ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያን በይፋ ሥራ አስጀመሩ- የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ስመጥር እንደሚሆን ገልጸዋል

አዲስ አበባ፡– የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ልክ እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ኢትዮ ቴሌኮምና መሰል ግዙፍ ተቋማት በአጭር ጊዜ ውስጥ ስመጥር ኩባንያ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ በይፋ ሥራ መጀመሩን ደወል በመደወል አበሰሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ይፋዊ ሥራ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ትናንት ሲካሄድ እንደገለጹት፤  የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአፍሪካ ትልቁን አየርን መንገድና ኢትዮ ቴሌኮም የሚያንቀሳቅስ ነው፡፡ እንዲሁም በአፍሪካ የመጀመሪያው ግዙፍ የኃይል ማመንጫ ግድብ የገነባ ነው፡፡ እነዚህን ኩባንያዎች የገነባ ኢኮኖሚ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያን በአጭር ጊዜ ውስጥ ስመ ጥር ኩባንያ እንደሚያደርግ ምንም ጥርጥር የለውም ብለዋል፡፡

የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ለኢኮኖሚው ፈርጀ ብዙ ጥቅም እንዳለው አመልክተው፤ የኩባንያዎችን፣ የኢንቨስተሮችና የሥራ ፈጣሪዎችን የገንዘብ ችግርን ይፈታል ብቻ ሳይሆን በሚታወቅ ዋጋ ለመገበያየት ዕድል የሚሰጥ፣ በገንዘብ እጥረት ምክንያት ሀሳብ እያላቸው ሥራ ለሚቸገሩ ወጣቶች በከፍተኛ ደረጃ የገንዘብ ምንጭ እንደሚሆን በአብነት ጠቅሰዋል፡፡

ከለውጡ በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ዋና ዋና ስብራቶች መጠገን እንዲችሉና ኢኮኖሚው እንዲሻሻል የሰው የኑሮ ዘይቤ እንዲለወጥ፣ ገቢው ማደግ እንዲችል አንዱ አበክረን የሠራንበት መስክ ዲጂታል ኢትዮጵያን መገንባት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ በዚህም ዲጂታሉ ዘርፍ ግብርናው፤ ኢንዱስትሪው፣ ቱሪዝም፣ ማዕድንና ሌሎችንም ሴክተሮችን ራሱ የዕድገት ምሶሶ ሆኖ እነዚህ የሥራ መስኮችን እያስተሳሰረ ኢኮኖሚያችንን ማሳደግና የነበሩትን ዋና ዋና ስብራቶች ማሻሻል እንዲችል ታሳቢ ያደረጉ ሥራዎች መሠራታቸውን ገልጸዋል፡፡

በእነዚህ ሥራዎች የሚያበረታታ ውጤት ማየት መጀመሩን ጠቁመው፤ በሥራ ዕድል ፈጠራ ዜጎች ኢትዮጵያ ሆነው ውጭ ሀገር ሥራ ተቀጥረው እንዲሠሩ በጀመርነው ጥረት ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ 35 ሺህ ወጣት ኢትዮጵያውያን ከሁለት ሺህና ከዚያ በላይ ዶላር ደመወዝ እያገኙ ማገልገል ጀምረዋል፡፡ በዚህ ረገድም ዲጂታል ኢትዮጵያ ከፍተኛውን ድርሻ ተወጥቷል ነው ያሉት፡፡

ከለውጡ በፊት ሞባይል የሚጠቀሙ ሰዎች 37 ሚሊዮን እንደነበሩ አስታውሰው፤ ይህ መቀየር አለበት ብንል በሠራነው ሥራ 80 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሰዎች በኢትዮ ቴሌኮም ብቻ የሞባይል ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን ተናግረዋል ፡፡

ተጠቃሚ ማፍራት ብቻ ሳይሆን ኢትዮ ቴሌኮምን በአፍሪካ የመጀመሪያው ትልቁ ተቋም ማድረግ መቻሉን ገልጸው፤ ይህን ለውጥ ማምጣት የቻልነው ባለፉት አምስትና ስድስት ዓመታት በሠራነው ዲጂታል ኢትዮጵያን የመፍጠርና የመለማመድ ሥራ ነው ብለዋል።

የዛሬ 3 ዓመት ገደማ በተጀመረው ሞባይል ባንኪንግንም ዛሬ 51 ሚሊዮን ሰዎች ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አመልክተው፤ ይህም በአፍሪካ ትልቁ የሞባይል ባንኪንግ አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በቴሌ ብር ሦስት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ 3 ነጥብ አምስት ትሪሊዮን ብር ግብይት የተፈጸመበት መሆኑን አመልክተው፤ ትልቅ ሀብት በቴክኖሎጂ ታግዘን እንድናንቀሳቅስ አድርጎናል ብለዋል፡፡

በሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ይህን ስኬት መድገም እንደሚገባ ገልጸው፤ ለዚህም መንግሥት ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይህን ለማሳካት የግሉ ሴክተር በእልህና በቁጭት ሊሠራ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

ለኢኮኖሚ እና ፋይናንስ ምሕዳራችን ታሪካዊ በሆነ እጥፋት የኢትዮጵያን የመጀመሪያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ደወል ደውልናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ባላት፣ ለብልፅግና ሰፊ እምቅ አቅም እና ምቹ መንገድ እየተነጠፈላት ባለችው ኢትዮጵያ ሙዓለ ንዋይዎን ያፍሱ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

ጌትነት ምሕረቴ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 3 ቀን 2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You