ኢትዮጵያ ከ91ሺህ በላይ የሰብል ዝርያዎችን በዘረመል ባንክ አስቀምጣለች

አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ ከ91 ሺሕ በላይ የዝርያ ናሙናዎችን በዘረመል ባንክ በማንበርና በማስቀመጥ ከአፍሪካ ቀዳሚ መሆኗ ተገለፀ።

የኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወት ኢንስቲትዩት አዝርዕትና ሆርቲካልቸር ብዝኃ ሕይወት ምርምር መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ውብሸት ተሾመ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዓለም አቀፍ ደረጃ

የብዝኃ ሕይወት ሀብት በጊዜ ሂደት እየተመናመኑ፣ በተለይ የአዝዕርትና ሆርቲካልቸር ዝርያዎች መካከል ተለያይነት እየጠፋ ይገኛል። የተለያዩ ሀገራት አንድ አይነት ዝርያ ለመያዝና ለመጠቀም ተገደዋል። ለከባድ አደጋም ተጋልጠዋል።

ኢትዮጵያ የአዝዕርትና ሆርቲካልቸር ሀብትና ዝርያዎች ተለያይነት ከሚታወቁ ሀገራት አንዷ መሆኗን አመልክተው፤ የኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወት ኢንስቲትዩትም ይህን ሀብት ዘላቂ ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በእጅጉ እየተባባሰ የመጣው የዝርያ ተለያያነት መቀነስ እንደማያሰጋት ጠቁመው፤ ይህን ስጋት ለመቀነስም በተለይ ዘመናዊ የዘረመል ባንክ (የጂን ባንክ) በማቋቋም የተለያዩ ዝርያ ናሙናዎችን እያነበረች ትገኛለች። የጂን ባንኩም ዘመናዊ፣ ከፍተኛ ሀብት የያዘና ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን ያሟላ ነው። በባንክ በውስጡ የሚገኙ ዝርያዎችም ዘርፈ ብዙ ፋይዳና ዋጋ እንዳላቸው ተናግረዋል።

በጂን ባንኩ ባለፉት አምስት አስርተ ዓመታት ከመላ አገሪቱ ከ91ሺህ በላይ ዝርያ ናሙናዎች ተሰብስበው እንዲቀመጡ መደረጉን ያመላከቱት አቶ ውብሸት፣ ይህም ከአፍሪካ አጠቃላይ 240 ሺህ ናሙና ብዛት አንፃር ከአንድ ሦስተኛ በላይ መሆኑን አስገንዝበዋል።

‹‹የጂን ባንኩም ሆነ በውስጡ የሚገኙት ሀብቶች የኢትዮጵያ ዝርያ የተለያይነት ተጠብቆ እንዲዘልቅ የሚያደርጉ፣ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የዓለምም ሀብት ናቸው›› ያሉት አቶ ውብሸት፤ እንደ ሀገር የዝርያ ሀብቶች እንዲጠበቁና ምርትና ምርታማነትም እንዲጨምር አስተዋፅዖ ከፍተኛ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የአደጋ ተጋላጭነትን በመቀነስ ረገድ ፋይዳው የጎላ መሆኑንና አንዳንድ ሀገራት በተለይም የተፈጥሮም ሆነ ሰው ሠራሽ አደጋዎችን ምክንያት ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ሀብታቸውን ለማጣት መገደዳቸውን ያስታወቁት አቶ ውብሸት፤ ይህ ስጋት ለማስቀረት በተለይም ተመሳሳይ ዝርያዎችን በተለያዩ አምሳያው ማዕከል የማስቀመጥ ተግባራትን ማከናወን የግድ እንደሚል አስገንዝበዋል።

ይህን ስጋት ታሳቢ ባደረገ መልኩ በተለይም የአፍሪካውያን ዝርያዎቹን በምዕራባውያን ሀገራት ማዕከላት እንደሚያስቀምጡ የጠቆሙት አቶ ውብሸት፤ ኢትዮጵያ በአንፃሩ መንግሥትም ለጉዳዩ በሰጠው ትኩረት ፍቼ ከተማ ላይ አዲስ አበባ የሚገኘውን ሁሉንም ዝርያ ኮፒ ለማስቀመጥ “ዱፕሊኬት ጂን ባንክ” ለማቋቋም እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸዋል። ይህን መሰል የጥንቃቄ ተግባራት ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ፋይዳው ለዓለምም ጭምር መሆኑንም አክለዋል።

ይሁንና በሀገር አቀፍ ደረጃ የጂን ባንክ ሁለንተናዊ አቅም በአግባቡ በመረዳትና በመጠቀም ረገድ ውስንነት እንዳለ፣ ይህን ተከትሎም ከፍተኛ የሀብት ብክነት እንደሚከሰትም አመላክተዋል። ይህን ለማስቀረት ግለሰቦችንን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ከኢንስቲትዩቱ ጋር በቅርበት መሥራት እንዳለባቸውና ዝርያዎች የሚሰጡና የሚያሰራጩትም ያለ ክፍያ መሆኑን አስገንዝበዋል። ይሁንና ከክፍያ ጋር ተያይዞ መመሪያ እየተዘጋጀ መሆኑንና ጠቁመዋል።

ታምራት ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ጥር 23 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You