ኢትዮጵያ ከአለም ገበያ የውጭ ምንዛሪ ከምታገኝባቸው ዘርፎች መካከል የቡና ገበያ ቀዳሚው ነው። በአገሪቱ ከፍተኛ የቡና ምርት ቢኖርም፤ ከጥራትና ሌሎች የአቅርቦት ችግሮች ጋር በተያያዘ በሚፈለገው ደረጃ የአለም ገበያን ሰብሮ መግባት ሳይቻል ቆይቷል። በቅርቡ ደግሞ ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› እንዲሉ ማንነታቸው ባልተለየ አካላት እየተካሄደ ያለው ቅሸባ ፤ ወትሮም እየተውተረተረ ያለውን የቡና ወጪ ገበያ እንቅፋት እየፈጠረበት ይገኛል። ይህም አገሪቱ የምታገኘውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ማሳጣት ብቻ ሳይሆን በዘርፉ የተሳተፉትንም ባለሀብቶች ፊታቸውን ወደ ሌላ እንዲያዞሩ እያስገደደ እንደሆነ ይነገራል።
ባለፉት ጥቂት ወራት ወደ ውጪ በሚላክ ቡና ላይ እየተካሄደ ያለው ስርቆት ማህበሩን ለኪሰራ ብቻ ሳይሆን በዘርፉ የሚኖረውንም ቆይታ እየተገዳደረው እንደሆነ የሚናገሩት የኢንፖርት ኤክስፖርት ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ባለቤትና ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ታደሰ ደስታ፤ ላለፉት አስራ ስምንት አመትታ በወጪ ንግድ ተሰማርተው ቡና ሲልኩ ቢቆዩም አሁን ግን የማህበሩ ህልውና አደጋ ላይ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡
እንደ አቶ ታደሰ ማብራሪያ፤ ከእዚህ በፊት ተመሳሳይ የቅሸባ ችግር ይገጥም የነበረው ቡናው በተሽከርካሪ ተጭኖ ሸራ አልያም ላስቲክ ለብሶ በሚንቀሳቀስበት ወቅት ከእያንዳንዱ ጆንያ በመቀነስ ነበር። ይህም ቢሆን ጭነቱ ጂቡቲ ሲደርስ ጆንያውን ቆጥረው ስለሚረከቧቸውና አንዳንዴም ስለሚመዘን ከእያንዳንዱ የሚቀሽቡት ከሁለት እስከ አስር ኪሎ ብቻ በመሆኑ ከአንድ መኪና የሚጎድለው እስከ ሁለትና ሶስት ኩንታል እሱም አልፎ አልፎ ነበር ።
አቶ ታደሰ እንደሚሉት፤ ይህንን ለማስቀረት በኮንቴነር አሽጎ ወደ መላክ ቢገባም ከቅርብ ግዜ ወዲህ በባሰ ሁኔታ በአንድ ዙር ከሚጫነው ግማሽ ያህሉን መውሰድ ጀመሩ። በአሁኑ ወቅት 320 ኩንታል ከሚጭን አንድ ኮንቴነር ከስልሳ እስከ መቶ ሀያ ኬሻ ጎድሎ ይገኛል። አንድ ኬሻ ስልሳ ኪሎ ግራም የሚይዝ ሲሆን ከተጫነው ግማሽ ያህሉ ተወሰደ እንደማለት ነው። አሽከርካሪዎች ከላኪው ሲሰጣቸው የመንግስት አካላት ባለበት ተመዝኖ ፈርመው ነው የሚረከቡት፡፡ ጂቡቲ ላይ ግን ኮንቴነሩን እንደታሸገ ነው የሚያስረክቡት፡፡ በመሆኑም ጉድለቱ የሚታወቀው ገዢው ሲረከብ ነው። የዚህ አይነት ስራ በተለያየ ጊዜ በአራት ኮንቴነሮች ላይ ተፈጽሟል። ይህ አይን ያወጣ ዘረፋ በዘርፉ የመቆየታቸውንም ነገር ጥያቄ ምልክት ውስጥ እያስገባው ይገኛል።
ከዚህ በፊት ከቡና ንግድ ጋር በተያያዘ ከጃፓን ጋር ችግር ተፈጥሮ እንደነበርና አሁንም አንዱ ጎድሎ የተገኘው ወደ ጃፓን ከተላከው ውስጥ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ታደሰ፤ እነርሱም ለኤምባሲያቸው ማሳወቃቸውንና አስፈላጊ ከሆነ ለብሄራዊ ባንክ ለንግድ ሚኒስትርም ሆነ ለሚመለከተው ክፍል እናሳውቅላችኋለን በማለት ድርጅቱ የጎደለውን እንዲከፍል ደብዳቤ መጻፋቸውን አንስተዋል፡፡
‹‹በተጨማሪም አሁን የጎደለው ካሳ ካልተከፈለ ሌላ ግብይት እንደማይፈጽሙም ነግረውናል። እኛ በትክክል ሳናጎድል ስለላክን መክፈል አንችልም፤ አንከፍልም ብንላቸው ደግሞ እነርሱ አማራጭ ስላላቸው መገበያየቱን ወደ ማቆም ይሄዳሉ። ይህንን ካደረጉ ለእኛ ብቻ ሳይሆን እንደአገርም ኪሳራ የሚያስከትል ይሆናል። በመሆኑም መንግስት ቢቻል የተለያዩ ምርቶች ሀገር ወስጥ ሲገቡ እንደሚደረገው የ‹‹ስካን ማሽን›› ቢያዘጋጅልን፤ አልያም ሁልጊዜ ኮንቴነሩ የሚመዘንበትን ሁኔታ ሊያመቻችልን ይገባል። ይህም ሆኖ ምናልባት ቢመዘን በማለት ባእድ ነገር ይቀላቅላሉ የሚል መረጃ እየደረሰን ስለሆነ በዚህ በኩልም መንግስት የተጠናከረ ክተትል ሊያደርግ ይገባል። ያጎደሉትን አሽከርካሪዎችም ሆነ አቀነባባሪዎች ላይ አስተማሪ የሆነ ህጋዊ እርምጃ መውሰድ ይጠበቃል›› ሲሉ አቶ ታደሰ አሳስበዋል።
በተመሳሳይ የተፍቲ ትሬዲንግ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ባለቤትና ስራ አስኪያጅ አቶ ፈይሰል አብዶሽ በበኩላቸው፤ ላለፉት አስር አመታት በዘርፉ ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸውን በማስታወስ የዛሬ ስድስት ወር ገደማ የገጠማቸውን ችግር ሲያብራሩም፤ ‹‹በቅርቡ በአንድ ተሽከርካሪ በሁለት ኮንቴነር ወደ አውስትራሊያና ኮሪያ ቡና ልከን ጭነቱ ከጂቡቲ በተለያዩ መርከቦች ሁለቱም ቦታ ይደርሳል። ቡናው ኮሪያ ሲደርስ 26 ኬሻ የአውስትራሊያው ደግሞ 25 ኬሻ ጉድሎ ይገኛል። ይሄ መረጃ ሲደርሰን ምክንያቱን ለማወቅ ኮንቴነሩ ሲታሸግ የተቀመጠችውን ባለ ቁጥር የእሽግ አለመከፈት ማመላከቻ ፎቶ ተነስተው እንዲልኩ ሲደረግ ከኢትዮጵያ ከታሸገበት ጋር የተለያየ ሆኖ ይገኛል። በዚህም የተነሳ በሚቀጥለው ሲጫን የጎደለውን አስበው ገንዘቡን ቀንሰው ለመስጠት አስበዋል። ይሄ ደግሞ እኛን ብቻ ሳይሆን ወደ ሀገር የሚገባውንም የውጪ ምንዛሪ የሚቀንስ ነው›› ብለዋል፡፡
‹‹እንደዚህ አይነት ነገር ገጥሞ አሽከርካሪው ቀርቦ በህግ እንዲጠየቅ ቢደረግም የሚያስረክብበት ወረቀት እጁ ላይ ስለሚኖር ነጻ ይወጣል። በመሆኑም መንግስትና የሚመለከታቸው አካላት ጂቡቲ ላይ ያለውን አሰራር አስተካክለው በተረጋገጠ አኳኋን በህጋዊ መንገድ የሚረካከቡበት አካሄድ መፈጠር አለበት። ከሁሉም በላይ ግን ሌቦቹ በየወቅቱ የተለያየ ዘዴ እየቀየሱ ስለሚመጡ የሚወሰደው ህጋዊ እርምጃ የተጠናከረ ሊሆን ይገባል። ከአመታት በፊት ተመሳሳይ ችግር ተከስቶ ነበር፡፡ ነገር ግን በወቅቱ ወንጀለኞቹ ከፍተኛ ቅጣት በመቀጣታቸው ለረጅም ዘመን ወንጀሉ ሳይሰራ ቆይቷል። በመሆኑም አሁንም ልክ እንደዛው መንግስት አስተማሪ እርምጃ ሊወስድ ይገባል›› ሲሉ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ግዛት ወርቁ በበኩላቸው ችግሩ የላኪዎቹ ብቻ ተደርጎ መወሰድ የለበትም ይላሉ። ዋና ስራ አስኪያጁ እንደሚያብራሩት ሀያ ቶን ተጭኖ አምስትና እስር ቶን ጎድሎ ሲገኝ የውጪዎቹ ተቀባዮች ለምን ይሄ ሆነ ? ማን አደረገው ? ብለው ሊያጣሩ አይችሉም። በድፍኑ ከዚህ አገር ጋር ግብይት አናደርግም ነው የሚሉት። አሁንም በተለያዩ ምክንያቶች የኢትዮጵያን ቡና ከአውሮፓ የሚገዙ የአሜሪካና የቻይና ኩባንያዎች አሉ። ይህን የሚያደርጉት ራሱን ቡናውን ከኢትዮጵያ ቀጥታ ለመግዛት እምነት በማጣት ነው። በተጨማሪም ሲጎድል ይከፈላል፤ የሚከፈለው ደግሞ በዶላር በመሆኑ ምንዛሬ ማግኘት ሌላ ችግር ነው። ባለፉት ሰባት ወራት ብቻ ከሁለት ሚሊየን ዶላር በላይ ኪሳራ ገጥሟል ተብሎ ይገመታል፡፡ ይህን ያህል ብር የውጭ ምንዛሬ እጥረት አለ እየተባለ በዶላር ሲከፈል በሀገሪቱ ላይ የሚፈጥረው ተጽእኖ ከፍተኛ ነው።
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ቡና የጥራት ደረጃ የሚታወቅ ቢሆንም እነዚህን መሰል ችግሮች ገበያውን እያሸሹት በመሆኑ የኢትዮጵያ ቡና ገበያ በውጪው አለም ማግኘት ያለበትን ደረጃ እያገኘ አይደለም። ከሀያ አመት በፊት በኒውዮርክ ፕራይስ የኢትዮጵያ ቡና (በ ኤል ቢ ፕላስ) ይሸጥ ነበር አሁን ‹‹ማይነስ›› ገብቷል። ከአለም ቡና አምራቾች ኤክስፖርት ከተደረገበት ዋጋ ዝቅተኛውን ድርሻ የሚያገኘው የኢትዮጵያ ገበሬ ነው፡፡ ይህም ችግሩ አገርንና ላኪውን ብቻ ሳይሆን አርሶ አደሩንም የሚገዳደር መሆኑን ያመላክታል። እነዚህን ከማጓጓዝ ጋር የተያያዙ ችግሮች ብቻ መቅረፍ ቢቻል እንኳ ወደ ውጭ የሚላውን በእጥፍ ማሳደግ ይቻላል፡፡
አቶ ግዛት አክለውም፤ ‹‹እነዚህ ሌቦች እንዴትና መቼ ይህን እንደሚያደርጉ አይታወቅም በማሽን የኮንቴነሩን በር እንደሚከፍቱትም ይነገራል፡፡ ላኪዎች ሲሰረቁ መኪናውን አሽከርካሪውን ጠቅሰው ያመለክታሉ፡፡ እስካሁን ተይዞ የተቀጣ ባለመኖሩ ግን በፖሊስ በኩል በቂ ክትትል እየተደረገ እንዳልሆነ ይሰማናል። በመሆኑም በመንግስት በኩል ጠንካራ ክትትልና ቁጥጥር መደረግ አለበት፡፡ በተጠርጣሪዎች ላይ ጠንካራ ምርመራ ማድረግና ጥፋተኛ ሆነው ሲገኙ እንደ ጉዳዩ ክብደት ቅጣቱንም አስተማሪ ማድረግ። የትራንስፖርት ሚኒስቴር ቡና ኮንትሮባንድ ጭኖ የተገኘ መኪናው እንደሚወረስ ብሎ ህግ በማውጣቱ ላለፉት ሁለት አመታት የቡናን የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴን በከፍተኛ ሁኔታ ለመቀነስ ተችሏል። በቅሸባም ለሚሰማሩ ተመጣጣኝ አስተማሪ ህግ ሊወጣላቸው ይገባል። በተለይ ከትራንስፖርት ሚኒስቴር ጋርና ከአሽከርካሪ ባለቤቶች ጋር በመስማማት ጂፒኤስ ያልገጠመ ቡና እንዳይጭን ስምምነት ማድረግ፤ መመሪያና ደንብ ማውጣት እና ማስፈፀም ይገባል›› ሲሉ የችግሩን ስፋት ከመፍትሄዎች ጋር ያቀርባሉ፡፡
‹‹ችግሩ አሳሳቢ መሆኑን በመረዳት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ስርቆቱን ለማስቆም እየሰራን እንገኛለን›› የሚሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የግብይት ዘርፍ ሃላፊ አቶ ሻፊ ኡመር ናቸው። እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ፤ ችግሩ ያለው በሚጓጓዝበት ወቅት ሲሆን፤ ስርቆቱ የሚፈጸመው ግን አገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ወደብ ላይ ነው የሚል ጥርጣሬም አለ፡፡ እስካሁን አስር ድርጅቶች ችግሩ ደርሶባቸው ያሳወቁ ሲሆን፤ ከእነዚህም 110 ቶን የሚደርስ ቡና ተቀሽቧል። መረጃው ከደረሰ ጊዜ ጀምሮ ከፌዴራል ፖሊስ ጋር በትብብር እየተሰራ ነው፡፡ ፌዴራል ፖሊስም መረጃ እየሰበሰበ በማጣራት ላይ ይገኛል።
በአሁኑ ወቅትም ከጉምሩክ ኮሚሽን ጋር በመሆን ኮሚቴ ተዋቅሮ በዘላቂነት ለመፍታት ውይይት እየተደረገ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ሻፊ፤ በቀጣይም ከጸጥታ ክፍል ሰራተኞች ጋር በመሆን ችግሩ በዘላቂነት እስከሚፈታ ድረስ የችግሩን ምንጭ በማስጠናት ጭምር እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡ ጂቡቲ ላይ ባለው የመረካከብ ሂደት ሚዛንና ባለሙያ ለማስቀመጥ ወጪ የሚያስፈልግ በመሆኑ ከሚመለከተው አካል በጀት ማግኘት እንደሚጠይቅ፤ ይህም ሆኖ እዛ ካለው ኤምባሲ ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን፤ ‹‹ጂ ፒ ኤስ›› ተሽከርካሪዎች ላይ መግጠሙ አስፈላጊ መሆኑ ስለታመነበት ለተሽከርካሪዎች ለማስገጠም ከትራንስፖርት ሚኒስቴር ጋር በመሆን እየተሰራ መሆኑን፤ አጠቃላይ ቡና የሚያንቀሳቅሱት መኪናዎች ምን አይነት መሆን አለባቸው የሚለውንም የሚያካትት መመሪያም እየተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 12/2011
ራስወርቅ ሙሉጌታ