ትናንት በርካታ ሁነቶችን ካስተናገደችው ጅማ ከተማ በዋዜማው አመሻሽ ላይ ገብተው ያደሩ ጋዜጠኞች፣ በማግስቱ ማልዶ ከተማዋ ከምታስተናግዳቸው ሁነቶች አንዱ ወዳለበት ጅማ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ተገኝተዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ግቢ ከወትሮው በተለየ መልኩ ደምቆና ተውቦ ይታያል፤ በአንድ በኩል የእንኳን ደስ አላችሁ ስጦታ እቅፍ አበባዎች የያዙ ቤተሰቦችና ተመራቂዎች የግቢው ጌጥ ሆነዋል፡፡ በሌላ በኩል የሆነ ፕሮጀክት እንደሚመረቅ የሚያሳብቅ ሪቫን ይታያል፡፡ ይህ እንዴት ሆነ፤ የሚል ጥያቄ ከተነሳ ደግሞ ዕለቱ ዩኒቨርሲቲው አንድም ለዓመታት ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ያስመረቀ መሆኑ ሲሆን፤ ሁለተኛም ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ያስገነባቸው ለማህበረሰብ አገልግሎት የሚሆኑ መሰረተ ልማቶችን ለምርቃት ያበቃበት የጣምራ ቀኑ ስለሆነ ነው፡፡
የዩኒቨርሲቲው የተማረ የሰው ኃይል የማፍራትና የማህበረሰብ አገልግሎት ሥራዎቹ ለፍሬ መድረስ ማሳያ በሆነው በዚህ የጣምራ ምርቃት መርሐ ግብር እለቱ የተማረ የሰው ኃይል ተግባሩ ውጤት የሆኑ 2ሺ178 ተማሪዎችን አስመርቋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 1ሺ29 በመጀመሪያ ዲግሪ፣ ከእነዚህ ውስጥ 238ቱ በህክምና የመጀመሪያ ዲግሪ ተመራቂዎች ሲሆኑ፣ 1ሺ145ቱ ደግሞ በድህረ ምረቃ፣4ደግሞ በሦስተኛ ዲግሪ መርሐ ግብሮች ያስተማራቸው ናቸው፡፡
የማህበረሰብ አገልግሎት ማሳያ ከሆኑት ተግባራት መካከልም፣ 40ሺ ሰው የመያዝ አቅም ያለው ስታዲየም፣ሰባት ሺ አምስት መቶ ሰው የሚይዝ ሁለገብ ማዕከል፣ አራት ሺ አምስት መቶ ሰዎችን የሚይዝ የስብሰባ አዳራሽ እንዲሁም ከ15 ሚሊዮን የሚልቁ ሰዎችን የማስተናገድ አቅም ያለው ዘመናው ሆስፒታልን ገንብቶ አስመርቋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ብቁ ባለሙያዎችን አሰልጥኖ ከማስመረቅ ባለፈ፤ ለማህበራዊ አገልግሎት የሚውሉ መሰረተ ልማቶችን ሰርቶ ለአገልግሎት ዝግጁ ማድረጉ የተጣለበትን አገራዊ ተልዕኮ ለመወጣት እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት ተመጋጋቢ በሆኑ መልኩ እያስኬደ ለመሆኑ ማሳያ መሆናቸውም ነው የተገለጸው፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ለሜሳ እንዳሉት፤ ዩኒቨርሲቲው በመማር ማስተማር፣ በምርምርና በማህበራዊ አገልግሎት ዘርፎች የተጣለበትን አገራዊ ኃላፊነት እየተወጣ ይገኛል፡፡ በእለቱ የተመረቁት ተማሪዎችም የዚሁ ተግባሩ አካል ሲሆኑ፤ የአካባቢውን ህብረተሰብ ጭምር ተጠቃሚ የሚያደርጉ ደረጃቸውን የጠበቁ መሰረተ ልማቶችን በማከናወን ላይም ይገኛል፡፡ስታዲየሙ፣ የሁለገብ ማዕከሉና የስብሰባ አዳራሹም የዚሁ ተግባሩ አካል ናቸው፡፡
በዕለቱ የተመረቀውና ከ15 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያንን ሊያገለግል የሚችለው ሆስፒታልም ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ከመደራጀቱም በላይ እስከ 800 ታካሚዎች አስተኝቶ ማከም የሚያስችልና የህክምና መሳሪያዎችም የተደራጁለት መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ዩኒቨርሲቲው የማህበረሰቡን ችግር ፈቺ የሆኑ ሳይንሳዊ ጥናቶችን በማድረግ ማህበረሰቡን የማገልገል ተልዕኮውን እየተወጣ ሲሆን፤ በቀጣይም እነዚህን ተግባራት አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡ ተመራቂዎችም በዩኒቨርሲቲው ቆይታቸው ባገኙት ልምድና እውቀት ታግዘው በተሰማሩበት ቦታ ሁሉ ህዝባቸውን በቅንነትና በታማኝነት ሊያገለግሉ ይገባል ብለዋል፡፡
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ወልደማርያም በበኩላቸው እንዳሉት፤ ዩኒቨርሲቲው በመማር ማስተማር፣ በማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎትና በምርምር ሥራዎቹ የሚታወቅ ሲሆን፤ በዕለቱ የታየውም የዚሁ ሥራው ውጤት ነው፡፡ በመሆኑም ይሄንኑ ተግባሩን ማጠናከርና የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ መስራት ይኖርበታል፡፡ ተመራቂዎችም በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፈው በብዙ ፈተና ውስጥ ለዚህ ስኬት መብቃታቸው ለህልማቸው መሳካት ያላቸውን ቁርጠኝነት ያሳየ ሲሆን፤ ይህ ግን የመጨረሻ መዳረሻቸው ሳይሆን አዲስ ምዕራፍ መጀመሪያቸው መሆኑን ተገንዝበው መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡
ተመራቂዎች በተለይም ሐኪሞች ሥራቸው አደጋ የበዛበትና ከፈጣሪ በታች የሰው ልጆችን ከሞት የመታደግ ተግባር መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሯ፤ ተመራቂዎች ለዚሁ ተግባር ራስን ሰጥቶ ለመስራት መዘጋጀት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ህይወታቸውን በስሜት ሳይሆን በምክንያት እንዲመሩ፤ ጓደኞቻቸው፣ የሚያነቧቸው መጻሕፍትና የሚመለከቷቸው ፊልሞች ሳይቀሩ የነገ ህልማቸውን ለማሳካት የሚያግዟቸው ሊሆኑ እንደሚገባም መክረዋል፡፡ ይሄን ሲያደርጉም ህዝባቸውን በቀናነት ማገልገል፤ የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል እንደሚችሉ በመጠቆምም፤ ለዚህ ደግሞ ከዘረኝነት፣ ሌብነትና ራስ ወዳድነትን ከመሳሰሉ ተግባራት ርቀው በሄዱበት ፍቅርና መደመርን በማስተማር የተጣለባቸውን አደራ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
«በቤተሰባዊ ችግር ውስጥ ሆናችሁ በማስተማር እነዚህን ውብ ምሑራን ለዚህ ያበቃችሁ ወላጆች፤ በመልካም እውቀት ቀርጻችሁ ለዚህ ያበቃችኋቸው መምህራን እንኳን ደስ ያላችሁ» በማለት ለተማሪዎች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ያስተላለፉት ደግሞ በዕለቱ በቦታው የተገኙት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ናቸው፡፡ ‹‹ልጆች ምን መሆን ትፈልጋላችሁ›› ሲባሉ ከሚናገሯቸው ሙያዎች አንዱ ሐኪም መሆን እንደሆነ በመጠቆምም፤ የዕለቱ ተመራቂዎች በተለይም ሐኪሞች ህብረተሰቡ ‹‹ሐኪም እንኳን መድኃኒቱ እጁ ያድናል›› የሚለውን ብሒል በተግባር የሚያይበትን ተቋም ከመገንባትና ለዚሁ ተግባር ከመትጋት አኳያ በአንድነትና በፍቅር መስራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡
«አንጀቴ ከሆዴ ተቆርጦ ከወጣ፤ እንግዲህ ሐኪሙ ምን ሊቀጥል መጣ፤» ይሉት የህዝቦች የብሶትና ምሬት ስሜትን በማንሳትም፤ ሐኪምነት ህሙማንን መንከባከብ፣ እውቀትን ለሌሎች ማካፈል እንዲሁም ለበሽታ መፍትሄ እስኪገኝ ድረስ ሳይታክቱ መመራመር መሆኑን ተገንዝቦ የህዝቦች አለኝታ መሆን እንደሚጠበቅባቸውም ተናግረዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ሐኪሞች ሰውነትን ከማከም በፊት የሰዎችን ልብ ማከምን ማስቀደም እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡ ይህን ማድረግ የሚችሉትም ቅድሚያ ከሙያ አጋሮቻቸው ጋር መደመር ሲችሉ፤ ከዛም አልፈው ለበጎ ነገሮች ሁሉ መተባበር ሲችሉ መሆኑንም አውስተዋል፡፡ ሐኪምነት ጥበብና መሪነት መሆኑን ተገንዝቦ በዚሁ ልክ እንዲሰሩ፤ ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲገቡ ህልም ይዘው እንደገቡ ሁሉ ሲወጡም አገርና ህዝብ የሚለውጥ ህልም ይዘው ሊወጡ እንደሚገባም አደራ ብለዋል፡፡
ተመራቂ ተማሪዎች በበኩላቸው፤ የዓመታት ልፋት ውጤታቸውን ማየት በመቻላቸው መደሰታቸውንና በተሰማሩበት ቦታ ሁሉ ህዝብን በቅንነት ለማገልገል መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡ አስተያየታቸውን ከሰጡን ተመራቂዎች መካከል የሜዲስን ተማራቂው ዶክተር ዮናታን ከማል እንዳለው፤ የዓመታት ልፋት ፍሬውን ከማየቱ ጋር ተዳምሮ የዶክተር አብይ በመድረኩ መገኘት እጅጉን አስደስቶታል፡፡ በመድረኩ በተላለፈው መልዕክት መሰረትም ህዝቡን በቅንነት ለማገልገል ከመዘጋጀት ባለፈም በገጠራማው የአገሪቱ ክፍል ጭምር ተሰማርቶ ለመስራት ተዘጋጅቷል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 30/2011
ወንድወሰን ሽመልስ