭ ባንኮች ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡበት የመጨረሻ ፊሽካ መነፋቱን የሚያመላክት ነው::
ስለዚህም የሀገር ውስጥ ባንኮች ችግሮቻቸውን ለይተው ከወዲሁ ተወዳዳሪ ለመሆን መዘጋጀት አለባቸው:: የሀገራችን የባንክ ዘርፍ በበርካታ ችግሮች የታጠረ ነው:: የመንግሥት እና የግል ባንኮች የብድር አሰጣጥ ችግር የሚታይበት ነው። በሌላም በኩል የዲጂታል ቴክኖሎጂ ፈጣን እድገት የኢትዮጵያን ባንኮች ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ ተግዳሮት መፍጠሩ አይቀሬ ነው::
ቴክኖሎጂ አገልግሎቶችን በማቀላጠፍ፤ የሠለጠነ የሰው ኃይል በማፍራትና ገንዘብ፤ ጊዜንና ጉልበትን በመቆጠብ ለአንድ ሀገር ዕድገትና ብልፅግና የማይተካ ሚና ይጫወታል:: በተለይም በአሁኑ ጊዜ የባንኮች የአገልግሎት አሰጣጥም ሆነ የኢኮኖሚ ዝውውሩ በቀጥታ የተያያዘው ከቴክኖሎጂው ጋር በመሆኑ እድገታቸውም ሆነ ውድቀታቸው ለዘርፉ በሰጡት ትኩረት ልክ የሚለካ ነው:: ከዚህ አንጻር የእኛ ሀገር ባንኮች ገና በእንፉቅቅ ላይ እንደሚገኙ ከምናገኘው አገልግሎት በቀላሉ መረዳት ይቻላል::
ከቴክኖሎጂ ባሻገር የፋይናንስ ተደራሽነቱም በትላልቅ ከተሞች ላይ ብቻ የታጠረ ነው:: በመሆኑም ከውጭ የሚገቡ ባንኮችም ተቀዳሚ የገበያ መዳረሻዎቻቸው ትልልቅ ከተሞችን እንዲሁም ጥሩ የፋይናንስ አቅም ያላቸው ነጋዴዎችን ያማከለ ብቻ ነው:: ይህ ደግሞ በቀላሉ በውጭ ባንኮች እንዲነጠቁ እና ለዘመናት ያፈሯቸውን ደንበኞች የማጣት አደጋ እንደሚያጋጥማቸው እሙን ነው::
በተደጋጋሚ እንደተገለጸውም የኢትዮጵያ ባንኮች ብድር ሲሰጡ የኖሩት ጥቂት ለሚባሉ ባለሀብቶች ነው:: ከእነዚህ ባንኮች ብዙኃኑ የከተማም ሆነ የገጠር ሕዝብ ተጠቃሚ አልነበረም። ሰፊው ሕዝብ ከባንኮች ተበድሮ ኑሮውን የሚሻሽልበት እና ከሀገር ውስጥ ባንኮች ሀብት ተቋዳሽ የሚሆንበት ዕድል ዝግ ሆኖ ቆይቷል:: ይህ ደግሞ ባንኮች ሕዝባዊ መሠረት እንዳይኖራቸው እና በጠንካራ መሠረት ላይ እንዳይቆሙ የሚያደርጋቸው በመሆኑ በቀላሉ በውጭ ባንኮች ተሸናፊ የሚሆኑበትን ዕድል ያሰፋዋል::
ስለዚህም ባንኮቻችን ከጥቂት ባለሀብቶች ተላቀው ሰፊውን ሕዝብ የሚያቅፉበት እና ተጠቃሚ የሚያደርጉባቸውን መሠረቶች ከወዲሁ ማስፋት ይጠበቅባቸዋል:: ይህ ካልሆነ የውጭ ባንኮች ይዘዋቸው በሚመጡ አማላይ አገልግሎቶች ሰፊው ሕዝብ በቀላሉ የመማረክ ዕድሉ የሰፋ ነው።
ከእነዚህ ነጥቦች በተጨማሪም ከወዲሁ መሻሻል ያለበት ጉዳይ የውጭ ምንዛሪ አቅም ነው። የውጭ ባንኮች አንዱ መወዳደሪያ ሜዳቸው የውጭ ምንዛሪ አቅማቸው ነው:: የውጭ ባንኮች ሲገቡ ይዘዋቸው ከሚመጧቸው ሀብቶች ውስጥ አስተማማኝ የውጭ ምንዛሪ ነው:: በቂ የውጭ ምንዛሪ ስለሚኖራቸውም ለኢንቨስተሮችና ለነጋዴዎች አስተማማኝ የሆነ የፋይናንስ አቅርቦት ይሰጣሉ:: ይህ ደግሞ በውጭ ምንዛሪ እጥረት እየተሰቃየ ያለው ኢንቨስተር እና ነጋዴ በሙሉ ግልብጥ ብሎ ወደነዚሁ ባንኮች መሄዱ ከወዲሁ ሳይታለም የተፈታ ሕልም ነው::
ስለሆነም ባንኮቻችን ደንበኞቻቸውን ጠብቆ ለማቆየትም ሆነ አዳዲስ ደንበኞችን ለመሳብ በቂ የፋይናንስ አቅም መገንባት እና የገቢ ምንጫቸውን ስብጥር መጨመር ይኖርባቸዋል:: አብዛኛው የባንኮቹ የገቢ ምንጭ ከብድር ወለድ የሚገኝ ነው። ወለድ በመሰብሰብ ላይ ከተመሠረተው አሠራር በተጨማሪም ሌሎች አዋጭ የሆኑ ውጤታማ የባንክ አሠራሮች እያጠኑ መተግበር የግድ ይላቸዋል::
ስለዚህም ባንኮቻችን የውጭ ምንዛሪ አቅማቸውን ማጠናከር እና ለተገቢው አገልግሎት ማዋል ይጠበቅባቸዋል:: በውጭ ምንዛሪ አመዳደብ እና አጠቃቀም ረገድ የሀገራችን ባንኮች በርካታ ክፍተቶች የሚታይባቸው ናቸው:: ባንኮች የውጭ ምንዛሪን የሚሰጡት በትውውቅ እና በምልጃ ከመሆኑም ባሻገር በጥቁር ገበያ ውስጥ በመሳተፍም የሚታሙ ናቸው:: ስለዚህም ይህ ኋላቀር አካሄድ ለውድድር እንቅፋት የሚሆን እና የሀገር ውስጥ ባንኮችን ጠልፎ የሚጥላቸው ክፉ ደዌ መሆኑም ተረድተው ከወዲሁ ከብልሹ አሠራር ራሳቸውን ማፅዳት ይኖርባቸዋል::
በእርግጥ የውጭ ባንኮች ወደ ሀገር ውስጥ መግባት ኅብረተሰቡ በርካታ ዕድሎችን እንዲያገኝ ዕድል ይሰጣል:: በሀገር ውስጥ ባንኮች የተነፈጉ ዕድሎች ለኅብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆኑ እና ኑሮውንም እንዲያሻሽል በር ይከፈትለታል:: እንደሀገርም ጥቅሙ የጎላ ነው:: አዲስ የውጭ ካፒታል ፍሰት መጨመሩ፣ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ ግኝት፣ የተሻለ የብድር አቅርቦት፤ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እና የባንክ አሠራሮችን የዳበረ እና የተጠናከረ የውድድር ዓውድ፤ የአገልግሎት ጥራት እና ምክንያታዊ ዋጋ እንዲሁም አጠቃላይ የባንክ አሠራር ቅልጥፍና ሊያመጣ መቻሉ ከጥቅሞቹ ውስጥ የሚመደቡ ናቸው::
እስከተጠቀሙበት ድረስም የውጭ ባንኮች መግባት ለሀገር ውስጥ ባንኮች መነቃቃትን የሚፈጥር ነው:: አዳዲስ አሠራሮች ይማራሉ፤ በቴክኖሎጂ ራሳቸውን እንዲያደራጁ ይገደዳሉ፤ በሠለጠነ የሰው ኃይል ራሳቸውን ያደራጃሉ፤ ጤናማ የውድድር መንፈስን ያዳብራሉ:: የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚያስረዱትም የውጭ ባንኮቹ ወደ ሀገር መግባት የእውቀት ሽግግር፣ የቴክኖሎጂ እድገት፣ የአስተዳደር እና ሌሎች ልምዶችን በመጋራት የሀገር በቀል ባንኮች ለደንበኞቻቸው የተሻለ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ያደርጋቸዋል ።
በዚህም ባንኮቹ የሳይበር ደኅንነታቸውን ማጠናከር፣ የብድር አገልግሎት ላይ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ጥናት በማድረግ የዋጋ እና የወለድ መጠናቸውን ማስተካከል፣ ከደንበኞች ጋር ባላቸው ግንኙነት ደንበኞች ወደ ባንኩ ሳይሆን ባንኩ ወደ ተጠቃሚዎች መሄድ ይኖርበታል ሲሉም ይደመጣሉ::
የደንበኞችን ፍላጎት በማሟላት ረገድ ፈጣን እና ዘመናዊ አገልግሎት ማቅረብ፤ ግለሰባዊ አገልግሎትና ተጠቃሚነትን መሠረት ያደረገ አሠራር በመፍጠር የኢንቨስትመንት አገልግሎት ላይ መሥራት ይገባ ቸዋል::
የዲጂታል ባንኪንግ ቴክኖሎጂን የበለጠ በማጠናከር ዘመናዊ የባንክ አገልግሎትን ማስፋፋት መሠረታዊ መሆኑን እነዚሁ ምሑራን ይመክራሉ።
ከዚህ ቀደም ያልታቀፉ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ አሠራር በመፍጠርም ጥቃቅን እና አነስተኛ ድርጅቶች የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ የፋይናንስ አቅማቸው እንዲጎለብት ያደርጋል ሲሉም ይናገራሉ። ከዚህ ውጭ ባለፉት 33 የነበረውን አሠራር ተከትሎ አትራፊ ሆኖ መቀጠል አዋጭ አለመሆኑን መረዳት ይገባል::
የኢትዮጵያ ባንኮች በሀገር ውስጥ ታጥረውና በአብዛኛው በፖሊሲ ጭምር ተደግፈው የቆዩ ስለሆነ ውድድሩን ከወዲሁ ሊፈሩት ይችላሉ። ሆኖም ለማይቀር ውድድር ራስን ከማዘጋጀት ውጪ አማራጭ የለም:: የውጭ ባንኮች እንዲገቡ መፈቀዱ በቀጥታ የሀገር ውስጥ ባንኮች ላይ ከፍተኛ አደጋ ያደርሳል የሚለውን እሳቤ በመተው ይዘዋቸው የሚመጧቸውን ዕድሎችን መመልከቱ የተሻለ ነው።
በእርግጥ መንግሥት የባንክ ዘርፉን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ሲያደርግ አዎንታዊ እና አሉታዊ ጎኖች እንደሚኖሩት ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው:: ሰሞኑን የብሔራዊ ባንክ ገዢ አቶ ማሞ ምሕረቱ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እየታተመ ለንባብ ከሚበቃው ከዘመን ኢኮኖሚ መጽሔት ጋር ባደረጉት ቆይታ ይህን ሃሳብ አፅንዖት ሰጥተው አብራርተውታል::
አቶ ማሞ እንዳሉት መንግሥት የውጭ ባንኮች እንዲገቡ ሲፈቅድ ይህ ዘርፉን ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት ማድረግ የሚያስገኘው ጥቅም ሊያመጣ ከሚችለው ጉዳት እንደሚበልጥ ስለታመነበት ነው:: ከዚህ አኳያ በቅርቡ የፀደቀው የባንክ ሥራ አዋጅ እና በቀጣይ አዋጁን ለማስፈጸም በሚወጡ መመሪያዎች መሠረት ከዚህ የፖሊሲ ውሳኔ ጀርባ የሚያስገኘውን ጥቅም የበለጠ ለማጎልበት እንዲሁም ሊያስከትል የሚችለውን የጎንዮሽ ጉዳት ለመቀነስ በሚያስችል አግባብ የሚደነነጉ እንደሚሆኑም ጠቁመዋል::
የብሔራዊ ባንክ ገዥ ለአብነት ብለው የጠቀሱት፤ በቅርቡ የፀደቀው የባንክ ሥራ አዋጅ ላይ የተቀመጡ ድንጋጌዎች ሲታዩ የውጭ ባንኮች እና ኢንቨስተሮች ባንኮች ላይ እና አጠቃላይ የባንክ ሥርዓቱ ላይ ሊኖራቸው የሚችለው የኢንቨስትመንት መጠንን የገደበ መሆኑን ነው:: ከዚህ በተጨማሪ ብሔራዊ ባንክ እንደአስፈላጊነቱ ፈቃድ የሚሰጣቸውን የውጭ ባንኮች ተቀጥላ ወይም የውጭ በባንክ ቅርንጫፍ ቁጥር፣ የኢንቨስትመንት ገደብ እንዲሁም ከአጠቃላይ የባንክ ዘርፍ ሀብት ውስጥ በውጭ ዜጎች በባለቤትነት ሊያዝ የሚችለውን መጠን አስመልክቶ በመመሪያ ገደብ ሊበጅ እንደሚችል ሥልጣን የሚሰጥ መሆኑን አብራርተዋል:: በመሆኑም የሚነሳው ስጋት ተገቢነት ቢኖረውም ያን ያህል አሳሳቢ እና ከቁጥጥር ውጭ ነው ተብሎ የሚወሰድ አለመሆኑንም ገልጸዋል::
ስለዚህም መንግሥት በተቻለ መጠን በፖሊሲ ደረጃ ከለላ ለማድረግ መሞከሩ የሚያስመሰግነው ቢሆንም እንደሀገር ውጤታማ ለመሆን ግን የዘርፉ ዋነኛ ተዋናይ የሆኑት ባንኮቻችን የራሳቸውን ቁመና ከወዲሁ መፈተሽ አለባቸው:: ሜዳው ይሄው፤ ፈረሱም ይሄው በተባለበት መድረክ ጨርቄን ማቄን ማለት አዋጭ ስላልሆነ ከወዲሁ መቀነትን ጠበቅ አድርጎ ለውድድር መዘጋጀት ይገባል::
እስማኤል አረቦ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ጥር 29 ቀን 2017 ዓ.ም