
በካዛኪስታን አክታው ከተማ አቅራቢያ የተከሰከሰው አውሮፕላን ይዟቸው ሲበር ከነበሩት ተሳፋሪዎች ውስጥ 38 መሞታቸው ተገልጿል። ንብረትነቱ የአዘርባጃን ኤየርላየንስ የሆነው አውሮፕላን ከባኩ ወደ ሩሲያዋ ራስ ግዛት ቺቺኒያ ዋና ከተማ ግሮዥኒ ለመድረስ እቅድ ይዞ የነበረ ቢሆንም አቅጣጫውን ቀይሮ ካዛኪስታን ውስጥ ተከስክሷል። አደጋው የተረፉት 29 ሰዎች ሆስፒታል ውስጥ ገብተው ሕክምና እየተደረገላቸው እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የበራራ ቁጥሩ ጄ2-8243 የሆነው ኢምብራኤየር አውሮፕላን ከታቀደው መንገድ ውጭ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎሜትሮችን በማቋረጥ ከካስፒያን ባሕር ጠረፍ በተቃራኒ ተከስክሷል። የሩሲያ የአቪዬሺን ዎችዶግ ወይም በራራ ተከታታይ ቡድን አደጋው የተፈጠረው በወፍ ምክንያት እንደሆነ ቢገልጽም የአቪዬሺን ባለሙያዎች ይህ የመሆን ዕድሉ አነስተኛ ነው ይላሉ።
ባለሥልጣናት የአደጋውን መንስኤ ምን እንደሆነ ወዲያውኑ አልገለጹም። ነገር ግን አደጋው የተከሰተው የዩክሬን ድሮኖች በዚህ ወር በደቡብ ሩሲያ የምትገኘውን የቺቺኒያ ግዛት ማጥቃቷ ከተገለጸ በኋላ ነው። አውሮፕላኑ ከበረረበት መስመር በቅርብ ርቀት ያለ የሩሲያ ኤርፖርት በትናንትናው እለት ጠዋት ተዘግቶ ነበር። ዩክሬን አውሮፕላኑ ሲያቀናባት የነበረችውን ግሮዥኒን በዚህ ወር ማጥቃቷን አልገለጸችም።
የአዘርባጃኑ ፕሬዚዳንት ኢልሃም አሌይቭ በደረሳቸው መረጃ መሠረት አውሮፕላኑ መንገዱን የቀየረው በአስቸጋሪ የአየር ሁኔታ ምክንያት ነው ብለዋል። ነገር ግን ፕሬዚዳንቱ አክለውም የአደጋው መንሰኤ እንደማይታወቅ እና ሙሉ ምርመራ መደረግ እንዳለበት ተናግረዋል። “ይህ የአዘርባጃን ሕዝብ ከባድ ኀዘን ውስጥ እንዲገባ ያደረገ አሳዛኝ ክስተት ነው” ነው ብለዋል ፕሬዚዳንቱ።
አውሮፕላኑ 62 መንገደኞችን እና አምስት የበረራ ሠራተኞችን አሳፍሮ ነበር። ካዛኪስታን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ከአዘርባጃን ከመጡ የልዑክ ቡድን ጋር አደጋው በደረሰበት አክታው ስብሰባ ባደረጉበት ወቅት የሟቾችን ቁጥር ይፋ ማድረጋቸውን ተጠቁሟል። የካዛኪስታን የአደጋ ጊዜ ሚኒስቴር አውሮፕላኑ ከመሬት ጋር ሲጋጭ የተፈጠረውን እሳት ማጥፋቱን እና ሁለት ሕጻናትን ጨምሮ በሕይወት የተረፉ ሰዎችን ማንሳቱን መግለጹን አል ዐይን ዘግቧል።
አዲስ ዘመን ዓርብ ታኅሣሥ 18 ቀን 2017 ዓ.ም