
ፍጹም ከ2010 ጀምሮ ፋብሪካ ውስጥ ይሠራ የነበረ ሲሆን ደሞዜ አነስተኛ ነው በማለት ሥራውን አቁሞ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት መኖርን ጀመረ፡፡ በአዲስ አበባ ከተማም መኖር ከጀመረ በኋላ የተለያዩ ሥራዎችን ሠርቷል፡፡ ነገር ግን በአዲስ አበባ መኖር እንዳሰበው ቀላል አልሆነለትም፡፡ ታዲያ ይህ ሰው በጉልበቱ ሰርቶ በላቡ አግኝቶ ከመኖር ይልቅ ሌላ ቀላል አማራጭን ፈለገ።
በዚህ ቀንም በአንድ ወዳጁ አማካኝነት ተጠቁሞ ከነበረው ከእርሱ በሥራ ልምድ ጋር የሚመሳሰል ሥራን እንዲቀጠር እድል ተመቻችቶለት የሥራ ቃለመጠይቅ አድርጎ ሲመለስ ቦታው ከቤቱ የራቀ በመሆኑ የሜትር ታክሲ አገልግሎትን ለመጠቀም ወሰነ።
ወይዘሮ ዝናሽ የአንድ ልጅ እናት ስትሆን በሰላሳዎቹ መጀመሪያ ላይ የምትገኝ ናት። ዝናሽ በገበያ ልማት (ማርኬቲንግ) የሥራ ዘርፍ ውስጥ በግሏ የምትሠራ ሲሆን በትርፍ ጊዜዋ የግል መኪናዋን በሜትር ታክሲ ሥርዓት ውስጥ በማስገባት እና የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ተጨማሪ የገቢ ማግኛ መንገዷ ነው።
ዝናሽ ለሰባት ዓመት ያክል የቆየ ትዳር የነበራት ሲሆን የመጀመርያ ልጇን ከወለደች በኋላ ከባለቤቷ ጋር በተለያዩ ምክንያቶች ግጭት በመፈጠሩ ግንኙነታቸው ተቋርጦ ዝናሽ ልጇን ለብቻዋ እያሳደገች ነው፡፡
ታዲያ በዚህ የሜትር ታክሲ አገልግሎት በቀን ውስጥ በርካታ ሰዎችን የምትተዋወቅ ሲሆን የተለየ የሥራ እድልን ታገኝበታለች፡፡ መልካም ሀሳብ ያላቸውም ሰዎች በሥራዋ ያግዟታል፡፡
ፍፁምና ዝናሽም በዚህ አጋጣሚ የተዋወቁ ሲሆን የነበራቸው የእርስ በእርስ ተግባቦት ከትራንስፖርት አገልግሎት በዘለለ የስልክ አድራሻ ተለዋውጠው ይበልጥ ወዳጅነታቸውን እንዲያጠናክሩ አድርጓቸዋል።
ፍፁም ዝናሽ ጠንካራ ሠራተኛ ስለመሆኗ፣ ልጇን ለማሳደግ የምትከፍለውን ዋጋ እና ያላትን ቀና አስተሳሰብ በግንኙነታቸው ተረድቷል። ታዲያ እርሱም የተለየ ክብርን ለማግኘት በማሰብ ሥራ ያጣውን ማንነቱን ሳይሆን ቢሆን የሚመኘውን ከእርሱ ጋር ፍፁም ግንኙነት የሌለውን መንገድ መርጧል።
ራሱንም ዶ/ር ፍፁም አልጀብራ ብሎ ተዋወቃት። በሥራውም በዘውዲቱ ሆስፒታል አዋላጅ እንዲሁም ባለው የትርፍ ሰዓት የተለያዩ ሁለት ሆስፒታሎች የሚሠራ ታታሪ የጤና ባለሙያ ማዕረግን ለራሱ አጎናፀፈ። ዝናሽ የተዋወቀችው ሰው መልካም እና ጠንካራ ነው የሚለውን በልቧ ማሰላሰል ይዛለች። ወዳጅነታቸው እየጨመረ ሲመጣም በተደጋጋሚ መገናኘት ጀመሩ፣ ነዋሪነታቸው በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስድስት ተቀራራቢ ስፍራ ላይ በመሆኑ ግንኙነታቸው ባደገ ቁጥር ዝናሽ ዶ/ር ፍፁም እሠራበታለሁ ወዳለበት ዘውዲቱ ሆስፒታል ታደርሰዋለች።
ወዳጅነት አንደኛው ለሌላው ያለውን ጥሩ እይታ የሚጨምር ሲሆን ፍጹም በመሀከላቸው ያለውን ግንኙነት ወደ ፍቅር ግንኙነት እንዲቀየር ጥያቄውን አቀረበ። አስቀድሞ በዝናሽ ዘንድ አመኔታ ለመፍጠር የራሱን ሥራ የሠራ ሲሆን ዝናሽ ጥያቄውን ውድቅ አላደረገችም። ምከንያቱም ከአንድ ብርቱ ሁለት መድሀኒቱ ነውና ይህ ሰው ሸክሜን የሚጋራኝ፤ ድካሜን የሚያቀል እና ቀጣይ የሕይወት ጉዞዬን አብሮኝ ይጓዛል ምቹ ረዳቴ ይሆናል በሚል መርጣዋለች።
ፍፁም ከዚህ በኋላ ሌሎች ተጨማሪ ገንዘብ ያስገኛሉ ያላቸውን ሀሳቦች ማምጣቱን ቀጠለ። ዝናሽ የሥራ ሀሳቡን ብትወደውም ጥድፊያውን ግን አልወደደችው ነበር። ዝናሽ እና ዶ/ር ፍፁም ከተዋወቁ በኋላ አብራት የምትኖረውን እናቷን እና ልጇን አስተዋውቃዋለች። እርሷ ግን ከነገራት ሙያው እና የሥራ ታታሪነት በቀር ስለቤተሰቦቹም ሆነ ስላለፈው የግል ሕይወቱ እንዲሁም የመኖርያ አድራሻውን በትክክል አታውቀውም ።
ፍፁም ግን ያሰበውን ነገር እውን ለማድረግ የተለያዩ መረጃዎችን በሙያዬ አውቃቸዋለሁ የሚላቸውን ልምዶች በመጨመር ያለውን የሕክምና ሙያ ተጠቅመው ክሊኒክ እንዲከፍቱ እና ለዚህም ከውጭ ሀገር የሕክምና እቃዎችን ማስመጣት ቀዳሚው ሥራ እንደሆነ አሳመናት።
ቀጣዩ ሥራም በሚያውቃቸው አስመጪዎች በኩል ለማምጣት በአጠቃላይ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ነገራት። እንደ ሰው ሸክምን የሚጋራና የተሻለ ሀሳብን የሚያቀርብ ሰው አይጠላምና ከሚያስፈልገው የገንዘብ መጠን ውስጥ ዝናሽ 500 ሺህ ብር እንድታግዘው ቀሪውን ግን ራሱ ሞልቶ እቃውን እንደሚያመጣው አሳመናት።
ዝናሽ በሀሳቡ እንደተስማማች ካረጋገጠ በኋላ ግን ሌላ ተጨማሪ ጊዜ ማባከን አልፈለገም፡፡ ነጋ ጠባ ወሬውም ስለዚሁ ጉዳይ ሆነ ፡፡ ዝናሽም እቃው ባጭር ጊዜ ከመጣ ሆስፒታሉን መክፈት ቀላል እንደሆነ ስላመነች ቀጣይ ሕይወቴ ከዚህ ሰው ጋር ያምርልኛል በማለት በሥራ ያጠራቀመችውን ገንዘብ ሰጠችው።
ያልታመነ ወዳጅ
ከዚህ ቀደም ዝናሽና ፍጹም በተደጋጋሚ ስለ ሥራቸውም ሆነ ስለሕይወታቸው ለማውራት ይገናኙ ነበር። ፍጹም ገንዘቡን ከተቀበለ በኋላ ግን ክሊኒክ ለመክፈት የሚያስፈልገንን ፍቃድ እያወጣው ሥራ በዝቶብኛል በሚል በሳምንት ውስጥ የሚገናኙበት ጊዜ እያጠረ መምጣቱን አስተውላለች። ነገር ግን ልትጫነውም አልፈለገችም።
እሱም የሕክምና ሥራ ባህሪ ይህ ነው የሚባል ትርፍ ሰዓት የለውም በሚል ሰበብ መደርደሩን ቀጠለ። ከሳምንት አልፎ ወራትን የተሻገረው የዚህ ሰው ብቅ ጥልቅ ማለት ያልጣማት ዝናሽ እፈልግሀለሁ መገናኘት አለብን ብላ ቀጠሮ አስያዘችው፤ እሱም በሀሳቧ ተስማምቶ የስልክ ንግግራቸውን ጨረሱ። ሰዓቱ ሲደርስም በተቀጣጠሩበት ቦታ የተገኘችው ዝናሽ ያልተዋጠላትን እና ቅር ያላትን ነገር ለማዋየት ነበር። ነገሩ ግን እንዳሰበችው አልሆነም።
ሀሳቧ ከእርሷው ጋር እንዳለ የቀጠረችው ሰውም ሳይመጣ ወደ ቤቷ ተመለሰች። ጉዳዩ ያበሳጫት ዝናሽ ከዚህ በላይ ትዕግስቷን መቆጣጠርም ሆነ ነገሮችን መቻል ተገቢ አለመሆኑን በመረዳት በተደጋጋሚ ስልክ መደወል ያዘች፣ ከዚህ ቀን በኋላ ለሥራ፣ ለወዳጅነት ለሕይወት አጋርነት የመረጠችው ይህ ሰው ወዳጅ አለመሆኑን ተገነዘበች።
በድንገት ትውውቅ ባመነችው አካልም ገንዘቧን እና እምነቷን እንደተበላች አወቀች። ነገር ግን ዝናሽ ተስፋ አልቆረጠችም ምክንያቱም ሙያውንና የሚሠራበትን ሆስፒታል ታውቃለችና ይህ ገንዘቧን የምታስመልስበት ቦታ እንደሆነ በማሰብ ወደ ዘውዲቱ ሆስፒታል አቀናች። በሆስፒታሉ የአዋላጅ ክፍል የተባለው ዶ/ር ፍፁም አልጀብራን አውቀዋለው የሚል አልተገኘም። ጉዳዩ ከባድ መሆኑን የተረዳችው ዝናሽ ጉዳዩን ለፖሊስ አመለከተች። የማይገባውን ጥቅም ለማግኘት የተጠቀመው ስልታዊ ሀሰተኛ ማንነት ግን ይህንን ሰው ለማግኘት ተጨማሪ ፍለጋዎችን ማድረግ ይጠይቅ ነበር።
ይህ የጀመረው በሰው ዘንድ መታመንን በመፍጠር የሚያደርገው የማታለል ሥራ በጣም ቀላል ድካም የሌለው ሆኖ ያገኘው ሌላ አማራጭ መፈለጉን ቀጠለ።
ለሥራው እንደ ሽፋን የሚጠቀመው ደግሞ አንድም ቅርበት ወዳጅነት፣ የራሱን ማንነት ከፍ በማድረግ ያልሆነውን ሆኛለሁ በማለት፣ በዚህም በትውውቅ፣ ከሰዎች ጋር ሆን ብሎ ግንኙነትን ይፈጥራል።
ሌላኛው መንገድ የሰዎችን ፍላጎት በማጤን አብዝተው የሚፈልጉትንና አንገብጋቢ የሆነውን የቤት ጥያቄ እፈታላችኋለሁ በሚል መቅረብ ጀመረ። አስቀድሞ ወዳጅ መስሎ በመቅረብ እና ተዓማኒነቱን ከፍ በማድረግ አንድ ጊዜ ሀኪም እንደሆነ እና ተደራጅተው በማኅበር መሬት ለመውሰድ እየተዘጋጀ እንደሆነ እና ሰው ስለጎደለው ቅድመ ክፍያ ከፍለው እንዲገቡ ያደርጋል። ሌሎች ሰዎችን እንዲሁ ለሥራ ኃላፊዎች ቅርበት አለኝ ባለስልጣናትን አውቃቸዋለሁ በለሚኩራ ክፍለ ከተማ ቦሌ ቡልቡላ ላይ ቤት አሰጣችኋለሁ በማለት እንደቅድመ ክፍያ በተለያየ ጊዜ ገንዘብ ሲቀበል ቆይቷል። በመሆኑም ከግል ተበዳይ ወይዘሮ ዝናሽ ላይ ማታለል ከፈፀመ በኋላ ለአንድ አመት ያክል ይህንን ተግባራት በመፈፀም እና አሳምኖ ገንዘብ ከተቀበለ በኋላ ስልኩን እና አድራሻውን አጥፍቶ በመሰወር ተደጋጋሚ ክስ ቀርቦበታል።
የወንጀል ዝርዝር
ተከሳሽ የማይገባውን ብልጽግና ለማግኘት በማሰብ ራሱን ሀኪም ነኝ በማለት እና ከተለያዩ ባለስልጣናት (የሥራ ኃላፊዎች ጋር ግንኙነት አለኝ መሬት አሰጣችኋለሁ በማለት ከሰዎች ጋር ያለውን ቅርበት ተጠቅሞ ለማሳመን በመሞከር ባደረገው የማታለል ተግባር በተለያየ ጊዜ በሰራው ወንጀል በሰባት የተለያዩ ክሶች ተከሷል፡፡
1ኛ ክስ ግንቦት 19/2014 ዓ.ም በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 06 ልዩ ስሙ ዘንባባ ተብሎ የሚጠራ ቦታ ላይ የግል ተበዳይ ዝናሽ አበራን ዶክተር ሳይሆን ነኝ ብሎ ማንነቱን በመደበቅ ዘውዲቱ ሆስፒታል አዋላጅ ነኝ በማለት በትርፍ ጊዜው ለገሀር ሆስፒታል እና የአፍሪካ የሕክምና ማዕከል እንደሚሠራ በመግለጽ ከተዋወቃት በኋላ በተደጋጋሚ በራይድ (የሜትር ታክሲ አገልግሎት) ዘውዲቱ ሆስፒታል እንድታደርሰው በማድረግ ዶ/ር ስለሆንኩ የሥራ ፍቃድ (የሙያ ፍቃድ አለኝ በማለት ፍቃድ እናውጣእና ክሊኒክ እንክፈት በሚል የሕክምና እቃ ለማምጣት 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ስለሚስፈልግ ተበዳይን 500ሺህ ብር ስጪኝ እና እኔ የቀረውን እሞላለሁ ብሎ በማታለል በተለያ ጊዜ 500ሺህ ብር በመቀበል፤
2ተኛክስ ነሐሴ አንድ 2014 ዓ.ም ተከሳሽ ቦታ (መሬት) አሰጥሀለሁ የተለያዩ ባለስልጣናትን አውቃለሁ ቡልቡላ እና ኮዬ ፈጬ መሀል ቦታ ላሰጣችሁ በማለት ቅድመ ክፍያ መክፈል አለባችሁ ብሎ31ሺህ ብር ተቀብሎ በመሰወር፣
3ተኛ ክስ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 692(1) ስር የተመለከተውን ሕግ በመተላለፍ ነሀሴ 2014 ዓ.ም የግል ተበዳይ ርብቃ ታመነን በአደይ አበባ ከረፋዱ ሶስት ሰዓት ከ30 (ተኩል) ላይ ቀጥሮ ትርፍ መሬት ላሰጥሽ በሚል 50ሺህ ብር ተቀብሎ ቦታው ይሰጣል ጠብቂ ብሎ በመሰወር፣
4ተኛ ክስ መስከረም 21/2015 ዓ.ም አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 03 በአንድ ተቋም ሥራ አስኪያጅ የሆኑ የግል ተበዳይ አበራ ድሪባን ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ቦሌ ቡልቡላ ቤት ለመውሰድ ተደራጅተናል 99 ሰዎች ሆነን አንድ ሰው ቀርቷል የሚሰጠውን ቦታ ብሎ ያዘጋጀውን በፎቶ በማሳየት ላስገባህ 12ሺህ ብር ቅድመ ክፍያ ክፈል በማለት ገንዘቡን ከተቀበለ በኋላ ጠብቅ በማለት በመሰወር፣ ተከሳሽ በዚሁ ወር መሀመድ ሰዒድ የተባለ ተበዳይን የማውቃቸው ባለስልጣናት አሉ ቤት ላሰጥህ በማለት 50ሺህ ብር በመቀበል እንዲሁም ከተከሰሰበት የማታለል ወንጀል
ሰባተኛ የክስ ዝርዝር እንዲሁ የግል ተበዳይን በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆነ በማታለል 25ሺህ ብር ተቀብሎ በመሰወር በሚል ዓቃቤ ህግ ተከሳሽ የከሰሰበት ነው፡፡
ማስረጃዎች
ዓቃቤ ሕግ ተከሳሽን ፍርድ ቤት ላቀረበበት ያልተገባ ብልጽግና ለማግኘት በሚል 7 የሰው ምስክሮችን ያጠናከረ ሲሆን ተበዳዮች በመታለል ተዘርፈናል ያሉትን የገንዘብ መጠን ወደ ባንክ አካውንቱ መግባቱን ከተለያዩ ባንኮች ባገኘው መረጃ 837 ሺህ ብር ከተለያዩ ሰዎች መቀበሉን ሊያረጋግጥ ችሏል።
በተጨማሪም ተጠርጣሪው በዘውዲቱ ሆስፒታል እንዲሁም እሠራባቸዋለሁ ባላቸው ሁለት የተለያዩ ሆስፒታሎች ሠራተኛ አለመሆኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ከተቋማቱ አግኝቷል። ይህንንም የተከሳሽ የእምነት ቃል በማያያዝ ለፍርድ ቤት አቅርቧል።
ውሳኔ
ተከሳሽ ፍጹም አልጀብራ በተከሰሰበት ሰው ማታለል ወንጀል ጉዳይ በክርክር ላይ የነበረና በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ ችሎት በቀን 26/02/ 2017 ዓ.ም ፍርድ ቤቱ ክስና ማስረጃ አገናዝቦ በሰጠው ውሳኔ 8 ዓመት ጽኑ እስራት እና ሁለት ሺህ ብር ይቀጣል በማለት ወስኗል፡፡
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 16 ቀን 2017 ዓ.ም