ተወልዶ ባደገበት የገጠር አካባቢ የኤሌክትሪክ ኃይል አልነበረም:: ምንም እንኳን በልጅነቱ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚባል ተጠቅሞ ባያውቅም የኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰጣቸውን ጥቅሞች ግን ጠንቅቆ ያውቃል፤ የተወለደበት አካባቢም የዚህ የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲኖረው ሲመኝ ኖሯል:: ምኞት ብቻ ሳይሆን በተግባር ሆኖ ማየት ይፈልግም ነበር::
የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን ወደዚህ መንገድ የሚያመራውን ሀሳብ አገኘ:: ሀሳቡ እውን ሆኖም ሁለት አይነት ጀነሬተሮች ለመስራት የቻለው ይህ የፈጠራ ባለሙያ ተማሪ አብዱራህማን ከድር ይባላል::
አብዱራህማን የ10ኛ ክፍል ተማሪ ነው:: ምንም አይነት የነዳጅም ሆነ የሶላር ኃይል ሳይጠቀሙ ኃይልን የሚያመነጩ ሁለት አይነት ጀነሬተሮችን መስራት የቻለው:: ጀነሬተሮቹ 60ና 150 ዋት ኃይል ማመንጨት ይችላሉ::
እሱ እንደሚለው፤ ጀነሬተር ቢገዛ የሚሰራው በነዳጅ ስለሆነ የነዳጁ ጭስ በጤና ላይ ጉዳት እና የአካባቢ ብክለት የሚያስከትል ከመሆኑም በላይ ወጪውም ከፍተኛ እንደሆነ ካሰበ በኋላ ይህን ሁሉ ችግር የሚፈታ ጀነሬተር ለመስራት አቀደ:: ‹‹ በአነስተኛ ወጪ ምንም ጉዳት የማያደርስ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰጥ ጀነሬተር እንዴት ሰርቼ መብራት በሌለባቸው አካባቢዎች ላይ ተደራሽ ማድረግ እችላለሁ የሚለው ሀሳብ ቀን ከሌት ሳወጣና ሳወርድ ብዙ ጊዜ ፈጅቶብኛል›› ሲል ያብራራል::
አምስተኛ ክፍል እያለ የጀመረውን ሀሳብ ከዳር ለማድረስ ሙከራ ሲያደርግ እስከ ሰባተኛ ክፍል ዘልቋል:: በዚህ ሂደትም ሞባይል ቻርጅ ማድረግ የሚችል አምስት ዋት ኃይል የሚያመነጭ ጀነሬተር ሰራ::
ሰባተኛ ክፍል ላይ የተከታተለው የፊዚክስ ትምህርት ለፈጠራ ሥራው ተገቢ እውቀት እንዳስገኘትለት ይናገራል:: በዚህ የቴክኖሎጂ ዘመን በዓለም ያለኤሌክትሪክ ምንም አይነት ሥራ መስራት አይቻልም የሚለው ተማሪ አብዱራህማን፤ ቴክኖሎጂን ለመጠቀምና ለማስፋፋት፣ ለኢንዱስትሪም ሆነ ለሌሎች ሥራዎች የኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ነገር መሆኑን ጠቅሶ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል የዓለም የጀርባ አጥንት መሆኑን ይጠቁማል::
ከውሃ፣ ከነዳጅና ከጸሀይ ኃይል የኤሌክትሪክ ኃይል አመንጭቶ ለሁሉም ተደራሽ ማድረግ የማይቻል በሆነበት ሁኔታ ምን አይነት ዜዴዎችን ተጠቀመን ይህን ወሳኝ የልማት አቅም ማመንጨት እንችላለን የሚለው ሀሳብ ሌላ አማራጭ በፈጠራ ሥራው እንዲያገኝ እንዳስቻለው ተማሪው ይናገራል::
በተለይ አካባቢ ላይ አሉታዊ ተዕጽኖ የማይፈጥር፣ በቀላል መንገድና ወጭ የሚሰራና አገልግሎት የሚሰጥ ኃይል እንዴት ማመንጨት ይቻላል የሚለውን ለማወቅ አቅዶ የኃይል ማመንጫ ዘዴዎችን በሙሉ በማጥናት ወደ ሥራ እንደገባ ይናገራል:: ለዚህም ለመጀመሪያ ጊዜ እንደ አባይ ግድብና የመሳሳሉት ከውሃ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጩበትን መንገድ በማጤን እሱም ያለምንም የኤሌክትሪክ፣ የጸሀይ ወይም የነዳጅ ኃይል የኤሌክትሪክ ኃይል ማግኘት እንደቻለ ይገልጻል::
ተማሪ አብዱራህማን ጀነሬተር ከመስራቱ በፊት ለሁለት ዓመታት ጥረት አድርጓል:: ስድስተኛ ክፍል የሳይንስ ትምህርት እንዲሁም በተለይ የሰባተኛ ክፍል የፊዚክስ ትምህርት የኤሌክትሮ ማግኔቲዝ ትምህርት መማሩ ሀሳቡን ለማዳበር እና ስለ ኃይል ማመንጨት በጥልቀት እንዲያጠና አስችለውታል:: ‹‹ተጨማሪ እውቀት ፍለጋም በኦንላይን ላይ ያሉ ዶክመንተሪዎችንና የመሳሰሉትን ለሥራው የሚረዱኝን ጽሁፎችንና ቪዲዮዎችን በመመልከት መረዳት የምፈልገውን በደንብ መረዳት ችያለሁ:: ይህም ሀሳቡን በደንብ ተረድቼ የፈጠራ ሥራውን ለመሥራት አስችሎኛል ›› ሲል አብራርቷል::
ሀይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይልን በመጠቀም ካለ ውሃ እንዴት ኃይል ማመንጨት ይቻላል ለሚለው መፍትሔ በማግኘት ባለ60 ዋት ኃይል ማመንጨት የሚችል ጀነሬተር መስራት ቻለ:: ጀነሬተሩ ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀስም፣ የሁሉንም ሕብረተሰብ ክፍሎች ችግሮችንም እኩል መፍታት ይችላል:: አስቸጋሪ በሚባሉ ቦታዎች ጭምር በሁሉም ቦታዎች በእኩል ጥቅም ላይ ሊውል የሚችልም ነው::
ለጀነሬተሮቹ ‹‹ከአብ ጀነሬተር›› የሚል ስያሜ ሰጥቷቸዋል፤ ስያሜውን ከአባቱ ስም የመጀመሪያውን ፊደል እና ከራሱ ስም ደግሞ የመጀመሪያ ሁለት ፊደላት በመጠቀም እንዳወጣውም ይገልጻል::
ከተማሪ አቡዱራህማን የፈጠራ ውጤቶች መካካል የመጀመሪያው ሙከራ ያደረገበት 60 ዋት ኃይል ማመንጨት የሚችል ጀነሬተር ነው:: ጀነሬተሩ የሚያመነጨው ትንሽ ኃይል ቢሆንም አንድ አምፑል፣ ቴሌቪዥን እና ስልክ ቻርጅ ያደርጋል::
ይህ የመጀመሪያ የፈጠራ ሥራው ለሁለተኛ ፈጠራ ሥራው መሠረት ሆኖ ሁለተኛውን 150 ዋት ኃይል ማመንጨት የሚችል ጀነሬተር መስራት አስችሎታል:: ‹‹ባለ60 ዋቱ የመጀመሪያው ጀነሬተር የሚያመነጨው ትንሽ ኃይል ቢሆንም እጄን ያፍታታሁበት የመጀመሪያ ሥራዬ በመሆን ለፈጠራ ሥራ መሰረት ሆኖኛል፤ ቀጣዩን እንዲሰራ ብርታና ሞራል ሰጥቶኛል›› ይላል::
ተማሪ አብዱራህማን እንደሚለው፤ ጀነሬተሮቹ በመብራት ኃይል የሚሰሩ ሁሉንም አይነት አገልግሎቶች መስጠት ያስችላሉ:: የተገጠሙላቸው ቁሳቁስ እስካልተቃጠሉ ድረስ የሚሰጡት ኃይል ሳይቀንስና ሳይጨምር ያለምንም መቆራረጥ አገልግሎት መስጠት ይችላሉ:: ቁሳቁሱ ቶሎ የማይቃጠሉና የማይበላሹ ቢሆኑም አጋጣሚ ሆኖ የሚቃጠሉና የሚበላሹም ከሆነ በቀላሉ ተቀይረው እንዲሰሩ ማድረግ ይቻላል::
ጀነሬተሮቹ ለአምፑል፣ ለቴሌቪዥን፣ ለስልክና ለመሳሳሉት በኤሌክትሪክ ኃይል ለሚሰሩ አገልግሎቶች የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ ይጠቅማሉ:: መብራት በሌለባቸው አካባቢዎችና መብራት ለሚጠፋባቸው አካባቢዎች አገልግሎት መስጠትም ይችላሉ::
እሱ እንዳብራራው፤ ጀነሬተሮቹ በቀላል ወጪ የሚሰሩ ከመሆናቸው በተጨማሪ በአካባቢ ላይ ምንም አይነት ጉዳት አያስከትሉም:: ጀነሬተር የመስራት ሀሳቡን ሲያመነጭ በቀላሉ ለመስራት የሚችልበትን ዘዴ ፍለጋ ላይ ትኩረት አድርጎ ሰርቷል:: የመጀመሪያ ጀነሬተሩን የሰራው በ2014 ዓ.ም ነው፤ ከመጀመሪያው የፈጠራ ሥራ ያገኘው እውቀትና ልምድ ሁለተኛውን የፈጠራ ሥራ መስራቱን እንዳቀለለት ይገልጻል::
ሁለተኛው የፈጠራ ሥራውንም በ2016 ዓ.ም እንደሰራው አስታውሶ፣ ይህንን ለመስራትም አስራ አምስት ቀናት ብቻ እንደፈጀበት ይገልጻል:: ሥራው ይህን ያህል የቀለለት ሊሰራው ያሰበውን ጀነሬተር አስቀድሞ በሀሳቡ አስቀምጦት ስለነበር ነው፤ በዚህም ስኬታማ በመሆኑ የሚፈልገው ከግብ ለማድረስ መቻሉን ያስረዳል::
እጁን ያፍታታበትና መነሻ የሆነው የመጀመሪያ የፈጠራ ሥራው እውቀትና ልምድ እንዲያገኝ ከማስቻሉ በላይ ብዙ እንዲያውቅና ሥራውን ይበልጥ በጥበብ እንዲሰራ እንደረዳው የሚናገረው ተማሪ አብዱራህማን፤ ሁለተኛው የፈጠራ ሥራው በአጭር ጊዜና በቀላሉ መስራቱ ከዚህ በመነጨ መሆኑን ይናገራል::
የመጀመሪያውን ጀነሬተር ለመስራት ብዙ ጊዜ እንደወሰደበት አስታውሶ፣ ጀነሬተሩን ለመስራት የሚያስፈልጉትን ቁሳቁስ በቅርበት ማግኘት ከተቻለ በቀላሉ መስራት እንደሚችል ይገልጻል:: ጀኔሬተሮቹን ለመስራት የሚያስፈልጉትን ግብዓት በቀላሉ ማግኘት ከቻለ በአንድ ቀን ብዙ ጀነሬተር ማምረት እንደሚችልም ያስረዳል::
ተማሪው እንዳብራራው፤ እነዚህን ጀነሬተሮች ለመስራት ከሚያስፈልጉት ጥሬ ግብዓቶች አብዛኛዎቹ በሀገር ውስጥ የሚገኙ ናቸው:: ለስራው ባትሪ፣ ዲኖሞ፣ የሙቀት መቆጣጣሪያ መሳሪያዎች እና የመሳሳሉት ያስፈልጋሉ:: የመጀመሪያውን ባለ60 ዋት ጀነሬተር ለመስራት 135 ብር ብቻ ነው ወጪ የተደረገው ፤ ሁለተኛውን ባለ 150 ዋት ጀነሬተር ለመስራት ደግሞ ሁለት ሺ92 ብር ወጪ ተደርጓል::
ተማሪ አቡዱራህማን ሁለቱም የፈጠራ ሥራዎች ተፈትሸው አገልግሎት ላይ መዋላቸውን ጠቅሶ በተለይ የመብራት እጥረት ባለባቸው አካባቢዎች ለሕብረተሰቡ ተደራሽ ሆነው አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ ይገልጻል:: በፈጠራ ሥራዎች ከአእምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት የባለቤትነት መብት ለማግኘት በሚያስችለው ሂደት ላይ መሆኑን አስታውቆ፣ በቅርብ የባለቤትነት መብት እንደሚያገኝ ይጠቁማል::
የፈጠራ ውጤቶች የመጀመሪያ ሙከራ ያደረገበት 60 ዋት ኃይል ማመንጨት የሚችል ጀነሬተር ለቤተሰቦቹ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ይገልጻል:: ሁለተኛው 150 ዋት ኃይል ማመንጨት የሚችል ጀነሬተርም እንዲሁ የኤሌክትሪክ ኃይል በሌለበት አካባቢ አርሲ ዞን ኮኮርሳ ወረዳ ጋጣ የምትባል አካባቢ ለሕብረተሰቡ አገልግሎት እየሰጠ ነው::
በዚህ አካባቢ ተደራሽ ሆኖ ለሕብረተሰቡ የመብራት አገልግሎቶች ለሚውሉ ለአምፑል፣ ለቴሌቪዥን ፣ የስልክ እና የመሳሳሉት እየሰጠ ይገኛል:: ‹‹ ጀነሬተሩን ለሰው ሰጥቼ ሕብረተሰቡ አገልግሎት እንዲያገኝ እያደረግኩ ነው:: ለምሳሌ ስልክ በ20 ብር ሂሳብ ቻርድ የሚደረግ ሲሆን፤ አገልግሎቱን እየሰጠ ያለው ሰው አምስት ብሩን ለራሱ በመውሰድ፤ 15 ብር ገቢ ያደርግልኛል›› ይላል::
ተማሪ አብዱራህማን በተለይ ሙከራ ተደርጎባቸው አገልግሎቱን እያገኙ ያሉ ሕብረተሰብ ክፍሎች የራሳቸው የሆነ ጀነሬተር እንዲኖራቸው በመፈለግ እንዲሰራላቸው እንደጠየቁት ይናገራል:: ለእዚህም አንድ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች አብረው ገንዘብ በማጠራቀም በጋራ የሚፈልጉትን አይነት አቅም ያለው ጀነሬተር ሊሰራላቸው ማቀዱን ጠቁሟል::
በተጨማሪም ለአንድ ከተማ ነዋሪዎች እስከ 20ሚሊዮን ዋት ኃይል ማመንጨት የሚችል ጀነሬተር ለመስራት አቅዶ እየሰራ መሆኑን ይገልጻል:: በአሁኑ ወቅት ደግሞ በአንድ አካባቢ ላይ ለሚኖሩ የሕብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎት ሊሰጥ የሚችል ባለ 1025 ዋት ጀነሬተር መስራት መጀመሩን ገልጾ፤ ጀነሬተሩን ለመስራት 750 ሺ ብር እንደሚያስፈልግ አስታውቋል:: አሁን ላይ የጀነሬተሩን ንድፍ አስቀምጦ አስፈላጊ ሥራዎች እየሰራ መሆኑን አመላክተዋል::
ወደፊትም ከትምህርቱ ጎን ለጎን የፈጠራ ሥራዎች እየሰራና እያሳደገ እንደሚሄድ የሚገልጸው ተማሪ አብዱራህማን፤ ‹‹አሁን ላይ ዋንኛ ትኩረቴ ትምህርቴ ላይ ቢሆንም የጀመርኩትን ጀነሬተር እየሰራሁ ለሕብረተሰቡ ተደራሽ አደርጋለሁ:: ሌሎች የሕብረተሰቡን ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉ የፈጠራ ሥራዎች ለመስራት አስባለሁ›› ይላል::
የፈጠራ ሥራ ትኩረት ሰጥቶ ለመስራት ብዙ ጊዜና ብዙ ጥረትና ሙከራዎችን ማድረግን እንደሚጠይቅ የሚገልጸው ተማሪ አብዱራህማን፤ የፈጠራ ሥራ የመስራት ውስጣዊ ፍላጎት ካለ ውጣ ውረዱ ቢበዛም ከታሰበበት መድረስ እንደሚቻል ያመላክታል:: እነዚህን የፈጠራ ሥራዎች ሲሰራ የቤተሰቦቹ ድጋፍና አስተያየት ከፍተኛ የሞራል ስንቅ እንደሆነው ጠቅሶ፣ ይህም ሥራዎቹን በትጋት እንዲሰራና ለውጤት እንዲበቃ እንደረዳው ይናገራል::
በተለይ ሀሳቡ ኖሯቸው የፈጠራ ሥራ ለመስራት የሚፈልጉ ተማሪ የፈጠራ ሥራ ባለሙያዎች የትምህርት ጊዜያቸውን በማይሻማ መልኩ ማስኬድ ይጠበቅባቸዋል:: መማራቸው ለእዚህ ሥራቸው ወሳኝ መሰረት የሚጥልላቸውና እውቀት እንደሚጨምርላቸው አውቀው ከትምህርታቸው ጎን ለጎን ፈጠራዎች መስራት አለባቸው ሲል አስገንዝቧል::
ተማሪው፤ የፈጠራ ሥራዎቹን ሁሉም ሰው አውቋቸው ተደራሽ እንዲሆኑ ለማድረግ በኦንላይን ፣ በማኅበራዊ ሚዲያዎችና በአውደርዕይ ላይ በማቅረብ እያስተዋወቀ ይገኛል:: ለሕብረተሰቡ የሚሰጡትን ጥቅም አይተው አውቀዋቸው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል ይጠቅማል ይላል::
እሱ እንዳለው፤ በቀጣይ የሰዎችን ፍላጎት መሰረት በማድረግ የተለያየ መጠን ያላቸው ጀነሬተሮች እያመረተ ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ አቅዷል:: ለኢንዱስትሪ፣ ለመኖሪያ ቤት እና በከተሞች የሚፈልጉ ሰዎች ካሉ በሚፈልጉበት ቦታ በሚፈልጉት ዋት መጠን እንደፍላጎታቸው እየሰራ ለማቅረብ ፍላጎቱ አለው::
በእዚህ መልኩ ወደ ማምረት ሲገባም ለሁለት ሺ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር እንደሚችል ይገልጻል:: ለአንድ ከተማም ይሁን ለፋብሪካ ትልልቅ ኃይል ማመንጨት የሚያስችሉ ጀነሬተሮችን የማምረት፣ ጀነሬተሮችን ሊቆጣጠሩ የሚችሉ ባለሙያዎችንም የማስልጠን እቅድ እንዳለውም አስታወቋል::
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ታኅሣሥ 22 ቀን 2017 ዓ.ም