በደብሩ መዳንን ናፍቀው፣ፈውስን ፈልገው የሚመላለሱ ብዙ ናቸው። በዚህች ቤተክርስቲያን አረፋፍዶ የሚያመሸው፣ ሰንብቶ የሚሄደው ጥቂት አይደለም። ውሎ አዳራቸውን ከደጃፏ ያደረጉ ምዕመናን በጠበሏ ተፈውሰው ለመዳን መክረሚያቸውን በስፍራው ካደረጉ ቆይተዋል። ወራትን በተሻገረ ቆይታቸው የነገውን መልካምነት እያሰቡ ዛሬን በፆምና በፀሎት ይበረታሉ።
በዚህ ስፍራ ከሩቅና ከቅርብ የመጡ አካባቢውን አጥለቅልቀውት ይውላሉ። በየቀኑ ከያሉበት የሚመላሱም ፈጣሪያቸውን ተማጽነው ከፀበሉ ተጠምቀው ይመለሳሉ። በሸክም የመጡ፣ ደክመው የደረሱና ተስፋና መላ የታጣላቸው በርካቶች በፀበሉ በረከትን አግኝተዋል።
በቤተክርስቲያኒቱ ዙሪያ ለኪራይ የተዘጋጁ ጠባብ ክፍሎች መክረሚያቸውን በስፍራው ለሚያደርጉ ጠበልተኞች ማረፊያ ሆነዋል። በተለይ በሱባኤ ጊዚያት በነዚህ ቤቶች መገልገል የተለመደ ነው። የፀበሉን ዝና ሰምተው ከሩቅ ስፍራዎች የሚመጡ በቤቶቹ አርፈው ከፀም ፀሎቱ ይካፈላሉ። በምልጃና ስግደትም ጊዚያቸውን አጠናቀው ይሄዳሉ።
በተቃራኒው ደግሞ በግቢው ዙሪያ በአነስተኛ መጠለያዎች ተከልለው የሚቆዩ ጥቂቶች አይደሉም። ከእንዲህ አይነቶቹ ጠበልተኞች አብዛኞቹ የገንዘብ አቅም ችግር ያለባቸው ናቸው።መዳንን መሻታቸው ግን ብርድና ቅዝቃዜውን እንዳያስቡት አድርጓቸዋል። ያላቸውን ለብሰው ያገኙትን ተቃምሰው በፀበሉ በረከት ያድራሉ።
አንዳንዶቹ ደግሞ የእነሱን ያህል ዕድል ያላገኙ ናቸው። ካለው ተጠግተው፣ ከፀበሉ ተጠምቀው የሚሰጣቸውን ጎርሰው ይውላሉ። አንዳንዴም ከመንገድ ወጣ ብለው የእግዜርን ስም ሲጠሩ ለነፍስ ያሉ በርካቶች አይጨክኑባቸውም። ከሳንቲምና፣ ከልብሱ ከእንጀራውና ከዳቦው ይመፀውቷቸዋል።
ብዙ ጊዜ በደብሩ አፀድ ለየት ያሉ ድምፆች ይሰማሉ። በእርኩስ መንፈስ ተይዘው የሚጮሁ፣በእግር ብረት ታስረው ለመታዘዝ የሚያስቸግሩ በርካቶች ናቸው። የቤተሰብን ጉልበት የሚፈትኑ በበዙ ጊዜም አቅም ላላቸው ተላልፈው ይሰጣሉ። እነሱም ከብርታታቸው በላይ በርትተው፣ከሃይላቸው በላይ አይለው ከፀበሉ ያጠምቋቸዋል።
በየቀኑ በዚህ ስፍራ የሚተመው ፀበልተኛ መልከ ብዙ ነው። ለመዳን መጥቶ የሚዘረፍና በፀበል ሰበብ ከደጃፏ ደርሶ የሌላውን ኪስ የሚዳስስ አይጠፋም። በርካታው ተደስቶ የሚሄደውን ያህል ገሚሱ ደግሞ አልቅሶና አዝኖ መመለሱ ተለምዷል።
አቶ አይተንፍሱ መንጌ እያደር ጤናቸው መቃወሱ እያሳሰባቸው ነው። እስከዛሬ የአቅማቸውን ያህል ህክምናውን ሞክረዋል። የአበሻ መድሃኒቱንም ቢሆን ደጋግመው አይተውታል።አልፎ አልፎም በአካባቢያቸው ካሉ የጠበል ስፍራዎች ጎራ ማለታቸው አልቀረም። ያም ሆኖ ግን ያሰቡትን ያህል ጤናቸው እንደቀድሞው አልሆነም።
በአንድ አጋጣሚ ግን መልካም የሚባል ዜና ለጆሯቸው ደረሰ። ይህ እውነትም አገር መንደራቸውን አስለቅቆ ከመላው ቤተሰባቸው ሊያርቃቸው ግድ ሆነ። ወዳጅ ዘመድን ባማከሩ ጊዜ ግን ከአብዛኞቹ የይሁንታን ምላሽ አገኙ። ለዘለቄታው ጤናቸው ይመለስ ዘንድ ከአዲስ አበባዋ የቁስቋም ማርያም ጠበል ቀን ከሌት መጠመቁን ከልብ አመኑበት።
አዲስ አበባ «የኔ» የሚሉት ወዳጅ ዘመድ አያውቁም። እሳቸውን አውሎ የሚያሳድርና አስታሞ የሚያድን ሁነኛ አጋር የላቸውም። የእሳቸው ዓላማ ከህመማቸው መዳን ነውና ይህ ሁሉ አላሳሰባቸውም። የአዲስ አበባ ሰው ለሌለው እንደሚሰጥ፣ ለተቸገረም እንደሚለግስ ሲሰሙ ኖረዋል።እሳቸውም «ስለነፍስ» ብለው ቢማጸኑ ብዙዎቹ እንደማይጨክኑባቸው አምነዋል።
አይተንፍሱ ሲያስቡ በከረሙበት ጉዳይ ወስነው ጓዛቸውን ይዘው ተነስተዋል። መክረሚያውን ባያዘልቃቸውም ለመንገድ የምትሆን ስንቅና ጥቂት የኪስ ገንዘብ አላጡም። የሚቆዩበትን ጊዜ ባያውቁትም እንደአቅማቸው ተዘጋጅተው መንገዳቸውን ካሰቡ ቆይተዋል።
ከተባለው ስፍራ ደርሰው በጠበሉ ድህንነት ለማግኘትም አብሮ አደግ ጓዳቸው ከጎናቸው ሆነዋል። እሳቸውም ቢሆኑ የጠበሉን በረከት ሽተው ከቤታቸው ለመውጣት ወስነዋል። ሀሳባቸው «ከአንድ ብርቱ ሁለት መድሃኒቱ» ሆኗልና ተደጋግፈው ለመቆም፣ ተጋግዘው ለመበርታት አስበው ወደ አዲስ አበባ አቅንተዋል።
ቃሊቲ አካባቢ ከምትገኘው የቁስቋም ማርያም ቤተክርስቲያን አፀድ በጥየቃ የደረሱት ሁለቱ ባልንጀሮች ዕለቱን ለጎናቸው ማረፊያ አላጡም። እነሱ ቤት ተከራይተው ከሚያድሩት ወገን አይደሉም። በአካባቢው መጠለያ ሰርተው ከሚኖሩት መካከልም አይመደቡም። የኪሳቸው አቅም ከአንዱ ጥግ ከማረፍ ሌላ ምርጫ አይሰጣቸውም። እነሱም ቢሆኑ ይህን ገምተው ወጥተዋልና ስለምቾታቸው አላሰቡም።
ውሎ ሲያድር አይተንፍሱና ጓደኛቸው ከፀበሉ እየተጠመቁ ሌሎችን መምሰሉን ለመዱት።ከቅዳሴው ታድመው፤ ከፆም ከፀሎቱ ተካፍለው ነጋቸውን በፈውስ ማሰብም ተስፋቸው ሆኖ ቀጠለ።በርካቶች ከትላንቱ ህመማቸው ተፈውሰው ቆመው ሲሄዱ ማየታቸው እነሱንም አበረታ። ጊዚያት በጨመሩ ቁጥር ጉስቁልናቸውን ረስተው በብርታት ለመቆም ታገሉ።
ጥቅምት 21 ቀን 2004 ዓ.ም
ብዙዎቹ ይህን ቀን በተለየ ሁኔታ ያከብሩታል። የማርያም ወርሐዊ ዕለት ነውና በርካቶቹ ምዕምናን ከያሉበት ደርሰው ከበረከቱ ይካፈላሉ። ጥቂት የማይባሉትም ዕለቱን ተመርኩዘው ከፀበሉ ተረጭተውና ተጠምቀው ለመሄድ በስፍራው ይደርሳሉ። ሁሌም ከዚህ ልማድ የማይቀሩት ቋሚዎቹ ጠበልተኞች ደግሞ ከሌሊት ጀምሮ ተገኝተው ማረፋፈዱን ለምደውታል።
አቶ አይተንፍሱና ባልንጀራቸውም የዕለቱን ፀበል ለመጠመቅ በስፍራው የተገኙት ከእኩለ ለሊት ጀምሮ ነበር። በርካቶች ከበረከቱ ለመካፈል በሚጋፉበት አጋጣሚ እነሱም ከሌሎች ጋር ተዳምረው የሚቀዳውን እየቀዱ፣ የሚታገዘውን እየረዱ ለጥምቀቱ ተራቸውን ይዘው ቆይተዋል።
ስፍራው እንደተለመደው በርከት ያሉ ድምፆች እየተሰሙበት ነው። በክፉ ደዌ ከተያዙና በእርኩስ መናፍስት ከታሰሩ አንዳንዶች በተለየ እየተደመጠ ያለው የአንድ ሰው ድምጽ ግን የብዙዎችን ትኩረት መሳብ ጀምሯል። ሁኔታውን ለማጣራት ጠጋ ያሉ አንዳንዶች ጉዳዩ በሁለት ሰዎች መካከል የተፈጠረ ጠብና ጭቅጭቅ መሆኑን አላጡትም።
የሰዎቹን ጠብና ያልተገባ ንግግር ያደመጡ በዚህ ክቡር ስፍራ እየሆነ ያለውን ተመልክተው ከልባቸው አዘኑ። ጥቂት የማይባሉትም ድርጊቱ ለቅስፈት እንደሚሰጥ ገምተው ሊገስጿቸው ሞከሩ።አንዳንዶች ደግሞ በሥጋት ተሸብበውና ዝምታን መርጠው በትዝብት ያይዋቸው ጀመር።አብዛኞቹም በሰዎቹ ያልተገባ ድርጊት ከመገረም አልፈው በብሽቀት በገኑ።
አቶ አይተንፍሱ ከነበሩበት ተነስተው ወደ መሐል ሲደርሱ የሁለቱን ሰዎች ምልልስ አደመጡ። በተለይ በዕድሜ ወጣት ከሚባለው ልጅ አንደበት እየተሰማ ያለው ንግግር መልካም የሚባል አይደለም። በግርግሩ መሐል ለግልግል የገቡት ሌላ ጎልማሳም ወጣቱን ከድርጊቱ ለማስቆም መቆጣት ጀምረዋል። ሐሳባቸውን የደገፉ ሌሎችም የንግግራቸውን ትክክለኛነት አምነውበታል።ሁሉም በስፍራው የመጣው ለመፈወስ ነውና እንዲህ አይነቱ ያልተገባ ምግባር አስደንግጦታል።እሳቸውን ተከትሎም ሁሉም ወጣቱን መቆጣትና መኮነን ጀምሯል።
ድንገት ግርግሩ መሐል የገቡት አቶ አይተንፍሱ በአጋጣሚ ከጆሯቸው ለደረሰው የወጣቱ ንግግር ተገቢ ነው ያሉትን ምላሽ ሰነዘሩ። ተሳዳቢው ወጣት ጥርሱን ነክሶ አይኑን እያፈጠጠ ለጠበኛው እንዲህ ይለዋል።
«ቆይ ሌሊት እመጣልሀለሁ አለቅህም!» ይህኔ ዛቻውን የሰሙት አይተንፍሱ በንዴት እንደበገኑ እንዲህ ሲሉ መለሱለት።
«አንተ ሌሊት የምትሄደው ማጅራት መቺ ነህ እንዴ?
ልጅ እግሩ ቶማስ የሰውዬው ንግግር የጣመው አይመስልም። የእሳቸውን ምላሽ ለጠበኛው እንደማበር አድርጎ ቆጥሮታል። ይህ ስሜቱ ደግሞ ለእሳቸውም ተገቢ ያልሆነውን ድርጊት እንዲደግመው እያነሳሳው ነው። ይህን ያስተዋሉት አቶ አይተንፍሱ ጠያፍ ስድቡን ሳይደግመው በፊት በከዘራቸው ቀደሙት። ምታቸውን እግሩ ላይ አሳርፈውም ቁጭ ብድግ እስኪል ደበደቡት።ሁኔታቸውን ያዩ ሌሎች ከመሐል ገብተው ገላገሉ። የዕለቱ ጠብና ውዝግብም በዚሁ ተቋጭቶ አለፈ ።
ጥቅምት 22 ቀን2004 ዓ.ም ውድቅት
ለሊቱ እንደተለመደው ጭር ብሏል። በየስፍራው ያረፈው ጠበልተኛ የቀኑ ውሎ ያደከመው ይመስላል። ከጥቂቶች በቀር አብዛኛው ጎኑን አሳርፎ ለማንቀላፋት እየሞከረ ነው። አንዳንዶች ደግሞ የሌሊቱን ጸሎት ለማድረስ በትጋት ላይ ናቸው። ከአብዛኞቹ መሐል ግን የአንድ ሰው ልብ አርፎ አልተኛም። ዓይኖቹ ለዕንቅልፍ ሳይከደኑ እንዳፈጠጡ ቆይተዋል። እጆቹ የያዙትን አጥብቀው እግሮቹ ወዳሰበው መንገድ እያፈጠኑት ነው።
በፍጥነት መገስገስ የጀመረው ወጣት ካሰበበት ሲደርስ ድንገት ሩጫውን እንደመግታት ብሎ ቆመ። በጨለማው መሐል በርካቶች መተኛታቸውን ቢያውቅም የሚፈልገውን ለመለየት አልቸገረውም። ዱላውን አጥብቆ እንደያዘ አይኖቹን ወደአንድ ጥግ ላካቸው። ግምቱ ውሉን አልሳተም። አቶ አይተንፍሱ ከበርካቶች መሐል ከላያቸው አንዲት እራፊ ደርበው ጋደም ብለዋል።
አሁን ቂም ያረገዘው ወጣት ልቡ ትኩስ ደም ሲረጭ እየተሰማው ነው። የትናንትናው ድርጊት በአይነህሊናው ይመላለስ ጀምሯል። ቀኑን ሙሉ የተጉዱ እግሮቹን እያሻሸ በስቃይ ያሳለፈውን ጊዜ በቀላሉ መርሳት አልቻለም። የአይተንፍሱ ንግግርና የሌሎቹ እርግማንም ከዱላው ያልተናነሰ እንደጎዳው አውቋል። አሁን ግን ለዚህ ሁሉ ድርጊት ሁሉም የሚገባቸውን ሊያገኙ ሰዓቱ እንደደረሰ ራሱን አሳምኗል።
እየተንደረደረ ከሰዎቹ መሐል ሲገባ የሚያደርገውን የገመተ አልነበረም። ድንገት አጥብቆ የያዘውን ወፍራም ቆመጥ በአቶ አይተንፍሱ ጭንቅላት ላይ ሲያሳርፍና የሲቃ ድምጻቸው ሲሰማ ግን ሁሉም ካንቀላፋበት ነቃ። ግርግሩ አይሎ ስፍራው በደም ሲበከል አካባቢው በእጅጉ ተረበሸ። የተኙት ሁሉ እየነቁ ሰው ሞተ፣ተገደለ እያሉ ስፍራውን በጨኸት አደባለቁት።
ከአይተንፍሱ ጎን የነበሩት ባልንጀራቸውም የሆነውን ባዩ ጊዜ ወጣቱን ለመያዝ ሞከሩ።አምልጦ እንዳይሄድም ፊት ለፊት ተጋፍጠው ይታገሉት ያዙ። ወጣቱ ለእሳቸውም ቢሆን በዋዛ አልተመለሰም። የያዘውን ዱላ አመቻችቶ እጃቸው ላይ አሳረፈው። መንገዱን አስለቅቆም በፍጥነት ተፈተለከ። ከበስተኋላው ሰዎች እየተከተሉት መሆኑን ያውቃል። እሱ ግን ዕቅዱን ሳይጨርስ ፈጽሞ መያዝ አይፈልግም። ከዚህ ቀጥሎ ያሰበውን መፈፀምና የልቡን መሙላት ይኖርበታል።
አሁን የደብሩ አስተዳዳሪና የጥበቃ ሠራተኞች ጉዳዩን ሰምተው ከስፍራው ደርሰዋል። ለሱባኤ በስፍራው የታደሙና በአካባቢው ያሉ ሁሉ ድንጋጤ ውጧቸው የሚሉትን አጥተዋል።አይናቸው እያየ ከእጃቸው ያመለጠው የአይተንፍሱ ጓደኛ ቁስላቸውን እያስታመሙ መጮህ ጀምረዋል። ክፉኛ ተመተው ደም የሚፈሳቸውን ባልንጀራቸውን ባዩ ጊዜም እንደማይተርፉ ገምተው፤ ጓዴ፤ ባልንጀሬ፥ ወንድሜ እያሉ ማልቀስ ይዘዋል።
ከግርግሩ መሐል አምልጦ ወደፊት የነጎደው ወጣት ከአንዱ የድንኳን ማረፊያ ገብቶ ሰው መፈለግ ይዟል። አሁንም ልቡ ማንን እንደሚሻ አላጣውም። ትናንት ከእሱ ተወዛግቦ ለዱላ መነሻ የሆነውን ጠበኛውን እየፈለገ ነው። ሩጫው ፈጽሞ አልተገታም። ጨለማውም ቢሆን ሊከልለው፤ ሊያግደው አልቻለም።
ወጣቱ ዓይኖቹን ጣል ከማድረጉ ፊት ለፊት ካየው ጎልማሳ ላይ ያቀደውን ለመፈፀም አልዘገየም። ደም ባሟሸበት ቆመጥ ዱላው ከተኛበት ድረስ ዘልቆ ደጋግሞ ደበደበው። ከዱላው ጫፍ የተገጠመው ፌሮ ብረትም በዕንቅልፍ የደከመውን ሰው አካል ሳይመረጥና ቦታ ሳይለይ ያሻውን ፈፀመለት። አሁንም ሰፈራው በደም ታጥቦ በጨኸት ሲታመስ «እግሬ አውጭኝ» ሲል ተፈተለከ ።
የሆነው ሁሉ ከሆነ ወዲህ ከኋላው የደረሱት ሰዎች ወጣቱን በእጃቸው አስገቡ። እሱን ያዩ ብዙዎችም ገና በጊዜ ዱላውን ይዞ ጠበልተኛውን ሲዞር ማምሸቱን አስታወሱ። በየስፍራው የወደቁትን ተጎጂዎች ወደ ሆስፒታል ለማድረስና ጉዳዩን ለማሳወቅ የፖሊስ ሃይልን የጠሩት የቤተክርስቲያኒቱ አካላት በአጭር ጊዜ ውስጥ ከስፍራው ለደረሱ የፍትህ አካላት ቃላቸውን ለመስጠት በምስክርነት ታደሙ።
የፖሊስ ምርመራ
ፖሊስ ወረዳ 5 ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ከምትገኘው የቁስቋም ማርያም ቤተክርስቲያን ግቢ ሲደርስ ገና ውድቅት ነበር። በአካባቢው ያሉትን ሰዎች አረጋግቶ ወንጀሉ ወደተፈፀመበት ስፍራ ሲገባም ተጎጂዎቹን ያገኛቸው በአሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ነበር። አስቀድሞ የከፋ ጉዳት የደረሰባቸው አቶ አይተንፍሱ ራሳቸውን ማወቅ በሚችሉበት አቅም ላይ ባለመገኘታቸው ቃል ለመስጠት የሚችሉ አልሆኑም።
ሁለተኛው ተጎጂ አቶ ድልነሳውም በጆሮዎቹ ደም እየፈሰሰው ራሱን ስቶ ወድቆ ነበር። መላው አካሉ ጉዳት ላይ በመሆኑም በቂ መረጃ ለመስጠትም ሆነ የምስክርነት ቃሉን ለማስመዝገብ በሚችልበት አቋም ላይ አልነበረም። በወቅቱ በአካባቢው በሚገኝ ጤና ጣቢያ ቢደርስም ጉዳቱ ከአቅም በላይ በመሆኑ ለከፍተኛ ህክምና ሪፈር ሊባል ግድ ነበር።
የአቶ አይተንፍሱ አብሮ አደግ ባልንጀራም የእጃቸው ጉዳት ቀላል የሚባል አልሆነም።ከምንም በላይ ግን ፈውስ ፍለጋ ካገራቸው ወጥተው ባልሆነ ፍፃሜ መመለሳቸው ክፉኛ ሐዘን ላይ ጥሏቸዋል። በወቅቱ ተገቢውን ህክምና ቢያገኙም ከቁስላቸው በላይ ይጠዘጥዛቸው የያዘው የጓደኛቸው ሁኔታ እያስከፋቸው ነው። ይባስ ብሎ ከቀናት በኋላ የባልንጀራቸውን ሞት የተረዱት ሰው ከፉኛ ልባቸው ተሰበረ። ለጤና ሲሉ ከሀገራቸው ወጥተው መርዶ ይዘው መመለሳቸው ከልብ አስለቀሳቸው።
ፖሊስ እነዚህን እውነታዎች ሁሉ በምርመራው ካለፈባቸው በኋላ ድርጊቱን ወደ ፈፀመው ተጠርጣሪ አነጣጠረ። ወጣቱ ቶማስ ኦላንጎ ይባላል። እሱም ከሀገሩ ወደዚህ ስፍራ ሲመጣ እንደ ሌሎች ሁሉ ፈውስን ፈልጎ ነበር። የዛን ዕለታውን ጠብ የጀመረው ድልነሳው ከተባለው ሰው ጋር ቢሆንም ለእሱ ተደርበው በከዘራ በመቱት አቶ አይተንፍሱ ድርጊት ቂም ይዞ ሲናደድ መቆየቱን አልደበቀም።
እሱ እንደሚለው ከሟች ጋር ትውውቅም ሆነ ጠብ አልነበረውም። እሳቸውን ለመግደል ባያስብም ለጠበኛው ያቀደው ሞት ዕጣ ፈንታቸው መሆኑ አስቆጭቶታል። ፖሊስ ከሰውዬው ጋር በተፈጠረ ድንገተኛ ውዝግብ ተጠርጣሪው ሌሎችን ለሞትና ጉዳት ስለመዳረጉ ከሰጠው የዕምነት ቃል አረጋግጧል።
አሁን በፖሊስ መዝገብ ቁጥር 150/04 የተመዘገበው የተጠርጣሪው የወንጀል ድርጊት በአግባቡ ተመዝግቦ ተጠናቋል። በወቅቱ በስፈራው የተገኙና ለወንጀሉ መፈፀም ምክንያት የሆኑ ፌሮ ብረትና ቆመጥ ዱላ በኤግዚቢት ተይዘዋል። የምስክሮች ቃል ተመዝግቦ ጉዳዩ በህክምና ማስረጃዎች ተጠናክሯል። በረዳት ሳጂን ሽታዬ ቢተው መርማሪነት የተሰናደው መዝገብም ክስ ይመሰረትበት ዘንድ ወደ ዓቃቤ ሕግ ተላልፏል።
ውሣኔ
የካቲት 27 ቀን 2007 ዓ.ም የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሦስተኛ ወንጀል ችሎት በተከሳሽ ቶማስ ላይ የቀረበውን የወንጀል ክስ አጠናቆ ለውሳኔ ተሰይሟል። ተከሳሹ ቶማስ ኦላንጎ በፈፀመው ሆን ብሎ ሰው የመግደል ወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱና ጉዳዩ በበቂ ማስረጃ በመረጋገጡ እጁ ከተያዘበት ጊዜ አንስቶ በሚታሰብ የአስራ አምስት ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ሲል ፍርድ ቤቱ ወሰኗል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ 13/2011
መልካምሥራ አፈወርቅ